በአገር ቤት በስልጣን ላይ ያለው በሕወሓት የበላይነት እና ሙሉ ቁጥጥር ስር ያለው ስርዓት በፌደራል ስም የሚጠራ አይደለም። ህወሓት <<ፌዴራል ስርዓት>> እያለ የሚቀልድበት የሁሉም ነገር የበላይ ሕወሃት የሆነበት ስርኣት ነው:፡ ገለታው ዘለቀ ለግንዛቤ የሚረዳ መፍትሄ የሚጠቁም ጽሁፍ እነሆ ብሏል።በጥሞና ሊነበብ የሚገባው ነው።
የኢትዮጵያ “የፌደራል ሥርዓት” ችግሮችና
አማራጭ መፍትሄዎች
ገለታው ዘለቀ
እንደ መግቢያ
ከዚህ በፊት “ኢትዮጵያ የፌደራል ሥርዓትን የምትከተል አገር አይደለችም” ብዬ ፅፌ ነበር። ዛሬም ትንሽ አዳብሬ በዚሁ ላይ ትንታኔ መስጠት አምሮኛል። ይህ ጽሁፍ ደግሞ እንዲነሳልኝ የፈለኩበት ምክንያት በቅርቡ የህወሃት አንጋፋ ታጋዮች የሆኑት አቶ ስዩም መስፍንና አቶ አባይ ፀሃየ በቅርቡ በኢትዮጵያ “ወቅታዊ” ጉዳይ ላይ የተሰኘ መግለጫ ሰጥተው ነበር። የነዚህን ከፍተኛ ባለስልጣናት ንግግር ያዳመጠ ሁሉ የየራሱን ምልከታ ያስቀምጣል። እጅግ ብዙ ሰው ግን አዲስ ነገር የማይገኝበት ወቅታዊ የማይባል ያደርገዋል። አገሪቱን ህዝባዊ ተቃውሞ በሚንጥበት በዚህ ሰአት ቢያንስ ስለብሄራዊ መግባባት ስለ ብሄራዊ እርቅ ስለ ይቅርታ ማውራት ተገቢ ነበር። የፓለቲካ መሪ ምንም እንኳን የያዘው አቅጣጫ ለራሱ አዋጭ ቢመስለውም ነገር ግን ህዝብ ካልተቀበለው ራሱን ይመረምራል። ይህ ግን በኛ ሃገር ፓለቲካ አለመታየቱ ያሳዝናል። ስልጣን ለሚወዱ ባለስልጣናትም የስልጣን እድሜ የሚጨምረው ይቅርታና መታረም መለወጥ ነበር።
በዚህ “ወቅታዊ” በተሰኘው የነዚህ የህወሃት መሪዎች መግለጫ ውስጥ አንድ ነገር ስላስደመመኝ በዚያ ላይ በተለይ ለነዚህ ለሁለቱ መሪዎችና ለተከታዮቻቸው ማስተላለፍ እፈልጋለሁ። በዚህ ገለፃ ወቅት አቶ ስዩም ስለ ፌደራል ስርአት ተናግረዋል። የኢትዮጵያ የፌደራል ስርአት “አለም የሚቀናበት” ነው ይሉናል። እንዴውም የኢትዮጵያ የፌደራል ስርአት የሌሎች ፌደራል አገሮችን የፌደራል ስርአት የገለበጠ ነው ይላሉ። ይህንን ሲያስረዱ የሌሎች ሃገራት የፌደራል ስርአት ፌደራሉ የተወሰኑ ስልጣኖችን ይሰጥና ከዚያ ቀሪው በሙሉ የኔ ነው ይላል ይሉናል። ይሰስታል አይነት ነው። ስልጣን የሚሸነሽነው ከላይ ያለው የፌደራል ስርአት ነው ይላሉ። በአንፃሩ የኢትዮጵያ የፌደራል ስርአት ደግሞ የተገነባው ብሄሮች ትንሽ ትንሽ ቆንጥረው ስልጣን ወርውረውለት የተቋቋመ የፌደራል ሥርዓት ሲሆን ብዙውን ስልጣን ግን ብሄሮች ለራሳቸው እየተደሰቱበት እንደሆነ ያስረዱናል። ይህንን ሳዳምጥ አቶ ስዩም በከፍተኛ ሁኔታ የፌደራልን ጽንሰ ሃሳብ አለመረዳታቸውን አሳየኝ። ተከታዮቻቸው ሁሉ እንዲሁ ከተረዱት በውነት ከስረዋል። እኚህ ሰው እንደኔው ተራ ሰው ቢሆኑ አልሟገትም ነበር። ነገር ግን እኚህ ሰውና ፓርቲያቸው ያመኑበትን ተግባራዊ የሚያደርጉና ያደረጉ በመሆናቸው የኝህ ሰው ግንዛቤ አገርን ስላወከ ነው ለሙግት ያስነሳኝ።
እንግዲህ በመሰረቱ የፌደራል ስርአት ብዙ አይነት ነው። እንደ ስምምነቱ ነው። በከፍተኛ ሁኔታ ስልጣን ለክልል የሰጡ ሃገራት በኮንፌደሬሽን ስርአት ይተዳደራሉ። ከዚያ በመለስ ደግሞ በተለያየ ግዝፈት በፓለቲካ ዩኒቶች መሃል ስልጣን እየተካፈሉ የሚኖሩ ደግሞ አሉ። ዋናው አቶ ስዩም የሳቱት ነገር በሌሎች ሃገሮች የፌደራል ስርአት ውስጥ ፌደራሉ ነው ስልጣን የሚሸነሽነው የሚለው ነው። ፌደራል ጥቂት ስልጣን ይሰጥና ሌላውን ለራሱ ይወስዳል ይላሉ። ይሄ ስህተት ነው። በሰኪዩላር የፌደራል ስርአት ውስጥ ስልጣን የሚያካፍለው ህገ
መንግስት ነው። በህገ መንግስት የስልጣን ክፍፍል ተቀመጠ ማለት የፌደራል መንግስት ስልጣን አዳይ ሆነ ማለት አይደለም። ሁሉቱም መንግስታት በተቀመጠላቸው ህግ መሰረት ይሰራሉ። ይህ ህገ መንግስት ደግሞ የሁሉ ነው። በአሜሪካ የፌደራል ስርአት ውስጥ ፌደራል መንግስት የስቴቶችን ስልጣን ሲፈልገው እየጨመረ ሲፈልገው እየቀነሰ አያድልም። ህገ መንግስቱን የማሻሻል ስልጣንም ቢሆን ለፌደራል መንግስት ብቻ የተሰጠ ስልጣን አይደለም። አቶ ስዩም ይህንን ማወቅ አለባቸው። የአቶ ስዩም የፌደራል ሥርዓት አረዳድና ትንታኔ እንዲሁም የኢትዮጵያን የፌደራል ስርአት በተመለከተ የሰጡት ግምት የተሳሳተ በመሆኑ እነሆ ዛሬ እሳቸው አለም ይቀናበታል ያሉት የብሄር ፌደራሊዝም ምን ምን ውጥንቅጥ እንዳለው፣ እንዴት እንዴት አድርጎ እየጎዳን እንደሆነ በዚህ ጽሁፍ ሥር እተነትናለሁ። ከሁሉ በፊት ግን የፌደራል ስርአት የፍልስፍና መሰረቱ ምን እንደሆነ በመወያየት ወደ ዋናው አሳብ ብንወርድ ሳይምረጥ አይቀርም።
የፌደራል ስርዓት የፍልስፍና መሰረቶች
የኢትዮጵያን የፌደራል ስርአት ለመተቸት ከመነሳታችን በፊት በፌደራል ስርአት ፅንሰ ሃሳብ ዙሪያ መወያየቱ ለግምገማችን መሰረት ይሆናል። እንደሚታወቀው የፌደራል የመንግስት መዋቅር የተፈጠረው በተባበረችው ኣሜሪካ የፖለቲካ መሪዎች ነው። እነዚያ የቀደሙት የተባበረችው ኣሜሪካ መሪዎች ኣንድ ወቅት የፈጠሩት ይህ የፌደራል ስርዓት የመነሻ ኣሳቡ ህዝብን በኣንድ ትልቅ ኣዳራሽ ውስጥ ኣስገብቶ ዙሪያውን ኮልኩሎ ከማስተናገድ ይልቅ ክፍል ክፍል ፈጥረንለት በነዚያ ክፍሎች ደግሞ የመንግስትን ስልጣን የሚጋሩ የስቴት መንግስታት ቢመሰረቱ ኣገልግሎት ይሳለጣል ከሁሉም በላይ ደግሞ ለህዝቡ የህግ ሪሶርሶች ይጨምራሉ ከዚህም በላይ ጠቅላላ የሆነውን የመንግስት ስልጣን በየስቴቱ ብናካፍል የሚሰጠው ስልጣንና ህገ መንግስት ጠቅላላ ነገር ሲሆን አተገባበሩ ግን ጥበብ (art) ይጠይቃል። ይህ ጥበብ ደግሞ
ከመንግስታት መንግስታት በየተወሰነ ደረጃ ሊለያይ ይችላል። ስቴቶች የፌደራሉን ስርዓት ህገ መንግስቱን ሳይጥሱ በኣሰራር ጥበብ ለመለያየትና ለመወዳደር እድል ስለሚሰጥ የስቴቶች ጥበብ መለያየት ለህዝቡ የህግ ሪሶርስ እንዲጨምር ምርጫዎች እንዲበዙ ስለሚያደርግ ለመልካም ኣስተዳደርና ለዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ እንዲሁም ለኢኮኖሚ እድገት ትልቅ ጠቀሜታ ያመጣል ከሚል ነው። በፌደራል ስርዓት ጊዜ ዜጎች የፖለቲካ ተሳትፎ ምህዳራቸው ይሰፋል። በክልልና በፌደራል ደረጃ ይመርጣሉ። ሁለት መንግስታት ይኖራሉ። ለዜጎች የሚያስቡ ተመራጮች ይበዛሉና ስለዜጎች ምክር ይበዛል። የፌደራል ስርዓት ማለት መንግስት የሚባለውን ጽንሰ ሃሳብ መዘርዘር ማለት ነው። መንግስት ተዘርዝሮ ሲሰራበት ኣገር የበለጠ ያተርፋል የሚል እምነት ኣለው። ስቴቶች እንደየአቅማቸው መክሊትን እየወሰዱ ይሰሩበታል። እነዚህ ስቴቶች መንግስት ይባሉ እንጂ ዜጎች ኣይኖራቸውም። ዜግነት በስቴት የሚወሰን ባለመሆኑ ስቴቶች የሚሰሩት ዞሮ ዞሮ ለዜጎች ሁሉ በመሆኑ ትልቁ ግብ ኣገርን በሁለንተናዊ መልኩ ማሳደግ ነው።
የፌደራል ስርዓት ከመነሻውም ዴሞክራቲክና ብዝሃዊነት ካለው ሰፊ ልብ የመነጨ ነው። ስልጣንን ማካፈል ለኣምባገነን መሪዎች በጣም ከባዱ ነገር ነው። ከብዙ ኣመታት በፊት የኣሜሪካ መሪዎች ይህንን ስርዓት ሲያመጡ ለዴሞክራሲ ስልጣንን ለማካፈል የቆረጡ ጀግኖች እንደነበሩ ያሳያል። በኣጠቃላይ የፌደራሊዝም ስርዓት ያመጣው ለውጥ ለብዙ ዘመናት ስልጣን በኣንድ ኣካባቢ ተጠቅልሎ የቆየውን ከማእከል በማውጣት ለስቴቶች ማካፈል ሲሆን በዚህ የኣስተኣደር ጥበብ አገርን በፍጥነት ለማሳደግ ይረዳል የሚል ነው። በሌላ በኩል በፌደራል ስርአት ስር ለከረመ አገር ወደ አምባገነን ስርአት የመመለስ እድልን ያጠባል። ስልጣን ስላልተማከለ ስቴቶችም ስለበዙ በቀላሉ ሃይልን ለመጠቅለል ስለሚያስቸግር አስቸጋሪ መሪዎች ቢመጡም አምባገነን ስርአት እንዳያብብ ያደርጋል። ሌላው የፌደራልን ሥርዓት ተመራጭ የሚያደርገው ነገር ደግሞ ማንነትን ለመንከባከብ ይረዳል ከሚል ነው። ማንነት ሲባል በተለይ የብሄር ማንነትን ለማለት ነው። ብሄሮች በቋንቋቸው እንዲዳኙ እንዲተዳደሩ ለማድረግ ከአሃዳዊ ስርአት ፌደራላዊ ስርአት ይመረጣል ይባላል።
የኢትዮጵያ የፌደራል ስርዓት ምን ይመስላል? ስንት ችግሮች አሉበት?
የፌደራል ስርዓት በተባበረችው አሜሪካ መሪዎች ከተፈጠረ በሁዋላ ሌሎች ኣገሮችም ይህንን ስርዓት ተማርከውበት እየተጠቀሙበት ነው። በርግጥ በዓለም ላይ ያለ የፌደራል ስርአት ሁሉ ኣንድ ኣይነት ኣይደለም። የኣሰራር ኣንዳንድ ልዩነቶች ኣሉ። ለምሳሌ የህንድን የፈደራል ስርዓት ስናይ ስቴቶች ህገ-መንግስት የላቸውም። ከካሽሜር ግዛት ውጭ ሌሎቹ ስቴቶች የሚጠቀሙት የሃገሪቱን ኣንድ ህገ መንግስት ብቻ ነው። የካናዳ የኣውስትሬሊያና የጀርመን የመሳሰሉት ኣገሮች የፌደራል ስርዓቶች በየተወሰነ ደረጃው የተለያዩ ናቸው። ይሁን እንጂ በመሰረታዊ መርሃቸው ማለትም ስልጣንን በማካፈል በኩል ሁሉም ሃገራት እምነቱ ኣላቸው። ወደ ኢትዮጵያ ስንመጣ የተለየ ነገር እናያለን። ኢትዮጵያ ስያሜዋ የኢትዮጵያ ፌደራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ መንግስት ነው። ከዚህ ስያሜ የምንረዳው የፌደራል ስርዓትን ተቀብያለሁ በትምህርቱ ተማርኪያለሁ የምትል ኣገር እንደሆነች ነው። ታዲያ የፌደራል ስርዓትን ልትቀበል የዘረጋችበት እጅ ደግሞ በቡድን በቡድን ነው። በህገ መንግስቷ መግቢያ ላይም እኛ ብሄር ብሄረሰቦች…… በሚል ነው ኣዲሱን ስርዓት ኣሃዱ ብላ የጀመረችው። ይህ መሰረታዊ እምነቷን ከፌደራል ስርዓት ጋር እንዴት ለማስኬድ እንደሞከረችና ያመጣባትን ችግር ኣንድ ሁለት እያልን እንመለከታለን።
በዚህ ጽሁፍ ውስጥ የምናየው ዋና ጉዳይ ሳይንሳዊ የሆነው የፌደራል ስርዓት
ከብሄር ፖለቲካ ጋር ሲገናኝ ምን ኣይነት መስተጋብር አንዳለውና ኣጠቃላይ ፌደራሊዝሙን በብሄር ላይ ማቆሙ ምን ያህል የፌደራልን ጽንሰ ሃሳብ እንዳፋለሰ በአጠቃላይም በሃገሪቱ ኢኮኖሚያዊ ፖለቲካዊና ማህበራዊ ጉዳዮች ላይ ያመጣውን ችግር እንዳስሳለን። የውይይታችን ማጠንጠኛዎች ሰባት ነጥቦች ሲሆኑ እነሱም፦ 1. የመንግስት ኣወቃቀር 2. የሃይል መካፈል ጉዳይ 3. የማንነት ጉዳይ 4. የዴሞክራሲ ጉዳይ 5. የኢኮኖሚ ጉዳይ 6. ለኣስተዳደር ኣመቺነት 7. አብዮታዊ ዴሞክራሲና ፌደራሊዝም ናቸው
በነዚህ ከፍ ሲል በዘረዘርናቸው ስድስት ማእዘኖች አንፃር የኢትዮጵያን የፌደራል ስርአት መተቸት አሁን እንጀምር።
- የመንግስት ኣወቃቀር
በመግቢያ ላይ ጠቆም እንደተደረገው በፌደራል ስርዓት ጊዜ መንግስት ሲዋቀር ሶስቱ የመንግስት አካላት ማለትም ህግ ኣውጭው፣ ህግ ኣስፈጻሚውና ህግ ተርጓሚው ተለይተው በሚገባ መዋቀር ኣለባቸው። ይህ የፌደራል ስርዓት ዋና ጉዳይ ነው። የመለያየታቸው ዋና ምስጢር በተለያየ ኣጋጣሚ ስልጣን የሚይዙ ባለስልጣናት እነዚህን ኣካላት መሳሪያ ኣድርገው ድሆች እንዳይበዘበዙ ነው። እነዚህ ሶስት ኣካላት ቼክና ባላንስ እያደረጉ እየተጠባበቁ ሲኖሩ ሚዛናዊ የሆነ ተጠያቂነት ያለበት ስርዓት ይፈጠራል። እነዚህ ሶስት ኣካላት ጎን ለጎን
እየተያዩ ቼክና ባላንስ እያደረጉ የሚጠብቁት ኣንድ ነገር ቢኖር የህዝብን ስልጣን ነው። እውተኛው የስልጣን ባለቤት ህዝብ በመሆኑ እነዚህ ሲስተሞች በህይወት ዘመናቸው ይህን የህዝብ ስልጣን ይጠብቃሉ። ያገለግላሉ። አነዚህ ሶስቱ የመንግስት መዋቅሮች ሳይለያዩ ከተፈጠሩ ተጠያቂነት ስለሚጠፋ ስልጣን ከህዝብ እጅ ይወጣና የጥቂቶች ፍላጎት መፈጸም ይጀምራል። ፍርድ ቤት ህግ ኣውጭው ኣስፈጻሚው ሁሉ የጥቂቶችን ፍላጎት እያስፈጸመ የሚኖርበት ሁኔታ ይፈጠራል።
እንግዲህ ኢትዮጵያ የፌደራል ስርዓት ኣራምዳለሁ ባይ ናት ብለናል። በርግጥ የብሄር ፌደራሊዝም የሚባለውን ፖለቲከኞች ኣይጠቀሙበትም። የፌደራል ኣገር ነን ብቻ ነው የሚሉት። ትንሽ ኣፈር ይሉበት ይመስላል። ተቃዋሚው ግን ፍርጥ አድርገው የብሄር ፈደራሊዝም ነው ያለው ይላሉ። መንግስት የፖለቲካ መሰረቴና የስልጣን ምንጮቼ ዘውጎች ይሆኑና ነገር ግን የፌደራል ስርዓት መርሆዎችን ኣከብራለሁ የሚል ነገር ያንጸባርቃል።
የብሄር ፖለቲካና ፌደራሊዝም ኣብሮ ሲመጣ ምን ሊከሰት እንደሚችል ቆየት ብለን እናነሳለን ለኣሁኑ ግን በኢትዮጵያ የብሄር ፌደራል ስርዓት ውስጥ ኣንዱ የሚታየው ነገር እነዚህ ሶስቱ ማለትም ህግ ኣውጭው ኣስፈጻሚውና ተርጓሚው ሲዋቀሩ የተፈጠረ ስህተት ኣለ። ይህ ስህተት ደግሞ በከፍተኛ ሁኔታ የነዚህን ሶስት ኣካላት ተለያይቶ የመፈጠር መርህ እንዲፈርስ ኣድርጓል።
በኢትዮጵያ ህገ መንግስት ኣንቀጽ 62 ንኡስ አንቀፅ 1 መሰረት የሃገሪቱን ከፍተኛ የፍትህ ስልጣን የያዘው የፌደሬሽን ምክር ቤት ነው። ይህ ምክር ቤት የዳኝነት ስራን ነጥቆ የወሰደ ሆኖ ነው የተዋቀረው። በዚህ ኣንቀጽ ላይ እንደተደነገገው የሃገሪቱን ህገ መንግስት የሚተረጉመው ይህ ምክር ቤት ነው። በሌሎች የፌደራል ኣገራት የሃገሮችን ህገ መንግስት የሚተረጉመው ኣካል ኣንድም የህገ መንግስት ዳኛ ተቋቁሞ ወይም ደግሞ የሃገሪቱ ከፍተኛው ፍርድ
ቤት ነው። የህገ መንግስት ፍርዱም ስራ በተፈጥሮው የህግ ስራ በመሆኑ ሃገሮች በባለሙያ ያሳዩታል። ባለሙያው ሲተረጉም ጣልቃ ሳይገቡ እየተዳኙ ይኖራሉ። ኣንድ የፖለቲካ ስልጣን ያለው መንግስት ፓርላማውን ኣቋቁሞ ህጎችን ያወጣል። እነዚህን ህጎች ያወጣሁት እኔ ነኝ ስሜታቸውን፣ ቋንቋቸውን የምረዳው እኔ ነኝና እኔው እተረጉማለሁ እኔው እፈጽማለሁ ኣይልም። ጠቅላላ ህጎችን ያወጣና ለባለሙያዎች ሲሰጥ እነዚያ ባለሙያዎች ይተረጉማሉ። በኢትዮጵያ ሁኔታ ግን የተለየ የሆነው እንደሚታወቀው የፌደሬሽን ምክር ቤት የሚዋቀረው በፖለቲካ ሰዎች በመሆኑ ይህ ኣካል የህግ ትርጉም ስራ ሲሰጠው የሚፈጠረው ችግር የመንግስት የስልጣን ክፍፍል ብቻ ሳይሆን ኣሰራርም ላይ ትልቅ ችግር ያመጣል። የህግ ባለሙያ የሆኑት ዶክተር ጸጋየ ረጋሳ ሲናገሩ ኣንዱ የዚህ ኣወቃቀር ትልቅ ችግር ኣፈጻጸሙ ላይ ነው ይላሉ። እንደሚታወቀው ፍርድ ቤት የወሰነውን ውሳኔ ለማስፈጸም ፖሊሲ ሊታዘዝ ይችላል። የፌደሬሽን ምክር ቤት ውሳኔ ሲያሳልፍ ውሳኔውን ተግባራዊ ለማድረግ የሚሄድበት መንገድ ህጋዊነት ኣጠያያቂ ነው። ከሁሉ በላይ ግን ይህ ምክር ቤት ዳኝነት እንዴት ይሰጣል? ይህ ጉዳይ ከህገ መንግስቱ ጋር ይሄዳል ኣይሄድም ካለ ቡሃላ እንዴት ነው የአፈፃፀም ሂደቱ? የሚለው ጉልህ ጉዳይ ነው። ለምሳሌ ኣንድ ጠቅላይ ሚንስትር የሆነ ግድፈት ቢያመጣ ፓርቲዎች ቢጋጩ ጉዳዩ ከህገ መንግስት ጋር ይሄዳል ኣይሄድም ለማለት ይህ ምክር ቤት እንዴት ገለልተኝነት ይሰማዋል? ካድሬዎች የተሰበሰቡበት ቤት እንዴት ብይን ይሰጣል? መንግስት ራሱ ህገ መንግስቱን የሚፃረር ከባድ ነገር ቢያደርግ ዳኛው ራሱ ኢህአዴግ ሆኖ ይመጣል ማለት ነው። ይህን ጉዳይ ስናጤን በኣሁኑ የመንግስት ኣወቃቀር ኢትዮጵያ የፍትህ ስራዋን ዋና ጉዳይ የፖለቲካ ውክልና ያላቸው ኣካላት ነጥቀዋት ይታያል። ይህ የሚያሳየው ደግሞ የሃይል ክፍፍል( Separation of power) እንደጠፋ ነው። ህግ ተርጓሚው የፓለቲካ ሰው በመሆኑ ነው ይህ ችግር እንዲከሰት ያደረገው። ለምሳሌ እንዲሆነን አንዳንድ ተግባራዊ ምሳሌዎችን እናንሳ። ወልቃይቶች ማንነታችን ተጎዳ በግድ ትግራይን ምሰሉ ተባልን ብለው ይከሳሉ። እነዚህ ወገኖች ይህን ክስ ይዘው ወደ ፍርድ ቤት አይሄዱም። ምክንያቱም የማንነቶችን ጉዳይ የሚያየው አካል የፌደሬሽን ምክር ቤት በመሆኑ ነው። ወልቃይቶች መንግስትን ከሰው እዚያው መንግስት ጋር ይሄዳሉ። ክልሎች ቢጋጩም ፈራጁ ያው የፌደሬሽን ምክር ቤት ነው። በህግ ተርጓሚው ውስጥ ኢህአዴግ የፓለቲካ ፓርቲ አባሎቹን
ዳኛ ስላደረገ ነው የሃይል መለያየት ጉዳይ በኢትዮጵያ የመንግስት ሥርዓት የፈረሰው።
በፌደራል ስርዓት ውስጥ የነዚህ ሶስት ስልጣናት መለያየት ዋና ጉዳይ ሲሆን ኢትዮጵያ ባዋቀረችው ሲስተም ግን ይህ ፎርሙላ ሲሰበር እናያለን። ከዚህ የተነሳም የኢትዮጵያ የፌደራል ስርዓት የፌደራል ስርዓትን ዋና መርሆን ለመከተል ያልቻለ ሆኖ እናያለን።
- የሃይል መካፈል ጉዳይ
የፌደራል ስርዓት ሲጀምር የሚያምነው ነገር ሃይልን ለስቴት መንግስታት በማካፈል ኣገልግሎትን ማሳለጥ ነው። በብዙ የፌደራል ኣገራት በፌደራልና በስቴቶች መካከል የሃይል መከፋፈል ኣለ። በኣንዳንድ ጉዳዮች ላይ ኣብረው ይሰራሉ በኣንዳንድ ጉዳዮች ላይ ለየብቻ ይሰራሉ። በኢትዮጵያ ሁኔታ ስናይ በርግጥ ክልሎች ሁሉ የየራሳቸው ህገ መንግስት ኣላቸው። የየራሳቸው ምክር ቤት ኣላቸው። ነገር ግን ሃይል ሲበዛ ፌደራል ኣካባቢ የተሰበሰበ ሲሆን ክልሎች ክንፍ ሳይኖራቸው ይበራሉ የተባሉ አካላት ናቸው። ሃይል በጣም ለመማከሉ የተጻፈ መረጃ ብዙ የለም። ነገር ግን የህዝቡ ግንዛቤ የሚያሳየው ግን ይህንን ሃቅ ነው። ኢትዮጵያ የብሄር ፌደራሊዝም ነው የማራምደው ብትልም የፌደራል ስርዓት ዞሮ ዞሮ የሚጠይቃት ሃይልን ለክልሎች ማካፈል ነው። ብሄሮች ራሳቸውን እንዲያስተዳድሩ ሃይል መስጠት ነው። ነገር ግን ይህ ኣልሆነም። ሃይል ተማክሏል። ለዚህም ነው ዛሬ የኦሮሞና የኣማራ ህዝብ የኮንሶና የኦጋዴን ወዘተ ህዝቦች በሃይል ያመጹት። ትልቁ ጥያቄያቸው ህወሃት የበላይ ሆኖ በየክልሉ ኣገልጋዮቹን እየሾመ እየጨቆነን ነው የሚል ነው። ይህ የህዝቡ ግንዛቤ የሚያሳየው ሃይል እንዳልተካፈለ ነው። እውነቱን እንነጋገር ከተባለ ህወሃት ተቃዋሚ ፓርቲዎችን ከሚጨቁነው በላይ የራሱን ኣጋር ድርጅቶች ኣጥብቆ ጨቁኖ የያዘ ድርጅት ነው። መጠቀሚያዎቹ ስለሆኑ እጅግ ኣጥብቆ የያዛቸው ናቸውና ነጻነት የላቸውም። እነዚህ ሰዎች ኣንድ ቀን ያበጠው ይፈንዳ ህወሃትን ኣባጠጥን አናታችን ላይ ወጣ ብሄሮቻችንንም ኣገራችንንም ጎዳን ብለው የፍርሃትን ቀንበር ሰብረው ካልተነሱ ህወሃት እንዲሁ
ጋልቧቸው መጓዙ ጥሞታል። በኣጠቃላይ እንደ ፌደራል ስርዓት ስናይ ኣንድ የፌደራል ስርዓት በተለይም የብሄር ፖለቲካ የምታራምድ ኣገር፣ የብሄሮችን መብት እስከ መገንጠል የተቀበለች ኣገር ስለ ራስ ማስተዳደር የምትዘምር ኣገር የሃይል መካፈል ጉዳይ ዋና ጉዳይ ነው። ብሄሮች የተፈጥሮ ሃብታችሁ ሁሉ በዋናንት የናንተ ነው ተብለው ነገር ግን በቴክኒክ ስልጣናቸው ከተቀማ የሃይል መካፈል ጉዳይ ዳዋ በልቶታል። ከዚህ ኣንጻር ስናይ ኢትዮጵያ የሃይል ክፍፍልን እየተደሰተችበት ያለች ኣገር ባለመሆኗ የፌደራል ስርዓትን እከተላለሁ ብትልም ከቶ ማን ሊሰማ።
- ማንነት
ከሰኪዩላር ፌደራሊዝም ዶክትሪን ጽንሰ ሃስብ የምንማረው ነገር ማንነትን መንከባከብ ሲባል የቡድን ወይም የብሄርን ማንነት ብቻ ማለት ኣይደለም። ብዙህ የሆኑ ሃገራት የፌደራል ስርዓትን የሚመርጡት ክልላዊ ማንነትንና ብሄራዊ ኣንድነትን ወይም ብሄራዊ ማንነትን ኣቻችሎ ጠብቆ ለመኖር ስለሚያስችል ነው። በሳይንሳዊ የፌደራል ስርዓት ውስጥ ሁሉም ማንነቶች እንክብካቤ ይሻሉ። ማንነትን ማሽቀዳደምና ከኣንዱ ማንነት ኣንዱ ይበልጣል ማለት የፌደራል ዶክትሪን ኣይመስልም። ማንነቶች እርስ በርስ ሳይጋጩና ኣንዱ ኣንዱን ሳይገዳደረው ማኖር የፌደራል ዶክትሪን ይመስላል። በመሆኑም ክልላዊ ማንነት ብሄራዊ ማንነትን ወይም ብሄራዊ ማንነት ክልላዊ ማንነትን ለማፍረስ ሳይጣጣሩ የሚኖሩበትን የመንግስት ስርዓት መቅረጽ ነው የፌደራል ስርዓትን መከተል ማለት። ወደ ኢትዮጵያ ስንመጣ ህገ መንግስቱ ወይም መንግስታዊ ስርዓቱ ሲዋቀር ኣንዱ ማንነት ኣንዱን በፈለገው ጊዜ ኣፍርሶት እንዲሄድ በር ከፍቶ ነው የተዋቀረው። የክልል መንግስት ከፈለገ ያለ ምንም ቅድመ ሁኔታ ፌደራሉን ሽርፍ ኣርጎ ገምሶት ሊሄድ ይችላል። ኣንቀጽ ሰላሳ ዘጠኝ የሚያሳየው ሃቅ ይህንን ነው። የኢትዮጵያ የፌደራል ስርዓት ሲዋቀር ክልላዊ ማንነት ብሄራዊ ማንነትን እንዲያፈርስ ተደርጎ የተዋቀረ በመሆኑ ከፌደራል ጽንሰ ሃሳብ በተቃራኒ የሚሄድ ነው። አቶ ስዩም ገልብጠነዋል የሚሉት ይህንን ከሆነ ተሳስተዋል። የሚገርመው ይህ አንቀፅ ሲፀድቅ ያልታየው ሌላው ጉዳይ ለምሳሌ ሌሎች ብሄሮች ሁሉ አብረው መኖርን ፈልገው ነገር ግን ኦሮምያ መገንጠል ቢፈልግ አገር መፍረሱን አለማስተዋሉ ነው። ኦሮሚያ ካለው የጂኦግራፊ
አቀማመጥ አንፃር ቢገነጠል ደቡብና ሰሜን አብረው መኖር ቢፈልጉም እንኳን መኖር እንዳይችሉ አድርጎ ይሄዳል ማለት ነው። ይህ የሚያሳየው ይህ አንቀጽ አንዱ ሌላውን እያፈረሰ እንዲሄድ የሚያደርግ የኢትዮጵያንና የአለምን ሁኔታ ያላገናዘበ ነው። ለምሳሌ የተባበረችው ኣሜሪካ ብዙ ስቴቶች ኣሏት። ነገር ግን እነዚህ ስቴቶች በፈለጉት ጊዜ የፌደራል መንግስቱን የሚያፈርሱበት ስርዓት የለም። በኣንጻሩ የፌደራል መንግስትም ስቴቶችን ኣያፈርስም። ሁለቱም መንግስታት ስልጣን እየተጋሩ አየተጠባበቁ የሚኖሩበት ስርዓት ነው የተዋቀረው። የፌደራል ስርዓት የሚባለው ይሄ ነው። የኢትዮጵያ የፌደራል ስርዓት ከፍ ሲል እንደገለጽኩት የክልል መንግስት የመብቶችን ጥግ ይዞ እስከ መገንጠል ሲሄድ ብሄራዊ ማንነት ምንም ጠባቂ በህገ መንግስቱ ኣልተበጀለትም። እንዴውም ይሄ የመገንጠል መብት ዋስታና ነው ይጠብቀናል እያሉ ይቀልዳሉ። ይህ ኣይነት ስርዓት በኣለም ኣልታየም። ለምን የኢትዮጵያ የፌደራል ስርዓት ኣንዱ ማንነት ኣንዱን እንዲያፈርስ ሆኖ ተዋቀረ ካልን ኣንዱ ችግር ለብሄር ማንነት የተሰጠው የተሳሳተ ትርጉም ነው። የብሄር ማንነትን የሰው ልጆች የመጨረሻ የማይነካ ጠገግ ኣድርጎ ማሰብ ያመጣው ችግር ነው። ነገር ግን ኣንድ ቡድን ኣንድ ቋንቋ እየተናገረም በጭቆና ስር ሊሆን ይችላል። በቤተዘመድና በጂዖግራፊ ክፍፍሎች ግፎች ሊደርስበት ሊቀበል ይችላል። ኣንድ ብሄር ብቻውን ሜዳ ላይ ሲያገኘው ማይክሮ ልዩነቶች እየጎሉ ወደ ማክሮ ያድጉና እስከ መገንጠል ይደርሳሉ። ሁለቱ ኮርያውያን በኣሳብ ስለተለያዩ ብቻ ተለያይተው ኣሉ። ሶማሊያ ኣንድ ብሄር የምትባል ሆና ሶማሌ ላንድ ተገንጥላ ትኖራለች። ሆሞ ጂኒየስ የሆኑ ኣገራት በግፍ ኣገዛዝ በኣድልዎ የሚኖሩ ኣሉ። በመሆኑም ይህን ጠገግ ዞሮ መግቢያ የመጨረሻ ዋስትና ኣድርጎ ማሰቡ ማህበራዊ ሳይንስ ይጎድለዋል። ለነገሩም ከብሄር በታችም ሌሎች ልዩነቶች ኣሉ። እነዚህ ልዩነቶችም ጠገግ ናቸው ነገር ግን የሰው ልጅ የማምለጫ ዓለት ተደርገው ኣይወሰዱም። ጠንካራ ጠገግ የሚባለው ቤተሰብ ሲሆን ይህም ቢሆን ስፋት ስለሌለው የሰው ልጆችን ሰፊ ፍላጎት ኣያረካምና የግድ ሰፊ ጠገግ የሰው ልጅ ይሻል። ይህ ጠገግ ደግሞ በመርህ ላይ የተመረኮዘ ሆኖ የተለያዩ ቤተሰቦችን ቋንቋና እምነቶችን ሁሉ ይዞ መኖር ይችላል። ዋናው ጉዳይ የስብስቡን መውጫና መግቢያ ህግጋት መርህ ሳይንሳዊ እንዲሆን ማድረግ የህጉን ጨዋታ ከደምና ከዘር በላይ ማዋል ነው። በመሆኑም ብሄርን ያን ያህል መብት ኣጎናጽፎ ብሄራዊ ኣንድነትን የኮንትራት ቤት ኣድርጎ መነሳቱ በዚያ ጠገግ ስር ያሉትን
ዜጎች ሁሉ ግራ ያጋባ የፌደራል ጠገግ ያደርገዋል። ኣገራቸው ዘላለማዊ ኣትመስላቸውም። አገር የሰው ልጆች ትልቁ ጠገግ ነውና ክብርና ትኩረት ይሻል። ዜጎች ሃገራቸው በየትኛውም ጊዜ የምትፈርስ ኣድረገው እንዲያስቡ የሚያደርግ ሥርአት መፈጠሩ ትልቅ ኪሳራ ነው። በመሆኑም ኣንድ የፌደራል ስርዓት ሲዋቀር እነዚህን ሁለት ማንነቶች እርስ በርስ እንዲጠባበቁ ተደርጎ መሆን ኣለበት። ሁለቱንም ጠገጎች መንከባከብ ያሻል።
ከዚሁ ከማንነት ጋር በተያያዘ የኢትዮጵያ የፌደራል ስርዓት ችግር ሁለቱን ማንነቶች እርስ በርስ እንዲፈራከሱ ኣድርጎ መዋቀሩ ሲሆን ሌላም ችግር ኣለበት። ለመሆኑ ብሄራዊ ማንነትን ችላ ብሎም ቢሆን የብሄሮችን ማንነትስ መጠበቅ ተችሏል ወይ? የሚል ጥያቄ እናንሳ። ባለፉት ሃያ ኣምስት ኣመታት ውስጥ የብሄሮች ማንነት የተጠበቀበት መንገድና ዘዴ ትክክል ኣልነበረም። በመሰረቱ ኣንድን ቡድን ማንነቱን እንጠብቅ ስንል በቋንቋው እንዲጠቀም በባህሉ እንዲጠቀምና እንዲኮራ ማድረግ ማለት ነው። ኢትዮጵያ ውስጥ የሆነው ምንድን ነው? ካልን የብሄሮችን ማንነት ለመጠበቅ ሲባል ብሄሮችን ከኣለፈ መጥፎ ታሪክ ጋር ማጋጨት ኣንዱ ዘዴ ነበር። በተለይ የኦሮሞና የደቡቡን ማህበረሰብ በኣጼ ምኒልክ ላይ ቂም እንዲይዙ የታሪክ ግድፈቶችን ወደ ኣንድ ብሄር እንዲያላክኩ የማድረግ ዝንባሌ በሃይል ነበር። መንግስት ይህን ጉልበት ለብሄርተኝነት ስሜት ማሳደጊያ ሲጠቀም የሃገሪቱ ማህበራዊ ሃብት ጠፋ። መተማመን እየተነነ መጣ። የጎኖሽ ግንኙነትን ኣሻከረ። ይህ ኣይነቱ የብሄርተኝነት እድገት ሰዎች በባህላቸው እንዲደሰቱ የሚያደርግ ሳይሆን ከሌላው ጋር በባለፈ ታሪክ እንዲናቆሩ የሚያደርግ ጸረ ፌደራል ስርዓት ነው። ይህ የእድገት ዘዴ ሄዶ ሄዶ ያንኑ ብሄራዊ ኣንድነትን እየጎዳ የሚሄድ ነው። በርግጥ በኣሁኑ ጊዜ ከሃያ ኣምስት ኣመት በሁዋላ በተለይ ኣማራና ኦሮሞ ይህን ነገር እየሰበሩት ይገኛሉ። መንግስት በርግጥ ይህን ሲያደርግ የነበረው ለኣንድ ጠባብ ቡዳን ጥቅም ሲል ነው። ይህ ኣካሄዱ ጸረ ፌደራል ዶክትሪን ነው በርግጥ። የፌደራል ስርዓት ፍላጎት ብሄሮች ማንነታቸውን በኣንድ በኩል እየገነቡ በሌላ በኩል ደግሞ ብሄራዊ ማንነታቸውን እንዲያሳድጉ እጅ ለእጅ እንዲያያዙ ነበር።
- የዴሞክራሲ ጉዳይ
የፌደራል ስርዓት የተፈጠረበትና የሚመረጥበት ኣንዱ ጉዳይ ሲስተሙ ዴሞክራሲን እንደ ልብ ያንሸራሽራል ከሚል ነው። የህግ ሪሶርስ ስለሚጨምር፣ ምርጫ ስለሚጨምር ዜጎች ታለንታቸውን እውቀታቸውን የሚያሳድጉበት ኢንቨስት የሚያደርጉበት መም ብዙ ይሆናል። ሰባዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶቻቸው የሚጠበቁበት ሲስተም ነው። ዶክትሪኑ ለቡድንም ለግለሰብም መብቶች የሚጨነቅ ይመስላል። ወደ ኢትዮጵያ ስንመጣ ግዙፍ ችግሮችን በዚህ ኣቅጣጫ እናያለን። ከመንግስት ኣምባገነናዊ ተፈጥሮ ባሻገር ሲስተሙ በራሱ የፈጠረው ግዙፍ የዴሞክራሲ ድርቅ (deficit ) እንዳለ እንመልከት።
የፌደራል ሲስተሙ ሲዋቀር እንደ ልዩነት የመጨረሻ ቅንጣት የታየው ብሄራዊ ልዩነት በመሆኑና ይህ ጠገግ እየተቆጠረ በነዚህ ጠገጎች ላይ የተመሰረተ የብሄር ፖለቲካ ስለተዋቀረ ዜገነት በመሃል ተረስቷል። ገና ሲጀምር ኢትዮጵያ የብሄር ብሄረሰቦች ኣገር ናት…. ብሎ የሚጀምር ህገ መንግስታዊ ስርዓት ያለ ሲሆን ዜጎች በነዚያ ቡድን ውስጥ ታጭቀው የሚታዩ ሲሆን ዜግነት በክልል ወይም በቡድን ስልቻ ውስጥ እንዲታፈን ተደርጓል። ዜጎች በኢትዮጵያ ኣገራቸው ውስጥ ከወዲያ ወዲህ ሲንቀሳቀሱ የዴሞክራሲ ድርቅ ይመታቸዋል። ለምሳሌ ያህል በሚሊዮን የሚቆጠሩ ኣማሮች ኦሮሚያ ይኖራሉ። እጅግ ብዙ ኦሮሞዎች በደቡብ በሰሜን ይኖራሉ፣ ወላይታዎች፣ ጉራጌዎች፣ ዶርዜዎች ወዘተ ተንቀሳቅሰዋል። እነዚህ ዜጎች ያለ ስልቻቸው ሲገኙ ዴሞክራሲያዊ መብታቸው ይሸራረፋል። ምክንያቱም ስርዓቱ የሚቆጥረው በነሲብ ወይም በጅምላ ስለሆነ ዜግነት ስለተዘለለ ነው። ቀላል ምሳሌ እናንሳ ብንል የሃረሪን ጉዳይ ማንሳት ይቻላል። ይህቺ ክልል ስትመሰረት ኣስራ ዘጠኝ ወረዳዎች ከኦሮምያ የተጨመረ ሲሆን ሃረሪዎች ስምንት በመቶ ገደማ ብቻ ናቸው። ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ኦሮሞዎችና ኣማራዎች ናቸው። በፌደራል ስርዓቱ እምነት ይህ ክልል በዋናነት የሃረሪ ነው። ይህ “በዋናነት የሃረሪ ተወላጆች ነው” ማለት ምን ማለት እንደሆነ ኣልተበየነም። ዋናው ጉዳይ ግን ዋና ያልሆኑ ዜጎች ግን ፖለቲካዊ መብታቸው ይሸራረፋል። በዚያ ክልል ኣማራ የሃረሪ ሊቀመንበር
መሆን ኣይችልም። የፈለገውን ያህል ህዝብ ቢመርጠውም ችሎታ ቢኖረውም ኣይችልም። ኦሮሞ ወይም ትግሬ የፈለገውን ያህል አቅም ቢኖረውም ሊመረጥ አይችልም። ያም ብቻ ሳይሆን የዚያ ክልል ዋና ባለቤት ባለመሆኑ ከፍተኛ የዜግነት መብቱን የጣሰ የፌደራል ስርዓት ነው የተመሰረተው። ይህ ኣይነት የፌደራል ስርዓት ኣገሪቱን የተለያዩ ኣገራት ህብረት ያስመስላታል እንጂ በፌደራል ስርዓት የምትተዳደር ኣያስመስላትም። ቤንሻንጉል ጉሙዝ ብንሄድም ተመሳሳይ ችግር ኣለ። ኣማራና ኦሮሞ ብዙ ያሉ ሲሆን በዚያ ያሉ እነዚህ ብሄሮች የዜግነት መብታቸው ይገፈፋል። በኣጠቃላይ ከክልሉ ውጭ የሚኖረውን የኢትዮጵያን ህዝብ ስናይ በብዙ ሚሊዮን የሚቆጠር ሲሆን በድምሩ ምናልባትም በቁጥሩ ከኦሮሞና ከኣማራ ቀጥሎ በሶስተኛ ደረጃ ይሰለፍ ይሆናል። እንግዲህ ይህ ሁሉ ሚሊዩን ህዝብን ነው በዚህ የፌደራል ስርዓት ውስጥ የክልል ዋና ባለቤት ያልሆነውና የዴሞክራሲና የዜግነት መብቱ የተገሰሰው። ይህንን ስናይ ከፍተኛ የዴሞክራሲ ደፈዚት ያለበትን የፌደራል ስርዓት ኢትዮጵያ እየተከተለች እንደሆነ መረዳት ይቻላል። ሌላው ለዴሞክራሲ ድርቅ የተጋለጠው ማህበረሰብ ደግሞ ቅይጡ ዜጋ ነው። ከሁለትና በላይ ብሄሮች የተወለደው ህዝብ ብዙ ሲሆን ይህ ህዝብ በዚህ መንግስት የፌደራል ስርዓት ጊዜ ቀርቦለት የነበረው ምርጫ ሳይንሳዊ ኣልነበረም። መንግስት ይህን ሁሉ ዜጋ ወይ ከናትህ ወይ ካባትህ ኣንዱን ምረጥ ተብሎ ነበር። ይሄ ሥነህይወታዊም ሆነ ማህበራዊ ሳይንስ የጎደለው ተራ የሰፈር ኣሳብ ነው። ይህ ችግር የመጣው ከፍ ሲል እንዳልነው የሰው ልጆችን ጠገግ ስናይ ኣገርን ሳይሆን የብሄርን ጠገግ አልፋና ኦሜጋ ኣድርገን ከማሰባችን ጋር ተሳስቶ የመጣ ችግር ነው። በሌላ በኩል ከተሞች ኣካባቢ ኣድገው ስለብሄር ደንታ የሌላቸው ቤተሰብ የማይጠይቁና የማይፈልጉ ብዙ ዜጎችም ይህ ስርዓት ኣስጨንቋቸዋል። ለነሱ ኢትዮጵያዊነት ብሄር ቢሆን ይመርጣሉ። እንዲህ ኣይነት ዜጎችን ያስጨነቀ የፌደራል ስርዓት ነው። በኣጠቃላይ ግን ለዴሞክራሲ እድገት ከፍተኛ መሰናክል ያለበት ስርዓት በመሆኑ የፌደራልን ትምህርት ይቃወማል። ስርአቱ ከላይ ሆኖ ማየት ያልቻለ ስለሆነ ከላይ ያለውን ትልቅ ጠገግ ከቁም ነገር አይቆጥረውም።
- የኢኮኖሚ ጉዳይ
የፌደራል ስርዓት ኣንዱ ዋና ኣጀንዳው ልማት ነው። ለኢኮኖሚ እድገት ትልቅ በር መክፈት የመሮጫ መም ማብዛትና ዜጎች ውጤታማ ትርፋማ እንዲሆኑ ማድረግ ነው። የኢትዮጵያን የፌደራል ስርዓት ለኢኮኖሚ እድገት ይመቻል ወይ? ስንል ሌላው በጣም ኣሳሳቢ ነገር ይታየናል። ከመነሻው የተፈጥሮ ሃብት ክፍፍል ላይ ግልጽነት የለውም። ክልሎች የራሳቸውን ሃብት ይጠቀማሉ ሲባል ምን ማለት እንደሆነ ኣልተበየነም። ከሁሉ በላይ ግን ኣንዱ ማንነት ሌላው እንዲያፈርሰው ሆኖ የተዋቀረ ኣገር እንደምን ሆኖ ነው ብሄራዊ ቅርስ የሚይዘው? ለብሄራዊ ቅርስ ብሄራዊ ኣንድነት ወሳኝ ነው። በቅርቡ የተከሰተን ምሳሌ ላንሳ። የመንግስት ሰዎች ተማሪዎችን ሰብስበው ለኣባይ ግድብ ብር ኣዋጡ ያላሉ። ከተማሪዎች የተጠየቀው ጥያቄ ግን ኣስደንጋጭ ነበር። ተማሪዎች ምንድን ነው ያሉት ገንዘባችንን ኣዋጥተት ኣዋጥተን ከገነባን በሁዋላ ይህ ኣሁን ግድቡ ያለበት ብሄረሰብ እኔ በቃኝ ብሎ ኣንቀጽ ሰላሳ ዘጠኝን ጠቅሶ ቢገነጠልስ? የሚል ጥያቄ ቀርቧል። ይሄ የሚያሳየው ዜጎች ለብሄራዊ ቅርስ ሃይላቸውንና ገንዘባቸውን ኢንቨስት እንዳያደርጉ የሚከላከል እንቅፋት መኖሩን ነው። በርግጥም መንግስትም ትንሽ ጅልነት ያለው ይመስላል። በኣንድ በኩል መገንጠል መብት ነው ብሎ ኢትዮጵያን የኮንትራት ኣገር ኣድርጎ ካዋቀረ በኋላ በሌላ በኩል ደግሞ ኑ ብሄራዊ ልማት እንስራ ብሎ እንዴት ይቀሰቅሳል። ከተለያየን ለማን ሸጠን እንካፈለዋለን። ውጥንቅጡ የወጣ ስርዓት ነው በውነት።
በሌላ በኩል ደግሞ መሬት የመንግስት ሲሆንና የዜጎች የመንቀሳቀስ መብት በክልል ሲገደብ ኢኮኖሚው እንዳያድግ ማድረጉ ኣያጠያይቅም። ከዚህ ችግር
በተጨማሪ የፖለቲካው ጨዋታ በብሄር ላይ በመቆሙ ለሙስና በጣም ተጋልጠናል። የኣንድ ቡድን ሃብት ያለልክ ሲያድግ ሌላው እየቆረቆዘ እንዲሄድ ኣድርጓል። እነ ኤፈርት የሀገሪቱን ኣንጡራ ሃብት የያዙ ድርጅቶች ሲሆኑ በዋናነት ሃብትነታቸው የትግራይ ነው ይባላል። ይህ ኣይነቱ የኢኮኖሚ እድገት ለዜጎች ምቾት ኣይሰጥም ብቻ ሳይሆን ለግጭትም መንስዔ ይሆናል።
በሌላ በኩል ኣንድ የኢኮኖሚ ምሁር የኢትዮጵያን ብሄራዊ ሃብት በተመለከት ጥሩ ግምገማ ኣድርገው ነበር። እኚህ ምሁር ያሉት ምንድን ነው ኣገሪቱ በኣጠቃላይ ሁለት ጊዜ የብሄራዊ ሃብት ዝውውር ኣድርጋለች ይላሉ። የመጀመሪያው የሃብት ዝውውር በደርግ ጊዜ የተካሄደው መሆኑ ነው። እንደሚታወቀው ኢትዮጵያ ከዘውድ ኣገዛዝ ስትላቀቅ ደርግ ያደረገው የመጀመሪያ ነገር የመሬት ኣዋጅ ነበር። በባላባቶች ተይዞ የነበረውን መሬት በኣንድ ለሊት ኣዋጅ ነጥቆ ለድሆች በገመድ ኣካፍሏል። ቀጥሎም የከተማ ትርፍ ቤትና ቦታን በሚመለከት በኣንድ ለሊት ኣዋጅ አውጆ ሁለት ቤት ያለውን ኣንዱን በመንጠቅ ያንን የተነጠቀውን ቤት ለቀበሌ እየሰጠ ድሆችን እያዳበለ ሸንሽኖ ኣድሏል። ይህን የሃብት ዝውውር ስናይ ውሳኔው ፖለቲካዊ ብቻ በመሆኑ የሃገሪቱን የረጅም ጊዜ የኢኮኖሚ እድገት ሳያገናዝብ የተወሰነ ነበር። ሃገሪቱ ሃብትን ስታዛውር ጥበብን ኣላሳየችም ለማለት ነው። የሆነ ሆኖ ግን መሬት የሌላቸው መሬት በማግኘታቸው የቀበሌ ቤት በመብዛቱ የተደሰቱ ፍትህ ወረደ ያሉ ብዙ ናቸው። ይሁን እንጂ ኣንዳንድ ምሁራን እንደሚሉት ሃብት ተበጣጠሰ ሃገሪቱ ለእድገት የሚያንደረድራትን ሁሉ በጣጠሰች ይላሉ። ስለሆነም ሁላችን ተያይዘን ተመሳሳይ ድሃ ሆነን ቁጭ ከማለት ውጭ የመጣ ነገር የለም እንዴውም ድህነት ወደ ገበሬው የገባው በዚህ ዘመን ነው ይላሉ። ያም ኣለ ይህ በወቅቱ ኢትዮጵያ የተከተለችው የሃብት ክፍፍል የሶሻሊዝም ርእዩትን መሰረት ያደረገ በመሆኑ ሁኔታው በደርግ በኩል በጣም ስሜታዊና የማይቀለበስ ኣይነት ነበር። ደርግ በዚህ ጉዳይ ላይ የባለሙያ ምክርም ሊሰማ ኣይፈልግም ነበር። ይህ የብሄራዊ ሃብት ዝውውር ከተጠናቀቀ በሁዋላ የሃገሪቱ ኣጠቃላይ እድገት በጣም ኣዝግሟል። ጎረቤት ኣገራት የተሻለ ሲራመዱ እኛ ዘገየን።
ደርግ በኢህኣዴግ ሲተካ ደግሞ ሌላው የሃገር ሃብት ዝውውር ተደረገ ይላሉ ምሁራን። ይህ ዝውውር እንደ ደርግ በህግና በግልጽ ሳይሆን በጣም ሲስተማቲክ በሆነ መንገድ የሃገር ሃብት ወደ ኣንድ ጠባብ ቡድን ተዛውሯል። ፖለቲካው ብሄርተኛ ሲሆን ስልጣኑን የያዘው ህወሃት የራሴ ወደሚለው ቡዽን ብዙ ሃብት ኣዛውሯል። ሲጀምር ሃገሪቱ ሃብታም ታፈራ የነበረው ብዙ ድሆችን እየጨመረች ነው። ብዙ ድሆችን እያፈራች ኣንድ ሃብታም ታወጣለች። ይህ ሃብታም ደግሞ በኣብዛኛው ከኣንድ ብሄር እንዲሆን በመደረጉ የተዛወረው ሃብት ለቅራኔ ምክንያት ሆኗል። ይህ ችግር የፖለቲካው ተፈጥሮ ስሜት ያመጣው በመሆኑ ከፌደራሉ ቅርጽ ጋር ይያያዛል። ዛሬ የኦሮምያና የኣማራ ኣንዱ ጥያቄ በኢኮኖሚ እኛ ተጎዳን ሃብት ወደ ኣንድ ጠባብ ቡድን ተዛውሯል ነው። ለምን ድሃ ሆንን ሳይሆን ያልንን ሃብት ወደ ኣንድ ቡድን ለምን ኣዞራችሁት ነው። የፍትህ ጥያቄ ነው። በሌላ በኩል መሬት የመንግስት በመሆኑና ባለመሸጥ ባለመለወጡ ግብርናው እንዳያድግ ኣድርጎታል። በዚህ የግብርና ፖሊሲ ኢትዮጵያ የቱንም ያህል ግብአት ብትጠቀም ኣታድግም። በአጠቃላይ ግን የብሄር ፌደራሊዝሙ ብሄራዊ ሃብት እንዳንይዝ የሃብት ክምችት ለጥርጣሬና ለግጭት መንስዔ እንዲሆን ሙስና እንዲጨምር ኣድርጎብናል።
በሌላ በኩል የኢትዮጵያን ፊስከል ፌደራሊዝም ስናይ የምንማረው ጉዳይ አለ። ሁሉም ክልሎች የራሳቸውን ባጀት ለመሸፈን ያላቸው አቅም ወደ 27 እና 28 ምን አልባት ቢበዛ 30 በመቶ ብቻ ነው። የሚያገኙት ገቢ ይህን ያህል ብቻ ነው የሚደግፋቸው። ሁሉም ክልሎች በአማካይ እስከ 70 በመቶ የሚሆነውን ባጀታቸውን የሚደጎሙት ከፌደራል መንግስት ነው። የፌደራል መንግስት እርዳታና ብድርንም ጨምሮ ነው ይህን ድጎማ የሚያደርገው። ይህ የሚያሳየው ሃገሪቱ ከኢኮኖሚ አንፃር ማእከላዊነት እንዳላት ነው። የፌደራል መንግስትም ከኢኮኖሚ አንፃር እጅግ ጠንካራ ነው። ብሄሮች ልባቸው እዚያ ፌደራል ላይ የተሰቀለውም ሰርተንም በርዳታም ያገኘነውን ፍትሃዊ በሆነ መንገድ እንድንካፈል የፌደራሉ ስልጣን ፍትሃዊ በሆነ መንገድ መከፋፈል አለበት ነው።
- ለኣስተዳደር ኣመቺነት
የሚገርመው ነገር እስካሁን ባየንበት ኣንግል በሙሉ ከፌደራል ጽንሰ ሃሳብ ጋር የሚጣረስ ስርዓት ነው ኢትዮጵያ የምትከተለው። ይህንን ሁሉ ካየን በሁዋላ ለመሆኑ እንዴው ለኣስተዳደርስ ይመቻል ወይ ብለን ብንጠይቅም ትላልቅ ችግሮች ተጋርጠውበታል። ሃረሪን የምታክል ኣራት መቶ ኪሎሜትር ስኮየር የማትሞላ ክልል ኣድርጎ በሌላ በኩል ደግሞ ኦሮምያን የሚያህል ግዙፍ ኣገር ኣንድ ክልል ኣድርጎታል። የክልሎችን ዲሞግራፊና ደንሲቲ ስናይ በጣም ለኣስተዳደር የማይመች ክፍፍል እንደሆነ እናያለን።
7 አብዮታዊ ዴሞክራሲና የፌደራል ሥርዓት
አብዮታዊ ዴሞክራሲ የሚባለው ነገር በኢትዮጵያ ውስጥ ከህገ መንግስቱም በላይ ቦታ የተሰጠው ይመስላል። በርእዮቱ ግልጽነት ላይ የሚነሱ ጥያቄዎች እንዳሉ ሆነው ምሁራን እንደሚሉት አብዮታዊ ዴሞክራሲ ቀድሞ የተፈጠረው በሌኒን ሲሆን ዓላማው ወደ ሶሻሊዝም ስርአት መሸጋገሪያ ይሆናል ተብሎ ነበር ይባላል። ይሁን እንጂ ኢትዮጵያ ደግሞ ወደ ሊብራል ዴሞክራሲ እጓዝበታለሁ ትላለች እያሉ የሚተቹ አሉ። ርእዮቱ ራሱ የተሳሳተ ባቡር ነው ነው ነገሩ። ትልቁ ጉዳይ ግን ይህ አብዮታዊ ዴሞክራሲ የሚባል ትምህርትና ልማታዊ መንግስት የሚባል ዶክትሪን የሚፈልገው አንድ ነገር ቢኖር ጠንካራ ማእከላዊነት ያለው ሥርዓት ነው። ህወሃት/ኢህአዴግ ሁሉ በአብዮታዊ ዴሞክራሲ ትምህርት ካልተጠመቀ ሞቼ እገኛለሁ የሚያሰኘው ትምህርቱ ዩኒፎርሚቲን ወጥነትን ስለሚጠይቅ ነው። ኢትዮጵያ ይህንን ርእዮት ከህገ መንግስት አብልጣ ይዛ በሌላ በኩል የፌደራል ስርአትን መተግበር አትችልም። ፌደራሊዝም በተፈጥሮው ሊብራል ነው። ለቀቅ ብሎ ስቴቶች በራሳቸው እውቀትና ችሎታ እንዲንቀሳቀሱ እድል የሚሰጥ ሲሆን አብዮታዊ ዴሞክራሲ ጠንካራ አሃዳዊ መንግስትን ይሻል። በአሁኑ ሰአት በገዢው ፓርቲ አካባቢ የዚህ ችግር ነፀብራቅ ብዙ ያልታየው በእውኑ የፌደራል ስርአት ስለሌለ ነው እንጂ እውነተኛ
የፌደራል ስርአት ቢኖር አብዮታዊ ዴሞክራሲ ችግር ፈጠረ ተብሎ ቶሎ ይጣል ነበር። ልማታዊ መንግስትነትም እንደዚሁ ነው። ከፍተኛ የሆነ ብሄራዊ ስሜትና አሃዳዊ አስተዳደር ይጠይቃል። እንግዲህ ሃገራችን እየሆነ ያለው ምንድን ነው? አገሩን ሁሉ በአብዮታዊ ዴሞክራሲ ለማጥመቅ እየተሞከረ በሌላ በኩል የፌደራል ስርአትን ለመጎተት ይሞከራል። አብዮታዊ ዴሞክራሲ እንኳን አቶ ስዩም የሚሉትን አይነት ፌደራሊዝም ይቅርና መድብለ ፓርቲን የሚሸከም ትከሻ የለውም። በጣም ወጥነትን ይሻል። በአጠቃላይ ያለው የፓለቲካ ውቅር ማለትም የብሄር ፓለቲካ፣ አብዮታዊ ዴሞክራሲ፣ልማታዊ መንግስት፣ የብሄር ፌደራሊዝም አብረው የማይሄዱ አንዱ ለአንዱ ጠንካራ ደጋፊ ያልሆኑ ናቸው። እነዚህ የማይደጋገፉ ነገሮች ሁሉ የሚተራመሱበት ስርአት ነው ያለን።
በአጠቃላይ ከመንግስት አምባገነናዊ ባህርይ በተጨማሪ ከፍተኛ የአወቃቀርና የርእዮት ችግሮች አሉብን።
ምን ዓይነት የመንግስት ስርዓት ያሻናል?
እንግዲህ ኣሁን ያለው የኢትዮጵያ የመንግስት ስርዓት ግዙፍ ችግሮችን የያዘ በመሆኑ ባስቸኳይ መለወጥ ይኖርበታል። ታዲያ ሲለወጥ ምን ኣይነት የመንግስት ስርዓት ያሻናል የሚለው ጥያቄ በጥብቅ መታየትና መጠናት ኣለበት። ከዚህ በፊት ደጋግሜ በጻፍኳቸው ጽሁፎች እንደጠቋቆምኩት ኢትዮጵያ አዲስ የመንግስት ስርዓት ያሻታል። ይህ ስርዓት ምን መምሰል ኣለበት ካልን ሰኪዩላር የፌደራል ስርዓት ሆኖ ነገር ግን የኣገር ኣስተዳደር ስናዋቅር ከተለመዱት ሶስቱ የመንግስት ኣካላት ማለትም ህግ ኣውጭው ህግ ኣስፈጻሚውና ህግ ተርጓሚው በተጨማሪ ኣንድ የአርበኞች ቤት ቢኖረንና አራት ሲስተሞች ቢኖሩን ጥሩ ነው። ይህ የኣርበኞች ቤት የባህል መሪዎችን የሚይዝ ከየባህላዊ ቡድኑ የተውጣጡ ኣባላትን የሚይዝ ሆኖ የባህልና የሰላም
ጉዳዮችን እየሰራ ተከብሮ ይኖራል። በዚህም የቡድኖች የባህላዊ ማንነት ይጠበቃል የእኩልነት ስሜት ይመጣል። የብሄር ኢንተርፕሩነርስ የተባሉት ቦታ ያገኛሉ። ሁለተኛው ክፍል ደግሞ ሶስቱን የመንግስት መዋቅሮች የሚይዘው መንግስት በህዝብ ምርጫ ስልጣን እየያዘ የሚኖር ይሆናል። እነዚህ ሶስቱ የመንግስት ስልጣኖች ቼክና ባላንስ እያደረጉ ይኖራሉ። የሃገሪቱ የስልጣን መወጣጫ ደግሞ የፖሊሲና የኣመለካከት ልቀት ብቻ እንዲሆን ማድረግ ያሰፈልጋል። ኢትዮጵያን ከብሄር ፖለቲካ በማላቀቅ ጨዋታው በብሄራዊ ኣጀንዳ ዙሪያ እንዲሆን መደረጉ የፌደራል ስርዓቱን ሰኪዩላር ወይም ሳይንሳዊ ያደርገዋል። ኢትዮጵያ ኣዲሱን የፌደራል ስርዓት ስታዋቅር በስቴቶችና በፌደራል መንግስት መሃል የስልጣን መካፈል የሚኖር ሲሆን ኣንዱ መንግስት ሌላውን እንዲጠብቅ ተደርጎ መዋቀር ይኖርበታል። በሌላ በኩል ደግሞ በኣሁኑ ሰዓት ያለውን የፍትህ ስርዓትና የፖለቲካ ሹመትን መጣበቅ ማላቀቅ ያስፈልጋል። የፌደሬሽን ምክር ቤት የሚሰራውን የህገ መንግስት ትርጉም ጉዳይ ኣፍርሶ ራሱን የቻለ የህገ መንግስት ትርጉም ፍርድ ቤት ማቋቋም ኣንዱ የኣዲሱ የፌደራል ስርዓት ስራ መሆን ያይኖርበታል።
ሌላው ትልቁ የኣዲሱ የፌደራል ስርዓት ዋና መሰረት ሊሆን የሚገባው የኢትዮጵያውያን አዲስ ኪዳን ነው። ይህ ማለት ካለፍንበት የፖለቲካ ስርዓትና ኣሁን ካለንበት የብሄር ፌደራሊዝም ኣንጻር ብዙ ብዥታዎች ተፈጥረዋል። የተፈጥሮ ሃብትን በሚመለከት፣ ባህላዊ ማንነትን በሚመለከት፣ የጋራ ሃብትን በሚመለከት ብዥታዎች ተፈጥረዋል። ይህንን ጉዳይ ለማጥራትና ኣገራችንን በማይነቃነቅ መሰረት ላይ ጥለን ወደ ልማት ለመግባት ኢትዮጵያውያን ኣንድ ከፍ ያለ ኪዳን መግባት ይኖርብናል። ይህ ኪዳን ህገ መንግስት ሳይሆን ከዚያ በላይ የሚውል ለትውልድ የምናሳልፈው ቃል ኪዳን ነው። በይዘቱ የምናነሳው ጉዳይ ያሉንን የተፈጥሮ ሃብትና እሴቶች ለኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነት መስዋዕት የምናደርግበት ከፍተኛ ኪዳን ነው። ይህ ኪዳን የፖለቲካ መሰረታችን የፌደራል ስርዓት መሰረታችን ይሆናል። በጠራ ማህበረ ፖለቲካ መሰረት ላይ ቆመን እንድንቀጥል ይረዳናል። በሌላ በኩል ኣዲሱ የፌደራል ስርዓት ሲዋቀር ስቴቶች የብሄር ስም ይዘው ሳይሆን ሌሎች ስያሜዎች እየተሰጧቸው እንዲዋቀሩ መደረግ ኣለበት። ከዚህ በተጨማሪ የፌደራል
ስርዓቱ ህገ መንግስታዊ ዳኛ ብቻ ሳይሆን ኦዲተርም ቢኖረው ጥሩ ነው። ይህ ኦዲተር ስቴቶችን የሚያነቃቃ ስራ እየቆጠረ የሚከታተል ቢሆን ጥሩ ነው። ይህ የፌደራልን ስርዓት ኣይጥስም። ይህ ኦዲተር ስቴቶችን ብቻ ሳይሆን የፌደራል ተቋማትንም የሚያነቃቃ ስራ የሚቆጥር ቢሆን መነቃቃትን ያመጣል።
አዲሱ የፌደራል ስርዓት ሲዋቀር የቋንቋ ኣጠቃቀምን በተመለከት ኣዲስ የቋንቋ ኣጠቃቀም መቀየስ ይኖርበታል። ኢትዮጵያ እንደ ሃገር ያላትን የጎኖሽና ቀጥታ ግንኙነት ለማሳለጥ የህብረት ቋንቋ ይሻታል። በዚህ መሰረት ኣንድ የህብረት ቋንቋ ይኖረናል። ከዚህ በሁዋላ ስቴቶች እንደ ሁኔታው እስከ ሁለት የሚደርስ ኦፊሺያል ቋንቋ እንዲኖራቸው ሊደረግ ይቻላል። ይህ ማለት የህብረቱ ቋንቋ እና ኣንድ በዚያ ስቴት ስር ያሉ ብዙ ሰዎች የሚናገሩት ቋንቋ ማለት ነው። ከዚህ በሁዋላ በመላው ሃገሪቱ በማዘጋጃ ቤት ደረጃ የህብረት ቋንቋና የኣካባቢ ቋንቋ ኦፊሺያል እንዲሆኑ ማድረግ ይቻላል። ይህ ኣሰራር በኢኮኖሚ ላይ የሚያመጣው ተጽእኖ ጉልህ ኣይሆንም። የግድ የብሄሮች መብት መጠበቅ ኣለበት። ስለዚህ ኢትዮጵያ በኣዲሱ ኣስተዳደር የቋንቋ ኣጠቃቀሟን እንዲህ ብታደርግ ሁሉም የሃገሪቱ ቋንቋዎች በታችኛው የስልጣን ርከን ላይ ስለሚሰሩ የቋንቋ አጠቃቀም ፍትህ ይወርዳል። ዜጎች በቋንቋቸው ኣገልግሎት ሲያገኙ ልማት ይፈጥናል። የሃገር ፍቅር ስሜት ይጨምራል። በመሆኑም ኣዲሱ ስርዓት በዚህ መንገድ ቢዋቀር የተሻለ ነው። ስርዓቱ ማንነትን ሊንከባከብ የሚችለው በዚህ መንገድ ቢሆን የተሻለ ይሆናል። የስቴቶችን ኣመሰራረት በተመለከተ የህዝብ ኣሰፋፈርን ለኣስተዳደር ኣመቺነትን እያዩ መመስረት ይገባል። ከዚህ በተጨማሪ ህገ መንግስቱ ስቴቶችና ፌደራል መንግስት የሚካፈላቸውን ስልጣኖች ለይቶ ማስቀመጥ ኣለበት። ሁሉቱ መንግስታት ኣብረው የሚሰሯቸውንም እንዲሁ በግልጽ ማስቀመጥ ይኖርበታል። ግልጽና ሃቀኛ የስልጣን ክፍፍል ያለበት ስርዓት መፍጠር ጥሩ ነው። በአጠቃላይ ኢትዮጵያ ፓለቲካዋን ከብሄር ፓለቲካ ማላቀቅና ባህልን በሌላ ጠገግ መጠበቅ ይኖርባታል። እንዲህ ስታደርግ የተሻለ ሥርአት ትመሰርታለች።
አስተያየት ወይም በጽሁፉ ዙሪያ ጥያቄ ካለ በሚከተለው አድራሻ ያገኙኛል
geletawzeleke@gmail.com እግዚአብሔር ኢትዮጵያን ይባርክ!
ህብር ሬድዮን በህብር ሬዲዮ ድህረ ገጽ ወይም በቀጥታ በስልክ ለማዳመጥ 712 -432-8451 መደወል ብቻ በቂ ነው በእንግሊዝ ለምትኖሩ በ01405770140 በስልክ ማዳመጥ ይቻላል። ዘወትር በድህረ ገጻችን፣ ከ googel app store Hiber Radio ወደ ስልክዎ በመጫን ካልሆነም በዘሐበሻ እንዲሁም በተጠቀሱት ስልኮች ማዳመጥ ይቻላል።