በኢትዮጵያ ያለው አገዛዝ በተጭበረበረውና መቶ በመቶ በዘረፈው ምርጫ <<አዲስ>> መንግስት መሰረትኩ ሊለው ይዳዳዋል። በሕወሓት የሚሽከረከረውን <<የፌዴራል>> ተብዬ መንግስት የሚመሩ ባለስልጣናት ተሾሙ ተብሏል። ብዙዎች ይሄ መቶ በመቶ በተዘረፈ ድምጽ የተመሰረተውን <<ፓርላማ>> ከማለት የኢህአዴግ ቋሚ ም/ቤት ማለት ጀምረዋል። በእንቅልፍ የተጀመረው ይሄ ጉደኛ <<ፓርላማ>> ሾማቸው ከተባሉት ውስጥ አንዳንዶች በስም እየተጠቀሱ ዝቅ አሉ ከፍ የሚል ጉንጭ አልፋ ክርክር ብጤ የሚያቀርቡ አሉ። የደላው አይነት ጨዋታ መሆኑ ነው። የሬድዋን ሁሴንና የጌታቸው ረዳ ሹመትን በደም ጥራት ለማየት ከሆነ ያስኬዳል። ጌታቸው ሕወሓት ሬዲዋን ደህዴን(የህወሃት አሽከር ናቸው)። ሁለቱም ከረባት አስረው አደባባይ እየወጡ በመዋሸት የሚወዳደራቸው የለም። ጠዋት የተናገሩትን መልሰው ይሽሩታል። አቶ ጌታቸው ዕውቁ የነጻነት ታጋይ አንዳርጋቸው ጽጌ ከየመን ተይዞ አዲስ አበባ ነው ያለው ሲባሉ <<በፍጹም>> ባሉ ማግስት ይዘነዋል ሲሉ ሽምቀቅ የለም። አቶ ሬዲዋን ያው ተለምደው <<እውነቱ ናፈቀኝ>> እተባሉ ቴሌቪዥን ላይ በወጡ ቁጥር ይቀለድባቸው ነበር። ለሁሉም የሰዎቹን ሹመት ጋዜጠኛ ኤልያስ ገብሩ በብዕሩ ዳሶታል። አንብቡለት።
(በኤልያስ ገብሩ)
አቶ ሬድዋን ሁሴን ከመንግሥት ኮሙኑኬሽን ጉዳዮች ጽ/ቤት ሚኒስትርነት በመነሳታቸው በጣም ደስ ብሎኛል፤ ተግባሩን ለተከታታለ፣ ለዚህ ትልቅ ቦታ የሚመጥን ሰው አልነበረምና፡፡ ሬድዋን ሥልጣኑን የብሽዘሽቅ ፖለቲካ ማራመጃ አድርጎት ነበር – ያውም በወሳኝ ህዝባዊ ጉዳዮች ላይ!!! አሸባሪው ISIS ውድ የሀገር ልጆችን አንገት በአደባባይ ሲቀላና አናታቸውን በጥይት ብሎ ሲደፋ፤ ‹‹ኢትዮጵያዊ መሆናቸው ገና አልተረጋጋጠም›› ብሎ በዜና ያስነገረ ሰው ነበር ሬድዋን! በህወሃቶች በል ተብሎና ታዝዞም ቢሆን እንኳ፣ ‹‹እምቢ›› የማለት ወኔው የለውም ማለት ነው፡፡ ሬድዋን በሚሰጣቸው መግለጫዎቹ፣ በ‹‹ምርጫ ክርክር›› ወቅትና በሌሎች ጉዳዮች ላይ የሚጣረስ ነገር ሲገልጽ እንደነበረ በስፋት ዘርዝሮ መግለጽ ቢቻልም ወቅቱ አይደለምና ልለፈው፡፡ የሬድዋንን ቦታ የተካው አቶ ጌታቸው ረዳም ቢሆን በአደባባይ ሲዋሽ እናውቀዋለን፡፡ አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ በበየመን የፀጥታ ሀይሎች ተይዞ ለኢትዮጵያ መንግሥት መሰጠቱን ተከትሎ ከሀገር ውጪ ከሚገኝ አንድ የሚዲያ ተቋም ጉዳዩን አስመልክቶ ለቀረበለት ጥያቄ መረጃው እንደሌለውና ጉዳዩንም እንደማንኛውም ሰው በማኅበራዊ ድረ-ገጽ መስማቱን ነበር በወቅቱ የገለጸው፡፡ በሌሎች ጉዳዮች ላይም፣ የተለያዩ ዓለምአቀፍ ስብሰባዎች ሲኖሩ፣ አውሮፕላን ውስጥ ቆጭ ብሎ ከውስጡ ጋር በግልጽ ያልተዋሃደ መልስ ለአገዛዙ ጋዜጠኞች ሲሰጥ በግሌ አስተውያለሁ፡፡ በባለፈው ዓመት ‹‹የምርጫ ክርክር›› ወቅትም ከዶ/ር ቴዎድሮስ ጎን ሆኖ፣ ለተቃዋሚዎች ብሽሽቅ የሚመስል መልስ ሲሰጥ እንደነበረ አይዘነጋም፡፡ …ብቻ በግሌ፣ አቶ ጌታቸው ለምቾቱ ቅድሚያ የሚሰጡ አይነት ሰው አድርጌ ነው የተረዳሁት፡፡ ቦታው ደግሞ ምቾት የሚቀድምበት አለመሆኑን እነበረከት ስምኦን ጠፍቷቸው አይሆንም፤ ‹‹የብሽሽቅ ፖለቲካውን ያስቀጥለው›› ካላሉ በስተቀር!!! እውነት እንነጋገር ከተባለ፣ ፖለቲካ ማናደድ እና ብሽሽቅ – ተኮር ከሆነ መዘዙ ከማንም በላይ ለባለቤቱ ነው፡፡ ጊዜያዊ ስልጣንን ምርኩዝ በማድረግ በማንአለብኝነት ዜጎችን በንግግር ማናደድ እና ተቀናቃኝ የፖለቲካ ሃይላትን ማብሸቅ ለቀድሞ ሟች ጠቅላይም አልበጀም፡፡ …ለማንኛውም ሬድዋንም ሄደ ጌታቸው ተተካ ለህሊና፣ ለእውነትና ለመርህ መኖር፣ ብሎም ሕዝብን ማገልገል እስካልተጀመረ ድረስ አዲስ ሚኒስትር እንጂ ለውጥ አይመጣም!!! ዳሩ፣ በሀሰት ውስጥ ሀሰት ሆነው ለቆሙት እነ‹‹መገርቱ ረጋሳ››ም በአደባባይ መግለጫ የሚሰጡበት ቀን ወጣላቸው እንበል እንዴ? (ረዥም ሳቅ ጨምሬበታለሁ) … ከሳቁ ስመለስ፣ የዛሬዋ ኢትዮጵያ የሚቀልድባት ሳይሆን ለእውነት የሚሰራላት ሰው ነው የምትሻው!!! መቀለዱ እና ቀልድን መለማመዱ ቆዩ ከበቁን!!!
የህብር ሬዲዮን ዘገባ ህብር ሬዲዮን ከድህረ ገጻችን በተጨማሪ በስልክ ለማዳመጥ 712 -432-8451 መደወል ብቻ በቂ ነው። በእንግሊዝ ለምትኖሩ በ01405770140 በስልክ ማዳመጥ ይቻላል። ዘወትር በድህረ ገጻችን ወይም ከgoogel store Hiber radio አፕሊኬሽንን ዳውን ሎድ በማድረግና ከዘሐበሻም ማዳመጥ ይቻላል።