ከኤርትራ የተመለሱ ሀገር ወዳድ ዶሮዎችን በተመለከተ በጋራ የተሰጠ መግለጫ

doro_sudan_er_01

ጋዜጠኛ ጌታቸው ሽፈራው(ከአዲስ አበባ)

ለበርካታ አመታት ከገበያ በመጥፋት የኢትዮጵያን ህዝብና መንግስት ለማራራቅ በሚፈልጉ የስግብግብ ነጋዴዎች ተላላኪ ፀረ ሰላም ዶሮዎች አማካኝነት ኤርትራ ውስጥ ሲደራጅ የነበረው የዶሮ ክምችት ብሔራዊ የመረጃና የደህንነት አገልግሎት በዚህ ሃይል ውስጥ ከነበሩ ሃገር ወዳድ ዶሮዎች ጋር ምስጢራዊ የሆነ የግንኙነት ስርዓት በመመስረት በተሰራው የተቀናጀ የኦፐሬሽን ስራ አማካይነት በተደራጀ መልኩ ጫጩቶቹን ጨምሮ ከነሙሉ አባላቱ መስከረም 1 ቀን 2008 ዓ. ም. ወደ ሃገሩ እንደገባ ማድረግ ተችሏል፡፡

ኤርትራ ውስጥ በግንባር ቀደምነት የኤርትራ መንግስት ባደራጃቸው ጥቃቅንና አነስተኛ የዶሮ አርቢዎች ማህበር የሰለጠኑት እነዚህ አሸባሪ ዶሮዎች ባደራጁት የጥፋት ሀይል ውስጥ ከሚገኙ ሃገር ወዳድ ዶሮዎች ጋር የተጀመረው ግንኙነት ከአንድ አመት በላይ የቆየ እድሜ ያስቆጠረ ነው፡፡ ወደ እናት ሀገራቸው የተመለሱት ዶሮዎች በአንድ በኩል ሃገራችን በዘመናዊ መንገድ እየተካሄደ ባለው የዶሮ እርባታ ምክንያት በርካታ ዶሮዎች በቂ ምግብና ውሃ ስለሚቀርብላቸው መብትና ጥቅማቸው እየተጠበቀላቸው መሆኑን በመገንዘባቸው፣ እንዲሁም ኤርትራ ውስጥ በአነስተኛ እና ጥቃቅን አርቢዎች የታቀፉት ፀረ ኢትዮጵያ ዶሮዎችን የጥፋት አጀንዳ እየተረዱ የመጡና በምንም መንገድ የዚህ የጥፋት ተልእኮ መሳርያ በመሆን ማገልገል የለብንም የሚል ጠንካራ እምነት የያዙ የቡድኑ የአመራር አባላት ከብሔራዊ የመረጃና ደህንነት አገልግሎት፣ ከኢትዮጵያ ዶሮ አርቢዎች ማህበር ጋር ምስጢራዊ ግንኙነት በመመስረት በተለያየ መንገድ የአሸባሪ ዶሮዎችን የጥፋት ተልእኮ በማኮላሽት በጋራ ሲሰሩ ቆይተዋል፡፡

በዚሁም መሰረት በቅርቡ የኤርትራ ዶሮ አርቢዎች በዶሮ እርባታ ማዕከላት እንዲታቀፉና ከፀረ ሰላም ዶሮዎች ጋር አብረው እንዲኖሩ ያዘጋጁትን ስምምነት ላይ የስብስቡ ኮር ሀይል የሆኑት ኳኩናዎች በእርባታ ማዕከሉ የሚገኙት ዶሮዎች ምክትል አዛዥ ሆነው ተመርጠው የነበር ቢሆንም በተሰጣቸው ተልእኮ መሰረት ሌሎች ሃገር ወዳድ ኳኩናዎችን በማሳመንና በማደራጀት የፀረ ሰላም ዶሮዎችን ተልእኮ ሲያከሽፉና አጠቃላይ ሂደቱን ልማታዊ መንግስቱና ይህ ልማታዊ መንግስት የፈጠራቸው የዶሮ አርቢዎች በሚፈልጉት መንገድ ሲመሩት ከቆዩ በኋላ ግዳጃቸውን እጅግ አኩሪ በሆነ መንገድ ፈፅመው በርካቶች የዶሮ እጥረት ይፈጠራል፣ ዶሮ ይወደዳል፣ ሳንገድፍ መዋላችን ነው ባሉበት በዘመን መለወጫ ቀን ወደ እናት ሃገራቸው ተመልሰዋል ለገበያ ቀርበዋው የስግብግብ ነጋዴዎችን አሉባልታ በማክሸፍ ገበያውን ለማረጋጋት ችለዋል፡፡

ወደ ሀገራቸው የተመለሱት ዶሮዎች ምንም እንኳ የኤርትራ ዶሮ አርቢዎችና ለእነዚህ ተላላኪ በመሆን ወደ ኤርትራ በመሄድ ፀረ ሰላም ተግባራቸውን ሲፈፅሙ የቆዩ የስግብግብ ነጋዴ ወኪል የሆኑ የፀረ ሰላም ዶሮ መሪዎች ኢትዮጵያ ውስጥ የዶሮ እጥረት እንዲኖር የነደፉትን አጥፊ ስልት በሚገባ ከተረዱ በኋላ ቶሎ ብለው ወደ ሃገራቸው በመመለስ እጥረቱን ለማቃለል ከፍተኛ ፍላጎት አሳይተዋል፡፡

በዚህ ከአንድ አመት በላይ የዘለቀ ምስጢራዊ ግንኙነት ከብሔራዊ የመረጃና የደህንነት አገልግሎትና ሀገር ውስጥ ከሚገኙት ዶሮ አርቢዎች በሚሰጣቸው አቅጣጫ መሰረት የሻዕቢያ ዶሮ አርቢዎቹንና የየሌሎች የጥፋት ሀይሎችን ተንኮልና ሴራ እያከሸፉ እንዲቆዩና መጨረሻ ላይ ፈንግል የሚባለው በሽታ የሚበረታበትን የክረምት ወር በሞቃታው የኤርትራ ክፍል አሳልፈው ህዝብ ዶሮ በሚፈልግበት የዘመን መለወጫ ላይ ግዳጃቸውን በሚፈለገው መንገድ አጠናቅቀው እንዲወጡ በተደረሰው መግባባት መሰረት ኦፐሬሽኑ በከፍተኛ ጥንቃቄ ለረጅም ጊዜ እየተመራ ቆይቷል፡፡

በዚህ ጊዜም በርካታ ለፀረ ሰላም አላማ የተመለመሉ የስግብግብ ነጋዴ ኳኩናዎችና ሌሎች ሀገር ወዳድ ጓደኞቻቸው ከሻዕቢያ ዶሮ አርቢዎች የተሰጣቸውን የጥፋት በተለይም የኑሮ ውድነትን እንዲያሻቅብ በማድረግ የኢትዮጵያ ህዝብን ከመንግስት የመነጠል የጥፋት ግዳጅ እንዲመክን በማድረግ፣ ኢንፎርሜሽኑ አስቀድሞ ለብሔራዊ የመረጃና ደህንነት አገልግሎት፣ ኢትዮጵያ ውስጥ ለሚገኙ የዶሮ አርቢ ማህራትና ሌሎች አጋሮች በማቀበል አስፈላጊ የሆነ ጥንቃቄ እንዲደረግ በማገዝ፣ ኤርትራ ውስጥ የሚካሄደውን ፀረ ኢትዮጵያ የዶሮ አርቢዎችና የስግብግብ ነጋዴ ዶሮዎች እንቅስቃሴ በተመለከተ ወቅታዊ ለብሔራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት ወቅታዊ መረጃ እንዲደርስ በማድረግ ከፍተኛ ሚና ተጫውተዋል፡፡ ከዚህም በላይ ኤርትራ ውስጥ በሚገኙ ዶሮ አርቢዎች ዘንድ የተመለመሉ ሀገር ውስጥ የሚገኙ ኳኩናዎች ኢትዮጵያ ውስጥ ሆነው ዶሮ ከገበያ እንዲጠፋና ህዝብም እንዲማረር ማድረግ አይችሉም በሚል ሀገር ውስጥ ሆነው ዶሮዎችን በማሳሳት ወደ ኤርትራና ወደ ሌሎች ሀገሮች ሲልኩ የነበሩ የስግብግብ ነጋዴ ፀረ ሰላም ዶሮዎች ሳይወዱ በግድ ሞቃታማ ወደ ሆነው ኤርትራ እንዲገቡ ተገደዋል፡፡ ከኢትዮጵያ ወደ ኤርትራ ያደረጉት ጉዞ፣ ውሃ ጥምና ሙቀትም ወሽመጣቸውን እንዲቆርጠው ለማድረግ ተችሏል፡፡

በእነዚህ ሀገር ወዳድ ኳኩናዎችና ጓደኞቻቸው የሚመራ ከ1000 በላይ የሚሆንና ሀገር ውስጥ ያለውን እጥረት የሚያቃልል የዶሮ ሀይልም አስቀድሞ በጋራ በተዘጋጀው እቅድ መሰረት በሁመራ በኩል ወደ ሃገራቸው እንዲገቡ ታስቦ የነበረ ቢሆንም ወደ ሃገራቸው ጉዞ ከጀመሩ በኋላ በአንድ የጭልፊት ቅጥረኛ ከሃዲና የዶሮ ለምድ የለበሰ አማካይነት በመጨረሻ ሰዓት ላይ ምስጢሩ ለጭልፊት ጆሮ በመድረሱና ከኢትዮጵያ ዶሮ አርቢዎች ጋር የነበረው ግንኙነት በድንገት የተቋረጠ ቢሆንም በዚያ አስቸጋሪ ሁኔታ ላይ ፈጣን የሆነ እርምጃ በመውሰድ እቅዱን ተግባራዊ ማድረግ ችለዋል፡፡ የኤርትራ የዶሮ አርቢዎች ፀረ ሰላም ዶሮዎች ባለቀ ሰዓት መረጃው ከደረሳቸው በኋላ ከኤርትራ ጭልፊቶች ጋር የጋራ ፀረ ሰላም ግንባር በመፍጠር በድንበር አከባቢ በመድረስ በሰማይና በምድር በሀገር ወዳዱ ሀይል ላይ ጥቃት በመፈፀም ለማስቆም ቢጥሩም በሀገር ወዳድ ዶሮዎች የሚመራው ሀይል ኦምሃጀርና ቀጥሎም ሱቅ አልከቲር በሚባል የድንበር ኬላ ላይ የጠበቀውን የኤርትራ ዶሮ አርቢዎች የዶሮ ሰራዊት ሙሉ በሙሉ በመደምሰስ እና በጠላት እጅ ሊወድቅ ይችላል ብሎ የገመተውን ላባ ነቅሎ በመጣል እንዲሁም ያያዘውን ያልተፈለፈለ እንቁላል በመከስከስና ወደ ሱዳን ሀምዳይት ተሻግሯል፡፡

በጉዞ ላይ እንዳሉ በገጠማቸው የጠላት ሀይል ምክንያት በሁለት ግንባር በኩል በተካሄደው ውጊያ ሀገር ወዳዱ የዶሮ ሀይል የሚመራው አመረር መንገድ በመዝጋት በቅድሚያ ከ600 ያህል ቄብና ጫጩት ዶሮዎች እንዲሻገሩ ካደረገ በኋላ ኳኩናዎችን የያዘው አብዛኛው የቡድኑ አመራር የነበረበት ከኋላ የነበረው ከ400 በላይ የሚሆን ሀይል ወደ ሃምዳይት መሻገር ችሏል፡፡

በዚህ ፍልሚያ ከፀረ ሰላም ዶሮ አርቢዎችና ከጭልፊቶች የተወጣጡት ከሰማይና ከምድር እየተመቱ የተደመሰሱ ሲሆን ለበዓል ገበያ ለመድረስ በሱዳን በኩል አድርጎ ወደ ኢትዮጵያ እየገሰገሰ የነበረው ሀይልም ቁጥራቸው ለጊዜው በውል ያልታወቁ ለእርድ ያልደረሱ ዶሮዎች ጉዳት ደርሶባቸዋል፡፡

በተመሳሳይ ጊዜ በሌላ ግንባር የነበሩ ቁጥራቸው ከአንድ መቶ በላይ የሚሆኑ ወደ ኢትዮጵያ በመግባት ላይ የነበሩ ዶሮዎች የጭልፊትና የዱር ድመትን ትኩረት ለማዛባት በሶስተኛ ግንባር ጥቃት እየተከላከሉና አስፈላጊ ሆኖ ሲገኝም በሰማይና በምድር ጥቃት እየፈፀመባቸው የነበረውን ሀይል አሸዋውን ተገን በማድረግ እየተከላከሉና እያጠቁ የገቡ ሲሆን ለመስቀል ገበያ ይደርሳሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡ ከሰማይና ከምድር በተፈፀመባቸው ጥቃት ተበታትነው የነበሩ ጫጩቶችም ወደ ኢትዮጵያ መግባታቸውን የቀጠሉ ሲሆን በአሁኑ ወቅት ኤርትራ ውስጥ የቀሩት እና መውጣት ያልቻሉ የቡድኑ አባላት እንቁላል የታቀፉ፣ በደንብ ያልነቁ ጫጩቶችና ለእርድ የማይውሉ አቅመ ደካማ ዶሮዎች ብቻ መሆናቸውን ለማወቅ ተችሏል፡፡

በዚህ አጋጣሚ ይህ ኦፐሬሽን በድል እንዲጠናቀቅ ከጅምሩ የትግራይ ክልላዊ መንግስት ያደራጃቸው ዶሮ አርቢዎችና ግንባር ቀደም እንቁላል ጣይ ዶሮዎቻቸው፣ ከፍተኛ ተሳትፎ የነበራቸው ሲሆን የአማራ ክልላዊ መንግስት ያደራጃቸው ዶሮ አርቢዎችና ተሸላሚ እንቁላል ጣዮቻቸውም ከፍተኛ አስተዋፅኦ አድርገዋል፡፡

ከዚህ በተጨማሪ ምን ጊዜም ቢሆን ኢትዮጵያ ውስጥ ሰፊ መሬት ውስደው ዶሮ በማርባት ከፍተኛ ፍላጎት ያላቸው እና አልፎ አልፎም ከኢትዮጵያ ዶሮ እየገዙ ለሀገራችን የውጭ ምንዛሬ በማስገኘት ላይ ያሉ የሱዳን ዶሮ አርቢዎች ወደ ኢትዮጵያ በመመለስ ላይ የነበሩት ዶሮዎች ሱዳን መሬት ውስጥ ከገቡበት ጊዜ ጀምሮ ጭልፊትና የዱር ድምት ጥቃት በመከላከል፣ አስፈላጊውን ጥራጥሬና ቀለብ በማቅብ፣ ዶሮ አገኘን ብለው በስስት ወደ እርባታ ማዕከላቸው ሳይወስዱ ወደ ኢትዮጵያ እንዲመለሱ አድርገዋል፡፡ በመጨረሻም ሀገር ወዳዱ የዶሮ ሀይል በኤርትራ ዶሮ አርቢዎች ድጋፍ ከተፈለፈሉት ጫጩቶቹን ጭምር በማስከተል ከእነ ሙሉ ሀይሉ በሰላም ወደ ኢትዮጵያ በመግባት ለበዓል ገበያ ደርሷል፡፡ በሀገራቸው እያጋጠመ ባለው የዶሮ እጥረት ከኢትዮጵያ እየገዙ እየወሰዱ ያሉት የሱዳን ዶሮ አርቢዎችም ዶሮዎቹን ወደ ኢትዮጵያ ከእነ ሙሉ አባላቸው እንዲገቡ ላደረጉት አስተዋፅኦ ከበዓል ማግስት ጀምሮ ያለ ቀረጥ ወደ ሀገራቸውን ዶሮ እንዲያስገቡ የወሰንን መሆኑን በዚህ አጋጣሚ ማሳወቅ እንወዳለን፡፡

የህብር ሬዲዮን ዘገባ ህብር ሬዲዮን ከድህረ ገጻችን በተጨማሪ በስልክ ለማዳመጥ 712 -432-8451 መደወል ብቻ በቂ ነው። በእንግሊዝ ለምትኖሩ በ01405770140 በስልክ ማዳመጥ ይቻላል። ዘወትር በድህረ ገጻችን ወይም ከgoogel store Hiber radio አፕሊኬሽንን ዳውን ሎድ በማድረግና  ከዘሐበሻም ማዳመጥ ይቻላል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *