የአቶ አስማማው ሀይሉ አጭር የሕይወት ታሪክ (1947-2008 ዓ.ም)

asemamaw_book_04

አስማማዉ ኃይሉ በጎንደር ክፍለ ሀገር በጎንደር ክተማ ከአባቱ ከአቶ ኃይሉ ጎንጉልና ከእናቱ ከወይዘሮ አለሚቱ ገረመው እንደ ኢትዮጵያ አቆጣጠር በኃምሌ 8 ቀን 1947 ዓ.ም ተወለደ። በጎንደር ከተማ የመጀመሪያ ደረጃና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን በቀድሞዉ የቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ት/ቤት ካጠናቀቀ በኋላ፤ ወደ አዲስ አበባ በማቅናት፤ እዚያ ለጥቂት ጊዜያት ቆይቷል። የኢትዮጵያ አብዮት እንደ ኢትዮጵያ አቆጣጠር በ 1966 ዓ.ም ሲጀመርና በተከተሉት ወራትም በወቅቱ በህቡዕ ተደራጅተዉ ራሳቸዉን ለኢትዮጵያ ህዝብ ለማስተዋወቅ ዝግጅት በማድረግ ከነበሩት የፖለቲካ ድርጅቶች ዉስጥ የኢትዮጵያ ህዝብ አብዮታዊ ፓርቲን (ኢህአፓ) ተቀላቀለ። ቀጥሎም ወደ አሲምባ በመሄድ የፓርቲዉን ሠራዊት የኢትዮጵያ ህዝብ አብዮታዊ ሠራዊትን (ኢህአሠ) እንደ ኢትዮጵያ አቆጣጠር በህዳር ወር 1968 ዓ.ም ተቀላቅሏል።

አስማማዉ በትግሉ በተንቀሳቀሰባቸዉና በተመደበባቸዉ ቦታዎች ትጉህ፤ ድርጅቱንና ህዝቡን አፍቃሪና ቀልድ አዋቂ እንደነበረ ጓዶቹ ይናገራሉ። በአሲምባና በሌሎች ምስራቃዊ የትግራይ አካባቢዎች በተንቀሳቀሰባቸው ቦታዎች የትግርኛ ቋንቋን አሳምሮ ሲናገር፤ የሳሆ ቋንቋን ደግሞ በመጠኑ ይናገር ነበር። አስማማዉ የአርሶ አደሩን ባህልና አነጋገር ቶሎ የመያዝ ትልቅ ስጦታ ነበረዉ። ጓዶቹ “የከተሜ” ባህላቸዉንና ንግግራቸዉን ወደጎን እንዲተዉ አስማማዉ ሳይታክት ያሳስብ ነበር። ከአሲምባ እስከ በለሳና ደብረታቦር እንዲሁም ጭልጋ በምድብ ቦታዎቹ ሁሉ አስማማዉ ማንበብና መጻፍ የማይችሉ አርሶ አደር የሰራዊት አባሎችን ፊደልና ቁጥር አበክሮ ያስተምር ነበር።

አስማማዉ ሠራዊቱን ለቅቆ ሱዳን በነበረበት የስደት አመታት ወቅት መንግስታዊ ያልሆነ ድርጅት ዉስጥ በመቀጠር ስደተኛዉን አገልግሏል። ወደ አሜሪካ አንደ ጎርጎርያን አቆጣጠር በ1987 ሲመጣ በመጀመሪያ የአሜሪካ የስደት ኑሮውን በፊላዴልፍያ መሰርቶ ኖሯል ። በመቀጠልም በዋሽንግተን ዲሲ፤ ኮሎምበስ – አሃዮ ፤ በሂዪስተንና ዳላስ – ቴክሳስ ከተማዎች ኖሯል። በእነኚህ የአሜሪካ ከተማዎች እየተዘዋወረ በኖረበትም ጊዜ ከበርካት ኢትዮጵያውያን ጋር እንዲተዋወቅና የቅርብ ጎደኝነትን እንዲመሰርት ሲረዳው፣ ሁሉም በአንድ ድምጽ የሚመሰክሩለት ልዪ ባህሪውን ማለትም ከሰው ተጋባቢነቱን፣ ሸጋ ጸባዩን፤ አንደበት ርትኡ ብቻ ሳይሆን የደራሲነት ክህሎቱንም ጭምር ነበር።

በፊላደልፍያ በነበረበት ጊዜ በናሽናሊቲ ሰርቪስ በኢሚግራንት አማካሪነት፤ አንዲሁም በፓርክ ዌይ፣ ኦል ራይትና በፋይቨ ስታር ኩባንያዎች ውስጥ ተቀጥሮ ሰርቷል። በፊላደልፍያ የኢትዮጵያ ኮሚኒቲ ጆብ ዴቨሎፐርና ኬዝ ወርከር በመሆን በከፍተኛ ሙያዊ ብቃት በርካታ የኮሚኒቲውን አባላት ሰራ በማሰያዝ፣ በማማከር፣ በማስተርጎም ደከመኝና ሰለቸኝ ሳይል በከፍተኛ ትጋት አገልግሏል። በዚሁ ጊዜም በራሱ ተነሳሺነት በአሜሪካ የተወለዱ ህጻናት የሃገራቸውን ባህልና ቋንቋ እንዳይረሱ በማሰብ የአማርኛ ቋንቋና ባህል ለታዳጊዎች አስተምሯል። በበጎ ፈቃደኝነትም በፊላደልፍያ የኢትዮጵያ ኮሚኒቲ ውስጥ በመጀመሪያ በቦርድ አባልነት፣ ቀጥሎም የኮሚኒቲው ምክትል ፕሬዜዳንት በመሆን በቅንንነት አገልግሏል። በኮሚኒቲው ይዘጋጅ በነበረው የኢትዮጵያ ኮሚኒቲ ዘጋቢ መጽሄትንም በአዘጋጅነት አገልግሏል። በፊላደልፍያ የስነጽሁፍና የግጥም ስብስብም ንቁ ተሳታፊ ነበር።

በሂዩስተን፣ ቴክሳስ ቆይታው በአለም አቀፍ ቀይ መስቀል ድርጅት በኢሚግራንት አማካሪነት በመቀጠር ከሜክሲኮና ከሌሎች ላቲን አሜሪካ አገሮች በድንበር ዘልቀው ወደ አሜሪካ ሲገቡ የተያዙ ኢትዮጵያውያንና ሌሎች ዜጎች ትልቅ ኢሚግሬሽን ነክ እርዳታ ሰጥቷል። በዚሁም አገልግሎቱ በቮይስ ኦፍ አሜሪካ ሬዲዮ ጣቢያና በሌሎች ተመሳሳይ መገናኛ ብዙሃን ላይ በመቅረብ የስደተኛ መብት ተሟጋችነቱን አስመስክሯል። በዋሽንግተን ዲሲ እየታተመ ይወጣ በነበረው “መስኮት” መጽሄት ውስጥም ከአዘጋጆቹ አንዱ ነበር።

በአሜሪካ ቆይታዉ አስማማዉ የታወቀና የተመሰገነ ገጣሚና ደራሲ ነበር። “ይድረስ ለአያ ሻረዉ” የተሰኘዉ ቀደምት ግጥሙ ከኢትዮጵያ ገጠር በቀጥታ ወደ አሜሪካ በስደት የመጣ አርሶ አደር ያየዉንና የገጠመዉን የትዉልድ ቀየዉ ለሚኖሩት ጓደኞቹና ቤተሰቦቹ በምናባዊ ግጥም ያስተላለፈበት ነበር። “ይድረስ ለአያ ሻረዉ” አድናቆትንና ዝናን ያተረፈ ግጥም ስለሆነ በአሜሪካ የመማክርት ሸንጎ ቤተ መጻህፍት በገጣሚዉ በአስማማዉ ኃይሉ ስም ባለቤትነት ተሰይሞ ይገኛል። ይህው ግጥም ለአስማማውም ከኢህአፓ/ ኢህአሠ አባልነቱ ወቅት ይታወቅበት ከነበረው “የሚስጥር” ወይም “የሜዳ” ስም ይልቅ “አያ ሻረዉ” የራሱ ታዋቂ መጠሪያው ሊሆን በቅቷል።

አስማማዉ ከ”ይድረስ ለአያ ሻረዉ” አስከትሎ አራት መጻህፍትን ደርሷል። የመጀመሪያ ሁለቱ ቅጾች “ከደምቢያ፣ ጎንደር እስከ ዋሽንግተን ዲሲ ” ቅጽ 1 ና ቅጽ 2 ታሪካዊ ልብ ወለድ ሲሆኑ በደራሲዉ ግለ-ታሪክ ህይወት ላይ ተመርኩዞ ያለፈበትን የህይወት ውጣ ውረድ የሚቃኝ ነበር። ሌሎቹ ሁለት መጽሃፍት ግን ስለ ኢትዮጵያ ህዝብ አብዮታዊ ሠራዊት (ኢህአሠ ) እውነተኛ ታሪክ ሲሆን ፤ የኢህአሠ ታሪክ እንደ ኢትዮጵያ አቆጣጠር ከ 1964-1970 ዓ.ም ቅጽ 1 ና የኢህአሠ ታሪክ አንደ ኢትዮጵያ አቆጣጠር ከ 1970-1972 ዓ.ም ቅጽ 2 በተሰኙ ጥራዞች የተካተቱና የሰራዊቱን ምስረታ ታሪክና የትግል ሂደት የተመዘገበበት ነዉ። አስማማዉ ኃይሉ የሠራዊቱን ታሪክ በመጽሃፍ መልክ በማሳተም ያደረገዉ አስተዋጽኦ የኢህአፓና የኢህአሠ ጓዶቹ በአንክሮ ሲያስታዉሱት ይኖራሉ።

አስማማዉ እነኚህን መጽሃፍት በሚያሳትምበት ወቅት ለበርካታ ወራት ኢትዮጵያ ዉስጥ ኖሯል፤ ብዙ ጓደኞችንም እዚያዉ አፍርቷል። በተለያየም ወቅት ማለትም እንድ ኢትዮጵያ አቆጣጠር በ 2004 አና 2007 ዓ.ም በሸገር ኤፍ ኤም የቅዳሜ የጨዋታ እንግዳ ፕሮግራም ላይ ስለራሱ ህይወትና ስለ መጽሃፍቶቹ ለተከታታይ ሳምንታት ሰፋ ያለ ቃለ መጠይቅ ሰጥቷል። የዜና ዕረፍቱም ኢትዮጵያ እንደተሰማ ይህው ሬዲዮ ጣቢያ ከዚህ ቀደም ካደረጋቸው ቃለ መጠይቆች ውስጥ በመምረጥ ያለፈውን የቅዳሜ የጨዋታ እንግዳ ፕሮግራም በሙሉ ለአስማማዉ የሃዘን መታሰቢያ እንዲሆን በማሰብ ቃለ መጠይቁን ከድምጽ ላይብረሪ በማውጣት በድጋሚ አስተላልፏል። ቃለ መጠይቆቹን በመላው አለም መከታተል አንዲቻል በድረ-ገጹ ላይ ተለጥፎ ይገኛል።

አስማማዉ በቅርቡም ኢትዮጵያ በነበረበትና አምስተኛ የሆነውን ታሪካዊ ልቦለድ መጽሃፉን ደርሶ በማጠናቀቅ ለህትመት የመጨረሻው የአርትዖት ሥራ ላይ ተጠምዶ በነበረበት ወቅት በሽታው አንደገና እየጠናበት በመምጣቱ በአስቸኳይ ወደ ኮሎምበስ፣ ኦሃዮ በመመለስ ህክምናውን መከታተል ጀመረ። ከጥቂት ጊዜም በኋላ በመጀመሪያ ወደ አሜሪካ ሲመጣ ከከተመባት ፊላደልፍያ ለህክምናና ለማገገምም ያመቸኛል በሚል ከጥቂት ወራት በፊት ሊመጣ ቻለ። በዚህ አጋጣሚም ቤተሰቦቹ ይህን የአስማማዉ መጽሃፍ በቅርቡ በማሳተም ሌላ የህይወቱ መዘከሪያ እንደሚያደርጉት ይታመናል።

አስማማዉ ባደረበት ጽኑ ህመም በፊላዴልፍያ ከተማ በሚገኘው የፔንሲልቫንያ ዩኒቨርሲቲ ሆስፒታል ተኝቶ በህክምና ሲረዳ ከቆየ በኋላ፤ እንደ ጎርጎርያን አቆጣጠር ዕሮብ ኦክቶበር 14 ቀን 2015 ዓ.ም ህይወቱ አልፏል። የቀብር ሥነስርዓቱም እንደ ጎርጎርያን አቆጣጠር ቅዳሜ ኦክቶበር 24 ቀን 2015 በፊላደልፍያ የደብረ ገነት ቅዱስ አማኑኤል ተዋህዶ ኦርቶዶክስ ቤተ-ክርስቲያን ፍትሃተ ጸሎት ተደርጎ በፌርውድ የመቃብር ቦታ ይከናወናል።

በመሪር ሃዘን የሚያስቡት የአስማማው ጓዶቹ፣ ጎደኞቹና ወዳጆቹ ለአስማማዉ ቤተሰቦች መጽናናቱን ይመኛሉ። ሆኖም ግን የአስማማዉ ኃይሉ ሥራዎች ህያውና ቋሚ በመሆናቸዉ ይጽናናሉ።

እግዚአብሄር የአስማማውን ነፍስ ይማር ።

የህብር ሬዲዮ አዘጋጆች በአፍላነት ዕድሜው ለኢትዮጵአ ሕዝብ መብት እና እኩሉነት አሲምባ በረሃ ወርዶ መሳሪአ አንስቶ የታገለውን፣ ያን ታሪክ በተባ ብዕሩ ኢሕአሰ(የኢትዮጵያ ሕዝባዊ አብዮታዊ ሰራዊት) ቅጽ አንድና ሁለት በሚል በተስፋ እና በወኔ ለኢትዮጵያ ትንሳዔ ለማምጣት የተጀመረው የትጥቅ ትግል የገጠሙትን ውስጥና የውጭ ፈተናዎች አብራርታል። ባለታሪክ እንደመሆኑ የዐይን እማኝነቱን ለትውልድ አሳልፏል።በዚህ አጋጣሚ ለመላው ቤተሰቦቹ፣ወዳጆቹ፣ የትግል ጓዶቹና በአጠቃላይ ለነጻነት ወዳዶች ሁሉ ሞቱ ትልቅ ዕጦት ነውና መጽናናትን እንመኛለን።

የህብር ሬዲዮን ዘገባ ህብር ሬዲዮን ከድህረ ገጻችን በተጨማሪ በስልክ ለማዳመጥ 712 -432-8451 መደወል ብቻ በቂ ነው። በእንግሊዝ ለምትኖሩ በ01405770140 በስልክ ማዳመጥ ይቻላል። ዘወትር በድህረ ገጻችን ወይም ከgoogel store Hiber radio አፕሊኬሽንን ዳውን ሎድ በማድረግና  ከዘሐበሻም ማዳመጥ ይቻላል።

 

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *