ምነው አሌክስ አብርሃም(ጌታቸው ይመር) ብዕርህ አቅሉን አጣ?

alex_abereham_page02
አሌክስ አብርሃም የፌስ ቡክ ገጽ ፎቶ

በማህበራዊ ሚዲያው በአገር ቤት ስመ ገናና እየሆኑ ከመጡት ጸሐፍት መካከል አሌክስ አብርሃም(ጌታቸው ይመር) ተጠቃሽ ነው። ታዲያ በራሱ አወዛጋቢ መሆን ይፈልግ ወይ ደባል ተልዕኮ ይኑረው አልፎ አልፎ የአንባቢውን ትኩረት ለመሳብ የሚያመጣቸው ርዕሰ ጉዳዮች በእርግጥም ጥርጣሬ የሚጋብዙ ናቸው። ሰው በመጻፉ ታስሮ በቀረበበት የፈጠራ ክስ ሳቢያ ሲፈረድበት ቢያንስ ለሰዎች የመናገር ነጻነት ዋጋ እሰጣለሁ የሚል ጠሀፊ ወይ ምሬቱን ይገልጻል ካልሆነም ዘመኑ ባመጣው የፍርሃት ብርድ ልብስ ተጠቅልሎ አይቶ እንዳላየ ያልፋል። ከዚህ ውጭ አሳሪዎችን አበጃችሁ ማለት ከጀመረ ያው ከእነሱ እንደ አንዱ ሆኖ መቆጠር ይጀመራል።የፕሬስ ስራ በእስር ቅጣት መፍትሄ አያገኝም። ነጻ ፍርድ ቤት በሌለበት እጅና አንደበት ታስሮ የተፈለገው ተነግሮብህ ራስህን የመከላከል ዕድል ሳታገኝ <<ተፈረደብህ>> ሲባል ይህን አምኖ ለመቀበል በራሱ የሞራል ተጠያቂነትን ያስነሳል። ምን ቢሆን በፕሬስ ላይ አሌክስ አብርሃም የነቀሳቸው ስህተቶች(የሰውን ጽሑፍ አወጡ)ን የመሰለ ስህተት በኢትዮጵያ እስር ቤቶች ያሳስር ብሎ በአደባባይ መናገር ትንሽ ያሳፍራል። ነገሩ መታረም ቢኖርበት እንኳን በዚህ መሰሉ ጭካኔ ይሁን ማለትን ምን አመጣው? ለዚህ ይመስላል በጋዜጠኛ ግዛው ታዬላይ ተሰዶም ሄዶ በተከሰሰበት የፈጠራ ክስ ሳቢያ 18 ዓመት መፈረዱን ተከትሎ <<አንዳንዴ እንኳን ይታስር ማለት ይልመድብን>> ማለቱን ካልወደዱለት መካከል ኢብራሂም ሻፊ የበኩሉን ብሏል። አንብቡለት።

ኢብራሃም ሻፊ

ሳድዝም መራር ተግባር ነው፤ ቃሉ ራሱ አፍ ላይ የሚመር ይመስላል፡፡ ስጠራው ቅፍፍ ይለኛል፡፡ የሌሎችን ሰዎች ውድቀት፣ ህመም፣ ምቾት አለመሰማት እና ስቃይን እያዩ ከልብ መደሰት፣ ጥርስን ማፍነክነክ፣ “ቪቫ” ብሎ በድል ስሜት እጅን እንደመቀሰር እና መፈንደቅ የሚል ትርጓሜ የሚሰጥ ነገር ምኑ ይወደዳል? ለአንዳንዶች ግን ቃሉ ብቻ አይጥማቸውም፤ ግብሩም ይዋጣላቸዋል………. ልክ ለእንደ አሌክስ አብረሃ ……..ጌታቸው ይመር…… (ኧረ በየትኛ ስሙ ልጥራው)አይነቱ!!!

ኢትዮጵያዊያን በሊቢያ በረሃ በአይኤስ ጭካኔ ታርደው ህዘብ ሲያነባ፣ ሲያለቅስ እና መከራ ከፈነቀለው ብሶት አደባባይ ሰልፍ ሲወጣ በዝምታ አድብቶ፤ መንግስት በጠራው የሁለተኛ ቀን ሰልፍ ላይ ገና በጠዋቱ “ፌዴራል ፖሊስ እና ህዝብ ተቃቅፈው እየተላቀሱ ነው፤ በዐይኔ በብረቱ ዐይቻለሁ” ብሎ የፌስቡክ ግድግዳው ላይ ውሸት የፃፈ እና ያስደበደበ ነውረኛ ነው፡፡ ህዝብ ሲራወጥ፣ በፖሊስ ቆመጥ ሲንገላታ፣ ህይወቱን ለማትረፍ ሲባትት እና የእስርቤት ደጃፎችን ላለመርገጥ ሲሸመጥጥ አሌክስ የኮምፒዩተር ኪቦርዱን እየጠቀጠቀ እና ፌስቡኩን እየተመለከተ ሲያፌዝ የነበረ የሳድስቶች አውራ ነው፡፡ ይህ ሳድስታዊ ባህሪ የተፀናወተው እና የማይለቀው በመሆኑ ከእርሱ ከፍ ያሉ የመሰሉትን በመሉ በመዝለፍ፣ በማንጓጠጥ እና በማሰቃየት ለመርካት ጥረትን አድርጎ ነበር፡፡ ዮሴፍ ገብሬ (ጆሲ)፣ ሰይፉ ፋንታሁን፣ ግሩም ኤርሚያስ፣ ቴዎድሮስ ካሳሁን (ቴዲ አፍሮ) እና በዐሉ ግርማ ላይ ጀምሮት የነበረውን የስም ማጥፋት ዘመቻ ከብዙ በጥቂቱ ማንሳት እንችላለን፡፡

እነዚህን ሰዎች እና ቤተሰቦቻቸውን ስቃይ ላይ ጥሎ እርሱ “ፈገግ” ሊል ቢፈልግም ህዝብ አልፈቀደለትም እና ውጥኑ መና ሆኖ ቀርቶበታል፡፡ የሰዎቹ እና ቤተሰቦቻቸው ስብዕና እጅግ ጠንካራ ነበር እና ከዘበትም ሳይቆጥሩት አልፈውታል፡፡ ለሳድስቶች ግን በፀብ ተጠምዶ “እኝ” ማለት፣ ሌሎችን ለማስፈራራት መሞከር እና የተለያዩ የስቃይ ዘዴዎችን መሻት ስራቸው ነው እና ለእነዚህ ሰዎች ውድቀት የተለያዩ ጉድጓድ በተደጋጋሚ ለመማስ ሞክሮ ነበር፤ በሁሉም ዘንድ ፊት ተነስቶ አዳፈነው እንጂ!!! በሰዎች ሁሉ ስቃይ፣ ውድቀት እና መከራ ከሚረኩት ሳድስቶች አንዱ የሆነው አሌክስ በቅርብ ደግሞ ” የሎሚ ጋዜጠኛ/ባለቤት (ግዛው ታዬ) እንኳን 18 ዓመታት እስር እና 300ሺህ ብር ቅጣት ተጣለበት” በማለት እውነተኛ ማንነቱን አሳይቶናል፡፡

የሰው ልጆች ውድቀት እና ስቃያቸው ነበር እና የሚያረካው አንድ የሚበልጠው የመሰለው ሰው እጅግ ዘግናኝ የእስር ቅጣት ሲተላለፍበት ጮቤ ረግጧል፡፡ ግዛው በሌለበት የተፈጠረ ክስ፣ ባልዋለበት የተሰማ ጭብጥ እና የቀረቡ ማስረጃዎች ለእንደ አሌክስ አይነቱ ጨካኝ ገልቱዎች ምንም አይደሉም እና ውሳኔውን “እንኳን” ብለው በደስታ እየፈነጠዙ ተቀብለውታል፡፡ ምክንያቱ ደግሞ “ፅሁፌን ሳያስፈቅደኝ መጽሔቱ ላይ አውጥቷል” የሚል ማስረጃ ያልቀረበበት እና እጅግ ተልካሻ ሰበብ ነበር፡፡ አሌክስ ከሳድስታዊ ባህሪው በተጨማሪ ማቋረጥ የማይችል ውሸታም ሆኖ እንጂ ግዛው ታዬ፣ የሎሚ ቅጥር ሰራተኞች እና ጋዜጠኞችን ብትጠይቋቸው መጽሔቱ ላይ ለወጡት እያንዳንዱ ጽሑፉ ክፍያን ተቀብሏል፡፡ “አዲስ ጉዳይ ስለምስራ እና ስሜ እዛ ላይ ስለሚወጣ እባካችሁ ስሜን አታውጡብኝ” የሚል ተማፅኖን እያቀረበ እንጂ ስግብግብ ነፍሱ አካሉን ረስታው እንደማታውቅ ይነግሯችኋል፡፡ ይሄንን ዘዴንም በብዙ መጽሔቶች ላይ ተጠቅሞ ስሙ ሳይወጣ (ከአዲስ ጉዳይ በስተቀር) ገንዘብ እንደሰበሰበበት ይመሰክሩበታል፡፡ ብሩን ለመቀበሉም በርካታ ጋዜጠኞችን እማኝ አድርጎ ማቅረብ ይቻላል፡፡ ሆኖም እንደ ጥሩ ማስረጃ እነዚህ መጽሔቶች ህትመት ላይ በነበሩበት ሰዐት ከመለማመጥ ውጪ ዘልፎ እና ወደፊት ገፍቶ አለመሄዱን ልብ ማለቱ በቂ ነው፡፡ ልምምጡም ስሙ ሳይጠቀስ ስራው ከሚወጣባቸው መጽሔቶች ጋር በሽርክና የሚደረግ (ለእነርሱም እንደማስታወቂያ ቢጤ መሆኑ ነው) በመሆኑ በፍፁም ወደ ክስ አምርቶ የማያውቅ እና ሊያመራ የማይችል መሆኑን ለመረዳት ቀላል ነበር፡፡

ሎሚ በመንግስት ክስ የተፈጠረበት አሌክስ እንደሚለው “የሰው አዕምሯዊ ንብረት ስለወሰደ” አይደለም፡፡ ክሱ “ያለ ታክስ ለአምስት ዓመታት ሰርተሃል” የሚል ነው፡፡ በአሁኒቷ ኢትዮጵያ መንግስት ዐይኑን ጥሎብህ፣ በአደባባይ የሚታተም እና የሚሰራጭ የህትመት ውጤት ሆነህ፣ ጋዜጦች እና መጽሔቶች በየጊዜው ከሚደረግባቸው ምርመራ አንፃር ለበርካታ ዓመታት ያለ ታክስ መስራትን የመሰለ የፈጠራ ክስን እናንተው አስቡት፡፡ መልዕክቱ መንግስትን ሚዛናዊ ሆነው ለፈተኑት ለኢትዮጵያ ነፃ ጋዜጠኝነት እና ጋዜጠኞች እንጂ ለግዛው ታዬ አለመሆኑን ተረዱት፡፡ ኢትዮጰያ ተመልሳችሁ ብትመጡ “ዋ!” የሚል መልክት እንደያዘም ማሰብ ትችላላችሁ፡፡ እንደ አሌክስ አይነቱ ሳድስት ግን ዐይኑ የሚያነበው ሌላ ነው እና የበላበትን ወጪት ሰብሮ ግዛው ታዬ 18 ዓመታት ሲፈረድበት ፈንጥዟል፡፡ እንደው ግዛው ታክስ ሳይከፍል ቢሰራ እንኳን “የኢትዮ ቻናሉ ሳምሶን ማሞ በተመሳሳይ ጥፋት ስንት ጊዜ ታሰረ? እንዴትስ ተፈታ? የሚል ንፅፅራዊ ነጥቦችን አንስቶ አንደመፃፍ ” እንኳንም ታሰረ……ያንሳል” ብሎ ተሳልቋል፡፡ ጊዜ የሁሉም ነገር መፍቻ ነው፡፡ ጊዜ አሌክስንም ሳድስታዊ ባህሪው ሳይታወቅ፣ የቅድሚያ ክፍያ እና ብድር ሳይቀር እየወሰደ ከሎሚ እና ሌሎች መጽሔቶች ጋር አሰርቶት ነበር፡፡ ጊዜ ደግሞ መንግስት የፈጠራ ክስን ይዞ ቀርቦ አጅግ ዘግናኝ ውሳኔን ሲያሳልፍ አሌክስን ማልያ አስቀይሮ እና ሳድስታዊ ባህሪውን አጋልጦ አሳይቶናል፡፡ ፍትህ፣ርትዕ፣ ዲሞክራሲ እና መልካም አስተዳደር በተደፈጠጡበት፣ ሙስና የህዝቡን አጥንት ሳይቀር እየጋጠ ባለበት፣የሀገር ፍቅር እንደ ጉም ተኖ ከጠፋበት እና ራስን የመቻል ብልሃት ፍፁም እንቆቅልሽ ከሆነበት የኢትዮጵያ ችግር የግዛው ታዬ 18 ዓመታት መታሰር በልጦበት “እንኳን…..ደግ አደረጉልህ” አስብሎታል፡፡ እኛ ግን እትርሳ እንለዋለን…….የጊዜ እንጂ የሰው ጀግና የለውም!!!

በጽሁፉ ላይ የሚቀርቡ ምላሾችን እናስተናግዳለን።

የህብር ሬዲዮን ዘገባ ህብር ሬዲዮን ከድህረ ገጻችን በተጨማሪ በስልክ ለማዳመጥ 712 -432-8451 መደወል ብቻ በቂ ነው። በእንግሊዝ ለምትኖሩ በ01405770140 በስልክ ማዳመጥ ይቻላል። ዘወትር በድህረ ገጻችን ወይም ከgoogel store Hiber radio አፕሊኬሽንን ዳውን ሎድ በማድረግና  ከዘሐበሻም ማዳመጥ ይቻላል።

 

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *