በፈጠራ የሽብርተኝነት ወንጀል ተከሰው አንድ አመት ከአምስት ወር በላይ ፍርድ ቤት ሲመላለሱ የቆዩት የዞን ዘጠኝ አባላት ከተከሰሱበት የሽብር ወንጀል መከላከል ሳያስፈልጋቸው በነፃ እንዲሰናበቱ ተወስኗል፡፡ የልደታ ፍርድ ቤት 19ኛ ወንጀል ችሎት ዛሬ ጥቅምት 5/2008 በዋለው ችሎት ከዞን ዘጠኝ አባላት መካከል 1ኛ ተከሳሽ ሶልያና ሽመልስ፣ 3ኛ ተከሳሽ ናትናኤል ፈለቀ፣ 5ኛ ተከሳሽ አጥናፍ ብርሃኔና 7ኛ ተከሳሽ አቤል ዋበላን መከላከል ሳያስፈልጋቸው ተከሰውበት ከነበረው የሽብር ወንጀል ነፃ በመሆናቸው ከእስር እንዲለቀቁ ወስኗል፡፡
በሌላ በኩል 2ኛ ተከሳሽ በፍቃዱ ሀይሉ በብሎግ ወጥተው በማስረጃነት ከቀረቡበት የፅሁፍ ማስረጃዎች መካከል አመፅ ቀስቃሽ ናቸው በተባሉት ፅሁፎች ከሽብርተኛ ወንጀል ወጥቶ በወንጀለኛ መቅጫ ህግ 257/ሀ እንዲከላከል ተወስኗል፡፡ በፍቃዱ ሀይሉ በዋስ እንዲወጣ ጥያቄ ያቀረበ ሲሆን የዋስትናውን ጉዳይ ለማየት ለጥቅምት 10/2008 ዓ.ም ተቀጥረሯል፡፡
የዞን ዘጠኝ አባላት ከታሰሩበት ጊዜ ጀምሮ ለአንድ ዓመት ከአምስት ወር ያህል ብይን ሲጠባበቁ የቆዩ ሲሆን ለብይን 5 ጊዜ እንዲሁም በአጠቃላይ ለ38 ጊዜ ፍርድ ቤት መመላለሳቸው ይታወሳል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ ብይኑን ተከትሎ የዞን ዘጠኝ ጦማሪያኑ በገጻቸው ባወጡት ማስታወሻ ነጻ በተባሉ ባልደረቦቻቸው ስም ያለ ሐጢያታቸው በእስር ሲሰቃዩ በቆዩበት ወቅት ከጎናቸው ለሆኑ ሁሉ እና በተለይም በትልቁ እስር ቤት(ዞን ዘጠኝ) የሚኖረውን ሕዝብን አመስግነው ተከላከል በተባለው በፍቃዱ ሀይሉ ጉዳይ ትግላቸው እስኪፈታ እንደሚቀጥል ገልጸዋል። ዛሬም ስለሚያገባን እንጦምራለን ብለዋል።
የህብር ሬዲዮን ዘገባ ህብር ሬዲዮን ከድህረ ገጻችን በተጨማሪ በስልክ ለማዳመጥ 712 -432-8451 መደወል ብቻ በቂ ነው። በእንግሊዝ ለምትኖሩ በ01405770140 በስልክ ማዳመጥ ይቻላል። ዘወትር በድህረ ገጻችን ወይም ከgoogel store Hiber radio አፕሊኬሽንን ዳውን ሎድ በማድረግና ከዘሐበሻም ማዳመጥ ይቻላል።