የኢንጂነር ሀይሉ ሻውል ዜና እረፍት በዚህ የለውጥ ዋዜማ አሳዛኝ ነው።መራር በሆነው ባለፉት ሃያ አምስት ዓመታት የኢትዮጵያ ተቃውሞ ትግል ታሪክ ስማቸው በግንባር ቀደምትነት የሚወሳ በተለይም ምርጫ 97ን ተከትሎ በቅንጅት ውስጥ የነበራቸው ሚና ጎልቶ ይታወሳል።የቅንጅቱ የጀርባ አጥንት የነበረው መኢአድ እስከ ቀበሌ ወርዶ እንዲደራጅ በአገሪቱ ዋና ዋና አካባቢዎች የተለያዩ ቢሮዎችን በመክፈት ትልቅ ሚና ነበረው ።ይህ ሲታወስ ኢንጂነር ሀይሉ በወቅቱ የሰጡት አመራር ይጠቀሳል። ምርጫ 97ን ተከትሎ ተጎትተው ታስረው በእስር ቤት በገጠማቸው ሕመም በሕክምና ባሉበት ታይላንድ ሕይወታቸው ማለፉ ሲሰማ አስደንጋጭ ነው። ዜና እረፍታቸውን ስንሰማ ብዙዎች እንዳሉት የተመኙት የኢትዮጵያ ሕዝብ የመብቱ ባለቤት የመሆን ሕልም እውን ሆኖ አይተው ብለን ተመኘን። በኢ/ር ሀይሉ ሻውል ሞት የተሰማንን ሐዘን በዚህ አጋጣሚ እየገለጽን ለቤተሰቦቻቸው፣ለትግል አጋሮቻቸውና በአጠቃላይ ስለ መብቱ ለታገሉለት ለጮሁለት ሁሉ መጽናናትን እንመኛለን። የኢ/ር ሀይሉ ሻውልን ዜና እረፍት ተከትሎ የእውነተኛው የመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት(መኢአድ) መግለጫ አውጥቷል።አያይዘን አቅርበነዋል።
የዲሞክራሲ አርበኛዉ ኢንጂነር ሀይሉ ሻዉል በማረፋቸዉ ጥልቅ ሐዘን ተሰምቶናል
ከእውነተኛው መኢአድ የተሰጠ መግለጫ (ከመላዉ የኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት ሕጋዊ አመራር የተሰጠ መግለጫ )
የመላዉ ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት መሪ እንዲሁም የቅንጅት መሪ የነበሩት ኢንጂነር ሀይሉ ሻዉል በማረፋቸዉ የተሰማን ሀዘን ጥልቅ ነዉ:: ሀይሉ ሻዉል በ1997 ዓም ቅንጅትን በመምራት የኢትዮጵያን ህዝብ ከዳር እስከ ዳር ያንቀሳቀሱ የዲሞክራሲ አርበኛ ነበሩ:: የኢትዮጵያ ህዝብ ዲሞክራሲን በምርጫ ስርዓት ሊተገብር የሚችል ስልጡን ህዝብ መሆኑንም ለአለም ህዝብ አሳይተዋል::ወያኔን እራቁቱን በማስቀረት እና ወያኔ ለሰላማዊ ምርጫ እጁን እንደማይሰጥም ኢንጂነር ሀይሉ ሻዉል የመሩት ቅንጅት ለመላዉ ኢትዮጵያ እና ለመላዉ አለም ምስክርነትን ሰጥቷል::
ሀይሉ ሻዉል መኢአድን መሚመሩበትም ጊዜ ሆነ ቅንጅትን በሚመሩበት ጊዜ በከፍተኛ ዉጣ ዉረድ ዉስጥ ያለፉ ለሚያምኑበት ነገር ግንባራቸዉን የማያጥፉ ፖለቲከኛ ነበሩ::
ሀይሉ ሻዉል በ2002ዓም ወደ ምርጫ ለመግባት መወሰናቸዉ እና ከመለስ ዜናዊ ጋር እጅ ለእጅ መጨባበጣቸዉን በፎቶ ግራፍ በማስደገፍ ሀይሉ ሻዉል ወያኔ ሆነ ብለዉ ብዙዎች ሰድበዋቸዋል::ሌላዉ ቀርቶ ወያኔን ሲያገለግሉ የነበሩ: የወያኔ ባለስልጣናት የነበሩ እና ከጊዜ ብኋላ ተቃዋሚ ሆንን የፖለቲካ ዘማዎች ሀይሉ ከመለስ ጋር ተጨባበጠ : በ2002 ዓም ወደ ምርጫ ገባ በማለት ሀይሉ ሻዉልን በወያኔነት ከሰዋቸዋል::አጠገባቸዉ የነበሩ ሰዎች ሀይሉ ገንዘቡን ያገኘዉ እና ሀብታም የሆነዉ ወያኔ ሆኖ ነዉ ሲሉም ከሰዋቸዋል:: የሀይሉ ሻዉልን ታሪክ ለመንጠቅ እና የሀይሉ ሻዉልን ተጋድሎ ለማኮስመን ኮሚቴ እና ግብረ ሀይል ተቋቁሞ ; ጋዜጣ እና ዌብሳይት ተከፍቶ : ሀይሉ ሻዉል የሚሳደቡ እና ሀይሉ ሻዉልን በወያኔነት የሚከሱ በርካታ ሀይላት ተፈልፍለዉ ነበር::አንዳንዶቹ አሁን ድረስ ሀይሉ ሻዉልን መክሰሳቸዉን የቀጠሉ አሉ:: አንዳንዶቹ የሀይሉ ሻዉል ከሳሾች በሀይሉ ሻዉል ዉድቀት ዉስጥ የተደበቁ ጸረ ኢትዮጵያዉያን ሲሆኑ ሌሎቹ ደግሞ ከሰዉ ስህተት ይልቅ የሰዉ ዉድቀቱል ለማዬት የሚጣደፉ ናቸዉ:: በርካቶች ቅንጅቱን ለራሳቸዉ አላማ በዚህ እና በዚያ ገነጣጥለዉ ሲያበቁ (አንዴ ቅንጅት የትምክህተኞች መሰብሰቢያ ሆነ በማለት: ሌላ ጊዜም ሀይሉ ሻዉል አምባ ገነን ሆነብን በማለት: አንዳንዴ ደግሞ አንዲት ኢትዮጵያ የሚለዉ አካሄድ አያወጣም በማለት) ለቅንጅት መፍረስ ግን ሀይሉ ሻዉልን ብቻ የሚከሱ አሉ::እዉነታዉ ግን ሀይሉ ሻዉል ለቅንጅት የዋሉለት ዉለታ እና ቅንጅት እዉን ይሆን ዘንድ የሰሩት ስራ የመሰረት ድንጋይ ነበር:: መላዉ ኢትዮጵያን በመዞር ከህዝቡ ጋር በማደር እና ከጠረፍ እስከ ጠረፍ በመንከራተት መኢአድ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ አባላትን እንዲያፈራ አድርገዉ ነበር:: በመሆኑም ሀይሉ ሻዉል ወደ ቅንጅቱ ሲቀላቀሉ አንድ ሚሊዮን ሁለት መቶ ሽህ አባላትን አስከትለዉ ነበር:: ይሄም የመኢአድ አባላት የቅንጅት የመሰረት ድንጋይ ነበር::አሁን ድረስ በመላ ሀገሪቱ ለሚደረጉት ተቃዉሞዎች የሀይሉ ሻዉል መሰረት የያዘ ስራ እና የመኢአድ ቆራጥ አመራር የሚስጢሩ ቁልፍ ናቸዉ:: ሀይሉ ሻዉል በሰሩት ስራ ላይ ቆመዉ የሚጨፍሩ የፖለቲካ ዘማዎች ግን የሀይሉ ሻዉልን ታሪክ ለመንጠቅ የሀይሉ ሻዉልን ታሪክ ማጉደፋቸዉን ቀጥለዋል:: የሀይሉ ሻዉልን ታላላቅ አስተዋጾዎች ከመናገር እየደበቁ የሀይሉ ሻዉልን ስህተቶች ብቻ ይሞዝቃሉ:: ሀይሉ ሻዉል የሰሩት ስራ ግን እንዲህ በቀላሉ የሚወሳ አይደለም ወይም የሚደበቅ አይደለም:: ሀይሉ ሻዉል የሰሩትን ስህተት ወይም ያደረጉትን አዎንታዊ አስተዋጽኦ ታሪክ ሊመዘግብላቸዉ የሚገባዉ በእዉነተኛ ሚዛን ላይ በማስቀመጥ እንጅ በጥላቻ እና በአሉባልታ ሚዛን ላይ አስቀምጦ አይደልም::
ቅንጅት ከፈረሰም ብኋላ ሀይሉ ሻዉልም እድሜአቸዉ እየገፋ ሲሄድ በዉጭ ሀገር እና በኢትዮጵያ በርካታ ደጋፊዎቻቸዉን አስቀይመዉ መኢአድንም አዳክመዉ ትክክለኞቹን አጋሮቻቸዉን ሳይሆን ግራ የተጋቡ ሰዎችን አግተልትለዉ መሄድ ሲጀምሩ ድርጅታቸዉን መኢአድን አምስት ቦታ እንዲከፈል አድርገዉት ነበር::የሆኖ ሆኖ የዛሬ ሁለት አመት አምስት ቦታ የተከፈለዉ ድርጅት ወደ አንድ እንዲመጣ በተደረገዉ ጥረት ሀይሉ ሻዉል እጅግ አዎንታዊ ትብብር ከማድረጋቸዉ በላይም በጠቅላላ ጉባኤዉ ላይ በመገኘት ትክክለኞቹን የድርጅቱን ታጋዮች በመደገፍ : ድርጅቱን ለማፍረስ የሚራወጡትን ደግሞ በመገሰጽ እንዲሁም የራሳቸዉን ስህተት በማመን የእዉነት አርበኛም መሆናቸዉን አስመስክረዋል::
የእዉነት አርበኛ የሆኑት ሀይሉ ሻዉል የሰሩትንም ስህተትም በማመን እንዲህ ሲሉ ንግግር አድረገዋል:- “እኔ ከንግዲህ ደክሜአለሁ:: በእድሜዬም መሄድ ምክንያት ብዙ ስህተተ የሆነ ዉሳኔ ወስኜ ሊሆን ይችላል:: ሀገሬ ኢትዮጵያን ለማገልገል ስደክም ብዙ ስህተት ሰርቼም ሊሆን ይችላል:: የሆኖ ሆኖ የሰራሁትን በጎም ሆነ ስህተት ነገር ለታሪክ እተዋለሁ:: እናንተ ግን ከእንግዲህ ብኋላ ታግላችሁ ማታገል ከፈለጋችሁ ከማሙሸት አማረ ጋር ቁሙ::ይሄን ልጅ እኔ በድዬዉ ነበር::የተሳሳቱ ሰዎችን ምክር አምኜ ድርጅቱንም ብዙ ቦታ እንዲከፋፈል አድርጌዉ ነበር:: ላለፉት ሶስት አመታት እነ ማሙሸትን ከድርጅቱ አግጃቸዉ ብቆይም ባደረግሁት ማጣራት የማሙሸት አማረ ቡድን መቼም የማይበርድ የፖለቲካ ትግል ፍላጎት እንዳለዉ እና መኢአድን ፍጹም የሚወዱ ብሎም የኢትዮጵያንም ህዝብ ከወያኔ ፈጽመዉ ለማላቀቅ የወሰኑ ወጣቶች መሆናቸዉን ማወቅ ችያለሁ:: አሁን ሁላችሁም እንድትረዱት የሚገባው ማሙሸት አማረ የማይናወጥ የትግል አላማ ያለዉ ወጣት በመሆኑ ልትተባበሩት እንደሚገባ ነዉ:: የሆኖ ሆኖ ግን እርሱን መሪ አድርጋችሁ መረጣችሁም ወይም ሌላ መሪ መረጣችሁም ዉሳኔዉ የራሳችሁ ነዉ::ግን ካሁን ብኋላ እርስ በርሳችሁ አትቆራቆሱ::እርስ በርሳችሁም አትከፋፈሉ::በኢትዮጵያ ፖለቲካ ዉስጥ አሳሳቹ እና አሉባልታ ነዥዉ ብዙ ነዉ::ወዳጅ መስሎ ቀርቦ እዉነተኛ ታጋዮችን እርስ በርስ የሚያጣላዉ ብዙ ነዉ:: ለትግሉ አንድ ተጠር ከማቀበል ይልቅ ትግሉን ለመተቸት የሚፋጠነዉ ግን ብዙ ነዉ:: ስለዚህ ጥንቃቄ እያደረጋችሁ ተጓዙ:: የኢትዮጵያ ፖለቲካ በማይታወቅ ምክንያት ተንኮለኞች: ሀሰተኞች:ከሳሾች: እና አሉባልተኞች ይበዙበታል:: ፊት ለፊት ከመሞገት ይልቅ በየጓዳዉ አሉባልታ መንዛት የሚቀናቸዉ ብዙዎች ናቸዉ::ስለዚህ በአሉባልታ ተጠልፋችሁ እንዳትወድቁ ተጠንቀቁ:: ተመካከሩ::የመጨረሻዉ ትልቁ የተማርኩት እዉነት ወዳጆቻችሁን በሀሰተኞቹ ጠላቶቻችሁ አሉባልታ ተታላችሁ ላለማስቀዬም መጠንቀቅ እንደሚገባ ነዉ::ይቅርታ ማድረግን ተማሩ::ይቅርታ መጠዬቅንም እወቁ::የኢትዮጵያ የተቃዉሞ ፖለቲካ ብዙ መቻቻል ካልተደረገበት በእርስ በርስ ትግል መጠፋፋት ይደመደማል::” ሲሉ ተናገረዉ ነበር::
የዲሞክራሲ አርበኛዉ ኢንጂነር ሀይሉ ሻዉል የሚያምንበትን ብቻ የሚተገብር ሳይሆን በአንድ ነገር ላይ እንደተሳሳተ ካመነም ስህተቱንም ለማመን ወደ ኋላ የማይል ጀግና መሆኑን ያስመሰከረ ታላቅ ፖለቲከኛ ነበር::
ምንም እንኳን በበርካታ የሀገር ሽማግሌዎች ጥረት እንዲሁም በኢንጂነር ሀይሉ ሻዉል አዎንታዊ ትብብር አምስት ቦታ ተከፋፍለዉ እና ተጣልተዉ የነበሩት የመኢአድ ልዩ ልዩ ቡድኖች በአንድ ላይ ተሰብስበዉ በአንድ ድምጽ ከ483 ተሳታፊዎች ዉስጥ 477 የጠቅላላ ጉባኤ ተሳታፊዎች አቶ ማሙሸት አማረን በድርጅቱ ፕሬዝዳንትነት ቢመርጡትም ወያኔ የመኢአድን ቢሮ ለአቶ አበባዉ እና ለዶክተር በዛብህ አስረክቦ እስካሁን ድረስ መኢአድን ለማጥፋት ከፍተኛ ስራ እየሰራ ይገኛል::በሚያሳፍር ሁኔታም ወያኔ በአሁኑ ሰዓት በመላ ሀገሪቱ ህዝቡን ሲገል እና ህዝብ የዲሞክራሲ መብቱን ስለጠዬቅ በወያኔ አፈሙዝ ሲቀጠቀጥ አበባዉ እና ዶ/ር በዛብህ የወያኔን ስራ ልክ ነዉ እያሉ መግለጫ የሚያወጡ ሆነዋል:: አበባዉ እና ዶ/ር በዛብህ ወያኔ በሚሰጣቸዉ ሚዲያ በመዉጣት የመኢአድ መሪዎች ነን እያሉ ይቀልዳሉ::ጀግናዉ የኢትዮጵያ ህዝብም ሲታረድ እና ሲገደል መገደሉን በመደገፍ ድምጻቸዉን ይሰጣሉ::
የሆኖ ሆኖ መኢአድን በአበባዉ እና በዶ/ር በዛብህ በኩል ለመጥለፍ ወያኔ አጠንክሮ ቢሰራም የወያኔ እቅድ ሁሉ ግቡን እንደማይመታ ደግመን ማሳሰብ እንፈልጋለን:: የመኢአድ ትግል እንዲህ ወያኔ እንደሚያስበዉ በቀላሉ የሚዳፈን አይሆንም:: መኢአድ በመላ ሀገሪቱ እንደ ዋርካ ስር የሰደድ ድርጅት ብቻ ሳይሆን አንዲት ኢትዮጵያ: አንድ ህዝብ የሚለዉ የማይቀለበስ የመኢአድ መርህ የመላዉ ኢትዮጵያ ህዝብ የመንፈስ ስንቁ ነዉ:: ስለሆነም የመኢአድ ትግል የኢትዮጵያ አንድነት: የኢትዮጵያ ዲሞክራሲያዊነት እና የኢትዮጵያ ብልጽገና እስኪረጋገጥ ድረስ ይቀጥላል:: ወያኔ የመኢአድን ቢሮ አንቆ ለአበባዉ እና ለዶ/ር በዛብህ ሰጣቸዉም አልሰጣቸዉም መኢአድ በኢትዮጵያዉያን አባሎቹ እና ደጋፊዎቹ ልብ ዉስጥ ቢሮዉን የከፈተ ድርጅት ነዉ::መኢአድ መንፈስ የሆነ ድርጅት ነዉ::የትግል አላማዉም የአንድ ሰሞን እሩጫ አይደለም::
ኢንጅነር ሀይሉ ሻዉልም በመጨረሻ የህይወት ዘመናቸዉ የተሳሳቱትን ስህተት በማረም የተከፋፈለዉ ድርጅትም ወደ አንድ እንዲመጣ እና በትክክለኞቹ የኢትዮጵያ ህዝብ ታጋዮች እንዲመራ የእዉነት ቃላቸዉን መስጠታቸዉ እጅግ የሚያስመሰግናቸዉ ስራ ነዉ:: ሰዉ በህይወት ዘመኑ ብዙ ስህተት እና ብዙ መልካም ስራ ሊሰራ ይችላል:: ኢንጂነር ሀይሉ ሻዉል ግን በህይወት ዘመናቸዉ ለኢትዮጵያ ዲሞክራሲ ግንባታ ያደረጉት ተጋድሎ ከማንም ፖለቲከኛ የላቀ እና እጅግ ታላቅ ሆኖ ተመዝግቧል:: ሀይሉ ሻዉል የሚያምንበትን በማድረግ የሚታወቅ: ቆራጥ እና ወያኔን ፊት ለፊት የተፋለመ የዲሞክራሲ አርበኛ ነበር:: ሀይሉ ሻዉል ኢትዮጵያዉያንን ከአጽናፍ እስከ አጽናፍ ያንቀሳቀሰ አርበኛ ነበር::ሀይሉ ሻዉል መላዉ ኢትዮጵያዉያን በአንድ ድምጽ እና በአንድነት አንድን ህብረ ብሄራዊ ፓርቲ ሊመርጡ እንደሚችሉ ቅንጅትን በመመስረት ብሎም በብልሃት በመምራት ለመላዉ አለም ያስመሰከረ የዲሞክራሲ አርበኛ እና ጀግና ነበር::
ሀይሉ ሻዉል ለኢትዮጵያ ዲሞክራሲ የደከመሙት ድካም እና ያደረጉት ተጋድሎ በዚህች አጭር የሀዘን መግለጫ ዘርዝረን መግለጽ አንችልም::
እግዚአብሄር ነብሳቸዉን በገነት ያኑረዉ እያለን ለቤተሰቦቻቸዉ እንዲሁም ለወዳጅ ዘመዶቻቸዉ መጽናናትን እንመኛለን::
ለገሰ ወ/ሃና
የመላዉ ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት (መኢአድ) የህዝብ ግንኙነት ም/ኃላፊ
ህብር ሬድዮን በህብር ሬዲዮ ድህረ ገጽ ወይም በቀጥታ በስልክ ለማዳመጥ 712 -432-8451 መደወል ብቻ በቂ ነው በእንግሊዝ ለምትኖሩ በ01405770140 በስልክ ማዳመጥ ይቻላል። ዘወትር በድህረ ገጻችን፣ ከ googel app store Hiber Radio ወደ ስልክዎ በመጫን ካልሆነም በዘሐበሻ እንዲሁም በተጠቀሱት ስልኮች ማዳመጥ ይቻላል።