ከሰይፉ ፋንታሁን ሰርግ በስተጀርባ በሄኖክ የሺጥላ

teddy_afro_on_concert_002_seyifu

ገጣሚ ሔኖክ የሺጥላ ከሰሞኑ የህወሃት <<ሞላ>> የሚለው የክህደት አስረሽ ምቺው ዘፈን በፊት ደመቅ ብሎ በማህበራዊ ሚዲያው ጭምር የሰይፉ ፋታሁን ሰርግ ብዙ ተብሎለት ነበር። ሰይፉን በተሌኢ በምርጫ 97 ወቅት ጌቶቹን ለማገልገል የሄደበትን እርቀት ያ ሁሉ ወጣት ደም ሲፈስ ምንም እንዳልጠፈጠረ አስረሽ ምቺው ከማስኬዱም በላይ አልፎ አልፎም መሰለውንና በል የተባለውን ዘለፋ መንግስት በጠላቸው ላይ ጣል ሲያደርግ ነበር። ገጣሚው በብዕሩ ወዲአ ወደማይረሳው ዕውነታ ሊወስደን የፈለገ ይመስላል። አንብቡት።

Emily Dickson ( Tell the truth but tell it Slant ) የሚል ግጥም አላት ። በጣም እወደዋለሁ ። እውነቱን ተናገር ፣ ግን ቀጥታ አትናገር ማለት ይመስለኛል ። ወደተነሳሁበት ሃሳብ በአዲስ መስመር ልገስግስ ።

ሕዝብ እየተራበ መሆኑ ከማንም የተደበቀ አይደለም ። ተማሪዎች በርሃብ ራሳቸውን ስተው የምወድቁባት ሀገር ልጆች መሆናችን ዛሬ የአደባባይ ምስጢር ነው ። በየሆስፒታሉ ደጃፎች ላይ በሽተኞች የሚከፍሉት አጥተው እንደሚሞቱ ሰምተናል ። ተመርምሮ የታዘዘለትን መድሃኒት መግዛት ባለመቻሉ ህይወቱ የሚያልፈው ሕዝብ ቁጥር ቀላል አይደለም ። በማዳበሪያ ዕዳ ተይዞ ፣ መሬቱን ለውጭ ከበርቴዎች ሰጥቶ ፣ የውቅያኖስ ውሃ እየቀዘፈ ህይወቱ ያለፈው ገበሬ ቁጥር ይህ ነው የሚባል አይደለም ። በዚህ ሰሞን እንኳ አርቲስት ሰለሞን ቦጋለ ፣ በኩላሊት በሽታ የታመመ ልጅን ለማዳን መኪናውን መሸጡ ፣ እሱን ሊያስታም ከሄደበት አስበዳሌ ሌላ የሚበላው የሚጠጣው የሌላ ልጅ እዛው( ሆስፒታል ) ውስጥ ማግኘቱ ፣ እና ወዘተ ሀገሪቷ አሁን የደረሰችበትን ውርደት ገላጭ ነው ።

ዛሬ ህጻናቶች ማደግ እና ማሳደግ የሚችል ቤተሰብ ስለሌላቸው ፣ በጉዲፈቻነት ይሰጣሉ ፣ ይሸጣሉ ። እህቶቻችን በየድህረ ገጹ ላይ እርቃናቸውን ለገበያ ይቀርባሉ ፣ ወንድሞቻችን በማንም ይረገጣሉ ፣ በጎማ እሳት ይቃጠላሉ ፣ ይታረዳሉ ፣ በየአሸዋው ይቀበራሉ ። ዛሬ ከማንነታችን ማሳያ ፣ ከምንነታችን ማስታወሻ እና መታወሻ ውስጥ ፣ አብይ የሚባሉት ነገሮች ሁሉ ወደ ጎን ገሸሽ ተደርገው ፣ አጥንት ( ሉሲ) እንግዳ ተቀባይ የሆነችበት ሀገር ልጆች ነን ። የውጭ ሀገር ( ሃያላን መንግስታትን ) የሚቀበሉት መሪዎቻችን ፣ ከመሀከላቸው አንዱም ኢትዮጵያዊነትን የሚገልጽ የሀገር ባህል ልብስ ለብሰው ሀገራቸውን ለማስተዋውቅ ስደፍሩ አላየንም ። የቁልቁሊት ጉዞው ቀጥሏል ፣ እየተገፈተሩ ሳይሆን እየተንደረደሩ መውደቅ ባህል ሆኗል ። ዛሬ ስለ ሀገር መኖር ፣ ስለ ቤተሰብ መኖር ፣ ስለ እምነት መኖር ፣ ሰው ስለሆነን ብቻ እንኳ መኖር አስቸጋሪ ሆኗል ።

ባንጻሩ ደሞ ፣ የሞላላቸው ፣ የሕዝባቸው ስቃይ አኪሩን ያቆመላቸው ፣ ሕዝብ ካልተካፈለው ሀብቱ ፣ ካልተሳተፈበት የጋራ ቤቱ ፣ ከማያውቀው ንብረቱ ፣ ያለ ከልካይ የዘረፉትን ወርቅ ፣ የቆፈሩትን እርሻ ፣ የቀሙትን መሬት ፣ በግል ካዝናቸው እየከተቱ ፣ የሀብት ጣራ ላይ ፣ የስም እና የዝና ማማ ላይ የወጡ ፣ በደም እና በንጹሃን ላብ የጨቀዬ ነጭ ኮሌታቸውን እያስተካከሉ ፣ በንዋይ የሰው ጫፍ ላይ ደርሰው፣ እነዛ አንቱ የተባሉት ፣ ሲሰርጉ ፣ ሲያሰርጉ ፣ የፈለጉትን ወጣት በስተርጅና ጎትተው ሲያስገቡ ፣ በአደባባይ ከንፈሯ ላይ ሳማት ፣ እቀፋት ፣ ደረትህ ላይ ለጥፋት እያሉ ሲሰብኩ ፣ አይተናል ። በነሱ ዓለም ሰው አልተራበም ፣ የጎዳና ተዳዳሪ የሚባል የለም ፣ እህቶች ጭናቸውን ለቱሪስቶች አይሸጡም ፣ ሀገር አድጋለች ፣ ሕዝብ ጠግቦ በልቷል ፣ ህንጻዎች እንደ ቁልቋል ጎን -ለጎን ቆመዋል ፣ ይበላል ፣ ይጠጣል ። ምንችግር አለ።

አዎ ሰይፉ ፋንታሁን ከነዚህ መጻጉ መሃይማን አንዱ ነው ። በስድስት ሚሊዮን ብር የጋብቻ ቀለበት ሰርግ ያደረገ ፣ ከዳር ዳር ( ከአዲስ አበባ እስከ አማሪካ ) ሚዜ <<የገዛ>> ያቆመ ፣ እንደ አንድ ትልቅ የሀገር ባለውለታ ፣ እንደ አንድ ትልቅ ታሪክ ሰሪ ፣ ሰርጉ የናኘ ፣ ስሙ የተጠራ ፣ ተማሪዎች በረሃብ ራሳቸውን ስተው በሚወድቁባት ሀገር ፣ ነጻነት ብርቅ በሆነበት ሀገር ፣ ችጋር በየሰው ቤት በገባበት ዘመን ፣ ስም ያለው ከበሮ ያስመታ ፣ ዳንኪራ የደነከረ ፣ <<ታላቁ !>> << ባለ ራአዩ!>> አርቲስት ።

አንዳንዴ ከኔ ይሆን ችግሩ ብዬ ፣ ትንሽ ወደ ሗላ መለስ ብዬ ፣ ሰይፉ ፋንታሁንን በምን እና በምን ስራው ነው የማውቀው ስል ራሴን ጠየኩ ። እኔ ሰይፉን የማውቀው ፣ ተከፍሎት ቴዲ አፍሮን ከ << አከሌ>> ጋ ሆኖ ሲሳደብ ፣ እኔ ሰይፉን የማውቀው ፣ ሕዝቡን ጋጠ ወጥነት ሲያስተምር ፣ ትላልቅ ሰዎችን ጋብዞ ሲያዋርድ፣ ሲዘልፍ ፣ ጸያፍ የሆኑ ቀልዶችን ለመሃረሰቡ ሲለቅ ፣ በአጠቃላይ እኔ ሰይፉን የማውቀው ኢ-ግብረገባዊ በሆኑ ባህርያቶቹ ነው ። ሰርፉን የደገሰለትም ሽማግሌ ፣ ከዚህ የተለየ ስብና ያለው ሰው አይደለም ። ይብለጥ የሚገርመኝ ግን ፣ እኛ ለነጻነት እና ፍትህ ፣ እውነት እና እኩልነት ቆመናል የምንል ሰዎች ፣ የኛ የኛ ሰዎች ሲሆኑ ፣ የወያኔ ጥፋት እና ክፋት አይሰራም እነዴ ? እንድትመልሱልኝ አይደለም የጠየኩት ፣ ራሳችሁን ትጠይቁ ዘንድ ብቻ ነው ። ከምንም በላይ ደሞ ይህ የሰይፉ ፋንታሁን ሰርግ ፣ በኢትዮጵያነታቸው እና በክብራቸው ጸንተው የቆሙ ውድ የኢትዮጵያ ልጆችን አንገት ለማስደፋት ፣ ልግባ አልግባ እያሉ በዝነ ልቦናቸው የሚዋዥቁትን ገፍትሮ ለማምጣት ፣ የተደረሰ ድግስ ነው ። በበኩሌ ፣ ወያኔ ለሞላ አስገዶም ፣ ሽማግሌው ለንዋይ ደበበ እና ለሰለሞን ተካልኝ ያደረጉትን ከሰይፉ ፋንታሁን ሰርግ ለይቼ አላየውም ። ምክንያቱም አንድ ስለሆኑ ። ግማሽ ሆዳምነት ; ከሙሉ ሆዳምነት እኩል ነው !

ቀጣይ የሰይፉ ፋንታሁን ስራዎች

መንግስት ላይ ያኮረፉ አርቲስቶችን እያግባቡ ወደ ሀገር መመለስ ይሆናል ። ማለቴ እንደ እንዬ ፣ ኩሪት ፣ ወዘተ እና ወዘተ ። ይህ የማይሆን ከሆነ ምን አለ በሉኝ ነው ያለው ያ ሠውዬ ። ለማንኛውም ለህሊናችን መኖር ብንጀምርስ ምን ይለናል ? ግማሽ እውነት አለ እንዴ ? ጠላት ቀለም አለው እንዴ ? ሞት በከለር እና ብላክ ዔንድ ዋይት የሚባል ተጀምሮ ይሆን ? እስኪ የሸገር ሚዜዎች ንገሩኝ ። የዲሲ አላልኩም !

የግርጌ ማስታወሻ

ደግ እና አሳቢ ለመባል ። ለሰርጌ ካሰብኩት ይሄን ያህል ለእንትን ረድቻለው የምትለዋ መራር ቀልድ ደሞ ጠሊቅ ነች !

የህብር ሬዲዮን ዘገባ ህብር ሬዲዮን ከድህረ ገጻችን በተጨማሪ በስልክ ለማዳመጥ 712 -432-8451 መደወል ብቻ በቂ ነው። በእንግሊዝ ለምትኖሩ በ01405770140 በስልክ ማዳመጥ ይቻላል። ዘወትር በድህረ ገጻችን ወይም ከgoogel store Hiber radio አፕሊኬሽንን ዳውን ሎድ በማድረግና  ከዘሐበሻም ማዳመጥ ይቻላል።

 

 

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *