Hiber Radio: ታሪካዊ ግዴታ –እስኪ ስለ እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ ሰብአዊ መብት መነጋገር እንጀምር– ዶ/ር አክሎግ ቢራራ (ሊያነቡት የሚገባ)

DR Akelog_001

እኛ ኢትዮጵያዊያን የፖለቲካ ልሂቃን ከአብዛኛው የኢትዮጵያ ሕዝብ አስተሳሰብና ፍላጎት የተለየ ኋላቀር የፖለቲካ ባህል ስንከተል ቆይተናል። ከፍተኛ ትምህርት ኖሮን መደማመጥ አንችልም፤ ለመናበብ አንችልም። ይኼ ችግር ብሄራዊ አደጋዎችን ፈጥሯል። በአገር ደረጃ የሚነጋገረው ልሂቃንና ምሁራን ቁጥር በጣም ዝቅተኛ ነው። ሁኔታውን ያባባሰው ስርዓቱ መሆኑ የሚያከራክር አይመስለኝም። ባለፉት ሃያ አምስት ዓመታት በጭቁን ሕዝቦች ስም በመነገድ በኢትዮጵያ ሕዝብ ላይ የተጫነው የቋንቋና የጎሳ መለያ ሕገመንግሥትና የክልል አስተዳደር ለሁሉም ኢትዮጵያዊያን ማፈኛና ለጥቂት የህወሓት ኪራይ ሰብሳቢዎች ሚሊየኔርነት መሳሪያ መሆኑ በሂደት እየታየ ነው። ይህ ኪራይ ሰብሳቢ ቡድን ሌሎችም ኪራይ ሰብሳቦዎች እንዲሆኑ አድርጓል። ኪራይ ሰብሳቢ በሞላበት አገር ድህነት፤ ረሃብ፤ ስደትና ውርደት እየባሰ ብሄድ አያስገርምም። ተቃዋሚውን ሽባ ያደረገውም ፍርሃት ከስርዓቱ ጋር የተያያዘ ነው። ስርዓቱ ለፖለቲካና ለኢኮኖሚ ፍጹም የሆነ የበላይነት (Absolute minority ethnic elite hegemony) ያገለገለው በትግራይ ሕዝብ ስም ለሚንቀሳቀሰው፤ ሆኖም የአብዛኛውን የትግራይ ሕዝብ አዘቅት ላስገባው ለህወሓት አባላት ነው።

ባለፈው ሃተታየ እንዳቀርብኩት፤ የዘውግ ወይንም የጎሳ ፌደራሊዝም ከጅምሩ የጀርባ ምስጢር ነበረው። ይኼውም በጭቁን ህዝቦች ነጻነት፤ መብትና ራስን ችሎ ማስተዳደር ስም፤ የህወሓትን የበላይነት ሕገመንግሥታዊ ሽፋን ስጥቶ የበላይነትን ተቋማዊ ማድረጉ ነው። የዚህ ሃተታ መሰረት ለዚህ ስርዓት ወለድ ተግዳሮት መፍትሄው በብሄራዊ ደረጃ መሰብሰብ፤ መደራጀትና አብሮ መታገል አስፈላጊ ሆኗል የሚል ነው። የህወሓት የበላይነት ሽፋን ኢህአዴግ የሚለው የብሄረሰብ ልሂቃን ስብስብና አገዛዝ ነው። ኢህአዴግ ሲባል አቻ ለአቻ የሆኑ ድርጅቶች ስብስብ አለመሆኑ በተደጋጋሚ ታይቷል። ውጤቱ ምንንድን ነው? ብለን ብንጠይቅ የሚከተሉትን እናያለን፤

አንድ፤ የኢትዮጵያ አንድነትና ሉዐላዊነት አደገኛ በሆነ ደረጃ መድከሙ። አንድ ኢትዮጱያዊ ከክልሉ ወጥቶ ወደሌላ ክልል ሲሄድ ልክ ከጎረቤት አገር እንደመጣ እንግዳ “ከየት መጣህ” ተብሎ ይጠየቃል። ይህ በአገር “እንግዳ” መሆን በአፄ ኃይለ ሥላሴና በደርግ መንግሥታት ፍጹም የማይታሰብ ነበር። አንድ የታወቀ ኢትዮጵያዊ ምሁር፤ ፕሮፌሰር ዳኛቸው አሰፋ በድህረ ገጾች እንዳስቀመጠው፤ “ለመሆኑ ኢትዮጵያ አለች ወይ” ተብሎ ከሚጠየቅበት ደራጃ የገባነው በህወሓት ዘመን መሆኑ ነው።

ሁለት፤ የጎሳ ልሂቃን ባይፈቅዱ ኖሮ የማንነት ጥያቄ የኢትዮጵያን ሕዝብ ሊለያየውና ሊበታትነው አይችልም ነበር። ሕዝቡ ይኼን በሚገባ ያውቃል። ሕዝቡን የምንለያየው የፖለቲካ ልሂቃኖቹና ምሁራኖቹ ነን። ከማንኛውም አገር በበለጠ ደረጃ የኢትዮጵያ ሕዝብ ጠባብ ጎሰኛና ብሄርተኛ ሆኖ አያውቅም። ጎሠኛ ቢሆን ኖሮ ብዙ እልቂት ይካሄድ ነበር። ሕዝቡ ተጋብቷል፤ ተዋልዷል፤ ተቻችሎ ይኖራል። የአድዋን የመቶ ሃያኛ ዓመት በዓል ስናከብር ማስታወስ ያለብን ድሉ የሁሉም ኢትዮጵያዊያን ድል መሆኑን ነው። ማንም ሳይስገድደው ገበሬው፤ ነጋዴው፤ የቢሮ ሰራተኛው፤ ወታደሩና ሌላው ከሁሉም የኢትዮጵያ ክፍሎችና ጎሳዎች ስንቁን ተሸክሞ ጣልያንን ተባብሮ አሸንፎ ወደመጣበት የመለሰው ከጎሰኛነትና ከጎጠኛነት ባሻገር ለአገሩ ነጻነት፤ ሉዐላዊነትና ለሕዝቡ ክብር ስለቆመ ነው። ዛሬ ማንነት መነገጃ ሆኗል፤ ትርጉም አጥቷል። የማንነት ጥያቄ ተቀዳሚ ሆኗል ሲባል አሁንም የሕዝቡን ልዩነት የሚያሳይ አይደለም። አንድ ግለሰብ በሞያው ገበሬ ወይንም ነጋዴ፤ በኃይማኖቱ ክርስቲያን ወይንም ሙስለም፤ በጾታው ወንድ ወይንም ሴት ወዘተ ሊሆን መብቱ ነው። ይኼን መብት ማንም ሊነፍገውና ሊከለክለው አይችልም። ከዚያ ባሻገር ግን በአገር ደረጃ “ጋናዊው እኔ ጋናዊ ነኝ” እንደሚለው ሁሉ ኢትዮጵያዊው “እኔ ኢትዮጵያዊ ነኝ” የማለት ግዴታችን ግልጽ ነው። በዜግነታችን መለያ ኢትዮጵይዊ ነን ካልን መኖሪያችን በጎሳዊ ክልል ምሽግ፤ ግንብና ድንበር ሊወሰን አይችልም። በእያንዳዱ ክልል የእያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ መብት ካልተከበረ የማንም መብት ሊከበር አይችልም። ይኼን ካልተቀበልን ከህወሓትና ሌሎች የጎሳ ስብስቦች ከሚሉት ምን ይለየናል?

በነገራችን ላይ፤ በጎሳ መለያየት በተመጣጠነ፤ በዘላቂና ፍትሃዊ የኢኮኖሚና የማህበረሰባዊ እድገት ላይ ከፍተኛ ተጽኖ አለው። ለምሳሌ፤ የኦሞ ሸለቆ፤ የቤኒ-ሻንጉል ጉሙዝ፤ የአፋር፤ የጋምቤላ፤ የኦጋዴን ሕዝብ በዜግነቱ ምን ያገኘው ጥቅም አለ?

ሶስት፤ የህወሓት ደጋፊዎችና ወፍ ዘራሽ ተጠቃሚዎች እንደሚሉት ሳይሆን የጎሳ ፖለቲካ ለሃያ አምስት ዓመታት ሊሰራ የቻለው የኢትዮጵያ ሕዝብ ስለተቀበለው አይደለም። ህወሓት ለብዙ ሽህ ዓመታት በወንድማማችነት፤ በእህትማማችነት ሲኖር የቆየውን ሕዝብ፤ በተለይ የአማራውንና የኦሮሞውን ሕዝብ እንዲጋጭ በማድረጉ ነው። ይኼን መከፋፈል ለድብቅ አጀንዳቸው የሚጠቀሙ ከፋፋዮች ቢኖሩም ሁኔታውን የፈጠረው የህወሓትና ተባባሪው የኢህአዴግ አመራር ነው። ለምሳሌ፤ ከጅምሩ ህወሓት ህብረብሄር የሆኑ የፖለቲካ ፓርቲዎችን፤ አገር ወዳዶችን፤ ምሁራንን፤ የሞያና ሌሎች ተቋሞችን በማፈራረሱ። በምትካቸው ልክ በፋብሪካ እንደሚመረቱ አድርጎ ለራሱ የሚጠቅሙትን መተኪያዎች አገር አቀፍ በሆነ ደረጃ ዘርግቷል። ፓርላማውን ለራሱ መገልገያ አድርጎታል። ሕግ አዉጭው፤ ሕግ ተርጓሚው፤ ሕግ አስፈጻሚው ህወሓት ነው። ፊት ለፊት ለይስሙላ የሚያስቀምጣቸው ግለሰቦች ከሌሎች ብሄረሰቦች የተወጣጡ ናቸው ተብሎ እንዲታመን ያደርጋል። ይህን ሽፋን (Camouflage) ሕዝቡ ያውቀዋል። ፊት ለፊትና በጀርባ ሆነው ፖሊሲ የሚያወጡትና የሚተገብሩት የህወሓት አባላት ናቸው። የሚጠቀሙባቸው አባባሎች ብዙ ናቸው፤ “ሕገመንግሥቱን ለማስከበር፤ ለመደጋገፍ፤ እድገቱን ለመቀጠል፤ ሽብርተኞችን ለመቆጣጠር” ወዘተ። እናንተን ማን ይቆጣጠራል የሚል ተቋም ወይንም ግለሰብ የለም፤ አይታሰብም። በአንድ ትንተና ላይ ጋርዲያን የተባለው የእንግሊዝ ጋዜጣ በትክክል እንዳስቀመጠው፤ ይህ አገዛዝ ኦርዌልያን (Orwellian) ወይንም የፖሊስ መንግሥት (Police State) ከሆነ ሃያ አምስት ዓመታት ሆኖታል። ከህወሓት ውጭ ያሉት የኢህአዴግ አባል ድርጅቶች ቢቀበሉትም ባይቀበሉትም የበላዩ ወይንም አለቃው ህወሓት ነው። የህወሓትን የበላይነት የማይቀበል የኢህአዴግ አባል ፈልጎ ለማግኘት አይቻልም። “ኢህአደጎች ራሳችሁን ከአምባገነኑ ህወሓት ነጻ አውጡ” ያለ ግለሰብ ትዝ ይለኛል።

አራት፤ ህወሓት ቀላል ድርጅት አይደለም፤ ምስጢር ይጠብቃል። ጠንካራ ስለሆነ ከፋፍሎናል። ህወሓት ይደጋገፋል፤ ይጠቃቀማል። ሌሎቹን አባል ድርጅቶች የማሳመን ችሎታው የሚደነቅ ነው። ያስፈራራል ወይንም ያባብላል፤ ይገዛል፤ ያከብራል፤ ይደልላል፤ ያደኸያል ወይንም በስውር ያሸሻል፤ ያባርራል ወዘተ። አጭበርብሮም ሆነ አስፈራርቶ ምርጫዎችን ለበላይነት ይጠቀማል። ቅንጅትና ህብረት የዘጠና ሰባቱን ምርጫ አሸነፉ። ህወሓት ማሸነፋቸውን አልተቀበለም። የራሳቸው የአመራር ድክመት መኖሩ ባይካድም፤ የሕዝብን ድምጽ የሰረቀው ህወሓት ነው። የፖለቲካ ሙስና በጭካኔ! ተሸንፎ ያሸነፉትን ይቅርታ የሚጠይቅ አገዛዝ ስኬታማ የሆነው በራሱ ጥንካሬ ሳይሆን ተቃዋሚው የተከፋፈለ በመሆኑ፤ የውጭ ድጋፍ ስላለው፤ ህብረብሄር ድርጅቶችን በማፈኑ፤ በማፈራረሱና ቆራጥ የሆኑ አገር ወዳድ ድርጅቶችና መሪዎች ባለመኖራቸውና እንዳይኖሩ በመደረጋቸው ነው። በተደጋጋሚ የታየውና አሁንም የሚደገመው ክስተት አንድ ነው። በጎሳ ተከፋፍሎ ራስን ማጋለጥ የፖለቲካ ክስረት አስከትሏል። የተከፋፈለ ህብረተሰብና ተቃዋሚ ሁሌም የሚያገልግለው ህወሓትን ነው።

እንደገና በ2010 ተወዳዳሪዎችን አፍኖ፤ ከፋፍሎና አስሮ ምርጫውን 99.6 በመቶ አሸነፍኩ አለ። አምስት ዓመት ቆይቶ በለመደው የፖለቲካ ጮሌነት በ2015 ይባስ ብሎ 100 በመቶ “አሸነፍኩ” አለ። ምርጫን መሳቂያና መሳለቂያ አደረገ። ሕዝብን ፍጹም በሆነ ደረጃ ተስፋ አስቆረጠ። የብሄረሰብ እኩልነት ተብሎ ይጠራ የነበረው ስርዓት የኦሮሞ ተወላጅ የሆኑ ኢትዮጵያዊያን ሲታፈኑ፤ ሲገደሉ፤ ሲሰወሩና ሲሰደዱ የጎሳ ፖለቲካ አስተዳደር የማያዋጣ መሆኑን አስመሰከረ። አንዳንድ ተመልካቾች አዲስ ምርጫ “በኦሮሚያ ክልል ቢካሄድ ይመረጣል” ይላሉ። ስር ዓቱ ነጻና ፍትሃዊ ምርጫ የማይፈቅድ መሆኑ እየታወቀ አዲስ ምርጫ ዋጋ ቢስ ነው። የሚያዋጣው ስርዓቱን መለወጥ እንጅ የይስሙላ ምርጫ አይደለም። እንዲያውም የኢትዮጵያን ሕዝብ በተከታታይ ማታለል ነው።

አምስት፤ “ታዲያ ምን አለበት፤ ተቃዋሚው ደካማና የተከፋፈለ ከሆነ፤ ኢህአዴግ ለምን አያሸንፍም? ጠንካራ ፓርቲና መንግሥት ከሌለ ኢትዮጵያ እንደ ሶማሊያና ኬንያ ትሆናለች፤ በአመጸኞች፤ ተገንጣዮችና ሽብርተኞች ትጠቃለች። እድገቷ ያቆማል። የመበታተን አድሏ ይባባሳል። የትኛው ተቃዋሚ ነው ከገዢው ፓርቲ ጋር ሊነጻጸር የሚችል?” የሚሉ ጥያቄዎችና ትችቶች ይሰነዘራሉ። አግባብ አላቸው። በአንድ አገር ሁለት ወይንም ከዚያ በላይ መንግሥታት ሊኖሩ አይችልም። በአንድ ፌደረላዊ አገር የተለያዩ፤ ራሳቸውን እንደ ጎረቤት አገር የሚለዩ አገሮች ሊኖሩ አይችልም። ሁለት ወይንም ከዚያ በላይ የሚሆኑ ራሳቸውን እንደ ነጻ አገር የሚቆጥሩ አገሮች አሉ ከተባለ ኢትዮጵያ የምትባል አገር የለችም ማለት ነው። ቁም ነገሩ ወደዚህ ችግር ያሸጋገረን ማነው? ብለን ብንጠይቅ የክልሎች ሕገመንግሥት ያወጡት የጎሳ ስብስቦች ናቸው፤ ህወሓት፤ ሻቢያና ኦነግ። ይኼን በሚቀጥለው ሃተታየ አቀርባለሁ።

የዚህን የተሳሳተ የጎሳ ፖለቲካ ሂደትና ውጤት እያወቅን፤ አንዳንዶቻችን አውቀንም ይሁን ሳናውቅ እነዚህን መሰረታዊ ችግሮች የፈጠረውን ገዢ ፓርቲና የብሄር ተቃዋሚዎችን በቀላሉ እየሸነገልን ነው። ህወሓት፤ ኢህአዴግን መቃወም አግባብ አለው። ሆኖም፤ ለመቃወም ብቻ ሲባል ብሄርተኞችን፤ ሽብርተኞችን፤ አመፀኞችን፤ ተገንጣዮችን፤ የውጭ ጠላቶችን ወዘተ መደገፍ እንዴት ሊያዋጣ ይችላል? ከአብዛኛው ሕዝብ እኩልነት፤ ፍትህና ዲሞክራሲ ምኞት ጋር ምን ግንኙነት አለው? የአገሪቱን በክልል መከፋፈል ተቀብሎ ኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊያን የሚሉትን እሴት የተመረኮዙ ስያሜዎች ለመጠቀም አለመቻል፤ ወይንም አለመፍቀድ የማንን ዘላቂ ግብ ያጠንክራል፤ ያገልግላል? ሕዝብን ከሕዝብ-ኦሮሞውን ከአማራው፤ ሁለቱን ከትግራዩና ከሌላው ሕዝብ–ጋር በማገናኘት፤ በማስታረቅና በማስማማት ፋንታ እንዲጋጭ የምናደርግበት ምክንያት ምንድን ነው? ከጥንት ጀምሮ ዛሬ ኦሮምያ በሚባለው ክልል ብዙ ሚሊየኖች የኦሮሞ ብሄረሰብ ያልሆኑ ኢትዮጵያዊያን ይኖራሉ። የኦሮሞ ሕዝብ በጎንደር፤ በጎጃም፤ በወሎ፤ በሸዋና ሌሎች ቦታዎች ይኖራል። እነለያይ ብንል ማን ከማን ይለያያል። በመፈቃቀድና ተፈቃቅዶ ችግሮችን በጋራ ከመፍታት የበለጠ አማራጭ የለም። አለያ፤ ከአንድ ችግር ወጥተን ወደሌላ ችግር መግባታችን አይቀርም። ያም ሆነ ይህ፤ የጎሳ ጥላቻና መከፋፈል ህይወትና ቆይታ የሚሰጠው እንቃወመዋለን ለምንለው ገዢ ፓርቲ ነው።

ለእውነተኛ ፍትህ ቆመናል ካልን መቀበል የሚኖርብን ተራው የኢትዮጵያ ሕዝብ የጎሳ ግጭት የማይፈልግ መሆኑን ነው። በሌላ በኩል ህወሓት ውስጥ ለውስጥ ኦሮሞ ያልሆነውን የሕብረተሰብ ክፍል የሌለ ጠላት ፈጥሮ “እኔን ካልደገፍክ ህልውናህ አስተማማኝ አይሆንም” የሚለውን የከፋፍለህ ግዛው ዘዴ መከላከል አለብን። አንዴ አኟኩን፤ ሌላ ጊዜ አማራውን፤ ሌላ ጊዜ የኦጋዴን ሶማሌውን፤ ሌላ ጊዜ የኦሞ ሸለቆ ኢትዮጵያዊውን፤ ሌላ ጊዜ የኦሮሞ ተወላጁን ወዘተ እያሰሩ፤ እያሳደዱ፤ እየወነጀሉ፤ እያፈራረሱ፤ ዜጎች በድብቅ እንዲሰወሩ እያደረጉ፤ ከደርግ በተለየ ጥበብ በማይታወቁ መንገዶች ተቃዋዋሚውን “እየሰወሩ” ተቃዋሚ ፓርቲ፤ ዲሞክራትና አገር ወዳድ የለም ማለት፤ ወይንም እየጨፈጨፉ አልጨፈጨፍኩም ማለት የፖለቲካ ጮሌነት ነው። ፈረንጆች ማኬቬሊያን የሆነ የፖለቲላ አመራር ይሉታል። የህወሓት አለቃዎችና ወራሾች ከዲሞክራቶችና አገር ወዳዶች ይልቅ ከአምባገነኖች ፈላስፋዎች የተማሩት ይልቃል።

ማኬአቬሊ (Machiavelli) በ 1513 The Prince በተባለው የፖለቲካ ፍልስፍና መጽሃፉ አንድ ቡድን ሌሎችን ፍጹም በሆነ ደረጃ የበላይ ሆኖ እንዴት እንደሚገዛ ትምህርት ያቀርባል። አራት የተለያዩ አምባገነን የሆኑ የመንግሥት ስርዓቶችን አጥንቶና መሰረት አድርጎ እያንዳንዳቸው እንዴት የበላይነታቸውን እንደሚያጠናክሩ ዘዴዎችን ይጠቁማል። ከእነዚህ መካከል ከፍተኛ ሚና ያለው የስለላና የወታደር ኃይል ተቋም ወሳኝ መሆኑን ይናገራል። ኃይል ያለው ይገዛል፤ ኃይል የሌለው ይገዛል የሚል መሆኑ ነው። ህወሓት ይኼን ጥበብ ሙሉ በሙሉ ተጠቅሞበታል፤ የአሜሪካ እርዳታ ለጥንካሬው መሰረት ሆኗል። ማኬያቬሊ እንዳለው የመሳሪያ የበላይነት በአንድ በኩል፤ በሌላ በኩል ግብረገብነት፤ ፍትህ፤ ሰብአዊነት አብረው አይሄዱም። የህወሓት ህልውናና አምባገነናዊው አገዛዝ እንዲቀጥል ከተፈለገ ህወሓት ጭካኔ ያለበት (Evil Political Actions) እርምጃ መውሰዱ የማይቀር ነው። ፈላስፋው ሁኔታዎች ሲለወጡ አምባገነን አገዛዝም እንደሚለወጥ ይናገራል። ሕዝብ በአንድ ድምጽ ተያይዞና ተባብሮ ከተነሳ የሚያቆመው ኃይል እንደሌለ ይታወቃል። በጎሳ መከፋፈላችን ይብቃ የምልበት መሰረታዊ ሃሳብ ይኼ ነው።

እርስ በርሳችን ከመጋጨት በላይ መጠየቅ ያለብን የሕዝብ ዐመጽ ተደጋጋሚ ሲሆንስ ህወሓት ራሱን ለመለወጥ ፍላጎት አለው ወይንስ የማኬያቬሊን ፍልስፍና ይከተላል? አላውቅም። የማውቀው የጭካኔ አገዛዝ ለጊዜው እርጋታ ቢፈጥርም መሰረታዊ የሆኑ ችግሮችን አይፈታም። መሰረታዊ ችግሮች የሚፈቱት የኢትዮጵያ ሕዝብ ለመብቱ በአንድ ድምጽ ሲነሳ ነው። በኦሮምያ፤ በጋምቤላ፤ በቤኒ ሻንጉል ጉሙዝ፤ በኦጋዴንና በሰሜን ጎንደር በተከታታይ የሚታየው የሕዝብ ዐመጽ ለገዢው ፓርቲ ስጋት እንደፈጠረ ይታያል። ሆኖም፤ ይህ ስጋት ወደ ለውጥ ሊሸጋገር የሚችለው የጎሳና ሌሎች ልሂቃን የእርስ በርስ ትችቱን ትተው ወደ አንድነትም ባይሆን ወደ እውነተኛ መተባበር ሲሸጋገሩ ነው። አንድነት ስል፤ ማንም ክፍል በተናጠል የአንድነት ጠበቃና ሃላፊ እንዳልሆነ ለማሳሰብ እፈልጋለሁ። የኢትዮጵያ ብሄራዊ አንድነትና ሉዐላዊነት የአንድ ወይንም የሁለት ብሄረሰብ ጉዳይ ብቻ አይደለም። የኢትዮጵያ ሕዝብ አንድነት ስል የሁሉም ሕዝቦች አንድነት ማለቴ ነው። ብሄራዊ አንድነት አስተማማኝ የሚሆነው የፌደራሉ መንግሥት መሪዎች የአገሪቱን ስብጥር ሕዝብ ሲወክሉ ነው። የአገርም ሆነ የሕዝብ ጥንካሬ መሰረት ኢትዮጵያዊያን “የእኔ መንግሥት ነው” ለማለት ሲችሉ ነው። የህወሓት ድክመት መሰረት የአንድ አናሳ ብሄረሰብ ፍጹም የበላይነት ነው።

ስድስት፤ በተከታታይ ጽሁፎቸ በማስረጃ እንዳሳየሁት፤ በሁሉም ወሳኝ በሆኑ የስለላና መረጃ፤ የመከላከያ፤ የፌደራል ፖሊስ፤ ቁልፍ የሆኑ ሚኒስትሪዎችና የአገር ንብረት ተቋሞች (State owned enterprises such as Ethiopian Airlines, Telecommunication etc.) ባለፉት ሃያ አምስት ዓመታት ፖሊሲና ውሳኔ ለማድረግ የሚችሉት ግለሰቦች ትግራዮች ናቸው። ይህ የአንድ ብሄረሰብ ፍጹም የሆነ የበላይነት በኢትዮጵያ ታሪክ ታይቶ የማይታወቅ ነው። ኢትዮጵያዊያን ብቻ ሳይሆኑ የውጭ ተመልካቾች ይኼ ሁኔታ አደገኛ መሆኑን በተደጋጋሚ አሳስበዋል። የኢትዮጵያን የመከላከያን ኃይል ተቋም ብቻ ብናይ ከኮሎኔል በላይ የበላይ እዙ አባላት ከሆኑት መካከል 97 በመቶ የሚሆኑት የህወሓት አብላት ወይንም ደጋፊዎች ናቸው፤ ከአንድ ብሄረሰብ የተወጣጡ ማለት ነው። (See on line “Ethiopia promotes 37 Senior Officers to the rank of general). ከአገሪቱ ዘላቂ ደህንነትና ከሕዝቧ አንድነት አንጻር ብናየው ይኼ ለትግራይ ሕዝብም አደገኛ ነው። ግልጽ ለማድረግ የምፈልገው የትግራይ ተወላጆች በእዙ ሚና አይኑራቸው ለማለት አይደለም። የእዙ ስብጥር የኢትዮጵያን ሕዝብ የሚወክል ይሁን ማለቴ ነው። ይህ ለኢትዮጵያ ደህንነት ወሳኝ ነው።

ሌሎቻችን፤ የህወሓት አባላትንና ደጋፊ ትግራዮችን ጨምሮ፤ መተቸት ያለብን “ለብሄረሰቦች እኩልነት” ቆምኩ የሚለው ህወሓት ይኼን የሚያስወቅስ ጎሳዊ አድልዎ በተደጋጋሚ መርህ ሲያደርግ አለመተማመንን እንደፈጠረና ይኼ አለመተማመን ወደ አደገኛ ሁኔታ እንደሚያመራ ማሳየትና መፍትሄ መፈለግ ነው። መተቸቱ ብቻ በቂ አይደለም። የእዙ ስብጥር ወሳኝ ነው ስል፤ የጋምቤላ ወይንም የጎንደር ወይንም የኦጋዴን ወይንም የኦሮምያ ወዘተ ሕዝብ የትግራይ  አዛዦችን፤ ልዩ ኃይሉን አጋዚን በሚያዩበት ጊዜ ምን እንደሚሰማቸው ለማጤን ይቻላል። የተጎዱት “እኛና እነሱ” እያሉ ቢናገሩ እንዴት ይፈረድባቸዋል። “እኛና እነሱ” የሚለው እጅግ በጣም አደገኛ መሆኑን ሁላችንም መገንዘብ አለብን።

በኢኮኖሚውም ያለው ሁኔታ ተመሳሳይ ነው። የዘመናዊውን ኢኮኖሚ የበላይነት ጥልቀት ባለው መልኩ ብናየው የበላይነቱን የያዙት የህወሓት አባላት፤ ታማኞችና ደጋፊዎች ናቸው። እዚህ ላይ ጥንቃቄ ማድረግ አግባብ አለው። አንድ፤ የወፍ ዘራሽ ተጠቃሚዎች መኖራቸውን መካድ አንችልም። የኢኮኖሚው የበላይነት በአብዛኛው የህወሓት ልሂቃን ይሁን እንጅ ከሌሎች ጎሳዎች የተወጣጡ አዲስ ሃብታሞች እንዳሉ መካድ አይቻልም። ስርጭቱ የመደብ መልክ እየያዘ ነው—አማራም፤ ጉራጌም፤ ኦሮሞም፤ ወላይታም፤ ሶማሌም፤ ክርስቲያንም፤ ሙስለምም ወዘተ ተሳታፊ ነኝ የሚል የመደብ መልክ የያዘበት ሁኔታ ተፈጥሯል። በአጭሩ፤ የህወሓት የኢኮኖሚ የበላይነት ባይካድም፤ ኪራይ ሰብሳቢ ሲባል የህወሓት አባላት ብቻ ናቸው ከሚል የተሳሳተ ድምዳሜ ላይ እንዳንደርስ ማለቴ ነው። ሁለት፤ አብዛኛው የትግራይ ሕዝብ የኪራይ ሰብሳቢው ክበብ ወይንም ቡድን አባል አይደለም። በእኔ ግምት አብዛኛው የትግራይ ሕዝብ ድሃ ነው፤ ሰርቶ አደር ነው፤ አገር ወዳድ ነው፤ የታፈነና ነጻነት የሌለው ነው፤ ባህሉን የሚያከብር መንፈሳዊ ሕዝብ ነው። ባጭሩ፤ የህወሓትን የበላይነት ከትግራይ ሕዝብ ሁኔታ እንለየው።

በቅርቡ ጠቅላይ ሚንስትር ኃይለማሪያም ደሳለኝ ስለ አገሪቱ ሁኔታ፤ በተለይ በኦሮምያና ሌሎች አካባቢዎች ስለተከሰተው ሕዝባዊ አመጽ ሲናገሩ ችግሩን የፈጠረው ስርዓቱ፤ መንግሥቱና አመራሩ መሆኑን አስምረውበታል። እሳቸው ያሉት ህዝብን ለመሸንገል ካልሆነ በከፊልም ቢሆን ያሉትን እጋራለሁ። ለምስታወስ፤ ስለመጥፎ አስተዳደርና ስለ ኪራይ ሰብሳቢነት ባህልም ተመሳሳይ ትችት አድርገው ነበር። ትዝ እንደሚለኝ ከሆነ “እኛ ከዚህ ስንወጣ ልክ እንዳልሰማን ሆነን ወደራሳችን ቡድኖች እንገባለን፤ ለውጥ አንዳናካሂድ ማነቆ እንሆናለን” በለዋል። ምንም የረባ ለውጥ አልታየም። አሁንም ያሉት የችግሩ መንስኤ “እኛው ኢህአዴጎች ነን (We in EPRDF are to blame)” ነው። ይኼን በመለስ ዜናዊ አገዛዝ የማይታሰብ መናገር ቀላል አይደለም። አሁንም በህወሓት ውስጥ የሚገኙ ግትሮች የችግሩን ጥልቀትና ስፋት የተረዱት አይመስልም። ጠቅላይ ሚንስትር ተሹሞ አገሪቱን ያለምንም ጫና ለመምራትና መፍትሄዎችን ለመፈለገ ካልቻለ “ጉልቻ” መሆኑ ነው፤ ሰው ጉልቻ አይደለም። ሌላው ቢቀር ለህሊናው ተገዢ መሆን ግዴታው ነው። እሳቸእ ስለተናገሩ የገዢው ፓርቲ የበላይ ህወሓት ይለወጣል ብሎ ማሰብ ራስን ማታለል ነው።

የማይካደው የፖለቲካ ክስተት አንድ ነው። ቀደም ሲል በጎንደር፤ በጋምቤላ፤ በኦጋዴን፤ ባለፉት አምስት ወራት በኦሮምያና በአዲስ አበባ የተካሄደውና የሚካሄደው የሕዝብ እምቢተኛነት መሰረታዊ የሆኑ የፖሊሲ፤ የመዋቅር፤ የአስተዳደርና የኪራይ ሰብሳቢነት ውጤቶች ናቸው። ሕዝብ እንዲሁ በራሱ ላይ ፈርዶ ልደብደብ፤ ልታሰር፤ ልሰወር፤ ልገደል፤ ልሰደድ ወዘተ አይልም። ሕዝብን ወደ እምቢተኛነት የሚወስዱት የሚከተሉት ናቸው፤  የፍትህ መጓደል፤ የሰብአዊ መብቶች መታፈን፤ የነጻነት አለመኖር  ጭፍን የሆነ ጎሳዊ አድልዎ፤ ጉቦ፤ ሙስናና ከሕግ ውጭ ከአገር የሚወጣ ግዙፍ ኃብት  የኑሮ ውድነት፤ የአቅርቦት ጉድለት  የሰብአዊ ክብር መውደም፤ ስደት፤ በወጣት ሴቶች መነገድ  የመልካም አስተዳደር መጉደል  ችግሮችን በግድያ፤ በአፈና፤ ዜጎችን በመሰወር፤ በመደብደብ ለመፍታት መሞከር  የመሬት ነጠቃና የዜጎች ከቀያቸው በተከታታይ መባረር፤ መገለል፤ መኖሪያ ማጣት

በአጠቃላይ ስመለከተው የኢትዮጵያና የኢትዮጵያ ሕዝብ መሰረታዊ ችግር ስርዓቱ ነው። በኢትዮጵያ ሕዝብ መካከል ያለውን ጥቃቅን የተለመደ የባህል፤ የልምድ፤ የቋንቋ ወዘተ ልዩነት ወደማይታረቅ ልዩነት እንዲሸጋገር የምንጎተጉተው የፖለቲካ ልሂቃንና ምሁራን ጭምር ነን። በአገዛዝና በአመራር ደረጃ ሲታይ፤ ተቃርኖው በአንድ በኩል ህወሓት በበላይነት በሚመራው ኢህአዴግ እና በሌላ በኩል በሕዝብ መካከል ነው። ችግሩ ሊፈታ የሚችለው ሕዝብ የስልጣኑ ባለቤት ሲሆን ነው።

ጠቅላይ ሚንስትሩ እንዳሉት ኢህአዴግ የፈጠረውን ችግር በእልክ፤ በጭካኔ፤ በማስፈራራት፤ በማሰር፤ በማቁሰል፤ በመሰወር ሊፈታው አይችልም። ሰውን ለመሰወር ቢቻልም ችግሩን ለመሰወር አይቻልም። ሊፈታ የሚችለው በፍትህ፤ በሕግ የበላይነትና በእውነተኛ ዲሞክራሳዊ አማራጭ ብቻ ነው።

በቅርቡ ክራይስስ ግሩፕ የተባለው ተቋም እንዲህ ብሎ ነበር፤   “ልክ እንደጎረቤት አገሮች፤ ኢትዮጵያን የገጠማት የፖሊሲ አማራጭ ጉዳይ ነው። የውስጥ ችግሮችን ለመፍታት ስርዓት ወለድ ጉዳዮች መፈታት አለባቸው”። ጠቅላይ ሚንስትሩ በቅንነትም ሆነ ሌላ ችግሩን “የፈጠርነው እኛው ነን” ካሉ የሚመሩት ፓርቲ ደፍሮ ለሕዝብ የፖለቲካ የበላይነት ማጎብደድና መገዛት አለበት።

“Ethiopia, like its immediate neighbours, is faced with difficult policy choices

involved in guarding against internal radicalisation through systematic (constitutionally questionable) interventions…The government, and donors keen to support global efforts against violent extremism, should always consider first, the risk of such interventions to the state’s neutrality as mediator..Above all, those backing interventions should always seek better understanding of what faith (ለምሳሌ) means to multi-ethnic, religiously diverse societies like (but not limited to) Ethiopia, in which the distinction between group and individual identity is often not well defined, and rival local actors are apt to make use of religious disputes where social and governmental constraints inhibit open political competition.” See Ethiopia: Governing

the Faithful. Crisis Group Africa Briefing N°117. Nairobi/Brussels, 22 February 2016

ህብር ሬድዮን በህብር ሬዲዮ ድህረ ገጽ ወይም በቀጥታ በስልክ ለማዳመጥ 712 -432-8451 መደወል ብቻ በቂ ነው በእንግሊዝ ለምትኖሩ በ01405770140 በስልክ ማዳመጥ ይቻላል። ዘወትር በድህረ ገጻችን፣ ከ googel app store Hiber Radio ወደ ስልክዎ በመጫን ካልሆነም በዘሐበሻ እንዲሁም በተጠቀሱት ስልኮች ማዳመጥ ይቻላል።

 

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *