ለመላው የእስልምና እምነት ተከታዬች እንኳን ለ1436 ኛዉ የኢድ አልአድሀ በአል በሰላም አደረሳችሁ እያልን መልካም ምኞታችንን ገልጸን ሳንጨርስ በሳውዲ የተሰማው አሳዛኝ አደጋን ተከትሎ ኢትዮጵያውያን በዚያ አሉ ወገኖቻቸው ሁኔታን ያሳስባቸዋል። የሀይማኖት ልዩነት ሳይኖር በየአገኙት አጋጣሚ በማህበራዊ ሚዲያው ሐዘናቸውን እየገለጹ ነው። በአገር ቤት ለሐጂ የሄዱ ወገኖችን ሁኔታ ቤተሰብ ማወቅ ይፈልጋል። በተለይ ሁኔታው ፈቅዶ መገናኘት ያልቻሉ ምን ያህል ስጋት ላይ እንደሚወድቁ መገመት ይቻላል። በሳውዲ የሚገኘው ጋዜጠና ነብዩ ሲራክ ተከታትሎ የደረሰበትን መረጃ እንደሚከተለው ጽፏል።
የመረጃ ግብአት … የሚና ጀማራት አደጋ … !
* ሰባት ሀገራት በአደጋው የሞቱባቸውን ዜጎች ዝርዝር አውጥተዋል * የኢትዮጵያ ሀጃጆች ሁኔታ እስካሁን አልታወቀም
ትናንት ማለዳ በሚና ጀማራት መዳረሻ በሆነው አንድ መንገድ በተፈጠረ ግፊያና መጨናነቅ ከሞቱት 717 ሰዎች መካከል ሰባት ሀገራት በአደጋው የሞቱባቸውን ዜጎቻችን ዝርዝር አውጥተዋል። ዝርዝሩን ካዎጡት መካከል ኢራን 131 ፣ ሞሮኮ 87 ፣ ህንድ 14 ፣ ፖኪስታን 7 ፣ አልጀሪያ 3 ፣ ኢንዶኖዥያ 3 እና ኒዘር ላንድ 1 መሆናቸው ተጠቁሟል ። በአደጋው ከፍተኛ ጉዳት ከደረሰባቸው ዜጎች መካከል ግብጽና ናይጀሪያ ይገኙበታል ቢባልም የሚሲዮን መስሪያ ቤቶቻቸው እስካሁን በአደጋው ስለተጎዱ ዜጎች ያወጡት መረጃ የለም !
በአደጋው ኢትዮጵያውያን ስላሉበት ሁኔታ ለማጣራት ባደረግኩት ሙከራ የሞቱና የቆሰሉ እንዳሉ ለማረጋገጥ ችያለሁ ። ሁኔታው በይፋ ስለመታዎቁ የጠየቅኳቸው እዚያው ሚና የሚገኙ የጅዳ ቆንስል አንድ ዲፕሎማት የሞቱና የቆሰሉ ስለመኖራቸው ለማረጋገጥ ያደረጉት ሙከራ እስካሁን አለመሳካቱን ገልጸውልኛል ። የማጣራቱ ሂደት የሚከዎነው ወደ ሳውዲ ሲገቡ በሰጡት የጣት አሻራ አስፈላጊና ግዴታ መሆኑን የሳውዲ መንግስት በኩል እንደተገለጸላቸው ጠቁመውኛል ። የማጣራቱ ሂደት ጊዜ እንደሚዎስድ በሌላ በኩል ከአንድ ከፍተኛ የጤና ጥበቃ ሰራተኛ ያረጋገጥኩ ሲሆን የሞቱትና የቆሰሉትን ለመለየት ብቸኛው አማራጭ ለሀጅ የመጡትን ሰብስቦ በሚደረግ ቆጠራ መሆኑንና ይህም በሌሎች የሀጃጅ ኮሚቴዎችና ዲፕሎማቶች በቅንጅት መስታት ብቸኛው አማራጭ መሆኑን ጠቁመውኛል!
በአደጋው ጉዳት ከደረሰባቸው ሃጃጆች መካክል በዛሬው እለት በአንዳንድ የጅዳ ሆስፒታሎች ሀጃጅ ቁስለኞችን መቀበል መጀመራቸውም ተጠቁሟል !
ይህ በእንዲህ እንዳለ በትክክል ከሳውዲ ጋር በትነረሽ በትልቁ የምትነታረከው ኢራን የሀጃጆች ለአደጋ መጋለጥ ከሳውዲ የዝግጅት ጉድለት ነው የሚል ነቀፋ እያሰማች ነው ። የአደጋው ዋና ምክንያት እየተጣራ ቢሆንም የሳውዲ ጤና ጥበቃ ሚኒስትር አንዳንድ ስርአትን ያልተከተሉ ሀጃጆች በፈጠሩት ግፊያና ትርምስ አደጋ መከሰቱን መግለጻቸው በኢራን ባለስልጣናትና ሚዲያዎች ነቀፋ ሰንዝረውባቸዋል ! በተፈጠረው አደጋ መነሻ ምክንያት ዙሪያ የታዘቡትን እንዲገልጹልኝ በስልክ ያነጋገርኳቸው አንዳንድ ሃጃጆች በተለይም የግብጽና የናይጀሪያ ሀጃጆች ከተፈቀደው መንገድ ውጭ ሲተላለፉ መጨናነቅና ግፊያ በመፍጠራቸው ለአደጋው መከሰት ዋና ምክንያት መሆኑን ጠቁመውኛል !
ቸር ያሰማን ፣ ተሞቱትን ነፍስ ይማር !
ነቢዩ ሲራክ መስከረም 14 ቀን 2008 ዓም
የህብር ሬዲዮን ዘገባ ህብር ሬዲዮን ከድህረ ገጻችን በተጨማሪ በስልክ ለማዳመጥ 712 -432-8451 መደወል ብቻ በቂ ነው። በእንግሊዝ ለምትኖሩ በ01405770140 በስልክ ማዳመጥ ይቻላል። ዘወትር በድህረ ገጻችን ወይም ከgoogel store Hiber radio አፕሊኬሽንን ዳውን ሎድ በማድረግና ከዘሐበሻም ማዳመጥ ይቻላል።