የጋዜጠኛ ሙሉጌታ ሉሌ መልካም ስም ከመቃብር በላይ ዘላለማዊ ሆኖ ይኖራል

Mulugeta_04

የጋዜጠኛ ሙሉጌታ ሉሌ ስርዓተ ቀብር በነገው ዕለት ማለዳ በሰሜን አሜሪካ ቨርጂኒያ ይፈጸማል። በውጭ የሚገኙ ኢትዮጵያ ነጻ ፕሬስ ጋዜጠኞች ፎረም የታላቁን ጋዜጠኛ ሙሉጌታን ህልፈት አስመልክቶ ያወጣውን መግለጫ አስከትሎ እናቀርባለን።

ሃሳብን በነጻነት የመግለጽ መብት እንዲረጋገጥ፤ ብሎም ለአዲሱ የፕሬስ ትውልድ ፈር ቀዳጅ የነበረው ጋዜጠኛ ሙሉጌታ ሉሌ ከዚህ አለም በሞት መለየቱ ለብዙዎች የኢትዮጵያ ነጻ-ፕሬስ ጋዜጠኞች እና ቤተሰቦች መሪር ሃዘን ነው። ጋዜጠኛ ሙሉጌታ ሉሌ በአንደበቱ እውነትን የመሰከረ፤ በሰላ ብዕሩ ሃቅን የፈነጠቀ ለኢትዮጵያ ጋዜጠኞች ምሳሌ ሆኖ ያለፈ ታላቅ ኢትዮጵያዊ ነው።

ጋሽ ሙሉጌታ ሉሌ በህይወት በነበረበት ወቅት መልካም ነገርን ሰርቶ አልፏልና በመልካም ተግባሩ ይታወሳል። የኢትዮጵያ ታሪክ ሲነሳ፤ የነጻ-ፕሬስ ጋዜጠኞች ታሪክ ይወሳል። የነጻ-ፕሬስ ጋዜጠኞች ገድል ሲታወስ ደግሞ፤ የጋዜጠኛ ሙሉጌታ ሉሌ መልካም ስም እንደ ፈርጥ ያንጸባርቃል።

በውጭ አገር የምንገኝ የኢትዮጵያ ነጻ-ፕሬስ ጋዜጠኞች፤ ጋሽ ሙሉጌታ ሉሌን እንደታላቅ ወንድም፤ እንደሙያ አጋር እና እንደ ጥሩ ምሳሌ እያነሱ መልካም ተጋድሎውን ያስታውሳሉ። መልካም ስም ከመቃብር በላይ ይውላልና የጋሽ ሙሉጌታ ስራ እና ስም ለዘለአለም በክብር ይታወሳሉ።

አምላክ ነፍሱን ይማር።

በውጭ የሚገኙ የኢትዮጵያ ነጻ-ፕሬስ ጋዜጠኞች

በዚህ አጋጣሚ አስቀድመን በፕሮግራማችን እንዳልነው ሁሉ በአንጋፋው ጋዜጠኛ ሙሉጌታ ሉሌ ሞት የህብር ሬዲዮ ዝግጅት ክፍል ሐዘናችንን እንገልጻለን ለወዳጅ ዘመድ፣ለሙያ አጋሮቹና በአጠቃላይ በሙያው አንደበት ለሆነው የኢትዮጵያ ሕዝብ መጽነናትን እንመኛለን።

የህብር ሬዲዮን ዘገባ ህብር ሬዲዮን ከድህረ ገጻችን በተጨማሪ በስልክ ለማዳመጥ 712 -432-8451 መደወል ብቻ በቂ ነው። በእንግሊዝ ለምትኖሩ በ01405770140 በስልክ ማዳመጥ ይቻላል። ዘወትር በድህረ ገጻችን ወይም ከgoogel store Hiber radio አፕሊኬሽንን ዳውን ሎድ በማድረግና  ከዘሐበሻም ማዳመጥ ይቻላል።

 

 

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *