የቀድሞው የአንድነት የሕዝብ ግንኙነት ሀላፊ ሀብታሙ አያሌው ከአገር ወጥቶ እንዲታከም በእስር ቤት በወሰዱበት የማሰቃየት እርምጃ ለህመም መዳረጉ ሳያንስ በፍርድ ቤት ስም ከአገር እንዳይወጣ ለተጣለበት እግድ ተደጋጋሚ ማመልከቻ አቅርቦ ውጤት አልተገኘም። ጠበቃ አምሐ መኮንን ሀብታሙን ወክሎ ጠቅላይ ፍርድ ቤቱን ዛሬ አርብ ላቀረበውእግዱ ተነስቶ ከአገር ወጥቶ እንዲታከም አቤቱታ ውሳኔ አላገኘም።ከጠበቃው አገኘውን ማስረጃ ጠቅሶ ጋዜጠና ኤልያስ ገብሩ ይህን ጽፏል፦ “ሀብታሙ አያሌው ከሀገር ወጥቶ እንዲታከም ያቀረባችሁት የእግድ ማስረጃ ደርሶናል። ግን በሀገር ውስጥ መታከም እንደማይችል አልተገለጸም። ህክምናውን ከሀገር ውጪ ብቻ መታከም አለበት የሚል በዶክተሮች የተወሰነ ማስረጃ ከደረሰን በማንኛውም ሰዓት እግዱን እናነሳለን። አሊያ በቀጣይ ማክሰኞ በሚኖረው የእነህብታሙ የፍርድ ቤት ውሳኔ ላይ እናየዋለን። በዚያን ቀን ሀብታሙን በተመለከተ አንድ ነገር እንወስናለን።” ብለዋል። ሀብታሙ ስለ ህመሙ ከጥቂት ሳምንት በፊት ለህብር ሬዲዮ በሰጠው ቃለ መጠይቅ ላይ አንዳንዴ ጣጣዬን ስጨርስ ያስወጡኝ ይመስለኛል ብሎ ነበር። የጤናው ደረጃ ሲከፋ ከእስር ቤት ሲወታ ከአገር አይውጣ ብሎ ማገዱ ሲከተል በእርግጥ አበቃለት ያሉ ይመስላል።
የሀብታሙ ጉዳይን በቅርብ እየተከታተለ የሚገኘውና በሆስፒታል አስታማሚው የትግል አጋሩ ዳንኤል ሺበሺ የሀብታሙ አያሌው ዕጣ ፈንታ ምን ይሆን ሲል ይጠይቃል አንብቡት።
የሀብታሙ አያሌው ዕጣ ፈንታ ምን ይሆን?
ቀን ሰኔ 24 ቀን 2008 ዓም (ከሌሊቱ 8:20) (በዳንኤል ሺበሺ) በዛሬው ቀን ሁለት ጉዳዎች ይጠበቁ ነበር። የመጀመሪያው እሱን ተቀብሎ ስለ ጤናው የሚከታተለው ሆስፒታል የሚሰጠው ውሳኔ ምን ይሆን ይሁን የሚል ሲሆን፣ ሌላይኛው ደግሞ የፌዴራል ጠቅላይ ፍ/ቤት በጠበቃቸው በኩል ለቀረበው የጉዞ እገዳ ይነሳ አቤቱታ ላይ ውሳኔን በተመለከተ ነበር። ሁለቱም ጉዳዮች መስማት በምጥ ላይ ለሚገኙ ወገኖቻችን አጓግ መሆናቸው ግልጽ ነው። የጉዞ እገዳን በተመለከተ አሁን ዝርዝር ነገር ውስጥ መግባት ባልፈልግም የፊታችን ማክሰኞ ማለትም ሰኔ 28 ቀን, 2008 ዓም ስለ ሀብታሙ ከምር ለተጨነቁት፣ ካንጀት ላለቀሱ በየሃይማኖታቸው ወደየፈጣሪያቸው ይግባኝ ላሉ ሁሉ ጮቤ የሚያስረግጥ ወሬ ሊኖር እንደሚችል በአምላኬም በኢት/ያ ህዝብ ጩኸትም ፅኑ እምነት አለኝ። <<የጭቁኖች እንባ የፈጣሪው ድምፅ ነውና።>
ስለዚህ ሀብታሙን ለማሳከም፣ ሀብታሙን ለመቀበል፣ ለመርዳትና ነፍሱ እንዲተርፍለት የተጋችሁ ሁሉ፣ ያደረጋችሁትና የሚታደርጉት ጥረታችሁ እንደተጠበቀ ሆኖ ጎን ለጎን የጉዞ ጊዜ እንዳይሰተጓግል የጉዞ ሁኔታዎች ዝግጅት ከወዲሁ እንዲጀመር ለመጠቆም እወዳለሁ። በዚሁ አጋጣም ዛሬ የአበቱታውን ምላሽ ለመስማት ወደ ኢፌዴሪ ጠቅላይ ፍ/ቤት ከመጡ ጦማሪያን፣ ዘውትር ከጎናችን ያልተለየን ጠበቃችን አቶ አመሃ መኮንን፣ እና ባህታዊ አባ ወንደወሰን (በነገራችን ላይ እኝህ አባት ሁልጊዜም ቢሆን በፀሎትና በማጽናናት ከጎኔ ተለይተውኝ የማያውቁ ሲሆኑ፣ ከሀብታሙ ጋር ባይተዋወቁም እንኳን ሳይለዩን እስከ ተኛበት ካዲስኮ ሆስፒታል ድረስ በመምጣት ፀሎት ያደረጉ፣ በዛሬው ቀጠሯችን እስከ ጠቅላይ ፍ/ቤት ድረስ ተጉዘው በዳኞች ፊት ቆመው በመንፈሳቸው የተማፀኑ አባቴ ናቸውና አመስግኑልኝ)። በተጨማሪ የአዲሳባ ነዋሪ፣ ለእረፍትና ለስራ ጉዳይ ከባህር ማዶና ከሀገር ውስጥ ገጠር አከባቢዎች ወደ አ,አ የመጡ ግለሰቦች የሆስፒታሉን ግቢውን አጣበውታል። የህዝቡ መትመም ከቀን ወደ ቀን እየጨመረ መምጣቱ ነገር የሰኩሪቲ ስጋትን ከመጫሩም ባሻገር በጠባቧ ክፍል ውስጥ ማስተናገድ አልተቻለም። ስለዚህ ለጥየቃ የሚመጣ ሰው ስሙን፣ የመጣበትን አከባቢ እና ለማለት የፈለገውን በማስተወሻ ደብተር ላይ እንዲተውልን አንድ መዝገብ በር አከባቢ ማስቀመጥ ግድ ሆነብን። ከአገር ውስጥ፣ ከገጠር፣ ከከተማ፣ እና ከውጭ ሀገር፣ የሚቃጭለው የስልክ ጥሪ፣ የያዝኳትን የቻይና ስሪቷን የእጅ ስልኬን ያሞቅና ጆሮ ግንዴን ማፍላት ይጀምራል። ነገር ግን ከጥልቅ ፍቅር የሚመነጭ ስሜት ስለሆነ የእያንዳንዱን ሰው ስልክ ጥሪ በትህትና ማስተናገድ ሌላው ሃላፊነቴ ነበር። በተመሳሳይ ሁኔታ በኢንተርኔት መስመሮች ለሚመጡ ጥያቄዎችም እንዲሁ,,,። በዚህ ሁሉ ምን አስተዋልኩ መሰላችሁ?? የሀገር ፍቅርን፣ ሀገር ማለት ደግሞ ድንበርና መንግስት የሚባል ነገርን ሳንረሳው፣ በቀዳሚነት ሰው መሆኑን፣ ሰው ፍቅርን ካአጣ አውሬ መሆኑን አስተዋልኩ። ታዲያ ፈጣሪያችን ሆይ ጤናና የሰው ፍቅር ስጠን ብንልስ?
የወጣት ሀብታሙን የጤና ሁኔታ የሚከታተለው ፕዚሺያን ውሳኔን በተመለከተ ዛሬ ከሰአት በኋላ (በቀጠሯቸው መሰረት) ጉብኝት ያደረጉት በሙያውም፣ በእድሜያቸውም የበሰሉ፣ በህሙማን፣ በአስተማሚዎችና በሰራተኞች እጅግ የከበሩ መሆናቸውን ነገረ ሁላ የሚያሳብቅባቸው ዶክተር ሲሆን፣ የመከሩን/ያዘዙን ነገር ቢኖር በሽታው ለተለመደ ህክምና ዘዴ ውስብስብ የሚያደርግ ነገር እያየሁ ስለሆነ አሁንም ለቀጣይ ሁለትና ሶስት ቀናት መከታተል እንደሚፈልጉ ፍንጭ ሰቷል።
አሁንስ በምን ሁኔታ ላይ ይገኛል? የሚል ጥያቄ ሰብአዊነት ከሚሰማው ሰው አእምሮ ውስጥ የሚፈልቅ ጥያቄ መሆኑ ግልፅ ነው። እስካሁን እየገለፅኩ እንደመጣሁ ሁሉ ወንድሜ ሀብታሙ እየኖረ ያለው በማደንዘዣ፣ በስቃይ ማስታገሻና በጉሉኮዝ ነው። ከዚህ የተነሳ አሁን ደህና ነው ሲባል ወዲያው እንደ ክረምት ፀሃይ ያሸልባል። በዚህ አይነት ሁኔታ አንድን የደከመ በሽተኛን ለምን ያህል ጊዜ ማቆየት እንደሚቻል ምላሹን ለጤና ባለሙያዎችና ለአንባቢያን ልተውው። ቸር ያሰማን!!
ሀብታሙ አያሌው ከመጨረሻው የፍርድ ቤት ቀጠሮ በፊት የጤናው ሁኔታ አሳሳቢ ደረጃ ላይ መሆኑና በእስር ቤት በደረሰበት ስቃይ ለጤና መታወክ መዳረጉን መግለጹ አይዘነጋም። የሀብታሙን ከመጨረሻው ፍርድ ቤት ቀጠሮ በፊት የሰጠውን ቃለ መጠይቅ አብረን አያይዘነዋል ።