የፓርላማ አባላት ሲባሉ በሌላው አገር ሽንጣቸውን ገትረው የሚሟገቱ፣ አንዱ ከሌላው ለሕዝብ ተሻለ እሰራለሁ የሚሉ፣ ከፍተኛ የፖለቲካ ስልጣን ያላቸው ፓርላማ መግባትም ቀላል አልሆነ ፈተና ነው። ባለፉት ሃያ ሶስት ዓመታት የኢትዮጵያ ፓርላማ በሕግ የተሰጠውን ስልጣን የማይጠቀም የገዢውን ፓርቲ ሰዎች ከ95 በመቶ በላይ ያሰባሰበ ነበር።የዘንድሮው ደግሞ ለይቶለት መቶ በመቶ ሆኗል። ያው በእንቅልፍ ተጀምሯል። ነገሩን አስቂኝ የማያደርገው እና ምን ያህል በአገርና በሕዝብ ላይ መቀለድ የት ላይ ያበቃል የሚያሰኘው ገዚው ፓርቲ እነዚህኑ እጅ ሰቃዮችና እንቅልፋሞች እየተጠቀመ በሕግ ስም ሲቀልድ የፈለገውን ሲአውጅ የሚውልበት ቤት መሆኑ ሲታሰብ ነው። ዛሬ ጋዜጠኞች፣ነጻ አሳቢ ዜጎች፣የፖለቲካ ፓርቲ ዋና ዋና ወጣትና አዛውንት መሪዎች ታስረው <<ጸረ ሽብር ሕግ>> እየተባለ የሚጠቀስባቸው በዚህ መንገድ በእንቅልፍና በእጅ ሰቀላ የወጣ ነው። በአገሪቱ አሳሳቢ ድርቅ አደጋ አለ። የስርዓቱ ትኩረት የዘንድሮውን የኢህአዴግ ቋሚ ም/ቤት (አንዳንዶች ዛሬም ኣሳስተው <<ፓርላማ>> ይሉታል) በእንቅልፍ ተጀምራል። ጋዜጠኛ ጌታቸው ሽፈራው ሁኔታውን ታዝቦ ከአገር ቤት ጽፏል። አንብቡት።
(በጌታቸው ሽፈራው)
አምስተኛው ምክር ቤት ልዩ ከሚያደርጉት ነገሮች መካከል በድሮ ስርዓት በተለየ በርካታ ሴቶች የምክር ቤቱ አባላት መሆናቸው ነው፡፡ እነዚህ ሴቶች የድጋፍ ድምፅ በሚሰጥበት ጊዜ ከወንዶች እኩል አንዳንዴም ፈጥነው እጃቸውን በማውጣት ምክር ቤቱ የሚያቀርባቸውን ዕጩዎች በሙሉ ድምፅ ለማሳለፍ የበኩላቸውን በማድረግ ብቃታቸውን በዓለም ህዝብ ፊት እያስመሰከሩ ይገኛሉ፡፡
ይሁንና በምክር ቤቱ የስራ ዘመን ሁለተኛ ቀን የምክር ቤቱ አባላት ተኝተዋል በሚል አንዳንድ እንቅልፍ ምን እንደሆነ በውል ያልተረዱና ምክር ቤቱን የጎዱ የመሰላቸው ሀይሎች ትችት እያቀረቡ ይገኛሉ፡፡ በመጀመሪያ ደረጃ እነዚህ ግንባር ቀደም አባላት ጠረጴዛቸው ላይ በግንባራቸው መደገፋቸውን እንጅ መተኛታቸውን የሚያሳይ መረጃ አልተገኘም፡፡ መተኛታቸው ባልተረጋገጠበት ሁኔታ ተኝተዋል እየተባለ መወራቱ ተኝቶም ሆነ ሳይተኛ ምክር ቤቱን በቀጥታ እየተከታተለ የነበረው ህዝብን ለማደናገር መሆኑ ግልፅ ነው፡፡ አይኑን የጨፈነና ፊቱን የተሸፋፈነ ሁሉ እነዚህ ተኝተዋል የተባሉት ሴት የምክር ቤት አባላት ለህንድ የተገኘውን መልካም ተሞክሮ በመጠቀም ሁለተኛው የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ እንዴት ማሳካት እንዳለባቸው በተመስጦ በማሰላሰል ላይ ስለመሆናቸው በቀላሉ የሚረዳው ቢሆኑም ለምክር ቤቱም ሆነ ለኢትዮጵያ ከማይተኙ አካላት መልካም ነገር መጠበቅ ግን የዋህነት ይሆናል፡፡ ይህን ምክር ቤቱ በዝርዝር የሚያየው ይሆናል፡፡
የምክር ቤት አባላቶቻችን ቢተኙ እንኳ ምክር ቤቱ ውስጥ መተኛት አይቻልም የሚል ህጋዊ መሰረት በሌለበት ትችት ማቅረብ ከተችዎቹ በስተጀርባ ያሉ አካላት ስለ ምክር ቤት ያላቸው እውቀት አናሳ እንደሆነ በግልፅ አሳይቷል፡፡ እነዚህ አካላት የምክር ቤት አባላቶቻችን መንግስታችንን በሀገራችንም ሆነ በምክር ቤቱ ያሰፈነውን ሰላም ተጠቅመው መተኛታቸው እንደማያስደስታቸውም ገሃድ ወጥቷል፡፡ የምክር ቤት አባላቱ ቢተኙ እንኳ የሚያሳየው መንግስታችን ከድሮ ስርዓቶች በተለየ ለሴቶች የሚሰጠውን ክብርና መብት ያሳያል እንጅ ሊያስተች አይገባም፡፡ የድሮ ስርዓትና የድሮ ስርዓት ባሎች ሴቶች በአደባባይ መተኛትን የማይቀበሉ ከመሆናቸውም ባሻገር ተኝተው ቢገኙ ይወስዱባቸው የነበሩትን እርምጃዎች ምን ያህል ፀረ ህገ መንግስታዊና ትዳር ሊበትኑ የሚችሉ እንደነበሩ ባለ ራዕዮ መሪያችን በዚሁ ምክር ቤት ከአንድም ሁለት ጊዜ ደጋግመው ገልፀውታል፡፡ በዚህ ረገድ አቶ መለስ ባለቤታቸው መተኛትን ጨምሮ የፈለጉትን መብቶች በማክበር አሁን በርካታ ሴቶች ወንዶችንም ይሁን የውጭ ሀይሎችን ሳይፈሩ በተከበረው ምክር ቤት ለመተኛት እንዲበቁ ትውልድ የማይረሳው ውለታ መዋላቸው፣ ከኢትዮጵያም አልፎ ለአፍሪካና ዓለም ምስሌ መሆናቸው መረሳት የለበትም፡፡
በሌላ በኩል የምክር ቤት አባላት በተለይም ሴቶችም ባለፉት ስርዓቶች ተነፍጓቸው የነበሩትን በደከማቸው ጊዜ በየትኛውም ቦታና ጊዜ የመተኛት መብትን በሚገባ እየተጠቀሙ እንደሚገኙ ምክር ቤቱ ገና በሁለተኛው ቀን የስራ ውሎው ማስመስከሩ እጅግ የሚያኮራ ሆኖ አግኝተነዋል፡፡ ሌሎች የምክር ቤት አባላት መብታቸውን በሚገባ እንዲጠቀሙ ልምድ እንደሚያስገኝላቸውም ይታመናል፡፡ በተጨማሪም ሴቶች ምክር ቤቱ ውስጥ መብታቸውን በስፋት እየተጠቀሙ እንደሚገኙት ወንዶች ሁሉ አምሽተው፣ ሲያስልጋቸውም ጠጥተው ሊገቡ እንደሚችሉ፣ በስራ የዛለ አእምሯቸውንም ለማሳረፍ እንዲመች የፓርላማውን ጠረጴዛ ማደሱም ምክር ቤቱን ሊያስመሰግነው ይገባል፡፡ በዚህ ረገድ ተኝተዋል ከተባሉት ሴቶች ጎን የተቀመጡት ወንዶችም ሊመሰገኑ ይገባል፡፡ ምንም እንኳ ምክር ቤቱ ላይ ትችት ያቀረቡ አካላት ሴት አባላት ብቻ እንደተኙ አድርገው በማቅረብ ምክር ቤቱ በፆታ የተከፋፈለና የማይስማማ አድርገው ቢያቀርቡም የፆታ ልዩነት ሳይገድባቸው ለበርካታ ሴት የምክር ቤት አባላት ልምድ እየሰጡ የሚገኙ በርካታ ወንድ የምክር ቤት አባላት መኖራቸውም ሊረሳ ይገባም፡፡ የእድገታችን ሚስጥርም ይህ የወንድና የሴት ምክር ቤት አባላት መብት በእኩል መጠበቁ ነው፡፡
ዋናው ቁም ነገር ግን እነዚህ የምክር ቤት አባላት በርካታ በዚህን ሰዓት በድካም ሆነ በሌላ ምክንያት በየ ቤታቸው ተኝተው የሚገኙ ዜጎች ወኪል እንደመሆናቸው ምክር ቤትም ውስጥ መተኛታቸው አግባብና ከኢትዮጵያ ህዝቦች መካከል በርካታ ቁጥር ያለውን የህብረተሰብ ክፍል በሚገባ መወከላቸውን በተግባር ያሳዩነት ነው፡፡ በሁለተኛ ደረጃ የምክር ቤት አባላቱ ሌት ተቀን የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅዱን ለማሳካት እንዲሁም ሌት ሌት ምክር ቤቱ ሌሎች ተዛማጅ ስራዎች በመስራት ላይ በመሆናቸው ምክር ቤቱ እጅ ከማውጣት ጀምሮ እስከ መተኛት ያላቸውን መብት ማክበሩ የሚያስደስትና ይበል የሚያሰኝ መሆኑን ተረድተናል፡፡ ለወደፊቱም ተጠናክሮ እንዲቀጥል ይደረጋል፡፡ በሌላ በኩል ግን ምክር ቤቱ መሪዎቹን በሙሉ ድምፅ በሚመርጥበት ወቅት ‹‹ፓርላማው አንድ አይነት አመለካከት የሚራመድበት ነው›› እያሉ ለመተቸት የፈጠኑ አካላት ቢኖሩም ከሴትም ሆነ ወንድ የፓርላማ አባላት ያልተኙና በከፊል ያንጎላቹ የነበሩ መሆኑ ሲታይ ምክር ቤቱ ልዩነት የሚንፀባረቅበትና የእነዚህ አካላት ትችት ምን ያህል ስህተት መሆኑን አስመስክሯል፡፡ በቀጣይም በርካቶች መንግስታችን ለፀጥታው ዘርፍ በሰጠው ልዩ ትኩረት ሀገራችንም ሆነ ሀገራችንን የወከለው ምክር ቤት ውስጥ ያለውን ፀጥታና መልካም አጋጣሚ ተጠቅመው በፈለጉበት ሰዓት፣ በአደባባይ እንዲተኙ ሁኔታዎችን ያመቻቻል፡፡
የምክር ቤት አባላትን የተሻለ እረፍት እንዲያደርጉ በማበረታታት ሶስተኛውን የትራንስፎርሜሽን እቅድ በተረጋጋ እና በአዲስ መንፈስ እናሳካዋለን! እያረፍን እቅዱን እንደምናሳካው ቃል እንገባለን!
የህብር ሬዲዮን ዘገባ ህብር ሬዲዮን ከድህረ ገጻችን በተጨማሪ በስልክ ለማዳመጥ 712 -432-8451 መደወል ብቻ በቂ ነው። በእንግሊዝ ለምትኖሩ በ01405770140 በስልክ ማዳመጥ ይቻላል። ዘወትር በድህረ ገጻችን ወይም ከgoogel store Hiber radio አፕሊኬሽንን ዳውን ሎድ በማድረግና ከዘሐበሻም ማዳመጥ ይቻላል።