አክሎግ ቢራራ (ዶ/ር)
ባለፈው ትንተናየ እንዳሳየሁት፤ የኢትዮጵያ እናቶች ልጆቻቸውን ወልደው በለጋቸው ሲቀብሩ ኖረዋል። የኢትዮጵያ ረዢም ታሪክ የተመሰረተው ያፈራቻቸው ልጆቿ ተቆርቁረው በህይወታቸውና በንብረታቸው ዋጋ ስለከፈሉ ነው። ከጀርባቸው ሆነው ስንቅ የሚያቀርቡላቸውና የመንፈስ ድጋፍ የሚሰጧቸው እናቶች ናቸው። እናት አገርና ወላጅ እናት ከዋጋና ከህይወት በላይ ናቸው፤ አይነገድባቸውም የምለው ለዚህ ነው። ከኢትዮጵያ መንግሥት ውጭ፤ ማንም የአፍሪካ መንግሥት እናት አገሩን ጠበቃ ሆኖ እንድትፈራርስ አያመቻችም። ከኢትዮጵያ ውጭ ማንም የአፍሪካ መንግሥት በወጣቱ ትውልድ ላይ ጭካኔ አያካሂድም፤ እናቶችን ለለቅሶ አይዳርግም። ዛሬ እንደሚታየው በጎሳና በቋንቋ ልዩነቶች ላይ የተመሰረተው የህወሓት/ኢህአዴግ ሕገመንግሥት ውጤት ቀስ በቀስ አገርን እንደሚያፈራርስ ከመንስኤው ያነጋግር ነበር። ለምሳሌ ምን የድብቅ ስትራተጅ ቢኖረው ነው ህወሓት ተከታታይ መንግሥታት ብሄራዊ ያደረጉትን፤ ከሁሉም ብሄረሰቦች የተወጣጣውን አገር ወዳድ የመከላከያ ሰራዊት አፍርሶ በአንድ ብሄረሰብ እዝ የበላይነት የተዋቀረ የፌደራልና ልዩ ፖሊስ፤ የስለላ መረጃና መከላከያ ተቋም የፈጠረው? መልሱን የኢትዮጵያ ሕዝብ ያውቀዋል። የመከላከያ ተቋም ዋና ሚና የአገርን ግዛታዊ አንድነት፤ ነጻነትና ሉዐላዊነት ማስከበር ነው። የአንድ አናሳ ጎሳ አውራ ፓርቲን ስልጣንን መታደግና ማንኛውንም ዘዴ ተጠቅሞ ማቆየት አይደለም።
የዚህ ሃተታ መሰረተ ሃሳብ ኢትዮጵያ ከፍተኛ አደጋ ላይ መውደቋን ለማሳየትና አደጋውን ለመከላከል አማራጭ ለማቅረብ ነው። ህወሓት/ኢህአዴግ ጨካኝና አምባገነን ቢሆንም አገራችን የሚያስፈልጋት የመንግሥት ለውጥ ብቻ አይደለም። “ጉልቻ ቢቀየር ወጥ አያሳምርም” እንዲሉ አንዱን አምባገነን በሌላ መቀየሩ መሰረታዊ ለውጥ አያመጣም። አስፈላጊው የስርዓት ለውጥ ነው። የስርዓት ለውጥ መሰረታዊ ስለሆነ በማያዳግም መልኩ ሁሉን ሕዝብ ማሳተፍ አለበት። ሁሉም የተሳተፈበት ስርነቀል ለውጥ ዘላቂነት ይኖረዋል። ለእድገት አስፈላጊ ነው። ካለፈው የምንማረው የንጉሰነገሥቱን መንግሥት ለውጠን የተካነው የወታዳራዊ አምባገነን መንግሥት ነው። የወታደራዊውን መንግሥት አስወግደን የተካነው የባሰውን የጎሳኞች ልሂቃን የበላይነትን ነው። የእነዚህ ውጤት ሕዝብን የስልጣኑ ባለቤት ያላደረጉ ተከታታይ መንግሥታትን መተካት ሆኗል። የችግሩ እምብርት ስርዓቱ አለመለወጡ ነው።
የስርዓት ለውጥ ስኬታማ የሚሆነው አገር ሲኖረን ነው። የመጀመሪያው ትርኩርት ኢትዮጵያን ተባብሮ ከአደጋ ማዳን ይሆናል። አገሪቱን ለማዳን የሕዝብ መተባበርን፤ ከቡድን፤ ጎሳና ጥቅም በላይ ለአገሪቱ ማሰብን ይጠይቃል። ሁላችንም በየፊናችን ነጻነት፤ ሰብአዊ መብቶች፤ ዲሞክራሲ፤ ልማት ወዘተ አስፈላጊ ናቸው እንላለን። እነዚህን ማንም አይቃወምም። የኢትዮጵያ ዘላቂ ጥቅሞች፤ ብሄራዊ አንድነትና ሉዐላዊነት፤ የሕዝቧ እኩልነትና ህብረት አስተማማኝ ካልሆኑ ዲሞክራሲና እድገት አይታሰብም። ለኢትዮጵያና ለኢትዮጵያ ሕዝብ ለምንቆረቆር የማቀርበው ሃሳብ መጀመሪያ መቀበል ያለብን ኢትዮጵያ የጋራ አገራችን መሆኗን እንቀበል የሚል ነው። የጋራ እናት አገር ከሆነች አገሪቱን ከመፈራረስ ማዳን ያለብን ሁላችንም ነን። በጎጠኛነት አስተዳደር የተቀነባበረው የህወሓት/ኢህአዴግ ስርዓት (Ethnic federalism) ስርዓት ከዚህ በፊት ተደርጎ በማይታወቅ ደረጃ የብሄረሰቦችን እኩልነት፤ ተከባብሮና ተደጋግፎ መኖር ስኬታማ ያደርጋል ተብሎ ነበር። የጎሳ ወይንም የክልል ፌደራል አገዛዝ ያስከተለው መለያየትን፤ ጥላቻን፤ የመገንጠል ዝንባሌን፤ የሽብርተኞችንና የአክራሪዎችን መጠናከር ነው። የውጭ ጠላቶ ደስ እንዳላቸው ማመን ያስፈልጋል።
ህወሓት በአማራው ብሄረሰብ ላይ የጥላቻና የማግለል መርህ ስለተከተለ ከአማራው ክልልና ከአዲስ አበባ ውጭ በአብዛኛው ኢትዮጵያ ማህል አገር የሚኖረውን የአማራ ሕዝብ እንዲወገድ፤ ቤቱና ንብረቱ እንዲወድም፤ ህልውናው ወደ አደጋ እንዲሸጋገር አድርጎታል። የወልቃይት ጠገዴ አማራ ሕዝብ ማንነቱ ተነጥቆ የትግራይ ክልል አካል እንዲሆን ተገዷል። መሬቱን ተነጥቋል። በጋምቤላ፤ አኟኩና ሌላው ነዋሪ መሬቱ እንዲነጠቅ አድርጓል፤ በሕዝቡ ላይ ግድያ አካሂዶበታል። የኦጋዴን ሶማሌዎች የሚዘገንን ጭካኔና ግድያ ተካጅሂዶባቸዋል። በኦሮሞው ወጣት ትውልድ ላይ የሚካሄደው ጭካኔ ሁኔታው ከቁጥጥር ውጭ እንዲወጣ አድርጎታል። ዛሬ ዜጎችን መግደል፤ ማፈን፤ እንዲሰወሩ ማድረግ፤ ዘር ማጥፋትና አሰገድዶ ከቀያችው ማስወገድ፤ ማንነታቸው እንዲጠፋ ማድረግ ወዘተ ለአገሪቱ ህልውና አደገኛ ሁኔታዎችን ፈጥሯል። ለዚህ በታሪክና በተከታታይ ትውልድ የሚጠየቀው የአገሪቱን ፖለቲካ አመራርና ኃብት በበለይነት የያዘው ህወሓት ነው። ስርዓቱ ይለወጥ የምልበት መሰረታዊ ምክንያት ይኼው ነው። ስርዓቱን ለመለወጥ የሚቻለው ለአንድ አገርና ለአንድ ሕዝብ አብሮና ተባብሮ መስራት ሲቻል ብቻ ነው። ጥሩና አስተዋይ የመንግሥት አመራር አለ ሊባል የሚቻለው ባለሥልጣናት የሚሰጡት ቅድሚያ ለራስና ለቡድን ሳይሆን ለአገርና ለመላው ሕዝብ
2
ሲሆን ብቻ ነው። አሁን ያለው አደጋ የሚያሳየው ከጎሳ ወደ አገር አቀፍ መሰብሰብና ፍትህ መሸጋገር ወሳኝ መሆኑን ነው።
የችግሩን መንስኤ የሚክድ አገዛዝ
ድጋፍ ይስጥ እንጂ ችግሩን የፈጠረው የውጭ ጠላት አይደለም፤ የውጭ ጠላት መግቢያ ቀዳዳ ማግኘቱ አይካድም። ለምሳሌ፤ የቀይ ባህር ሙሉ በሙሉ የአረቦች ኃይቅ እየሆነ ነው። በዘላቂነቱ ሲታይ ማን ይጎዳል? የሚጎዳው መላው ወንድማማቹ የኤርትራና የኢትዮጵያ ሕዝብ ነው። ሁለቱ ሕዝቦች ከሚለያያቸው ይልቅ የሚጋሯቸው ትሥስሮች ያመዝናሉ–ባህል፤ ታሪክ፤ ኃይማኖት፤ጋብቻ፤ የኢኮኖሚ መደጋገፍ፤ ብሄራዊ ደህንነት አስፈላጊነትና የወደፊት እድገት ወዘተ። የኤርትራና የኢትዮጵያ ሕዝብ እንደገና መተባበሩ የማይቀር ነው። ለራሱ ማንነት፤ ክብርና ህይወት ሲል። ሆኖም፤ ሁለቱም አገሮች ቅንነት፤ አርቆ አስተዋይነት፤ ሕዝብን የፖለቲካ የበላይ ያደረገ አመራርና መንግሥት ያስፈልጋቸዋል። እራሳችን እንጠይቅ፤ ጥላቻውን፤ መገንጠሉን፤ ጦርነቱን፤ መጠላለፉን ማን አመቻቸው? መልሱ ግልጽ ነው። መለስ ዜናዊ የበላይ ባለሥልጣን በነበረበት ወቅት በራሱ ፈቃደኛነት ለተባበሩት መንግሥታት ዋና ጸሃፊ የሽግግሩ የኢትዮጵያ መንግሥት የኤርትራን መገንጠል ይደግፋል ብሎ ነው።
ኤርትራን ካስገነጠለ በኋላ ብዙ ሽህ ወገኖቻችን የሞቱበትን ጦርነት አካሄደ፤ አሰብን ሳያስመልስ ተመለሰ። የመለስ ዜናዊ ቅርስ ኢትዮጵያን ወደብ አልባ ማድረጉ ብቻ ሳይሆን ሕዝቧን በጎሳና በቋንቋ መከፋፈሉ ጭምር ነው። ዛሬ በየትኛውም ቦታ የኢትዮጵያ ሕዝብ በጎሳ ፖለቲካ እየታመሰ ነው። በሰሜን ጎንደር፤ በኦሮሚያ፤ በኦጋዴን፤ በጋምቤላና ሌሎች ቦታወች ገዢው ፓርቲ ተወጥሯል። መወጠሩ ብቻ ሳይሆን፤ ለችግሮቹ አጥጋቢና አግባብ ያለው መልስ ለመስጠት አልቻለም። በሕዝብ የተነሳውን አምቢትኛነት ሁሉ በሌሎች ያመካኛል፤ አመካኝቶ ይቀጣል። የሕዝብ ዐመጽ ሲኖር ሌሎች፤ አመጸኞችን ጨምሮ፤ የምስጢር አጀንዳዎችን ለመጠቀም እንደሚሞክሩ አምናለሁ። ለምሳሌ፤ አል ጀዚራ ዶሃ ስለ ኢትዮጵያ እድገታዊ መንግሥት በምርምር የተደገፈ ጥናት አቅርብ ብሎ ጋብዞኝ የሰማሁትና የተከራከርኩት “የኢትዮጵያ ሕዝብ በሃይማኖት እንደተከፋፈለ፤ ኢትዮጵያ አረቦችን ለመጉዳት የዓባይን የተሃድሶ ግድብ እንደምትገድብ” ወዘተ ይነገር ነበር። ከእኔና ከባለቤቴ በስተቀር ለኢትዮጵያ ብሄራዊ ጥቅም የተከራከረ የለም። ከወሓት/ኢህ አዴግ ስልጣን በፊት፤ የኢትዮጵያ ሕዝብ በመከባበር፤ በመተሳሰብ፤ በአንድ ላይ የኖረ ሕዝብ መሆኑን ለማስረዳት ሞከርኩ። በግልጽ የሚታየው አረቦች ስለኢትዮጵያና ስለ ሕዝቧ ያላቸው አመለካከት የተለየ መሆኑን ነው። ኢትዮጵያ ወንዞቿን የመጠቀም መብት እንዳላት ለማስረዳት ሞክረናል። ይኼን ሳደርግ የማይደገፍ መንግሥት መደገፌ አይደለም። የኢትዮጵያን ብሄራዊ ጥቅም የደገፍኩት ዋና ምክንያት ስለማምንበት ነው።
ገዢው ፓርቲ መሰረታዊ የፖሊሲና የአስተዳደር ችግሮችን ለመፍታት አይችልም
ችግርን ለመፍታት የችግሩን መነሻ ማወቅ ያስፈልጋል። ባለፉት ሃያ አምስት ዓመታት በገዢው ፓርቲ፤ በተለይ በህወሓት የበላይነት ብልቂያጥ/ብልቃጥ የተሞላው የብሄረሰቦች ልዩነትና ጥላቻ መርዝ የአገሪቱን ማህበረሰባዊ ግንኙነቶችና የአገሪቱን ዘላቂ ጥቅም መርዟቸዋል፤ በክሎታል። የመንግሥት ተቋማትን ተጠቅሞ ሕዝብን ከሕዝብ በመለያየት ቆይታውን የሚያመቻቸው ህወሓት አሁንም አደጋውን አላየውም። ትኩረቱ ከበላይነት ላይ ነው። ተከታታይ ችግሮችን ለመፍታት የሚሞክረው በሌሎች በማመካኘት ነው። ችግሩን ራሱ ፈጥሮ በሌሎች ማመካኘት እሰከመቸ ያዋጣል? ለምሳሌ፤ ሕገመንግሥቱ ማንም ኢትዮጵያዊ በየትኛውም ኢትዮጵያ መሬት፤ ንብረት፤ ቤት ወዘተ ሊይዝ ይችላል፤ ይኼን መብት የሚቀማው የለም ይላል። በአፈጻጸም ሲታይ ይኼ አልሰራም። ካልሰራ ሕገመንግሥቱም አልሰራም ማለት ነው። ሕገመንግሥቱ ካልሰራ መለወጥ አለበት ማለት ነው። የፌደራሉ መንግሥት ሚና ሕጎችን ማስከበር ከሆነ ለምን የኢትዮጵያዊያንን መብቶች ለማስከበር አልቻለም? ካልቻለ ስልጣኑን ለምን ለሌሎች ለመስጠት ወይንም ከሌሎች ጋር ለመጋራት አይፈልግም? ብለን መጠየቅ ብሄራዊ ግዴታችን ነው።
ብዙ የአገር ውስጥና የውጭ ታዛቢዎች እንደሚሉት፤ ህወሓት አደጋውንም ቢያየው፤ የመረጃ፤ የስለላ፤ የልዩ ፖሊስና የመከላከያ እዙንና ኃይሉን በበላይነት ስለሚቆጣጠረው ሕዝቡን በመሳሪያ ኃይል ታዛዥ አደርገዋለሁ የሚል እምነት አለው። አገሪቱ ከቁጥጥር ውጭ ብትሆንስ? የሚል ጥያቄ ቢቀርብስ። ለዚህ አንቀጽ 39 መሳሪያ ይሆናል የሚሉ ብዙ ተመልካቾች አሉ። ህወሓት ስልጣን ከያዘብት ጀምሮ የትግራይን ድንበር ከሱዳን ጋር እስከሚዋሰን ድረስ አስፋፍቷል። የውስጥ መስፋፋት ችግር የለበትም የሚሉና የሌለ ታሪክ የሚፈጥሩ እንዳሉ አውቃለሁ። ድንበሩን በኃይል ለውጦ አንዱን ብሄረሰብ ከመሬቱና ከኑሮው ማስወገድ ጸረ-ዲሞክራሲና ኢ-ስብአዊ ከመሆኑም በላይ አብሮ ለመኖር አያስችልም። ለተከታታይ ትውልዶች ጥላቻንና ግጭትን ይፈጥራል። የሕዝብ ግጭት ተከታታይ ሲሆን አገር ይፈርሳል። ለዚህ ነው፤ አገር ወዳዶች አንዱን ዜጋ አስወግዶ ሌላውን መተካት ጸረ-ኢትዮጵያ አቋም ነው የሚሉት። ይኼ በግልጽ የተካሄደና የሚካሄድ የአገር ውስጥ የመሬት ነጠቃ፤ ቅርሚትና የፖለቲካ ንግድ ተከታታይ የጋራ ታሪክ ላለውና በአንድ አገር አብሮ ለሚኖር ሕዝብ ለምን አስፈለገ? ብለን ብንጠይቅ መልሱን ለማሰብ አያስቸግርም። በአጭሩ፤ ሁኔታዎች ከቁጥጥር ውጭ ቢወጡ ለመገንጠል ያስችላል። መገንጠል ግን ሰላምን አያመጣም።
3
የኢትዮጵያ የመከላከያ ተቋም እንደዱሮው ብሄራዊ ቢሆን ኖሮ ከማንም ጎራ የሚመጣን መገንጠልና የሕዝብ እልቂት ይከላከለው ነበር። ህወሓት ይኼን የሚያኮራ ታሪክ ያለው ተቋም አፈራርሶ ኤርትራን እንድትገነጠል አድርጓል። የባህር በሯን ዘግቷል። የዛሬው የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት የበላይ እዝ ጎሳዊ በመሆኑ የሚከተለው ፖሊሲና ተግባር ህወሓት የሚያዘውን ነው። ዘጠና ሰባት በመቶ የሚሆነው የበላይ እዝ የትግራይ ብሄረሰብ አባልትን ያካተተ ነው። የኢትዮጵያን ሕዝብ አይወክልም ማለት ነው።ዘመናዊውኑን የኢኮኖሚ የበላይነት የያዙት የህወሓት አባላት፤ ቤተሰቦችና ደጋፊዎች ናቸው። ህወሓት ተጠልቶ የትግራይን ሕዝብ የሚያስጠላው ለዚህ ነው። የመከላከያ እዙ የኢኮኖሚ የበላዩ አካልና ተጠቃሚ ሆኗል። የራሱ ጥቅም ከህወሓት ባለሥልጣናትና ተባባሪዎች አይለይም። ተጠቃሚ ስለሆነ እዙ በሙሉ የሚወክልው ህወሓትን ነው። ታዛዢነቱ ለህወሓት ነው። የህወሓት የበላዮች በኦሮሚያ የተከሰተውን ሊቆም የማይችል የሕዝብ ዓመጽ በብሄራዊ መግባባት፤ በውይይት፤ በድርድር፤ በእርቅና በሰላም ለመፍታት በመሞከር ፋንታ የህወሓትን ጀኔራሎች በሕዝቡ ላይ ጭነውበታል። ይህ የክልል መፈንቅለ መንግሥት መሰረታዊውን የፖሊሲና የመጥፎ አስተዳደር ችግር ሊፈታው አይችልም። ተመሳሳይ ሕዝባዊ አመጾች በሌሎች ክልሎች ቢከሰቱ፤ ለምሳሌ በጎንደር የሚካሄደው ተመሳሳይ ሕዝባዊ አመጽ፤ ተመሳሳይ ወታደራዊ መፈንቅለ መንግሥት ሊካሄድ ነው? መፈንቅለ መንግሥቱ የት ላይ ያቆማል? የህወሓት ጀኔራሎች አገሪቱን በሙሉ በበላይነት ከያዙ ኢህአዴግ የሚባለው የፓርቲ መርህና አገዛዝ አከተመለት ማለት ይሆናል። ኦሮሞዎች አክትሞለታል ቢሉ አልደነቅም። ጎንደሬዎችም መንግሥት የለም ሲሉ ቆይተዋል፤ የሚሰማቸውና የሚተባበራቸው አላገኙም።
በየትኛውም ቦታ ይሁን በሕዝብ ላይ የሚካሄድ ጭካኔ ለተከታታይ ዓመታት የሚያስከትለውን አደጋ ለመገመት ይቻላል።
አንድ፤ ሕዝቡ በመንግሥቱ ላይ ያለው ጥላቻና እምቢተኛነት እየጠነከረ ይሄዳል፤
ሁለት፤ መግባባትን ያመጣል፤ ዲሞክራሲን ያጠናከራል ተብሎ የተመሰረተው በቋንቋና በጎሳ የተዋቀረው የጎሳ ፌደራሊዝም እንዳልሰራ ያሳያል፤
ሶስት፤ የኑሮ ውድነት፤ የስራ አጥነት እየተባባሰ ሄዷል።
በቁጥሩ አንጋፋ የሆነው የኦሮሞ ሕዝብ ያልተቀበለውን ፌደራሊዝም ማን ይቀበለዋል? የአማራው፤ የአፋሩ፤ የጋምቤላው፤ የትግራዩ ወዘተ ሕዝብ ይቀበለው አይቀበለው በምን ሊረጋገጥ ይችላል። በእኔ ግምት ብቻ ሳይሆን ጥናት፤ አብዛኛው የኢትዮጵያ ሕዝብ የአሁኑን ሕገመንግሥት አይቀበልም። የማይቀበልበትን ምክንያቶች በሌሎች የፖለቲካ ኢኮኖሚ ትንተናዎቸ አቅርቤአለሁ። በአጭሩ ሕገመንግስቱ የአንድ ብሄረሰብ፤ ማለትም የህወሓት መጠቀሚያና መቆያ መሳሪያ ሆኗል። ሕገመንግሥቱ ሁሉን የሚያገለግል፤ ለሁሉም ዜጎች መብቶች የቆመና ሕገመንግሥቱ የሚለውን የበላይ ባለሥልጣኖች ወደ ስራ ቢተረጉሙት ኖሮ የስልጣን መፈራረስ፤ መሽጋሸግና መድክም (Rapid dedgradation of Federal government authority in the entire country) አይኖርም ነበር።ላስምርበት የምፈልገው መሰረተ ሃሳብ፤ የፖለቲካ አመራሩ ሊፈታው ያልቻለውን ቀውስ የመከላከያ ኃይሉ ሊፈታው አይችልም። የመከላከያ ተቋሙ ገዢው ፓርቲ የፈጠረውንና ሊፈታው ያልቻለውን ችግር እንዴት ሊፈታው ይችላል? ሊፈታው አይችልም። የደርግ አገዛዝ የወደቀበት ዋና ምክንያት የሕዝቡን መብትና ስልጣን የራሱ ስላደረገና ችግሮችን በመሳሪያ ኃይል እፈታለሁ ወደሚል ውዥንብር ስለገባ ነው።
ሆኖም፤ አገሪቱ እንዳትፈራርስ ከተፈለገ የመከላከያ ኃይሉ ብሄራዊ ግዴታውን መወጣት አለበት። ብሄራዊ ግዴታውን ሊወጣ የሚችለው ራሱን ከፓርቲው በላይ ለማድረግና ኢትዮጵያዊ ለመሆን ሲችል ነው። በዘላቂነት ሲታይ ገዢውም ፓርቲ ሆነ ተቃዋሚዎች ሕገመንግሥቱ፤ ማለትም ስርዓቱ ለምን እንዳልሰራ ደፍረውና ቆርጠው መነጋገር አለባቸው። መነጋገር ስል በአንድ በኩል በገዢው ፓርቲና ደጋፊዎቹ፤ በሌላ በኩል በተቃዋሚዎች፤ አገር ወዳድ ታዋቂ ግለሰቦች፤ በሕዝቡና በሌሎች በሚያገባቸው ስብስቦች መካከል ማለቴ ነው። ኢትዮጵያዊያን ከአሁኑ አስከፊ ሁኔታ መጥቀን ለመውጣት ከፈለገን መነጋገር፤ መወያየትና መደራደር መቻል አለብን።
እውነተኛ እኩልነትና የሕግ የበላይነት መርህ ይሁን
የኦሮሞ ሆነ የአፋር፤ የትግራይ ሆነ የአማራ ወዘተ ሕዝብ ከሁሉም በላይ የሚፈልገውና የሚመመኘው መብቱና ነጻነቱ እንዲከበርለት ነው። ሕዝቡ ነጻነት ቢኖረው በሰላም አብሮ መኖርንና አብሮ ማደግን ይመርጣል። አብሮ ለመኖርና አብሮ ለማደግ ፍትህ፤ እውነተኛ እኩልነት፤ የሕግ የበላይነትና ዲሞክራሳዊ አገዛዝ ወሳኝ ናቸው። እነዚህ ሁኔታዎች እስከተመቻቹ ድረስ የኢትዮጵያ ዘላቂነትና ደህንነት ዋስትና ይኖራቸዋል። ይኼን የሚወስነው ሕዝብ እንጅ የፖለቲካ ልሂቃን መሆን የለባቸውም። ሕዝብን እያሰቃዩና እየለያዩ እርጋታ፤ ሰላም፤ እድገት፤ ደህንነትና ዘላቂነት ሊኖር አይችልም። እድገት አለ ተብሎ የሚለፈፈው መፈተሽ ያለበት ከአብዛኛው የኢትዮጵያ ሕዝብ ኑሮ መሻሻል አንጻር ነው።
4
በቅርቡ ኢኮኖሚስት የተባለው መጽሄት የጥቁር አፍሪካን የእድገት እንቅስቃሴ ሲዘግብ እንዲህ ብሏል። “ውጣ ውረድ፤ የአስተዳደር ችግር፤ ሙስናና አምባገነን አገዛዝ ቢኖሩም ከሳሃራ በታች ከሚገኙ 49 መንግሥታት መካከል ከአረብ አገሮች ጋር ሲነጻጸሩ በአገዛዝና በእድገት በኩል ጥቁር አፍሪካ የተሻለ ውጤት እያሳየች ነው…ከእነዚህ መካከል ለሕዝባቸው ህይወትና ኑሮ መሻሻል የተሻለ ውጤት የሚያሳዩት ነጻነት ያላቸውና ዴሞክራሳዊ የሆኑ አገሮች ናቸው–እንደ ናይጀሪያ፤ ጋና፤ ኬንያ፤ ታንዛኒያ፤ ዛምቢያ፤ ደቡብ አፍሪካ፤ ናሚቢያ፤ ቦትስዋና ያሉት። እነዚህ ሙሉ በሙሉ ነጻ ሆነው ብሄራዊ ተቋማትን አጠናክረዋል።” በሌላ በኩል እንደ “ሰሜንና ደቡብ ሱዳን፤ አንጎላ፤ የመካከለኛው አፍሪካ፤ ዚምባብዌ፤ ዩጋንዳ፤ የኮንጎ ዲሞክራሳዊ ሪፐብሊክ፤ ሶማሊያ፤ ኢትዮጵያና ኤርትራ ምንም ነጻነት፤ ፍትህና ዲሞክራሳዊ አገዛዝ የሌለባቸው፤ በውስጥ የጎሳ ግጭት የተበከሉና ለሕዝባቸው የኑሮ መሻሻል የሚዳሰስና የሚታይ ነገር የማያሳዩ ናቸው” ይላል (The Economist, The World in 2016: A Revolution from Below and Continental Drift).
ዘገባው የፖለቲካ ነጻነትና ዲሞክራሳዊ አገዛዝ፤ ዘላቂነትና ፍትሃዊነት ያለው እድገት ቀጥታ የሆነ ግንኙነት እንዳላቸው ያሳያል። ይኼን መሰረተ ሃሳብ ሙሉ በሙሉ እጋራለሁ። የአፍሪካ ልማት ባንክ የዛሬ ዓመስት ዓመት ያካሄደውን ጥልቀት ያለው የእድገት መስፈርቶችና በቅርቡ የደቡብ አፍሪካው ስታንደርድ ባንክ ያካሄደውን ሰፊ ጥናት መሰረት በማድረግ በአማካይ ሲታይ አፍሪካ ባለፉት 15 ዓመታት በአመት 5 በመቶ የሚገመት እድገት አሳይታለች። የኢትዮጵያ እድገት ከዚህ ከፍ ይላል የሚለውን ለመቀበል አስቸጋሪ ነው። ከፍም ዝቅም ቢል ቁም ነገሩ ይኼ ከመቸውም ጊዜ ከፍ ያለ የእድገት መጠን ምን ውጤት አሳየ? የሚለው ነው። በአፍሪካ ልማት ባንክ ስሌት የአፍሪካ መካከለኛ መደብ 300 ሚሊየን ሕዝብ ደርሷል ይል ነበር። ግዙፍ መሆኑ ነው። ልክ ዓለም ባንክ እንደሚያደርገው ስህተት፤ ባንኩ ቀረብ ብሎ ያላየው ጉዳይ አለ። ይኼውም፤ ልክ እንደ ኢትዮጵያ በሌሎች ታዳጊ የአፍሪካ አገሮች የእድገቱ ውጤት ለጥቂቶች ገቢ፤ ኃብትና የድሎት ኑሮ ማስገኘቱ ነው። ምንም እንኳን ከድህነት ነጻ ለመውጣት የነፍስ ወከፍ ገቢ ዓለም ባንክ ለኑሮ አስፈላጊ ነው ከሚለው በቀን ከሁለት ዶላር በላይ የሚያገኙ አፍሪካዊያን ቁጥር አድጓል ቢባልም ይኼ ገቢ ምን እንደሚገዛ አልተብራራም። የአቅርቦት እጥረት ባለበት አገር የዋጋ ግሽበት የተለመደ ነው። በእኔ ግምት ጠቅላላ የአገር ገቢና የነፈስ ወከፍ ገቢው ብቻ የኑሮ መሻሻልን አያመለክትም፤ ዋናው የመግዛት አቅምና የግለሰቦች ኑሮ መሻሻል ነው። በቀን ገቢው ሁለት ዶላር ወይንም ከዚህ በታች የሆነውን ወደጎን እንተወውና በመግዛት አቅም ገቢው በቀን ከሁለት ዶላር በላይ ቢሆንስ ብንል በስታንዳርድ ባንክ ዘገባ የመካከለኛው መደብ ሕዝብ ቁጥር ግማሽ ይሆናል።
የእድገትን መረጃዎች ማስመሰል
በቀን ሁለት ዶላር እንኳን ቴሌቪዢን፤ ዘመናዊ ቤትና ሌላ ለመግዛት የእለት የምግብ ፍላጎትን ለማሟላት አይችልም። በስታንዳርድ ባንክ ጥናት መሰረት ቴሌቪዢንና ሌሎች የቅንጦት እቃዎች ለመግዛት የሚችለው አፍሪካዊ መካከለኛ መደብ ብዛት ከ 15 ሚሊየን አይበልጥም። “የዚህ አንድ ሶስተኛው የሚኖረው ናይጀሪያ ነው፤ ሌሎቹ በአስር የአፍሪካ አገሮች ይኖራሉ፤ አብዛኛዎቹ ነጻና ዲሞክራሳዊ አገዛዝ ያላቸው ናቸው። ነጻነትና ዲሞክራሳዊ መንግሥት ያላቸው ሃብታም ይሆናሉ፤ የዚህ ክፍተት ያለባቸው ደሃ ሆነው ይቆያሉ ወይንም የባሰ ደሃ ይሆናሉ ማለት ነው። የእርስ በርስ ግጭት ድህነትን ያባብሳል ማለት ነው። “There are just 15 million middle-class people in 11 sub-Saharan Africa’s biggest economies. Almost a third of these live in Nigeria; hardly any are in Ethiopia.” በኢትዮጵያ መስፈርቱን የሚያሟላ የመካከለኛ መደብ አባል የለም። ይህ በሚባልበት ጊዜ የማይበሳጭ የትግራይ፤ የአማራ፤ የአፋር፤ የኦሮሞ፤ የወላይታ ወዘተ ሕዝብ ሊኖር አይችልም። እድገት ቢኖርም የእድገቱ ውጤት የጥቂቶችን ኪስ ሞልቷል ማለት ነው። የወደፊቱን ወጣት ትውልድ እድል የሚወስኑት የእነዚህ የጥቂት የህወሓት ቤተሰቦች ልጆች ይሆናሉ ማለት ነው። የኢትዮጵያ ሕዝብ በጋራ ሆኖ ትኩረት መስጠት ያለበት ለመልካም አስተዳደር፤ ለፍትህ፤ ለእውነተኛ እኩልነትና ሕዝብን መዓከልና የበላይ ለሚያደርግ ዲሞክራሳዊ አማራጭ መሆን አለበት እያልኩ የምክራከረው ለዚህ ነው። ደሃ፤ ጥገኛና ኋላ ቀር ሆነን እንድቀጥል ከፈለግን የህወሓትን የበላይነትና የእርስ በርስ ግጭቱን መቀበል አግባብ አለው።
ከዚህ አሰቃቂ ሁኔታ መላቀቅ ግዴታችን ነው ካልን ግን በብሄራዊ ደረጃ፤ በአንድነት ለለውጥ መታገል አለብን ማልት ነው። በእኔ ግምት፤ አንዱ ነጻ ሆኖ ሌላው ታፍኖ ሊኖርና ከድህነት ነጻ ሊወጣ አይችልም። ሌላው በኢትዮጵያ በገሃድ የሚታይ ሁኔታ የመካከለኛው መደብ አለማደግና የኢትዮጵያን ስብጥር ሕዝብ ስርጭት አለማንጸባረቅ በመተባበርና በመተሳሰብ ለፍትህ፤ ለነጻነትና ለዲሞክራሲ የሚደረገውን ሕዝባዊ አመጽ በመጠኑም ቢሆን ይገታዋል። ጥቂት ኃብት ያገኘው ስርዓቱ ምን አደረገ ማለት ጀምሯል። ችግሩ የተቃዋሚውና የአመጸኞች ነው ወደሚል የተሳሳተ ግንዛቤ አምርቶታል። ገዢው ፓርቲ የሚጠቅምበት የፖለቲካ ዘዴ ስርዓቱ የፈጠራቸውን ጥቂት ባለሃብቶችና በረሃብ የሚሰቃየውንና ኩራዝ መብራት የሚጠቀመውን ሕዝብ ጥገኛ አድርጎና በጎሳ ከፋፍሎ በአንድነት እንዳይነሳ ጫናዎች በማደረግ ነው።
5
የውሸት የእድገት መስፈርቶች ጉዳት
አገራቸውን በፍጥነት በማሳደግ ላይ ያሉ አገር ወዳድና ዲሞክራሳዊ የአፍሪካ አገሮች ለአገራቸው አንድነትና ዘላቂነት ያልተቆጠበ ጥረት ያደርጋሉ። ሕዝባቸው ከድህነት ነጻ እየወጣ ወደ መካከለኛው መደብ ሲሸጋገር በሕዝብ መካከል የቆየው የጎሳ ልዩነት እየጠፋ እንደሚሄድ በተግባር እያሳዩ ነው። ቦትስዋና ከጎሳ በላይ ናት። ናይጀሪያ ነጻና ፍትሃዊ ምርጫ አካሂዳ የእስልምና ተከታይ ጀኔራል ፕሬዝደንት እንዲሆኑ መርጣለች። እኒህ የጸረ-ሙስና አባት ሊባሉ የሚችሉ መሪ አገር ወዳድ ከመሆናቸውም በላይ ሽብርተኞችን በማያወላውል ደረጃ እየተዋጉ ነው። የተዘረፈው ኃብት እንዲመለስ ጥረት እያደረጉ ነው። ናይጀሪያ በኢንዱስትሪ እንድታድግ እያደረጉ ነው። የግሉ ክፍል በናይጀሪያኖች የበላይነትና ቁጥጥር ስር እንዲውል አመቻች ሁኔታዎች እየፈጠሩ ነው። ለክልሎቻችንና ለጎሳዎቻችን የተለየ ትኩረት ከምንሰጥ ይልቅ ሁሉም ለሚጋራት ለአገር እንክብካቤ እንስጥ ስል ከሌሎች የአፍሪካ አገሮች ልምድ በመማርና ኢትዮጵያዊያን የሚያኮራ ታሪክና የተፈጥሮ ኃብታችን ባለቤትነት ልምድ እንዳለን በመቀበል ነው። እናስብ፤ በጎሳ ተከፋፍላ የነበረችው ናይጀሪያ ( ቢያፈራ) አንድ ስትሆን በአንድነቷ የታወቀችው ኢትዮጵያ እንዴት ወደኋላ ወደሚወስድ፤ መከፋፈልና መበታተን ወደሚያስከትል ስርዓት ተሸጋገረች? ብሎ መጠየቅና መልሱን መስጠት አግባብ አለው። ሌሎች ተቆርቋሪ አፍሪካዊያን የሚጠይቁት ይኼን ነው።
በአገር ደረጃ የሚያስብ ትውልድ እንከባከብና እንደገና እንዲያብብ እናድርግ
ማንኛውም አገር፤ ጎሳ ወይንም ኃይማኖት ተተኪ ትውልድ ያስፈልገዋል። ይህ ተተኪ ትውልድ ጠንካራ የሚሆነው በመለያየትና በጥላቻ፤ በጉራ፤ በትምክኸተኛነት፤ በእርስ በርስ እልቂት፤ አንዱ ሌላውን በማዋረድ፤ በኪራይ ሰብሳቢነት ባህልና ልምድ አይደለም፤ አብሮና ተከባብሮ በመኖርና በማደግ ነው። ታንዛኒያ በአስደናቂና በማይለወጥ ደረጃ የሰጠችው ትኩረት ለብሄራዊ መግባባት፤ ለሕዝቧ አንድነትና እኩልነት ነው። እንደ ታንዛኒያና ናይጀሪያ፤ ጋናና ዛምቢያ ዘላቂነትና ፍትሃዊነት ያለው ለውጥ የሚያሳዩ አፍሪካዊ አገሮች በአስተሳሰብ እየቀደሙን ነው፤ ይኼን አንካድ። የሚያስቡትና የሚሰሩት ለዘላቂ አገርና ትውልድ ነው። አሁን በኢትዮጵያ የሚታየው የአብሮና ተቻችሎ የመኖር ታሪክ ወደ መፈራረስ እያመራ መሆኑ ለሌሎች አፍሪካዊያን አሳፋሪ እየሆነባቸው ነው። የኢትዮጵያ መንግሥታት ለጥቁር አፍሪካ ነጻነት የአቅማቸውን አድርገዋል። ዛሬ የአገራችን ሕዝብ እየታፈነና አገራችን እየፈረሰች ወደ ሌሎች፤ በተለይ ዲሞክራሳዊ ወደሆኑ የጥቁር አፍሪካ አገሮች እንሰደዳለን። በመታገል ፋንታ፤ ከችግሩ እየሸሸን ማለት ነው። በአገር ቤትም ያለው ችግሩን ይሸሻል። ለምን ትሰደዳላችሁ ብለው ሲጠይቁን ምን መልስ እንደምንሰጥ አይታወቅም፤ እነሱ ግን ያውቁታል። ረሃብና የምግብ እጥረት እንዳለ፤ የስራ እድል እንደሌለ፤ ነጻነት እንደሌለ፤ የብሄረሰቦች ግጭት እንዳለ ወዘተ ያውቁታል።
ኢትዮጵያን የሚያውቁ አፍሪካዊያን ሁሉም ቦታ ስርዓቱ የፈጠረው የጎሳ ግጭትና መናጋት እንዳለና ሰላም እንደሌለ ያውቃሉ። በራሳቸው ልምድ እንዳዩት ሁሉ፤ ሰላምና ደህንነት ሲበከሉ ኑሮም አብሮ እንደሚበከል ያውቃሉ። በተለየ ደረጃ የሚጎዱት ሴቶች፤ ህጻናት፤ ሽማግሌዎች፤ ጡረተኞች መሆናቸውን ያውቃሉ። ብዙዎቹ ኢትዮጵያዊያን የሚሰደዱት ወደ ኬንያ፤ ታንዛኒያ፤ ዛምቢያ፤ ናሚቢያ፤ ደቡብ አፍሪካ ነው። ይኼ ተከታታይ ሁኔታ ለምን አያሳፍረንም? ለምን አያስተባብረንም? ለምን አያስማማንም? የሚሰደዱት ከሁሉም የህብረተሰብ ክፍሎች ናቸው፤ እናቶች፤ እህቶች/ዎንድሞች/ ዘመዶች ወዘተ አሏቸው። የሚሰደዱበት ምክንያት ግልጽ ቢሆንም እናቶች በተናጠል ይጨነቃሉ። የትግራይ ደሃ አናት ከአማራ ድሃ እናት ጋር አትነጋገርም። እናቶችን የሚያስተባብራቸው ተቆርቋሪ ቡድን የለም። አገራችን ምን ሆኗ ነው ለልጆቻችን ህይወት የማትቆረቆረው ብለው ራሳቸውን ይጠይቃሉ። ጥያቄውን የሚመልስ ባለቤት ወይንም ባለሥልጣን ወይንም ተቃዋሚ ክፍል ፈልጎ ለማግኘት አይቻልም። በተመሳሳይ ኢትዮጵያን ለማዳን የሚቆረቆሩ ግለሰቦችና ቡድኖች ቢኖሩም በአንድነት ሆነው ለአገሪቱ ዘላቂነት ሃላፊነት ወስደው ባለቤት አልሆኑም። እንተባበር የሚለው የሚሰለች ብሂል ተደጋጋሚ ሆኖ ትርጉም-የለሽ ሆኗል። አገሪቱ የወላድ መካን ሆናለች የሚያስብል ሁኔታ እንዳለ መካድ አይቻልም።
የአገርን ጤናማነት ከሕዝብ ህይወትና ኑሮ ለይቶ ለማየት አይቻልም። የናይጀሪያ ኢኮኖሚ አደገ ሲባል የመካከለኛው መደብ እያደገ ሄደ ማለት መሆኑን ከላይ አሳይቻለሁ። በሶማሊያ እንዳየነው አገር ስትጎዳና ስትወድቅ አብሮ የሚጎዳውና የሚወድቀው ሕዝብም ነው። አገር ስትጠነክር ሕዝብም ይጠነክራል። እናቶች በተደጋጋሚ የተጎዱት ከሁለት አንጻር ነው።
አንድ፤ ልጆቻቸው የአገራቸውን ነጻነትና ግዛታዊ አንድነት ሲታደጉ መሞታቸውና መቁሰላቸው። ለምሳሌ በኢትዮጵያና በኤርትራ መካከል በተካሄደው ትርጉም የለሽ ጦርነት ከሁለቱም ሕዝቦች ከሰባ ሽህ በላይ ሰው ሞቷል፤ አብዛኛው ወጣት። በቅርቡ በኦሮሚያ እንደሆነውና እንደሚሆነው ወጣቶች ለፍትህ፤ ለእኩልነትና ለእድገት ሲታገሉ እነደወጡ መቅረታቸው፤ መሰወራቸውና በገፍ መሰደዳቸው ተከታታይ ሆኗል። በአገር ደረጃ ብናየው፤ በደርግ ዘመን ብቻ ኢትዮጵያ አንድ የተማረ ወጣት ትውልድ አጥታለች። ይኼ ትውልድ የተማረው በደሃው ሕዝብ ኃብት ነው። ደሃው የባከነውን ወጣቱን ትውልድ ከፍሎ ያስተማረው ለእልቂትና ለስደት አልነበረም፤ ራሱን ከድህነት ነጻ አውጥቶ አገሩንና
6
ሕዝቡን እንዲያገለግል ነው። የአሁኑ አገዛዝ ብሷል። ብዙ ሚሊየን የተማረ የሰው ኃይል በስደት ይኖራል፤ አሁንም ይሰደዳል። የየመን መንግሥት 400,000 ኢትዮጵያዊያን ስደተኞች በየመን ብቻ እንደሚኖሩ ዘግቦ ነበር። በሳውዲ አረቢያ፤ በኩዌይት፤ በተብበሩት የአረብ ኤምሬቶች፤ በሌባኖን፤ በካታርና ሌሎች የአረብ አገሮች ሰብአዊ መብታቸው ታፍኖ፤ በእስር ቤት ታጉረው የሚኖሩትን ቁጥር ለማወቅ አስቸጋሪ ቢሆንም ብዙ እንደሆኑ አውቃለሁ። የአገራቸው መንግሥት መብታቸውን ለማስከበር የወሰደው አንድም እርምጃ የለም። እንዲያውም በስደቱ ይነግድበታል። ኢትዮጵያ ግዙፍ የተማረ የሰው ኃብት አላት፤ የሚኖረው በውጭ ነው። ይኼን ግዙፍ የሰው ኃብት ወደ አገሩ ገብቶ፤ መብቱ ተከብሮ ኢትዮጵያንና የኢትዮጵያን ሕዝብ እንዲያገለግል የጠየቀው የመንግሥት ባለሥልጣን የለም።
ሁለት፤ ምንም እንኳን መንገድና ሌላ መሰረተ ልማት ቢስፋፋም ሴቶችና አብዛኛው የተማረው ክፍል የእድገቱ ውጤት ተካፋይ አይደሉም። ነጻነት፤ ፍትህ፤ የሕግ የበላይነትና እውነተኛ ዲሞክራሳዊ መንግሥት እስካልተቋቋመ ድረስ ሁኔታው አይለወጥም። በሃያ አምሥት ዓመታት የእድገት ታሪክ ከሌሎች የአፍሪካ አገሮች ጋር ተመጣጣኝ የሆነ የመካከለኛ-ገቢ መደብ ለመፍጠር ያልቻለና ረሃብን ለመቅረፍ ፍላጎትና አቅም የሌለው ስርዓት በሚቀጥሉት 25 ዓመታት የተለየ ውጤት ያስገኛል ብሎ መገመት ራስን ማታለል ነው። አይቻልም። ለማጠናከር የምፍልገው ሃሳብ የእናቶችና የወጣቶች ጤናማነትና የአገር ደህንነት የተያያዙ መሆናቸውን ነው። ጤናማ አገር ጤናማ እናቶችና ተከታታይ ትውልድ ይኖሯታል። ወጣቶች ለፍትህ ሲታገሉ ማፈንና መጨፍጨፍ ጤናማነት አያሳይም። የባሰውን ህወሓት/እህአዴግ በአገራቸው ተፍጨርጭረው ራሳቸውን እንዲችሉና አገራቸውን ዘመናዊ እንዲያደርጉ አመቻች ሁኔታን ከልክሏል።
ብሄራዊ መግባባት፤ እርቅና ሰላም አስቸኳይ ሆኗል
ምን መፍትሄ አለ? ይሔን ጽሁፍ ለማጠቃለል፤ አፓርታይዷ ደቡብ አፍሪካ በዘር ጥላቻ የተመረዘች አገር ነበረች። የጥቁሩን ሕዝብ በጭካኔ ትጨፈጭፍ፤ ታስር፤ ታጉርና ታሳድድ ነበር። ለብዙ አስርት ዓመታት የደቡብ አፍሪካ ኢኮኖሚ፤ ለጥቂት ነጮች አይተውት የማያውቁት ገቢና የድሎት ኑሮ ከማመቻቸቱ ባሻገር ለማምረት፤ ለብዙሃኑ የጥቁር ሕዝብ የስራ እድል ለመፍጠር ያልቻለበት ዋና ምክንያት የስርዓቱ ትኩረት ሕዝብን አፍኖና ቀጥቅጦ በመግዛት ላይ ስለሆነ ነው። በጥቂት ነጮች የበላይነት ይተዳደር የነበረው ስርዓት ለስለላ፤ ለአፈናና ሌላ የሚያወጣው ኃብት ብዙ ፋብሪካዎች ሊያሰራና የስራ እድል ሊፈጥር ይችል ነበር። ኔልሰን ማንዴላ አፈናውና ግድያው የማያዋጣ መሆኑን ካሳሰቡ በኋላ አማራጭ አቅርበው የስርዓት ለውጥ አምጥተው ነበር። ይኼም አማራጭ ሁሉን አቀፍ የሆነ ዲሞክራሳዊ መንግሥት እንዲቋቋም ማድረግ ነበር። አስተዋይ የሆኑት የደቡብ አፍሪካ መሪዎችና አባቶች፤ በተለይ ማንዴላና ዴስሞንድ ቱቱ ለሃገራቸውና ለሕዝባቸው በመቆርቆር ስርዓቱ ከስሩ መለወጥና እንደገና መመስረት አለበት የሚል መርህ ተከተሉ። ብሄራዊ መግባባት፤ እርቅና ሰላም እንዲካሄድ አድርገው የሰላም መሰረት ጣሉ። ዛሬ ኢትዮጵያ የሚያስፈልጋት ገዢውን ፓርቲ፤ ሁሉንም የፖለቲካና የማህበረሰብ ስብስቦችና ተቋሞች፤ መንፈሳዊ መሪዎችና አባቶች፤ እውቅና ያላቸው ግለሰቦች የሚያካትት የብሄራዊ መግባባት፤ ውይይት፤ የፖለቲካ ድርድር፤ እርቅና ሰላም ጉባኤና ስብሰባ ማካሄድ ነው። የኢትዮጵያ ሕዝብና ልሂቃን ፊት ለፊት ሆነው ለመነጋገር ካልተቻሉ አደጋው እየተባባሰ ይሄዳል። ስለሆነም ይኼ ጉዳይ ጊዜ የሚሰጥ አይመስለኝም፤ በአስቸኳይ መካሄድ አለበት።
ህብር ሬድዮን በህብር ሬዲዮ ድህረ ገጽ ወይም በቀጥታ በስልክ ለማዳመጥ 712 -432-8451 መደወል ብቻ በቂ ነው በእንግሊዝ ለምትኖሩ በ01405770140 በስልክ ማዳመጥ ይቻላል። ዘወትር በድህረ ገጻችን፣ ከ googel app store Hiber Radio ወደ ስልክዎ በመጫን ካልሆነም በዘሐበሻ እንዲሁም በተጠቀሱት ስልኮች ማዳመጥ ይቻላል።