ሳንፈራ በመሰከርን! ከዓለም ፀሐይ ወዳጆ

Mulugeta_lule_new_pic_01

ሳንፈራ በመሰከርን!

ጥቁር ካለበስን አናሞግስ ላፈር ካልገበርን አናወድስ

ይኸው እንግዲህ ተሰበሰብን በሞት መሐላ ልናድስ

ሙሾ ልናወርድ መጣንልህ ብድር ውለታ ልንመልስ

ደግነትህን ልንዘምር በቃላት ቅያሜ ልንክስ

ሃገሬም ገዷ አላማረም ላፈሯ ተምግተህ ኖረህ

አፈሯን እንኳን ሳትቀምስ በስደት ሰው አገር ቀረህ

አእምሮህ በጠላት ድርጊት ጣትህ በብዕር ሲደማ

ሳንበጅ ለእኛው ነፃነት ጆሮአችን ለእኛው ሳይሰማ

ለአገር፣ ለወዳጅ፣ ቤተሰብ ለቃላት ውበት ጥብቅና

ደከመኝአልከን በድንገት ሲያጡኝ ቢያውቁበት አልክና

ምሥጋና የምናቀርበው አድናቆት የምንቸረው

ሳንፈራ ምንመሰክረው በድን ሲሆኑ ብቻ ነው

በሕይወት አንዳንዱ እልፈት ከመግለፅ እንኳ ይከፋል

ከፍቅር አይበልጥም እንጂ ሕመሙ ከቃል ይገዝፋል

ላንድ አፍታ ዳግም ብትመጣ ላንዲቷ ሰዓት ብናይህ

ያልደፈርነውን በደፈርንዋርካ ነህ !” “ዕንቁ ነህ!” ባልንህ

በቁምህ ካወቅንህ በላይ ለእኛነት ታስፈልጋለህ

ተስፋ ነህ! ነፃነት ላጣ ጋሽዬ የት ትሄዳለህ?

ማጨለም ይቻላል እንዴ ያን ሁሉ ጨዋታ ለዛ ?

ፈገግታን አክስሞ መግደል በቅፅበት እንዲህ በዋዛ

ቤተመፃሕፍት ይሞታል እንደሰው ሳጥን ይገባል?

ባሕርን ማን ይቆልፋል ? ውቅያኖስ ማን ይገድባል?

ላንተም እንደሰው አንድ ሞት መሆኑን ማን ሰው ያስባል?

ይኖራል ብለው ነግረውን ለካስ ታሪክም ይጠፋል

የሰውም የአገርም ሚስጥር እንደጉም እያዩት ያልፋል

በአጀብ፣ በሆታ፣ በእልልታ ወደ አገራችን ሳንገባ

በስደት በሞት አለቅን እየተራጨን በእንባ

ላንድ አፍታ ጋሽዬ! ላንድ አፍታ ዳግም ብትመጣ ላንዲቷ ሰዓት ብናይህ

ሳንፈራ በመሰከርንባሕር ነህ!” “ መዝገብ ነህ!” ባልንህ

ለአንጋፋው ጋዜጠኛ ለሙሉጌታ ሉሌ ከዓለም ፀሐይ ወዳጆ 10/08/15

One Comment on “ሳንፈራ በመሰከርን! ከዓለም ፀሐይ ወዳጆ”

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *