እሁድ አመሻሽ:: በፈረንጆቹ አቆጣጠር ታህሳስ 06 ቀን 2016:: የአሜሪካን ክረምት የገባ የማይመስል ብርሃናማ ቀን ነበር። የዋሽንግተን ዲሲና አከባቢዋ ነዋሪ የሆንን ኢትዮጵያውያን በኮሎምቢያና 16ኛው ጎዳና መገጣጠሚያ ላይ በሚገኘው (ኮሎምቢያ ሃይት የትምህርት ማዕከል) የማይቀርበት ቀጠሮ ይዘናል። ወደ አደራሹ የምንሄደው የጣይቱ የባህልና የትምህርት ማዕከል ከሌሎች አገር ወዳጆች ጋር በመሆን ከኢትዮጵያ ያስመጡትን ቴያትር ለማየት ነበር። አብሬአቸው የምሄደው የቅርብ ወዳጆቼ የቴያትሩ ደራሲ እና ተዋንያን ጋር የቀረበ ግንኙነት ያላቸው በመሆኑ፤ ዘወትር ስለ ቴያትሩ ሲነግሩኝ የማዳምጣቸው ጆሮዬን እንደ ጥንቸል አቁሜ ነበር። በተለያየ ጊዜ ወግ ቢጤ ስንጭር ወደ ስደት ከመምጣታቸው በፊት ከአምስት ጊዜ ያላነሰ ተመላልሰው ቴአትሩን እንደተመለከቱት ሲያጫውቱኝና ከድራማው እየቀነጨቡ አባባሎችን ሲያጎኑት እኔ ቴያትሩን ባለመመልከቴ መንፈሳዊ ቅናት ያድርብኝ ነበር። “ማነው እያዩ ፈንገስ?…..ማነው ጋሼ ቆፍጣናው?” እያልኩ እራሴን እጠይቅ ነበር። በእያዩ ፈንገስ ፌስታል ውስጥ የተዶለተው ሰምና ወርቅ ምን እንደሆነ ለማወቅ መሻቱ ነበረኝ። “ሜዳ ጠፋ ተብሎ ተራራ የሚናድበት ሃገር” አይነት ፍርድና ቅጣት እየተሰጠ እንደሆነ በቴያትር ሲገለጥ ለማየት ፍላጎት ያሳድራል።
እርግጥም ባልተለመደ ሁኔታ ለሁለት ሰዓት ተኩል ያህል በአንድ አርቲስት ብቻ የሚተወን ቴአትር ይህን ያህል ቀልብ መግዛት ከቻለ በይዘቱም በአቀራረቡም ሆነ ስሜት ኮርኳሪነቱ ወደር የማይገኝለት መሆን አለበት። ከየትኛውም የኪነ-ጥበብ ዘርፍ ውስጥ የቴአትር ስራ ረቀቅ ያለ ጥበብና ሳይንስ የሚጠይቅ ይመስለኛል። ከሩቅ ሆኜ (“ባላዋቂነት”) እንደተመለከትኩት ከሆነ ኪነ-ጥበብ ሳይንስም ጥበብም ነው። ሳይንስ የሚሆንባቸው ምክንያቶች በአለም አቀፍ ደረጃ ተቀባይነት ያላቸው መርሆች(principles)፤ በሙከራ እይታና ምርመራ የሚዳብሩ እውቀቶች ፤ በመንስኤና ውጤት መካከል ግንኙነት መኖር (Cause and effect relationship)…ወዘተ ሊጠቀስ የሚችል ነው። ኪነ-ጥበብ ከስያሜው ጀምሮ “ጥበብ” የሚል ቃል ከመኖሩም ባሻገር አንድ የታሰበን አላማና ግብ ለማሳካት መዘጋጀቱ፤ የግልና የቡድን ልዩ ችሎታ በመጠቀም ለዛ ባለው መንገድ መልዕክት ማስተላለፍ መቻሉ፤ የተግባር እውቀትና የፈጠራ ችሎታ መጠቀሙ፤…..ወዘተ ኪነ-ጥበብን “ጥበብ” የሚያስብለው ይመስለኛል።
እናም በወጣት በረከት በላይነህ ተደርሶ ግሩም ዘነበ የተጫወተውን “እያዩ ፈንገስ፡ ፌስታሌን” ቴአትር ከላይ ባስቀመጥኳቸው የሳይንስና ጥበብ መመዘኛዎች መመልከት እንዳለብኝ አሰብኩኝ። እውነት ለመናገር ከብዙ ወራቶች በፊት በቴአትሩ ዙሪያ የሰማኋቸው አጓጊ ትርክቶች ግምቴን ከፍ ስላደረጉት (“Pygmalion effect”) የመድረክ ትወናውም በጠበኩት ልክ ላይሆን ይችላል የሚል ስጋት ነበረኝ። የአመራር ሳይንስ ፀሃፊ የሆኑት ዊትሊና ጆንሰን እንደገለጡት ቀመር ከሆነ የሚታሰበው ውጤት የተገኘው ውጤትና ድርጊት(ባህሪ) ልዑል ድምር ነው (Performance expectation= Result + Action & Behavior)። ይህም ሆኖ ገና ቴያትሩ ሲጀመር በአይነ-ህሊናዬ ከቀረጽኩት በላይ በተመስጦ ተዋጥኩ። ለሰከንዶች እረፍት ሳይሰጥ የሰዎችን አእምሮ መቆጣጠር የቻለው የታሪክ ፍሰት ሌሎች ነገሮችን ለማሰብ ፋታ አልሰጠኝም። የታሪኩ ዋና ባለቤት እያዩ ፈንገስ መንገዴን ሞላው። ተመላለሰበት።
***
የቴአትሩ መሰረታዊ ጥንካሬ በአዲስ አበባ ብሎም በኢትዮጵያ መሬት ላይ የወረደውን መራር እውነታ ለመጋፈጥ(Confront the Brutal facts) የደፈረ መሆኑ ነው። ይሄ ብቻ አይደለም። ቴአትሩ መራሩን ሀቅ የተጋፈጠ ብቻ ሳይሆን የነገን ተስፋ የሰነቀ ነው። መራሩ እውነታ ፦ ምሃገራችን ያለችበት አስከፊ ሁኔታ በእልህና እውቀት ተኮር በሆነ መንገድ የማወቅ ነው። ተስፋው ደግሞ ለራስ የሚሰጥ ክብር፣ በአከባቢው ምን እየተካሄደ እንደሆነ የማወቅ ዝግጁነት፤ እምነትና መተማመንን እንደ ቁልፍ ማህበራዊ ካፒታል የሚወስድ፤ ለተገቢው ሰው ክብርና እውቅና መስጠትን፣…. ከመቀበል ይልቅ ለመስጠት ያለ ፈቃደኝነት፤ ለቀዳሚ ጉዳዮች ቅድሚያ መስጠት (put first things first) እና ወድቆ መነሳት መቻሉን የሚያሳይ ነው። *ቴአትሩን እየተከታተልን አንድ በኢትዮጵያ ፖለቲካ ጉዳይ ላይ ንቁ ተሳታፊ የሆነና አጠገቤ የተቀመጠ ምሁር ወደ ጆሮዬ ጠጋ ብሎ “ደራሲውና አርቲስቱ ወደ ሃገር የሚመለሱ ይመስልሃል?” የሚል ጥያቄ ደጋግሞ ጠየቀኝ። የጠያቂዬን ያህል ስጋት ባይገባኝም ከጥርጣሬ ውጭ አልነበርኩም። በአገር ቤት የደረሰባቸውን ማስፈራሪያ፣ ጥቃትና አዳራሽ ክልከላ እንዲሁም ከኢትዮጵያ የሚመጡ አርቲስቶች በምዕራቡ አለም ዝግጅታቸውን አቅርበው ወደ ኢትዮጵያ ሲመለሱ አገዛዙ ያደረሰባቸውን በመስማቴ ነበር ከጥርጣሬ መውጣት ያልቻልኩት። ከጥቂት ወራት በፊት “የቴዎድሮስ ራዕይ” የሚለውን ቴአትር ካቀረቡት ተወንያን መካከል አርቲስት ቴዎድሮስ ተስፋዬ ላይ አገዛዙ ያደረሰበት አሳዛኝ እርምጃ የቅርብ ጊዜ ትዝታ ነው። እርግጥም ህብረተሰብን መቅጣት በጀት የሚያደርግ ብቸኛው የፕላኔቷ መንግስት ግለሰቦች ላይ ጡንቻውን ቢያሳፍር ላይገርም ይችላል።
ከላይ ለማሳየት እንደተሞከረው ደራሲ በረከትና አርቲስት ግሩም አገራችን ኢትዮጵያ በተለይም መዲናችን አዲስ አበባ እየተጋፈጠች ያለችው መራር ሃቅ ቁልጭ አድርገው አቅርበዋል። የአዲስ አበባ ህዝብ ባጋጠመው ዘርፈ ብዙ ችግር ምክንያት ሰማይ እንደ አክንባሎ ተደፍቶበት ፈጣሪውን “ለምን ፈጠርከኝ” ብሎ እስከማማረር መድረሱን ያመለክተናል። እንደ እውነቱ ከሆነ በትንሹ ጉዳይ አምላኩን ማመስገን ወግና ባህሉ ያደረገ ህዝብ ወደ ምሬት ገብቶ መመልከት የውድቀቱን ደረጃ የሚያሳይ እንደሆነ ይነግሩናል። ሰው በሰውነቱ ብቻ ክብር የሚሰጠው የመዲናችን ነዋሪ ባጋጠመው “የከተማ ችጋር” ምክንያት እርስ በእርስ እንደ አውሬ ሲነጣጠቅና ጥርስ ፈልቅቆ ምግብ ሲቀማማ የምናይበት አስደንጋጭ ሁኔታ መፈጠሩን ይነግሩናል። ነዋሪው ውስጥ የሰፈሩት የቀን ጅቦችና ጆሮ የሌላቸው አፈ-ጮማዎች መሬቱን እየቀሙ በአንድ ወር ውስጥ ቪላዎች ገንብተው ሲንደላቀቁ አዲስ አበቤው “መሸ-አዳሪ”እንዳደረጉት ይተርክልናል። አፈር በእጁ ጠራርጎ አቧራ እፍፍ ብሎ በቆርቆሮ አዳራሽ፣ በድልድይ ስር፣ በአውቶብስ መጠበቂያ፣ በመሃል ጎዳና…. ወዘተ እንዲተኛ በማድረግ አቅመ-ቢስ ቆሽማዳ አደረጉት። እነዚህ ልበ-ደልማጦች የሀብትና ስልጣን ጥማታቸውን ለማርካት የህዝብ ንብረት እንደ ጆፌ አሞራ በመውረር ነዋሪውን እርቃኑን አስቀሩ። መሬት ጠብ በማይል ድለላና ሽንገላ የሚቀይረው ልብስ ሳይኖረው በደረቁ ላጩት።
ወጣት በረከትና (ግሩም) በሚማርክና በሚያስደምም ብዕራቸው (አንደበታቸው) አገዛዙ የሚከተለውን የፍለጠው ቁረጠው ፖሊሲና ጆሮ ያልፈጠረበት የውሸት ፕሮፖጋንዳ ህዝቡን ምን ያህል እንዳማረረ ለማሳየት ሞክረዋል። ርግጥም የሚጠጣ ውሃ በሌለበት ሃገር ውስጥ “የውሃ ቀን”…“የእጅ የመታጠብ ቀን” የሚሉ ኩነቶችን በመንደፍ ለሳምንታት ነዋሪውን በ”ተወዳጁ ኢቲቪ” ማደንቆር ከዚህ አስተሳሰብ ውጪ ሊሆን አይችልም። (እነዚህ ኩነቶች ሲፈጠሩ እኔም በፕሮፖጋንዳው ማሽን ውስጥ ነበርኩና ከአዳራሹ ሳልወጣ ሂሳቤን ማወራረዴን አንባቢያን እንድታውቁልኝ ይሁን::)እርግጥ እነሱ ባይገልጡትም ትላንት “ባንዲራ ጨርቅ ነው” በማለት ያዋረደ ሰው “የባንዲራ ቀን” ብሎ ሲያከብር በፕሮፖጋንዳ ማሽኑ ማሳየት የጆርክ አርዌልን “Nineteen Eighty-Four” ከማስታወስ ውጭ የሚፈይደው ነገር የለም።…ጭካኔን ደግነት፤ ..ረሃብን ጥጋብ፤… ደንቆሮነትን ምሁርነት፤ …ሞት ህይወት የሚሆንበት የኦርዌል መፅሀፍ!!…… የሰው ስጋ ተቆርሶ በሚበላበት ሃገር ስለ ጥጋብና ምርት መትረፍረፍ የሚወራበት!….የህፃናት ጡጦ ተነጥቆ በሚጠጣበት ሀገር ውስጥ ስለ ብሔራዊ ነፃነት የሚሰበክበት!…እሸት ለመጥበስ የሰው ቤት በሚቃጠልበት ቀዬ ስለ አብሮ መኖር የሚሰበክበት! የኦርዌል መፅሀፍ!
***
በረከትና ግሩም የተጋፈጡት ሌላው መራር ሀቅ የኢትዮጵያ ህዝብ ሞራል ከየትኛው ዘመን በበለጠ መላሸቁን ነው። አገዛዙ በተለያየ መንገድ በሚያደርሰው በትር የሞራል ውድቀትና የተሸናፊነት ስሜት እየተፈጠረ መሄድ ችሏል። ፍርሃት በህብረተሰቡ ውስጥ እየነገሰ ሄዷል። ህዝቡ ከአገዛዙ ጋር በምንም አይነት መንገድ ለመሰለፍ ፍላጎት የሌለው ቢሆንም በፍርሃት ቆፈን በመያዙ በማያወላውልና የማያመነታ መንገድ ልበ-ቆራጥ መሆን አልቻለም። በተለይም የአዲስ አበባ ህዝብ ምስለኔ መደዴዎችና ማንዘራሾች ከተማዋን ወረው ከገደል ጫፍ እየወሰዷት እንደሆነ እየተመለከተ የራሱ አንገት እስኪታነቅ እያብሰለሰለ ይኖራል። መንገዱ በባልጩት ድንጋይ እየተሞላ እያየ “ይንጋት ብቻ!” በማለት በአርምሞ የሚቀመጥ ህዝብ ሆኗል። መንገዱን (ሀገሩን) ተቀምቶና ምርኩዙን ተሸክሞ መኖሩን እያየ አሁንም “ይንጋት ብቻ!” ብሎ የሚዝት ነዋሪ!
የሚገርመው ነገር የሞራል ዝቅጠቱ እየከፋ የሄደው በውስን የህብረተሰብ ክፍል ብቻ አለመሆኑ ነው።…. ህዝቡን ማንቃት በሚገባቸው ምሁራን፤….. በአምስት አመት አንዴ ለአምስት ወራት ብቅ የሚሉት የፖለቲካ ፓርቲዎችና አመራሮች”፤ “በመቶሺዎች ጉቦ እየተቀበለ በፍትህ ዙፋን ተቀምጦ፣ ብይን የሚሰጥ ዳኛ”፤ አርቲስት የህዝብ አይን፣ ጆሮ አፍንጫ፣ ኩላሊት፣ እግር፣ ጉበት ነው እያሉ የሚያላዝኑ አርቲስቶች”፤ …. “እውነትን መሻት፣ በህሊና ዳኝነት መመራት፣ የሙያ ተአማኒነትና ተቀባይነት ቅብርጥሶ የሚል የስነ-ምግባር መመሪያ አለን የሚሉ ጋዜጠኞች”፤ …. “የህዝቡን የመስዋዕትነት ፍሬ ለመቋደስ ብቻ ያሰፈሰፉ በሁለት ቢላዋ የሚበሉ የመስቀል ወፍ ዲያስፖራዎች” …..ወዘተ ሆነው መገኘታቸው ነው። የቀድሞ ባይሎጂ መምህር እያዩ የአሁኑ የጎዳና ተዳዳሪ እያዩ ፈንገስ የሚነግረን ታሪክ ይሄንን ነው። እንደ ፍቅር እስከመቃብር ጉዱ ካሳ የአገዛዙን ባህሪ በአደባባይ ፍርጥ የሚያደርጉት ደግሞ ጋሼ ቆፍጣናው ናቸው። መፍራት ያልፈጠረባቸው ጋሽ ቆፍጣናው የመንግስትና ህዝብ ውሃና ዘይት መሆን ባልታሰበ ሰዓት ዱብ ሲያደርጉት አንዳንድ በኮሎንቢያ ሃይት የታደሙ ተደራሲያን እጢያቸው አብሮ ዱብ ይል ነበር።
አጠገቤ የተቀመጠው ምሁሩና ፖለቲከኛው ወዳጄ ጣቱን እየቆጠረ “ሦስት የወያኔ ልጆች፣ የእንጀራ ልጆችና ጉዳይ አስፈፃሚዎች” ተመለከትኩኝ ይለኝ ነበር። እንደ እውነቱ ከሆነ ያንን ሁሉ የጋሽ ቆፍጣናውን የብረት ሰንሰለት ግርፊያ በየደቂቃው እየሰሙ መቀመጥ “የጠቅላይ ሚኒስትር ሐይለማሪያም” እና “የሃይለማሪያም ማሪልን ብራንዶዎች” የጭንቅላት ደረጃ ይጠይቃል። ምን አይነት ጭንቅላት?
◾በቅዝምዝም ፋንታ ፍየል የሚወረወርበት እርባና ቢስና ጅላጅል ጭንቅላት!…..
◾“ቁንጮ ሁነን ምራን!” ተብሎ ሲሰጠው አሰጣጡ ሳይገባው የሚቀበል አድርባይ ጭንቅላት!
◾መከበር ምሱ ባይሆንም በወጉ ለመናቅ ራሱን ያላዘጋጀ ወላወልዳ ጭንቅላት!
◾በአገሪቷ ላይ “ምን እየተካሄደ እንደሆነ” የማይገባው ወሬ አቀባይና የሰው ንዑስ! …….
◾“ህብረተሰባዊነት! ድል ለሰፊው ህዝብ!” የሚል የጅል ዘፈን ተሸክሞ የሚዞርና እንደፈረስ የሚያናፋ…..
◾መንገዱን ተቀምቶ ሲያበቃ በምርኩዙ የሚኮፈስ ገረንገሬ!
◾ሆስፒታል ህሙማን ሊጠይቅ ሄዶ “ዋናው ጤና ነው” ብሎ የሚመለስ ጭንቅላት!…..
◾አይደለም የጥያቄ ቅደም ተከተል ጥያቄው ምን እንደሆነ የማያውቅ ጭንቅላት!…
(ዶ/ር ቴዎድሮስ አድሃኖም በአለም የጤና ድርጅት ጥያቄና መልስ ላይ ያሳዩት መዝረክረክ ልብ ይላል:: “መልሱን ተወው ጥያቄው ከገባህ ይበቃል!” አለ እያዩ ፈንገስ። ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የሚገኝበት የቂርቆስ ክ/ከተማው እያዩ ፈንገስ!)
***
ወደተነሳንበት ለመመለስ “እያዩ ፈንገስ ፌስታሌን” ቴያትር መራሩን እውነታ የተጋፈጠው ከገዛ ጓደኞቹ ጭምር ነው። ይሄም ያለምንም ጥርጥር በራስ መተማመኑን ያሳያል። በራስ መተማመኑን ብቻ ሳይሆን ብቃታቸው አስተማማኝ መሆኑን ያመላክታል። በራስ መተማመኑ ወደ ላይ አንጋጦ ከሚያወራው አለቃው ጋር (አምላኩ ይመስለኛል) በልበ ሙሉነት እንዲያማክረው ተረድቶታል። የተፈጥሮ ስጦታውን፣ የሙያ ብቃቱንና እምቅ ጉልበቱን ተጠቅሞ የፈለገውን አላማ ለማሳካት አስችሎታል። የትራንስፎርሜሽናል ሊደርሺፕ ፀሃፊ የሆነው ዴቪድ ላውራንስ በራስ መተማመንና ብቃት ቀጥተኛ ግንኙነት (Direct Relationship) እንዳላቸው ይገልጣል። አስተማማኝ ሙያዊ ብቃትና በራስ መተማመን መቀናጀት ሲፈጥር ከፍተኛ ውጤት ይመዘገባል። የዚህ ቴያትር ትልቁ ጉልበት ስሩ የሚመዘዘው ከእንደዚህ አይነት ውህደት ነው።
በሌላ በኩል ብቃት ኖራቸው በራሳቸው የማይተማመኑ ወይም ብቃቱ ሳይኖር መተማመኑ ያላቸው አርቲስቶች አሉ። ለዚህ ጥሩ ምሳሌ የሚሆኑ በርካታ አርቲስቶች አሉ። በእኔ እምነት አንዳንዶቹ አርቲስት ከፍተኛ ብቃት ያላቸው ናቸው። በራስ መተማመኑ ደግሞ ከዜሮ በታች በኔጋቲቭ ሊሰላ የሚችል ነው። አድርባይነቱ ሲጨመርበት በራስ መተማመኑ ባለ ሁለት አሃዝ ኔጋቲቭ ይወርዳል። በዚህ ምክንያት በስራ ላይ የማይውል(የሚባክን) ችሎታው እጅግ በጣም ብዙ ነው። በተመሳሳይ መንገድ ከፊል አርቲስቶች በብቃት ባልተደገፈው የራስ መተማመን በሀገረ ኢትዮጵያ የሚስተካከላቸው አርቲስት ያለ አይመስለኝም። ብቃት የጎደለው በራስ መተማመን ትሩፋቱ ስለራስ የተጋነነ ስሜት መያዝ በመሆኑ የመጨረሻው ውጤት ባዶ ጉራ (ትዕቢት) ይሆናል። አሊያም እንደ ኢትዮጵያ ባሉ አምባገነንና ዘረኛ ስርአት ባለባቸው ሀገሮች ጀግንነት በዘር የተወረሰ ተደርጎ እንዲታይ ኢንዶክትሬት ስለሚደረግ ፍርሃትን በቀላሉ መሻገር የሚችሉበት እድል ሰፊ ነው።
(እከሌ የሚባለው ተዋንያን (አርቲስት) የሚፈረጀው በዚህኛው ጎራ ነው የሚለውን ለአንባቢያንና ለእራሳቸው አርቲስቶች ትቼዋለሁ።)
***
“እያዩ ፈንገስ ፌስታሌን” ቴያትር ሌላው የገለጠልን ቁም ነገር እኛ ኢትዮጵያውያን ምቀኝነትና በቀለኝነት እንደ አንድ የህይወታችን መመሪያ አድርገን እየተንቀሳቀስን መሆኑን ነው። የምቀኝነታችን ደረጃ የእያዩ ፈንገስን አለቃ በሚያስቸግር መልኩና ክፋትን እንዲሰራ ወደ ምድር ከተወረወረው ሰይጣን በሚያስቀና ሁኔታ መሆኑን እንመለከታለን። በቴያትሩ ላይ ሰይጣን “ኢትዮጵያውያን ምግባሬን ነጠቁኝ” በማለት ወደ ሰማይ አንጋጦ ለአለቃ አቤቱታውን ሲያቀርብ እንመለከታለን። እዚህ ላይ በጣም አሳዛኝ የሚሆነው የመቀኝነት ደረጃው የሆቴል ትርፍራፊ ምግብ እስከመከልከል የሚደርስ ጥግ ድረስ መሄድ መቻሉን መመልከታችን ነው። ለነገሩ ትርፍራፊ በጉርሻ መልኩ በሚሸጥበት ከተማ ሌላው በነፃ እንዳይጠቀም መከላከሉ የፈጠረና ያሳደገንን ማህበረሰብ እሴቶች ለይቶ ካለማወቅና በራስ ላይ የወረደ አመለካከት ከመያዝ የሚመነጭ ቢሆንም የመከሰት እድሉ ዜሮ አይደለም።
ተወደደም ተጠላ በራሱ ላይ የከበረ አመለካከት የሌለው ሰው በማህበረሰቡ ላይም እንዲሁ ይሆናል። በቴያትሩ ላይ እንደተመለከትነው ጋሽ ቆፍጣናው ያከራዩት የ “ተወዳጁ ኢቲቭ” ጋዜጠኛ በላሸቀና እንጨት እንጨት በሚል ቋንቋ ራሱን ያረከሰ በመሆኑ የፈለቀበትን ህብረተሰብ ሊያከብር አልቻለም። ጋዜጠኛው ራሱን ብቻ የሚወድና በአለቆቹ ዙሪያ የሚሽከረከር በመሆኑ የዜጎችን ሸክም መሸከም አልቻለም። ባለስልጣናትና ባለፀጋው(ባለሀብቱ) አንድም ሁለትም መሆናቸውን የሚሰማው እንኳን ከጋሽ ቆፍጣናው ሆኗል። ለነገሩ ጋዜጠኛው አከራዩ የሚሉትን አጥቶት አይደለም። ይልቁንስ የሆነውንና የማያምንበትን መስሎ ለመታየት በሚያደርገው ጥረት ከራሱ ጋር መታረቅ ባለመቻሉ ምክንያት የመጣ ነው። ከራሱ ጋር መታረቅ ያልቻለ ሰው ደግሞ በሂደት ጥርጣሬንና ሰዋዊ ያልሆነ ባህሪን እያዳበረ በመሄድ ጥላቻና ምቀኝነት መሞላቱ አይቀርም። በማህበረሰቡ ላይ ወደር የሌለው ጥላቻ የሚፈጠርበት ግለሰብ ጤንነት አጠያያቂ ከመሆኑም ባሻገር የሚፈጠረው አደጋ ነጥሮ ወደራስ መመለሱ አይቀርም። ተራራን ንዶ ሜዳ ለመፍጠር የሚተጋ ግለሰብ በተራው እንደ ሸንኮራ አገዳ ተመጦ ሲጣል አውላላ ሜዳ ላይ ግርሻቱን ይጋተዋል። የማነስ ፈንገስ!!
“በፌስታሉ” ቴአትር ምቀኝነት የወለደው “የማነስ ፈንገስ!” ሰተት ብሎ ወደ በቀለኝነት ሲገባ እንመለከታለን። ከሁሉም የከፋው የበቀለኝነት መስፋፋቱ ከግለሰብ አልፎ “ኢትዮጵያዊነት” ላይ ያነጣጠረ መሆኑ ላይ ነው። በኢትዮጵያውያን መካከል ጥላቻ፣ አለመተማመን፣ የጠላትነት መንፈስ እንዲሰርጹ በታቀደ መልኩ እየተሰራ መሆኑ “ኢትዮጵያዊነት”እንዲደበዝዝና ዝቅ ብሎ እንዲታይ እየተደረገ ነው” ጠላቶች የበቀል ጅራፋቸውን ጠርብ ጠርብ የሚያክሉ የእልፍኝ አስከልካዮችንና ለመታመን ሲሉ ቆዳቸውን የሚገፉ ተበቃዮችን በመመልመል አሰማርተዋል። የስነ-ልቦና ምሁራን እንደሚነግሩን ከሆነ እንደዚህ አይነት መሪዎች ለመታመን ሲሉ የሚሄዱበት ርቀት ከጳጳሱ ቄሱ የሚሆንበት እድል ሰፊ ነው። እንደዚህ አይነት ሰዎች እንደ ህጻን ልጅ ናቸው። በየጊዜው ሙገሳና ውዳሴ ይፈልጋሉ። እንደ ሟቹ መለስ ዜናዊ በተለያዩ መድረኮች የተለያዩ ነገሮች የሚናገሩ በመሆኑ የወረተኝነት አቋም ያራምዳሉ። መዳረሻቸው አስመሳይነት የተላበሰ በቀል ነውና ሊያርማቸውና ሊያርቃቸው የሚፈልገውን በሙሉ እንደ “አባት ገዳይ” አድርገው ይቆጥራሉ። አንዳንዶቹ ከግማሽ ክፍለዘመን በፊት “አሜሪካን ፈርስት” የሚል መሪ ቃል ከፋሺዝም መርሆ የቀዳው አሜሪካዊ ሲቪል ቨርትስ የፖለቲካ አቅጣጫ እንደ አዲስ ግኝት ሊጠቀሙበት የሚፈልጉ “ዶናልድ ትራምፖች” መኖራቸው እሙን ቢሆንም አስተሳሰባቸውን ታግለን ማስጣል አልቻልንም።
(በነገራችን ላይ የቀድሞ አለቆቼ “ኢትዮጵያ ትቅደም” የሚለው ፍልስፍና ከፋሺዝም የተቀዳ መሆኑን ደጋግመው ሲናገሩ አድምጫለሁ። እውነታውን ለታሪክና ለመሪ ቃሉ ባለቤቶች እንተወውና የቀድሞ አለቆቼ ከደርግ እጅግ በጣም አንሰው “ቅድሚያ ትግራይ” ሲሉ መኖራቸውና የውርስ ተከታይ ማፍራት መቻላቸው አሳዛኝ ይሆናል። ነገ ኢትዮጵያን የመምራት ፍላጎት የሚሰንቅ የለውጥ አመራር (ትራንስፎርሜሽናል ሊደር) መጀመሪያ ትግሬነቴ፣ አማራነቴ፣ ኦሮሞነቴ፣ ጉራጌነቴ፣ ከንባታነቴ፣ ሲዳማነቴ….. ወዘተ ማለት ከጀመረ ኢትዮጵያዊነት ህብሩን በሁለተኛ ደረጃ አንዳንዱም አልፎ ሄዶ በጠላትነትና ተበቃይነት እያስቀመጠ ነው።)
***
የእያዩ ፈንገስ ፌስታሌን ቴአትር ከፊል ጭብጥ ወደ ማጠቃለል እያመራሁ ነኝ። ይሁንና አንድ የማጠቃለያ ሃሳብ አእምሮዬን መላልሶ ይጎበኘኝ ጀምሯል። የአዲስ አበባ (ኢትዮጵያ) መፃኢ እድልና እጣ ፋንታ ምን ሊሆን ይችላል?…. አላውቅም። የሞተ ተስፋ ግን የለኝም። ለሊቱም እንደሚነጋ እምነት አለኝ። መንገዱን ሹል ድንጋዮች እንደተጠቀጠቁበት ባውቅም የነፃነት ጉዞአችን እንደማይስተጓጎል ራዕዩ አለኝ። እንደ እያዩ ፈንገስ መራሩን ሀቅ እስከተጋፈጥን ድረስ “ከጨለምተኝነት” የምንወጣበትና ለሊቱ የሚነጋበት ጊዜ ሩቅ አይደለም። ይሄ እውን እንዲሆን ግን መሰረታዊ ጥያቄዎቻችንን የሚመልስ ቁጭትና ንዴት ውስጥ መግባት ይኖርብናል። የኢትዮጵያን ሁኔታ “በኢትዮጵያዊነት” ስሜት ውስጥ ሆነን በቁጭት ማየት፣ መስማት፣ መጋፈጥና ማሰላሰል ያስፈልጋል። ከ”ተዋራጅነት ስሜት” መውጣት የምንችለው ከልባችን መናደድ ስንችል ብቻ ነው። ኢትዮጵያን ከወረሯትና በጥቁር ፕሮፖጋንዳ ከሞሏት የቀን ጅቦችና የሌባ አይነ ደረቆች መላቀቅ የምንችለው መተባበር ስንችል ብቻ ነው። በተመሳሳይ መንገድ ኢትዮጵያ እንድትፈርስ የቁም ቅዠታሞችንና የማፍረስ ፕሮግራም ነዳፊዎችን ወደ ሰገባቸው ማስገባት የምንችለው ስንናደድ፣ ጨጓራችን ሲላጥና ቆሽታችን ድብን ሲል መሆኑን ልናውቅ ይገባል። ለዚህም ከወዲሁ መዘጋጀት ይኖርብናል። አንጋፋው ብዕረኛ ሙሉጌታ ሉሌ “ሰው ስንፈልግ ባጀን” በሚለው መጣጥፍ መናደድ ትልቅ ነገር እንደሆነ ይገልጥልናል።
እንዲህ በማለት፣
“መናደድ ትልቅ ነገር ነው። መናደድ ብንችል ደግሞ አንዱ የዚች አገር ማዳኛ የትግል መቅደም ይሆናል። ግን ለመናደድ ለመብሸቅና ከተቻለም እህህህ ብሎ ደም ለመትፋት ዝግጁ መሆን አለብን።…. ችግሩ አንናደድም። ንዴታችን ወጥቶ ወደ ተግባር ሲተረጎም አይታይም። ግን በየቤቱ፣ በየመሸታ አዳራሹ፣ በየቢሮው ፋይዳ የሌለው ንዴት በንዴት ቋንቋ ሲገለጥ እሰማለሁ። እነዚህን ሰዎች ደግሞ ልሰማቸው አልፈልግም። ጆሮዬ የተራበው ሌላ ሌላ ነገር ነው። ባጭሩ የተግባር እርምጃ።”
አንጋፋው ብዕረኛ እንደገለጠው ውርደታችንን ነቅሰን ማውጣት ይኖርብናል። የእያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ ከቄዬው መፈናቀል፣መገደል፣ መታፈን፣ መሰደድና መጥፋት ሊያሳስበን ይገባል።…በመሰደባችን፣ በመዋረዳችንና ሱሪያችን ከመቀመጫችን ዝቅ ተደርጎ በእሳት አርጩሜ በመገረፋችን ሊወቀስ የሚገባው ማነው? ማለት ይኖርብናል።….. ራሱን ከውርደት ማዳን የተሳነው ግለሰብ ራሱን ተወቃሽ ሳያደርግ ማንን ሊያደርግ ይችላል? “የሚጥለውን የማያውቅ የሚያነሳውን አያውቅም” ማለት ይሄ ነው።
ኧረ ለመሆኑ ስንት አመት የሃዘን ማቅ ለብሰን “አበስሁ ገበርሁ” እያልን ህይወታችንን እንገፋለን?….. በዙሪያችን ምን እየተካሄደ እንደሆነ ሳይገባን በ”ማነስ ፈንገስ” ተመተን እንኖራለን? …እርስ በራስ መተማመን እና በራሳችን እምነት (faith) አጥተን ተስፋችን እየሞተ እንኖራለን…እስከመቼ በማናውቀው የጥቁር ሰማይ ላይ የመንገዳችንን ኮከብ አብርቶ የሚያነጋልን ሰው (“ይንጋት ብቻ!) በመፈለግ እንቧትራለን?…. ኧረ! እስከመቼ ጆሮ ያልፈጠረበት አፍኖ ገዥ አፍንጫውን ፎንኖ እንዲገዛን እንፈቅዳለን? ….. እኮ! እስከመቼ ባለስልጣንና ባለሃብት መለየት በሚያቅት ልጓም የሌለው የስልጣን በቅሎ ላይ ቁጢጥ ያሉትን እየተመለከትን የጾም ሽለላና ቀረርቶ እያሰማን እንዘልቀዋለን?…..እስከመቼ በተስፋ መቁረጥ ውስጥ ሆነን ጠላትና ወዳጃችን መለየት አቅቶን እጃችንን ወደ ትክክለኛው ሰው መዘርጋት ተስኖን እንኖራለን?…..
አረረም መረረም ዛሬ ያለንበት ደረጃ የመንገዱ ቀይ መብራት ደምቆ የሚታይበት ነው። መንገዱ ደግሞ ሀገር ነው!….
“አለቃ! መንግስትህ በቅዱስ መፅሃፉ ደጋግመህ ወዳወሳሃት ኢትዮጵያ ይመጣ ዘንድ ፍቃድህ ይሁን! አሜን!”
ህብር ሬድዮን በህብር ሬዲዮ ድህረ ገጽ ወይም በቀጥታ በስልክ ለማዳመጥ 712 -432-8451 መደወል ብቻ በቂ ነው በእንግሊዝ ለምትኖሩ በ01405770140 በስልክ ማዳመጥ ይቻላል። ዘወትር በድህረ ገጻችን፣ ከ googel app store Hiber Radio ወደ ስልክዎ በመጫን ካልሆነም በዘሐበሻ እንዲሁም በተጠቀሱት ስልኮች ማዳመጥ ይቻላል።