ኢህአዴግ ማለት የአስመሳዮች ጥርቅም ነው ብል አልተሳሳትኩም! እድሜ ለአቶ ሙክታርና ለወይዘሮ አስቴር!

eprdf_002

(የትነበርክ ታደለ)

ይህን ታላቅ ርእስ ለመጻፍ ስነሳ ራሴን እንደ ሰማእት ቆጥሬዋለሁ። እውነት ለመናገር አሁን ሀገራችን ባለችበት ሁኔታ ይህ ርእሰ ጉዳይ “ብሞትም ብኖርም” ተብሎ የሚጻፍ ሀሳብ ነውና እንግዲህ አምላክ ያውቃል። እና ስለ አስመሳይ የኢሃዴግ አባላት የተሰማኝና ልበል…

1) የኦሮምያ ፕሬዚዳንት ኦቦ ሙክታር ከዲር …..(ቲቸር) (ስለዚህ ሰውዬ የማውቀውን ከማውራቴ በፊት ስለ አስመሳዮቹ የካናዳ ፖለቲከኞች ጥቂት ልበል) ካናዳ ለኦሮሞ ብሄረሰብ አባላት ምርጥ መጠጊያ መሆኗን እናውቃለን። በተለይም የአሜሪካዋ ሚኒሶታ በቅርቡ አንድ የመኪና መንገድ “የኦሮሞ መንገድ” በማለት ሰይማለች። በሚኒሶታ ክፍለ ከተማ የሚገኙ የኦሮሞ ተወላጅ ኢትዮጵያውያን ቁጥራቸው ብዙ በመሆኑ ይህንን መንገድ በስማቸው ቢሰየምላቸው ይበል እንጂ ቅር የሚያሰኝ አይደለም። (እኔን የሚያበሳጨኝ ግን እነዚህ ሰዎች ብዙ ጊዜ ስለ ውጪው ኦሮሞ እንጂ ስለ ሀገር ቤቱ ኦሮሞ ያላቸው እውቀት ቀጫጫ መሆኑ ነው!)

ይበልጥ ቅር የሚያሰኘው እነዚህ ዜጎች በጂማ ከተማ “የነጋሶ መንገድ” የሚባለውን ጎዳና አለማወቃቸው ነው። የነጋሶ ጎዳና የሚባለው ከአሮጌ ጎማዎች የተሰራው ድልድይ ሰውዬው የሀገራችን ፕሬዚዳንት በነበሩበት ዘመን ብዙም ለአገልግሎት የማይውል የፈረስ ጋሪ መንገድ (ከኩሎ በር ወደ ሸዋ በር የሚወስድ) ተራ መንገድ ( ነገር ግን እስከ አራት ሚሊየን ብር) ፈጀ የተባለና (የተበላበት) መንገድ መርቀው የከፈቱትን መንገድ የዛሬዎቹ የኦሮሞ አቀንቃኞች የማያውቁት መሆኑ ነው።

እርግጥ በሚኒሶታ የሚገኙ ኦሮሞዎች የማያውቁት የጂማን ጎዳናዎች ብቻ ሳይሆን የጂማ ነዋሪዎችን ጭምር ነው። እነዚህ ሰዎች ጂማን በአንድ ቅርጫት ውስጥ ጠቅልለዋታል። ጂማ ሲባል ከኩሎ ኮንታ፣ ከካፋ ሻካ፣ ከጃንጄሮ (የም)፣ ከጉራጌና ከብዙ ብሄሮች የተሰራች ታሪካዊ ከተማ መሆኗን አያውቁም፤ ማወቅም አይፈልጉም። ሌላው ቀርቶ ከተማዋን የቆረቆሩት አባጅፋር አንኳ ከካፋና ከጃንጄሮ ። ሚስቶች እንዳላቸውና ይህም በክልሉ ስልጣናቸውን እንዳደላደለላቸው ማመን አይፈልጉም። የካናዳ ኦሮሞዎች ችግራቸው ይሄ ነው” እውነቴን ነው! የኦሮሞን ፖለቲካ ወደ ኋላ ከሚመልሷቸው ብዙ ነገሮች አንዱና ዋናው እውነታን መዋጥ አለመቻል ነው።

እስኪ በኔ ሞት የአርሲ ኦሮሞነት እንዴት በጂማ ላይ እውነት ሆኖ ሊሰራ ይችላል? ከዋሸሁ ፈትኑኝ? ከፈለጋችሁ በቋንቋው ወይም በባህሉ ፈትኑኝ?! ፈጽሞ አንገናኝምኮ! ጂማ በአባጅፋር ምሎ ቢሞት አይቆጨውም! ከነተረቱ “አባጂፋር ኮሶ ቢጠጡ ጂማ ሁሉ ቀዘነ” አይደል የሚባለው? አርሲ ደግሞ በአውሊያው ይምላል! ሸዋ ታቦት ይዘክራል፣ ተክልዬን ይማጸናል። ጂማ አብሮ ስለመኖር ይተርካል፤ ከወሎ ዱበርቲ ጋር ይስማማል፤ ከወለጋ “ዋቀዮ ጋር ይጣላል፣ ያ አላህ! ብሎ ይጸልያል፣ ሼኮታ ቡኮ ብሎ ይማልዳል”።

እውነት ለመናገር የጂማ ኦሮሞ ስለ ኢሬቻና ቃሉ ሰምቶ ያውቃል? ለጂማ ሰው ቃሉ ማለት ጠንቋይ ነው። ስለ ቃሉ ቢሰማም “ወላሂ ሀራም ነው!” ይል እንደሆን እንጂ “አዳኮቲ” ..”ባህሌ ነው!” ብሎ አይቀበለውም።

What am I saying? የጂማ ሰው ከነችግሩ አሁንም አለ። ቤቱን ለመንገድ ስራ ለቆ! ኑሮውን ነገ ይመጣል ለተባለ ልማት ትቶ.! የተሰጠውን የጫካ ኑሮ አሜን ብሎ ተቀብሎ፣ ጣሊያን የሰራለትን ቤት አፈራሶ፣ ሴት ልጆቹን ሀረብ ሀገር ለግርድና ልኮ፣ እስኪ ግዜ ይለፍ ብሎ ኒካ ያሰረላትን ሚስቱን ስደት ልኮ …ዛሬም በትእግስት አለ!! ..

ያቺ የሚያውቃት የደቡብ ምእራብ የብረሀን ፈርጥ ተመልሳ ትመጣ ይሆናል ብሎ ዛሬም በተስፋ ይጠብቃል። የጂማ ሰው ልማትን ይታገሳል! ለውጥን ይታገሳል! እንቁራሪት በሞላበት ቤት ውስጥ ዛሬን እየኖረ ነገን በመልካም ያስባል።

….ግን ኦቦ ሙክታርና አዴ አስቴር እውነት የጂማ ህዝብ ተስፋ እንደጣለባችሁ ናቸሁ? እውነት የጂማ ህዝብ ምንም እንኳ ለስልጣንና ለእውቀት ብቁ ባትሆኑም “እስኪ ይሁን” ብሎ እንደፈቀደላችሁ ናችሁ? ~ አይደላችሁም! ረዥም ዘመን ጠብቋችኋል! እናንተ ግን ለማእከላዊው መንግስት ከመገበር በስተቀር ለአካባቢያችሁ ህዝብ ምንም እንዳላመጣችሁ እኔ ምስክር ነኝ!

ኦቦ ሙክታር! እርሶ (በምክትል ጠቅላይ ሚኒስቴርነት ማእረግ ሲመረጡ) እኔ የእርሶን አንዳንድ ወዳጆቾን አስተያየት ጠይቄ ነበር። ምን እንዳሉኝ ያውቃሉ?! “ሂድ ከዚህ!” ብለው አባረሩኝ! ማንም ስለእርሶ አስተያየት መስጠት አልፈለገም! ምክኒያቱም (ሰዎቹ እንደሚሉት) እርሶ ለስልጣንዎ እንጂ ስለ ጂማ ከተማ እድገት ወይም ስለ ህዝቡ ምንም ሀሳብ የተሻለ ሀሳብ አልነበረዎትም!

ወይዘርዎ አስቴር ማሞ…. ለርሶ ጉዳይ ብዬ ከጂማ አልፌ እስከ ኢሉባቦር ደርሼ ነበር። የርሶም ጉዳይ ያው ነው። “ወዳጆችዎ እንደነገሩኝ ከሆነ እርስዎ ስለስልጣንዎ እንጂ ስለ ክልሉ ማሰብ ካቆሙ ዘጠኝ አመት አለፈዎ!”

……ወጣም ወረደ ስለተሰባሰባችሁበት ፓርቲ ለመናገር እናንተ መነሻ ነጥቤ ናችሁ! ዛሬም ብዙ አዳዲስ ሀሳብ መፍጠር የሚችሉ ወጣቶች ልክ እንደናንተው ታፍነው ቀሩ! የሀገርን ችግር መቅረፍ የሚችሉ ጉልበቶች ክልል ላይ ዳገት ሲቧችሩ ደከሙ!……ጥያቄያችንን አሳንሰው አይተውት ለከፋ ችግር ዳረጉን!……አሁን ሃሳቤ ሳያልቅ …አቆምኩት! ምን ለማለት ፈልጌ ነው?! ጥያቄው አልተመለሰም! እናም በሰው ፊት የሚያቆም ምንም ግርማ ሞገስ የላችሁም!!! (እመለስበታለሁ!)

 

የህብር ሬዲዮን ዘገባ ህብር ሬዲዮን ከድህረ ገጻችን በተጨማሪ በስልክ ለማዳመጥ 712 -432-8451 መደወል ብቻ በቂ ነው። በእንግሊዝ ለምትኖሩ በ01405770140 በስልክ ማዳመጥ ይቻላል። ዘወትር በድህረ ገጻችን ወይም ከgoogel store Hiber radio አፕሊኬሽንን ዳውን ሎድ በማድረግና  ከዘሐበሻም ማዳመጥ ይቻላል።

 

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *