ነብዩ ሲራክ(ከሳውዲ)
* ከንጉሱ እስከ ደርግ በድርቅ ቸነፈር በሚሊዮን የሚቆጠሩ ዜጎች ሲጠቁ የስርዓቱ ተቃዋሚዎች የአድሃሪ ፊውዳል ፣ ያልሰመረ አገዛዝ ውጤት እንደሆነ ይናገሩ ነበር
* ንጉሱም ፣ ደርግም ኢህአዴግም የሚያስተዳድሩት ህዝብ በረሃብ እየተጠቃ ከሃላፊነት ለመሸሽ ረሃቡን መደበቅ ሙያ አድርገውታል አይተናል ፣ እያየንም ነው … ግን ለማናቸውም አልጠቀመም !
* ከአንድም ሁለት ሶስቴ በዘመነ ኢህአዴግ ” ረሃብ ቸነፈር ገባ !” ሲባል ችግሩን ገላልጦ ለመፍትሔ እንደመትጋት የሆነውን ለመደባበቅ ሲሞከር ” የተቃዋሚዎች ፕሮፖጋንዳ ነው !” ተባለ … ዝም አልን …
* የአለም መገናኛ ብዙሃንና የመንግስታቱ ድርጅት ” በሚሊዮን የሚቆጠር ኢትዮጵያዊ በርሃብ ፣ ችጋር ቸነፈሩ ሊቀጠፍ ነው ! ሰው እየሞተ ነው! ” ሲሉና መረጃ ሲያቀርቡ ፣ ሮጦ የማያመልጠው ሲቀጠፍ እማኞች በገሃድ እየመሰከሩ መረጃውን “ተፈጥሮን ትግል አንገጥም አይነትና የማይመች ውሸት ሲነገር መስማት ያማል ! በዚህ መልኩ ጸሃይ የሞቀውን እውነት የተባለውን መረጃ ያለ መረጃ ፣ ማስረጃ ለመሞገት የመንግስት ከፍተኛ ኃላፊዎች ምላሽ ለመስጠት እየተሞከሩ ነው …እኛም አያልቅብን አወገዝነው ” ያሳፍራልም ” አልን !
* ” እንኳን ዘንቦብሽ … ” እንዲሉ ቀድሞውኑ በኑሮ ውድነት ማሻቀብ የተማረሩት ዜጎች አስፈሪውን ረሃብ ሽሽት አቅም ያላቸው አስከፊውን ስደትን ሙጥኝ ብለው ወደ ሳውዲ እየጎረፉ ለመሆኑ ቋሚ እማኝ አጋጥሞኛል … ሲሰሙት ልብን በሃዘን ይሰብራል !
* ከመሀል ከተማ አዲስ አበባ በመንግስት ስር ባሉ መገናኛ ብዙሃን ዛሬ የሰማነው መረጃ ደግሞ የስልጣን ዘመናቸውን ላጠናቀቁ ፣ የመንግስት ባለ ጥቂት ስልጣናት ወደ 25,000,000 ሃያ አምስት ሚሊዮን የሚጠጋ የሀገር ሃብት የፈሰሰበት መኖሪያ ቤት ሊሰራ መሆኑን ስለ ሚፈሰው መዋዕለ ንዋይ ኃላፊዎች አይናቸውን በጨው አጥበው በድፍረት እየነገሩን ነው … የሸገር ኤፍ አምን 102.1 ስሙና ፍረዱ እዘኑ ፣ እነሆ ህዝብና ሀገር ተንቋል !
* የመንግስት ባለስልጣኖቻችን ከሳውዲ ጋር የሁለትዮሽ ስምምነት ሳይደረግ ተደረገ ብለው በሌል ስምምነት ግማሽ ሚሊዮን ዜጋ በኮንትራት ስራ ስም ወደ ሳውዲ ላኩ ፣ ጥቂቶች ናጠጡበት ብዙዎች ተጎዱ ! ኮንትራት ተብየው ከጥቅሙ ጉዳቱ በላያችን ላይ ተጫነ ! እስካሁን የድረሱልኝ ድምጽ እየተሰማ የመብት ጥበቃ አጎደሉብን !
* ያለ ጥናትና በቂ ዝግጅት ወደ ሳውዲ በኮንትራት ስራ ስም የተጋዙት እህቶች ” አብደው ” ሰሩት የሚባለው ወንጀል ዛሬም የሳውዲ መገናኛ ብዙሃን ሽፋን ከመሆን አላባራም ! ይህን መረጃ እየጻፍኩ እያለሁ ” ኢትዮጵያዊቷ የቤት ሰራተኛ የአሰሪዎችዋን ልጅ ልትገድል ስትል ተያዘች !” ተብሎ አሰቃቂውን ወንጀል በታዋቂው የ MBC 1 ዘገባ መመልከታችን እውነት ነው … ይህ የኃላፊዎቻችን አሰራር ብልሹነታችን ውጤት አይደለምን ? ይህስ ገጽታ የምንለውን የሃገር ስም አላጎደፈውም ?
* ባለስልጣኖቻችን መከራውን በመቶ ሽዎች ጫንቃ ሳያነሱልን ሳንመክርበት ሳንዘክርበት ከሳውዲ ጋር ሌላ አዲስ ስምምነት ተረቅቆ ስምምነት ትግበራው በቀጣይ ወራት እንደሚደረግ እየተነገረን ነው ! … ሌላ መከራ እየተጫብን አሁንም ብዙዎች መቃወም እንኳ ገዶን ዝም ብለናል… !
* ሀገሪቱን በአመራታቸው አሳደግን ያሉት የቅንጦት ቪላ ሲሰራላቸው ፣ ሲሸለሙ ፣ ያደገችው ሃገር ዜጎች የእድገቱ ተጠቃሚ አልሆኑም !
* የየአመቱ ከ10% ያለፈ እድገት የተባለው ባልቀረፈው የኑሮ ውድነትና በአስተዳደር በደል መድልኦ ነዋሪው አልተመቸውም ፣ ጉልበት ያላቸው የሃገር ተስፋዎች በኑሮና ፖለቲካው ተማረው አስፈሪውን ባህር በርሃውን ደፍረው ድህነቱን ሸሽተው ሞትን ደፍረው መሰደዳቸውን አላቆሙም !
* ለአደገችው ሃገር ነዋሪዎች እስከ እናድግ ባይ ፣ ስደተኞች መከራችን በዝቷል ፣ የአደገችው ሃገር ባለስልጣናት ግን የምንናገረውን እየሰሙ ” የዝሆን ጀሮ ይስጠኝ !” ማለቱ ሳትገዳቸው እውነቱን “ውሸት ” እያሉ ከህዝብ ጋር መኖር ገዷቸዋል ! ከህዘብ በተቋርኖ መኖርን ሙያ ብለው ሲኖሩ እኛ የጉድ ሃገር በማለት እንቆዝማለን !
ይህም ያማል … ያማል …. ያማል !
ነቢዩ ሲራክ ህዳር 1 ቀን 2008 ዓም
የህብር ሬዲዮን ዘገባ ህብር ሬዲዮን ከድህረ ገጻችን በተጨማሪ በስልክ ለማዳመጥ 712 -432-8451 መደወል ብቻ በቂ ነው። በእንግሊዝ ለምትኖሩ በ01405770140 እና በአውስትራሊያ 0280725172 በስልክ ማዳመጥ ይቻላል። ዘወትር በድህረ ገጻችን ወይም ከgoogel store Hiber radio አፕሊኬሽንን ዳውን ሎድ በማድረግና ከዘሐበሻም ማዳመጥ ይቻላል።