(በታምሩ ገዳ)
የአገራቸው የመገበያያ ገንዘብ(ካዋቻ ) የመግዛት አቅሙ45% መዳከሙ ፣የመዳብ ማእድን ምርት ዋጋ ማሽቆልቆል(ዛምቢያ በአለም 10ኛዋ በአፍሪካ ደግሞ 2ኛዋ መዳብ አምራች ነች) ፣የኢነቨስትሮች መሽሽ እና የኢኮነሚያቸው ባልተጠበቀ ሁኔታ እየተንኮታኮተ መምጣት ፣ በተፈጥሮ መዛባት እና በድርቁ ሳቢያ የምግብ ዋጋ በከፍተኛ ደረጃ ማሻቀብ እና የኤሊትሪክ ሃይል አቅርቦት እጥረት ያሳሰባቸው የዛምቢያው ፕ/ት ኢድጋር ሉንጉ መፍትሄው በርካታ የገንዘብ ኖቶች ማሳተም ፣ዋንኛዋ ሸሪኳ ከሆነችው ከኮሚኒስት ቻይና ተጨማሪ የገንዘብ ብድር እና ለአለም አቀፉ ማህበረሰብ የአስቸኳይ ጊዜ የምግብ እርዳታ ጥሪ ላይ ብቻ መንጠልጠል ሳይሆን “ሁሉም የአገሪው ህዝብ በነገው እሁድ ጥቅምት 18 2015 እኤአ በመሰባሰብ ኢኮኖሚው እንዲያድግ እና ገንዘባቸው እንዲጎለብት የመዝናኛ ስፍራዎች አሰረሽ ምቼው እና ስታዲዮሞችም ለጊዜው ሆያ ሆዪውን ተወት አድርገው በመዲናይቱ ሉሳካ በሚገኘው የአርበኞች ስታዲዮም ውስጥ ተሰባስበው ብሔራዊ ጾም እና ጸሎት እንዲያደርጉ” በቅርቡ ጥሪ አሰተላልፈዋል ።
ይህ የፕ/ቱ ብሔራዊ የጾም እና የጸሎት ጥሪን በተመለከተ የተለያዩ ተቃውሞ እና ድጋፎች የተሰነዘሩ ሲሆን ዛምቢያ ፖስት የተባለው ጋዜጣ እንደዘገበው የሰራተኛ ሚኒስትሩ ፋክሶን ሻመዳ “የእኛ ጥበበኛነት ውጤት አልባ በመሆኑ ፣ የእግዜአብሔር ጣልቃ ገብነት ለመጠየቅ ተገደናል።” ብለዋል።ምንም እንኳን ዛምቢያ 85%በላይ ህዝቧ ክርስቲያኖች ቢሆኑም የእስለምና እምነትን ጨምሮ የተለያዩ አምነት ተከታዮች በነጻነት የሚኖሩባት አገር ነች።“ይህ በሄራዊ የጾም እና የጸሎት ቀን ማካሄድ ባቻ ሳይሆን በፖለቲካዊ አመለካከታቸው ፣ በጾታቸው፣ በባህላቸው እና በዘራቸው የተለያዩ ወገኖች ሰላሉ “በጋራ ከቆምን አንጸናለን ፣ከተከፋፈልን ግን ሰለምንወድቅ “የበሄራዊ እርቅ ፣ይቅር መባባል እና መግባባት ቀን(Reconciliation and Forgiveness day ) ይሁንልን” በማለት የጠየቁም አልታጡም።
የቀደሞው የአገሪቱ ብሔራዊ የእግር ኳስ ቡድን ተጨዋች እና የወቅቱ የፈዴሪሽኑ ፕ/ት ካሉሺያ ቡዋላ “ጊዜው ከፈጣሪ ጋር መነጋገር ያለብን ፣ እራሳችንን እና ኢኮኖሚያችንን የምናደሰበት ወሳኝ ወቅት በመሆኑ እሁድ እለት የሚካሄዱት የእግር ኳስ ወደደሮች በሙሉ ታግደዋል ወደ መጪው አሮብ ጥቅምት 21 2015 ተዛውረዋል” በማለት ካሉሻ የፕ/ቱን ጥሪን በደሰታ ተቀብሏል። መቼም ሁሌ የጋራ መግባባት የሚባል ነገር ከባድ በመሆኑ ይህንኑ የፕ/ቱ ብሄራዊ የጾም እና የጸሎት ጥሪን በተመለከተ የሰሜናዊ ምስራቅ የ አገሪቱ የጎሳ መሪ የሆኑት ናቲምቡ ” እናንተው (ፖለቲከኞች) የሰራችሁትን ምስቅልቅል እራሳችሁ መጠገን ሲገባችሁ እግዜብሔር ተአምር እንዲያመጣ መለምን ‘ቅሌት’ ነው።”ብለዋል።የኢኮነሜ ተነታኞች በበኩላቸው “የተነሸዋረረው የ ኢኮኖሚ ፖሊሲን አስተካከሉ እና ጸሎቱን ማካሄድ ትችላላችሁ። ሲሉ የፕ/ቱ ጥሪን ኮንነዋል። ፕ/ት ሉንጉ ሰልጣን የተረከቡት የቀድሞው ፕ/ት ሚካኢል ሳታ በድንገተኛ አደጋ መሞታቸውን ተከትሎ ነው ።
ታዲያ የዛምቢያው ፕ/ት የጾም እና የጸሎት እናደርግ ጥሪን ሰመለከተው የእኛም አገር ነገር ከ ፊቴ ድቅን አለ። ድሮ ቤተሰብ ሙሉ የሚያስተዳድረው 100 ብር ዛሬ”መጥቶ ነበር፣ እርሱም እንደ ወፏ በረረ … ወዘተ” እየተባለ ሲሾፍበት፣ ድሮ ኢትዮጵያዊነት ኩራት ነው እንዳልተባለ ዛሬ “እነዚህ ረሃብተኞች መጡብን ” እየተባለ የባዳን እስር ቤቶች የሰደተኛ ወገኖቻችን ማጎሪያዎች መሆናቸው፣ በቅርቡ ኢኮነሚው “በ ሁለት ዲጂት አድጓል፣ ምርታችንንም ለወጪ ገበያ ልናቀርብ ነው ” እንዳልተባልን ዛሬ ከ8 ሚሊዮን በላይ ሕዝብ ረሃብ አንጃብቦታል እና ደረሱልን መባሉን ሰንሰማ ፣ ድሮ ጎጆ ለመወጣት “ የሰው ፍጡር ብቻ ይሁን/ትሁን” እንዳለ ተባለ ዛሬ የብሄር እና የሃይማኖት ማጣራቱ በራሱ ታላቅ ፈተና መሆኑ፣ደሮ የህግ አንቀጽ ሳይጠቀስ “ አረ በሰንደቅ አላማው! “ ከተባለ ብቻ ሁሉም ከሕግ በታች እንዳልነበር ዛሬ ግን ችግሮች ሲፈጠሩ “ፊደራል ፣አጋዚ ፣አድማ በታኝ ወይም የእሳት አደጋ ማጥፊያ መጣ ቢባል”፣ የሕገ መንግስቱ /የወንጀለኛ መቅጫው አንቀጾች ቢጠቀሱ እንኳን ደም ፈሶ ካላዩ የማይረኩበት ዘመን መደረሱ፣ ድሮ አንድ የአገር መሪ ሆነ የሃይማኖት አባት ሲገሰጥ የሚፈራ እና የሚከበር ዘንድሮ መሪዎች ግርማ ሞገሳቸው ጠፍቶ እራሳቸው ተግሳጽ ተቀባዮች የሆኑበት ዘመን ላይ መድረሳችን በሚነገርበት በዚህ ፈታኝ ወቅት ከእኛ ከ ኢትዮጵያዊያን በላይ ጾም ፣ጸሎት ፣ እርቅ እና የቅር መባባል ማን ያሰፈልገው ይሆን? ብዮ እራሴን ጠየቅሁ።ለነገሩማ ወደሰልጣን ኮርቻ ሲወጡ እውነተኛውን መንገድ እረሱት እንጂ ጠ/ሚ/ሩም ቢሆኑ መሰረታቸው “በጌታ ቤት” ውስጥ አልነበር?
በዚህ አጋጣሚ መሪዎቻችን ፣ፖለቲከኞቻችን እና አክቲቪስቶቻችንም …ወዘተ ቢሆኑ ከዛምቢያው ፕ/ት እና ከሕዝባቸው ሰሞነኛው ብሔራዊ ርብርቦሽ ትምሀርት ቢቀስሙ የሂኛው መንገድን ቢመለከቱት የምንናፈቀው የሰላም እና የመረጋጋት ዘመን እሩቅ አይሆንም ፣እነርሱም ቢሆኑ በታሪክ ውስጥ የማይነጥፍ ውለታ ሰሪዎች ይባላሉ።
የህብር ሬዲዮን ዘገባ ህብር ሬዲዮን ከድህረ ገጻችን በተጨማሪ በስልክ ለማዳመጥ 712 -432-8451 መደወል ብቻ በቂ ነው። በእንግሊዝ ለምትኖሩ በ01405770140 በስልክ ማዳመጥ ይቻላል። ዘወትር በድህረ ገጻችን ወይም ከgoogel store Hiber radio አፕሊኬሽንን ዳውን ሎድ በማድረግና ከዘሐበሻም ማዳመጥ ይቻላል።