በታምሩ ገዳ
ሳሊህ ፋሪህ የእስልምና ሃይማኖት ተከታይ ሲሆን በሙያው ደግሞ መምህር ነበር።ታዲያ ባለፈው ታህሳስ 2015 አኤ አ የሶማሊያው ነውጠኛው እና አክራሪ ቡደን አልሽባብ ኬኒያ ውስጥ ማንዲራ ከተባለ አካባቢ ወደ ናይሮቢ ለሃይማኖታዊ በአል በሕዝብ መጓጓዣ መኪና ተሳፍረው የነበሩ ተሳፋሪዎችን በማሰቆም ክርስቲያንኖችን ከሙስሊም ተሳፋሪዎች በመለየት ሙስሊም የሆኑትን በነጻ በመልቀቅ 28ቱ ክርስቲያኖችን ወዲያውኑ ሲገደሏቸው የእሰልምና ሃይማኖት ተከታዩ ሳሊህ ከተሳፋሪዎቹ አንዱ ነበር ። ይሁን እና ሳሊህ “ክርስቲያን ወገኖቻችንን ለአክራሪዎች አሳልፈን አንሰጥም “ ከሚሉ ሙስሊም ወገኖቹ ጋር በመሰለፉ ከአክራሪው አልሸባብ ታጣቂዎች በተተኮሰበት ጥይት በእጁ እና በታፋው ላይ በደረሰበት ጉዳት ሳቢያ ናይሮቢ ከተማ ውስጥ በሕክምና ሲረዳ ቆይቶ ባለፈው ሰኞ ከዚህ አለም በሞት ተለይቷል ።
ሰማእቱ ሳሊህ በወቅቱ ሰለነበረው መጥፎ ሁኔታ ለቢቢሲ ራዲዮ በሰጠው አማኝነት “ አሸባሪዎቹ ወደ ተሳፈርንበት መኪና መጥተው ሙሲሊሞች ካላችሁ እራሳችሁን ከክርስቲያኖች ባስቸኳይ ለዩ እናነተን አንነካችሁም ፣ በነጻ መሄድም ተችላላችሁ አሉን። እኛ ግን 62ታችን ተሳፋሪዎችን ልቀቁን አለበለዚያ ሁላችንንም እዚሁ ግደሉን አልናቸው ታጣቂዎቹ ተደናግጠው ያገኙትን ገደለው እኔንም በጥይት አቁስለውኝ ከሰፍራው ተሰውሩ ። እኔ እስከሚገባኝ ድረስ የሃይማኖት ልዩነት ካለሆነ በቀር ሁላችንም አንድ በመሆናችን ሙስሊሞች ክርስቲያኖችን ሊንከባከቡ ክርስቲያኖችም ሙስሊሞችን ከጥቃት በመታደግ በሰላም እና በጋራ መኖር የግድ ይለናል ።” ሲል ሰለ ሰላም እና መቻቻል የነበረውን ጽኑ አቋሙን ተናገሯል ። በሙስሊም ሃይማኖት ስረአት እና ደንብ መሰረት ማንዲራ ከተማ ውስጥ ማክሰኞ እለት ስርአተ ቀብሩ የተፈጸመው ሰማእቱ ሳሊህ በኬኒያ መንግስት ዘንድ እውነተኛ ብሔራዊ ጀግና የሚል ስያሚ የተሰጠው ሲሆን የሞምባሳ አካባቢ የሙስሊሞች ካውንስል ሰብሳቤ የሆኑት ሺክ ጁማ ናጎው “ፋራህ ቅዱስ ቁራን የአንደን ሰው ህይወት ማዳን የአጠቃላይ የሰው ልጅ ዘርን ማዳን ነው የሚለውን አሰተምሮትን በተግባር የፈጸመ ትክክለኛ ሙስሊም ነው ።” ብለውታል። ሰማእቱ ሳሊህ ስላደረገው ሃይማኖታዊ እና ሰብ አዊ ተጋድሎ በክርስቲያን ወገኖቹም በኩል ታላቅ አክብሮት እና አድናቆት አልተለየውም። የኬኔያ ባብቲስት ኮንቨንሽን ቤ/ክን አስተዳዳሪ የሆኑት ዊሊንግተን ሙቲሶ “ነፍሱን ሰለክርስቲያኖች ህይወት ሲል በመያዣነት ያቀረበ ታላቅ ሰማእት ፣በሞቱ የብዙዎችን የተዛባ ሃይማኖታዊ አመለካከትን የቀየረ(ሁሉም ሙስሊሞች አክራሪነትን ይደግፋሉ ተብሎ የሚወራው ፍጹም ሃሰት መሆኑን በተግባር ያሰመሰከረ) ወገናችን ፣ ክርሰቲያኖች ዘወትር የሚኮሩበት እና የሚዘክሩት ታላቅ ሰው ነው ።”ብለውታል ።
በማንዲራ አካባቢ የሮማን ካቶሊክ ቤ/ክ ሃላፊ የሆኑት ጆን ሞሶዮካ እንዲሁ” አሸባሪዎች ሃይማኖትን ሸፋን ማድረግ እንደማይችሉ ፣ሃይማኖትም ቢሆን ከፈጣሪ ጋር መገናኛ እንጂ የሰዎች መከፋፈያ መሳሪያ ያለመሆኑን ወንድማችን ፋራህ በሚገባ አሰተምሮናል ።” በማለት ክርስቲያናዊ እና አባታዊ የሆነው ምስክረነታቸውን ሰጥተዋል። ራሺድ የተባለው የሳሊህ ወንድም በበኩሉ ለኬኒያው “ዘ ስታር “ጋዜጣ ሰለ ሟቹ ወንድሙ መሰዋትነት ሲገልጽ”የወንደሜ መሞት በኬኒያዎች መካከል የተለያዩ ሃይማኖተኞች እና የማህበረሰብ ክፍሎች እንዴት ተቻችለው እንደሚኖሩ መንገድ ጠራጊ ነው ብዩ ተሰፋ አደርጋለሁ።” ሲል ተናገሯል። ሳሊህ ምንም እንኳን የጎረቤት ኬኒያ ተወላጅ ቢሆንም የከፈለው መሰዋትነት በየትኛውም ጠርዝ ይሁን በየትኛውም ስፍራ በጎሳ ፡በጽንፈኝነት እና በጠባብነት ለወደቁ ወገኖች ትልቅ ትምህርት አለው አርሱም ተቻችሎ እና ተፈቃቅሮ ለመኖር ዋንኛ መለኪያው የጎሳችን፣ የቋንቋችን፣ የሃይማኖታችን እና የእውቀታችን ግዝፈት እና ምጥቀት ወይም የውጫዊ አካላችን ልዩነት ሳይሆን ክቡር የሆነው ሰው መሆናችን ብቻውን ከበቂ በላይ መሆኑን ነው። ፈጣሪያችን እግዚአብሔር/አላህ የወንድማችን የሳሊህ ነፈሱን ይማረው !!!!።
ህብር ሬድዮን በህብር ሬዲዮ ድህረ ገጽ ወይም በቀጥታ በስልክ ለማዳመጥ 712 -432-8451 መደወል ብቻ በቂ ነው በእንግሊዝ ለምትኖሩ በ01405770140 በስልክ ማዳመጥ ይቻላል። ዘወትር በድህረ ገጻችን፣ ከ googel app store Hiber Radio ወደ ስልክዎ በመጫን ካልሆነም በዘሐበሻ እንዲሁም በተጠቀሱት ስልኮች ማዳመጥ ይቻላል።