Hiber Radio : በኢትዮጵያ በረሃብ ሳቢያ ዜጎች እየሞቱና ከቀዬያቸው እየተሰደዱ መሆኑን ገለጹ፣የዕርዳታ እህል ለተረጂዎች እየተሰጠ አለመሆኑን አጋልጠዋል

ethio_famaine_008

መንግስት በርሃብ ለተጎዱት ዜጎች እርዳታ እየሰጠ እንዳልሆነ ቀያቸውን ለቀው አዲስ አበባ የገቡት የርሃቡ ሰለባዎች ለነገረ ኢትዮጵያ ገልፀዋል፡፡ ከወሎ የተለያዩ አካባቢዎች በርሃብ የተጠቁ ዜጎች ህይወታቸውን ለማትረፍ ወሎ ውስጥ ከሚገኙት ከተሞች አልፈው ወደ ጎጃም፣ ጎንደርን እንዲሁም አዲስ አበባ እየተሰደዱ ሲሆን አዲስ አበባ በርካታ ተጎጅዎች ህፃናትን አዝለው እየለመኑ ይገኛሉ፡፡ የነገረ ኢትዮጵያ ሪፖርተር ካነጋገራቸው መካከል ሁሉም መንግስት ለርሃቡ ተጎጅዎች እርዳታ እየሰጠ እንዳልሆነ ገልፀዋል፡፡ ቤተሰቦቻቸውና ጎረቤቶቻቸውም እንደነሱ ቀያቸውን ጥለው ወደ መተማ፣ ሁመራ፣ ባህርዳር፣ ደሴ፣ እንዲሁም ወደ አዲስ አበባ መሰደዳቸውን በሀዘን ገልጸዋል።

ወሎ ውስጥ ጮሬ ሶዶማ ከተባለ ቦታ ተነስታ እንደመጣች፣ አዲስ አበባ ከገባች ሶስት ሳምንት እንደሆናት የገለፀችውና ሁለት ህፃናትን ይዛ ስትለምን ያገኘናት፤ በግምት በ30ዎቹ መጨረሻ ዕድሜ የምትገኝ እናት ‹‹የመጣነው የሚላስ የሚቀመስ ስለሌለ ነው፡፡ ከብቶቻችን አልቀዋል፡፡ አዝመራ የሚባል የለም፡፡ ሰው በርሃብ እያለቀ ነው፡፡ እኛ ሴቶቹ ወደ ከተማው ስንመጣ ወንዶቹ ደግሞ ወደ ሁመራና መተማ ሄደዋል፡፡ እኛም ከዚህ የመጣነው ጉልበት ስላለን ነው፡፡ አብዛኛዎቹ ደካሞች በዛው አካባቢ ቀርተዋል፡፡›› ስትል በሀዘን ገልፃልናለች፡፡ መንግስት እርዳታ አይሰጥም ወይ ብለን ላነሳንላት ጥያቄም ‹‹ምንም እርዳታ አልተሰጠንም፡፡ እርዳታ ቢሰጥ ኖሮ ቤታችን ጥለን አንመጣም ነበር፡፡ ባያበቅልም መሬት አለን፡፡ የከተማው ሰው ይሻላል ብለን ነው ወደዚህ የመጣነው›› ስትል ስለ ርሃቡ አስከፊነትና መንግስትም እርዳታ እየተሰጠ እንዳልሆነ መግለጻን ዘገባው አስፍሯል፡፡

ባለቤቷ ወደ መታማ ሲሄድ እሷም ቤቷን ጥላ ወደማታውቀው አዲስ አበባ እየጠየቀች እንደመጣች የገለፀችልን ወጣት በበኩሏ ‹‹ቤቴ ተፈትቷል፡፡ ባለፈው አመት ከብቶችም እህልም ነበረን፡፡ ዘንድሮ ግን ምንም ነገር የለም፡፡ ጊዜው ከፍቷል፡፡ ባሌ ወደ መተማ ሄዷል፡፡ እኔም ልጄን አዝዬ እስከ ደሴ በእግሬ መጣሁ፡፡ ከዛ በኋላ እየለምንኩ ከዚህ ደርሻለሁ፡፡ ማንም እርዳታ አልሰጠንም፡፡›› ስትል ስለሁኔታው ለነገረ ኢትዮጵያ ሪፖርተር ገለጻለች፡፡

ከመርሳ ወረዳ እንደመጡ የገለፁልንና ከልጃቸው ልጅ ጋር እየለመኑ ያገኘናቸው የ65 አመት አዛውንት በበኩላቸው ‹‹ዝናቡ ሲቀር ከብቶቻችንም ሞቱ፡፡ አዝመራ የሚባልም ነገር የለም፡፡ ከመርሳ ደሴ እየለመንኩ መጣሁ፡፡ ደሴም እንደኛ ብዙ ሰው አለ፡፡ አገኝ ብሎ በየከተማው ተሰራጭቷል፡፡ ወደዚህ ይሻላል ብዬ በለመንኳት ተሳፍሬ መጣሁ፡፡ ርሃቡ ሲብስብን ወደማናውቀው አገር መጣን፡፡›› ሲሉ የርሃቡን አስከፊነት ገልጸዋል፡፡

‹‹እርዱኝ!›› እያሉ እየለመኑ ያገኘናቸው ከኬሚሴ አካባቢ እንደመጡና ከ8 ቀን በፊት አዲስ አበባ እንደደረሱ የገለፁልን ሌላኛዋ እናትም ቤታቸውን ጥለው እንደመጡና፣ ሌሎች ቤተሰቦቻቸው ወደ የት እንደሄዱ እንኳን እንደማያውቁ ለነገረ ኢትዮጵያ ገልፀዋል፡፡ መንግስት እርዳታ እየሰጠሁ ነው እንደሚል ስንገልፅላቸው ‹‹ለእኔ አልደረሰኝም፡፡ እርዳታ ተሰጠኝ ያለም አልሰማሁም፡፡ እርዳታ ቢሰጥማ ከዚህ ድረስ አልመጣም ነበር፡፡ አሁን ነው ከከተማው ሰው ትንሽ ትንሽ እያገኘን ያለነው፡፡ በየ ከተማው ስንደርስ ሰው አይነፍገንም›› ሲሉ ከህዝብ እንጅ ከመንግስት እርዳታ እንዳላገኙ መግለጻቸው በዘገባው ተካቷል ፡፡

ካሳንቺስ አካባቢ ልጅ አዝለው ታክሲ ተሳፋሪዎችን ምንም አይነት ቃል ሳያሰሙ ልጃቸውን በመዘርጋት ብቻ እንዲረዷቸው እየጠየቁ ያገኘናቸው እናትም የራሳቸውንና የታዘለውን ልጅ ነፍስ ለማዳን ቀያቸውን ጥለው ወደ አዲስ አበባ መምጣታቸውን ለነገረ ኢትዮጵያ ዘጋቢ ገልፀዋል፡፡

የርሃቡ ተጎጅዎች አዲስ አበባ ውስጥም ነፍሳቸውን ለማቆየት በጠራራ ፀሀይ ሲለምኑ እንደሚውሉና ምቹ ያልሆነ ቦታ አንድ ላይ የሚያድሩ በመሆኑ ልጆቻቸው ለበሽታ እየተጋለጡ እንደሆነ ገልፀዋል፡፡ ተማሪ የነበሩና በርሃቡ ምክንያት ለማቋረጥ የተገደዱት ልጆቻቸው ከእነሱ ጋር ወይንም ወደ ሌላ አካባቢ ነፍሳቸውን ለመዳን መሰደዳቸውን፣ በያለፉበት ከተማም በርካታ ስደተኛ እንዳለም በዚሁ ዘገባ ተመልክቷል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ በስልጣን ላይ ያለው አገዛዝ ባለስልታናት ዛሬም ድረስ የዘንድሮውን ድርቅ ተከትሎ የተከሰተውን የረሃብ አደጋ ትክክለና መረጃ የማይሰጡ ሲሆን በድርቁ ሳቢአ የሰው ሕይወት መጥፋት መጀመሩን፣በተለይ በአርብቶ አደር አካባቢዎች ቀድሞ ከብቶች በገፍ መርገፋቸውን ሳይቀበል የቆየ ሲሆን አቶ ሀይለማሪያም ደሳለኝ ድርቅ ካሊፎርኒያም አለ ማለታቸው አይዘነጋም። የቀድሞው የኮሚኒኬሽን ሚኒስትር ሬድዋን ሁሴንከብቶች የሞቱት በድርቅ ሳቢአ ሳይሆን በሰኣቱ ውሃ ስላልጠጡ ነው ማለቱም አይዘነጋም። አገዛዙ ዛሬም ከድርቁ ይልቅ ለፓርቲ ስብሰባዎች፣<<ተሃድሱ>>ለሚባሉ የፓርቲ ድግሶችና የአበል ክፍያዎች በቢሊዮን ብር የአገሪቱን ሀብት እያባከነ ሲሆን ለረሃቡ አደጋ ተገቢውን ትኩረት አለመስጠቱ ለሕዝቡ ደንታቢስነቱን ያሳያል የሚሉ በርክተዋል።

ድርቁን ተከትሎ በትክራይ ክልል የማጅራት ገትር በሽታ የተከሰተ ሲሆን የክትባት ዘመቻ መጀመሩን በሌሎች አካባቢዎች በረሃቡ ሳቢአ የተከሰቱ በሽታዎች ትክረት እአገኙ እንዳልሆነ አስቀድሞ በህብር ሬዲዮ ባለፈው ዕሁድ ጥቅምት 21 ቀን 2008 መዘገባችን ይታወሳል። በዚሁ ዘገባ እንደተጠቀሰው የመንግስታቱ ድርጅት የምግብ ፕሮግራም በኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት የተከሰተው የረሃብ አደጋ የከፋ እንዳይሆን አስቀድሞ አሳስቧል።አሁን የእርዳታ እህል የሚፈልገው የድርቁ ተጠቂ 8.5 ሚሊዮን በላይ ወደ 15 ሚሊዮን በላይ ሊያድግ እንደሚችል ያወጣውን ማስጠንቀቂያ የአገዛዙ ባለስልጣናት ትኩረት አለመስጠታቸውን ረሀብ ከተከሰተባቸው አካባቢዎች የመጡት ተጎጂዎች የሰጡት አስተያየት አጋልጧል።

 የህብር ሬዲዮን ዘገባ ህብር ሬዲዮን ከድህረ ገጻችን በተጨማሪ በስልክ ለማዳመጥ 712 -432-8451 መደወል ብቻ በቂ ነው። በእንግሊዝ ለምትኖሩ በ01405770140 እና በአውስትራሊያ 0280725172 በስልክ ማዳመጥ ይቻላል። ዘወትር በድህረ ገጻችን ወይም ከgoogel store Hiber radio አፕሊኬሽንን ዳውን ሎድ በማድረግና  ከዘሐበሻም ማዳመጥ ይቻላል።

 

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *