Hiber Radio: ዛሬ አቶ በቀለ ገርባ በውስጥ ከነቴራ፣ በቁምጣና በባዶ እግራቸው ፍርድ ቤት ቀረቡ፣‹‹የማረሚያ ቤቱ ኃላፊዎች እስካልተቀየሩ ድረስ ሕይወታችን የከፋ አደጋ ላይ ነው፤ …ለቀጣይ ቀጠሮ መገኘታችንምም እርግጠኞች አይደለንም››፣‹‹ወደጨለማ ክፍል ወሰዱን፡፡ ከመካከላችን የተወሰኑትንም ክፉኛ ደበደቧቸው››፣ ‹‹እንደዜጎች እየተቆጠርን አይደለም›.አቶ በቀለ ገርባ

አቶ በቀለ ከእስር በፊትና እነ አቶ በቀለ ገርባ ዛሬ በፍርድ ቤት ሲቀርቡ በሩቅ የተነሳ
አቶ በቀለ ከእስር በፊትና እነ አቶ በቀለ ገርባ ዛሬ በፍርድ ቤት ሲቀርቡ በሩቅ የተነሳ

የዛሬው የፍርድ ቤት ውሎ የተለመደ የፍርድ ቤት ስቃይ የተደመጠበት ብቻ አይደለም።ይሄ ስርዓት ውሎ ባደረ ቁጥር የሚመሩት ወሮበሎች ምን ያህል ዝቅ ሊያደርጉን የቆረጡ መሆናቸውን በልዩ ልዩ መንገድ ለማሳየት የቆረጡበት ነው።የተራቆቱት ነጻነት ወዳዶች ሁሉ ናቸው። የተዋረደው መብቱ የተረገጠው ሁሉ ነው።እነ አቶ በቀለ በባዶ እግርና በካናቴራና በቁምጣ ፍርድ ቤት እንዲቀርቡ የወሰኑት የህወሃት መሪዎች በእርግጥ ውርደታቸውን እያፋጠኑ ለመሆኑ ጉልህ ማሳያ ነው።በደርግ ጊዜ ሆነ ተብሎ የሚነገር የእስር ቤት ታሪክ ሰምተን ነበር። አንድ ከፍተኛ የደርግ ባለስልጣን ከርቸሌን ሊጎበኝ ይሄዳል አሉ። ያው የተለመደ ጉብኝት ድርጎ ሊወጣ ሲል አንድ ደፋር የጊዜው የፖለቲካ እስረኛ <<እባካችሁ ይሄን እስር ቤት አድሱት አስተካክሉት ያው ነገም ለእናንተ ነው >> ይላል። የደርግን መጨረሻና የደርግ ባለስልጣናትን የከርቸሌ ኑሮ ለሚያውቅ ያ ሰው እውነትም አርቆ አስተዋይ መሆኑን ይረዳል፡የሆነው ሆኖ የዛሬውን የእነ አቶ በቀለ ገርባ ሁኔታ ስናይ እነዚሀ ሰዎች ለራሳቸው የነገ ዕጣ እያሰቡ እንዳልሆ ገባን። ለማንናውም በቀደም <<ፈተና ተሰረቀ አገር ተጎዳ>> ብላችሁ ኡኡ ስትሉ የነበራችሁ ደንባሮች እስቲ ለባለስልጣኖቻቹህን ንገሯቸው ጉድጓዳችሁን ምነው ራቅ አድርጋችሁ መቆፈር መቼ ነው የምታቆሙት በሉልን። የተዋረዱት እነሱ እንጂ እነ በቀለማ ዛሬ ብቻ ሳይሆን ለሕዝብ የቆሙ እለት ጀምሮ ከብረዋል።የፍርድ ቤቱን ውሎ የጋዜጠኛ ኤልአስ ገብሩ ዘገባ እነሆ፦

በኤልያስ ገብሩ

‹‹በባለፈው ቀጠሯችን ለብሰን ፍርድ ቤት ልንቀርብ የነበረውን ጥቁር ልብስ አውልቁ ተባልን፡፡ አናወልቅም አለን፡፡ የፈለግነውን የመልበስ ሕገ-መንግስታዊ መብታችን ነው፡፡ ጥቁር ልብስ የለበስነውም፤ ከ50ሺህ በላይ የአንድ ብሄር ተወላጆች እስር ቤት መገኘታቸውንና በዚህ ዓመትም በጥቂት ወራት ውስጥ ከ200-300 የሚደርሱ የኦሮሚያ ክልል ተወላጆች መገደላቸውን በማዘን ለመግለጽ ነው፡፡ ድርጊታችንም ይሆን የነበረው የፍርድ ቤትን አሰራርን ምንም በማይነካ መልኩ በሰላም ነው፡፡ ይሄ አይሆንም ተብለን ዛቻና ስድብ ተደሰብን፡፡

ትናንት ከሰዓት በኋላ ዛሬ ፍርድ ቤት የምንቀርብ ሰዎች ለይተን ከየክፍላችን እንድንመጣ ተደረገ፡፡ ልብሶቻችንንም ይዘን እንድንወጣ አደረጉ፡፡ ከልብሶቻችን መካከል ጥቁር ልብስ እየተፈለገ ተወሰደ፡፡ እኛም ‹ልብሶቻችንን በሙሉ ልትመልሱልን ይገባል› ብለን ጠየቅን፡፡ ወደጨለማ ክፍል ወሰዱን፡፡ ከመካከላችን የተወሰኑትንም ክፉኛ ደበደቧቸው፡፡ የተደበደቡት ሰዎች እዚሁ ስላሉ ለችሎቱ መናገር ይችላሉ፡፡ ልብሶቻችን ሜዳ ላይ ተበትኖ ስለነበረ ሌሎች እስረኞች የሚፈልጉትን ወሰዱ (ተቀራመቱት)፡፡ የተረፈውን አምጥተው ክፍላችን ውስጥ አስቀመጡት፡፡

ዛሬም ድረስ ምግብ አልበላንም፡፡ እጆቻችን ጥዋት ድረስ በካቴና ታስሮ ነበር፡፡ በዘረኝነት ላይ የተመሰረተ ድርጊት ነው የተፈጸመብን፡፡ የኦሮሞ ተወላጅ ብቻ እየተመረጠ ተደብድቧል፡፡ የታሰርንበት ቦታ በዘረኝነት ላይ የተመሰረተ ተቋም ነው፡፡ ‹አንተ ነህ እንዲህ የምታደርገው፡፡ እናገኝሃለን› ብለውኛልም፡፡ ፍርድ ቤቱ ተለዋጭ/ ተቀያሪ ማቆያ ቦታ ያዘጋጅልን፡፡ አሁንም ተመልሰን ቂሊንጦ ስንሄድ ምን እንደሚደርስብን አናውቅም፤ ስጋት አለን፡፡ የማረሚያ ቤቱ ኃላፊዎች እስካልተቀየሩ ድረስ ሕይወታችን የከፋ አደጋ ላይ ነው፤ በጣም ያሰጋናል፡፡ ለቀጣይ ቀጠሮ መገኘታችንም እርግጠኞች አይደለንም፡፡ ቤተሰቦቻችን እንዳያዩን እየተደረገ ነው፡፡ ዛሬም ፍርድ ቤት ቅጥር ግቢ ውስጥ ከገባን በኋላ ሰዎች እንዳያዩን ተደርጓል፡፡ እንዲህ የተድበሰበሰ ነገር መንግስት ለምን ይሰራል? እንደዜጎች እየተቆጠርን አይደለም፡፡››

[ይህንን ልብ የሚነካ ንግግር ከአንድ ሰዓት በፊት በፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት 19ኛ ወንጀል ችሎት ቆመው ሲናገሩ ያደመጥኳቸው በጸረ-ሽብርተኝነት ወንጀል ተከስሰው ከ22 ሰዎች ጋር የፍርድ ሂደታቸውን የሚከታተሉት አቶ በቀለ ገርባ ነበሩ፡፡ አቶ በቀለ በዛሬው የችሎት ወሎ ከፊል ሰውነታቸውን የሚሳይ የውስጥ ነጭ ከነቴራ (ፓክ-አውት)ና ጥቁር ቁምጣ ለብሰው በባዶ እግራቸው ነበሩ፡፡ (ሌሎች አምስት ተከሳሾችም ተመሳሳይ አለባበስ ለብሰው ነበር) በቅርብ ርቀት እንዳየኋቸው ከሆነ፣ የግንባራቸው ደምስር ጎሎቶ ይታያል፡፡ እንቅልፍ አለመተኛታቸውንም ፊታቸው ይናገራል፡፡ በችሎቱ የነበሩ ከ10 በላይ ወታደሮች (መሳሪያ የታጠቁም ጭምር) የአቶ በቀለን ንግግር በተመስጦ ሲዳምጡ አስተውያለሁ፡፡ …እንግዲህ 25 ዓመታትም ታልፎ፤ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት አያያዝ በእስረኞች ላይ አንድም ይህንን ይመስላል፤ ማዘን ብቻ!]

ህብር ሬድዮን በህብር ሬዲዮ ድህረ ገጽ ወይም በቀጥታ በስልክ ለማዳመጥ 712 -432-8451 መደወል ብቻ በቂ ነው በእንግሊዝ ለምትኖሩ በ01405770140 በስልክ ማዳመጥ ይቻላል። ዘወትር በድህረ ገጻችን፣ ከ googel app store Hiber Radio ወደ ስልክዎ በመጫን ካልሆነም በዘሐበሻ እንዲሁም በተጠቀሱት ስልኮች ማዳመጥ ይቻላል።

 

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *