Hiber Radio: “የቀውስ ተከላካይ ካቢኔ” በዶ/ር አክሎግ ቢራራ

hiber-radio-tplf-new-cabinet-001

የቀውስ ተከላካይ ካቢኔበዶ/ር አክሎግ ቢራራ  

ህወሓቶች ኢትዮጵያ የገጠማትን ቀውስ ራስን በመገምገምና ሹም ሽር በማድረግ እንወጣዋለን የሚል የተሳሳተ መርህ ሲከተሉ ቆይተዋል። አሁንም ስህተቱን ደግመውታል። በአጼ ኃይለ ሥላሴ ዘመነ መንግሥትና በደርግ አገዛዝም መሰረታዊ ችግሮችን ለመፍታት ሙከራ የተደረገው ባለ ሥልጣናትን በመተካት ነበር። የተተኩት ግለሰቦች በሞያቸውና በትምህርታቸው አሁን ከተሾሙት ግለሰቦች ቢበልጥ እንጅ አያንስም ነበር። ያለፉት ስርዓቶች መሰረታዊ ችግሮችን ለመፍታት ስላልቻሉ ወድቀዋል። ህወሓቶች ከዚህ የውድቀት ምሳሌ አንድም ትምህርት አልቀሰሙም። ሕዝቡን፤ በተለይ ወጣቱን ትውልድ ስለናቁትም ይሁን ሌላ፤ ጥገናዊና ሽንግልናዊ ለውጥ አድርገን የአፋኙን ስርዓት እድሜ እናራዝመዋለን የሚል መርህ ተከትለዋል። “እኔ ብቻ አውቃለሁ” የሚል የአንድ ብቸኛ ወይንም አውራ ፓርቲ የበላይነት ጣጣውና መዘዙ ብዙ ነው። ከእነዚህ መካከል አንዱ ራሱን የሚገመግመው ከራሱ ጋር ብቻ መሆኑ ነው። በኢኮኖሚውም መርህ ኢትዮጱያን የሚያነጻጽረው ከደርግ ጋር ነው። ከሯዋንዳ ጋር አይደለም፤ ከቦትስዋና ወይንም ናምቢያ ወይንም ቬትናም ጋር አይደለም።

የሕዝብን ድምጽ አፍኖ፤ ብዙ ሺህ የዐማራ፤ የኮንሶ፤ የጋምቤላ፤ የአፋር፤ የኦሮሞና ሌሎች ወጣቶችን ገድሎ ቁጥራቸውን ቀንሶ ይናገራል። ብዙ አስር ሺዎችን አስሮና እንዲሰወሩ አድርጎ በቅርቡ ባወጣው ዘገባ “ያስርኳቸው 11,600 ብቻ ናቸው” ይላል። እነዚህ ቢሆኑ መታሰራቸው ትክክል ነው? ብለን ብንጠይቅ እነዚህ የአመጸኞች አባላት ናቸው የሚል መልስ እናገኛለን። በዐማራው፤ በኦሮሞው፤ በአፋሩና በሌላው ክልል የኢኮኖሚው እንቅስቃሴ ቁሞ አሁንም ድርብ አሃዝ እድገት አለ ይላል።

1.“የኮማንድ ፖስትአገዛዝ 

“በኮማንድ ፖስት” ለመግዛት፤ ለማፈን፤ ለመግደልና ለመሰወር፤ ተቀናቃኝ የሆነን ሁሉ መብት ሙሉ በሙሉ ማፈን ያስፈልጋል። አንድም ታዛቢ እንዳይኖር ማድረግ ያስፈልጋል። ሕዝቡ በጨለማ ዐለም እንዲኖር ማድረግ ያስፈልጋል።  የማህበራዊ መገናኛ–ኢንተርኔት፤ ትዊተር፤ ፌስቡክ፤ ሞባይል፤ ቪይበር ወዘተ” ፍጹም በሆነ ደረጃ የተዘጉበት ምክንያንት ለዚህ ነው። ገዢው ፓርቲ ይህን ሲያደርግ “ለሕዝቡ ህይወትና ኑሮ፤ ለሰላምና ለእርጋታ፤ ለአገሪቱ ዘላቂነት እና አገሪቱን ከውጭ ጠላቶች ለመከላከል” በማሰብ ነው ይላል። በምንም የማይቀበለው ሃቅ አንድ ነው። ለሰላምና እርጋታ ዋና ማነቆ የሆነው ራሱ መሆኑን ሊቀበል አልቻለም፤ ወደፊትም አይቀበልም። የቆመውና የሚከራከረው ለራሱ ህይወትና ዘላቂነት ብቻ ስለሆነ የሕዝቡ ድምጽ ከስሌቱ ውስጥ ገብቶ አያውቅም፤ አሁንም አልገባም፤ ወደፊትም አይታሰብም። ሕዝቡ ያለው አማራጭ በመተባበርና በመናበብ፤ ራሱን ማደረጀትና ለራሱ መብት መታገል ይሆናል ማለት ነው።

በጠቃላይ ሚንስትር ኃይለማሪያምና አማካሪዎቻቸው ግምት ግምገማ፤ መተካትና መተካካት ማለት የተንገዳገደውን ስርዓት ትንንሽ ለውጥ አድርጎ፤ ስርዓቱን ለማቆየት የሚችሉ የተፈተኑ፤ የተገመገሙ፤ ቢያንስ ታማኝም ባይሆኑ ለስርዓቱ አደገኛ የማይሆኑ በሞያቸው እውቅና አላቸው ብሎ የገመታቸውን ግለሰቦችን፤ በታማኝነታቸውና በችሎታቸው አመዛዝዝኖ መሾም ሆኗል። እነዚህ አዲስ ሹማምንት በሞያቸው፤ በከፍተኛ ትምህርታቸው ወዘተ የታወቁ ሊሆኑ ይችላሉ። ሆኖም፤ የሚያገለግሉት ስርዓት አፋኝ፤ ጨቋኝ፤ ለወጣቱ ትውልድ እና ለሌላው አብዛኛው ሕዝብ ታዛዢና ተገዢ ያልሆነ ነው። ለስርአቱና ለአገልጋዮቹ በብዙ ሺህ የሚቆጠረው መስዋእት የሆነው ወጣት ትውልድ “ቁጥር” ነው። በብዙ ሺህ የታሰረው ወጣት ትውልድ ቁጥር ነው። በብዙ ሺህ እንዲሰወር የተደረገው ወጣት ትውልድ ቁጥር ነው። ከ102 ሚሊየን ሕዝብ ብዙ አስርት ሽዎች ቢሞቱ፤ ቢታሰሩና ቢሰወሩ ምንም አይደል የሚል ኢ-ሰብአዊ፤ ኢ-ፍትሃዊ፤ ኢ-ሕዝባዊ እና ኢ-ዲሞክራሳዊ ስርዓት ነው። እነዚህ ለፍትህ፤ ለእኩልነት ወዘተ መስዋእት የሆኑ ወጣቶች በብዙ ሚሊየን የሚገመት ወጣት ተተኪ ትውልድ እንዳላቸው አልተገነዘበውም። መስዋእት ለሆኑት ተቆርቋሪ እንደሆነ አልተረዳውም፤ ቢረዳውም ቁም ነገር አለው የሚል እምነት የለውም። በእኔ ግምትና እምነት ይህ ትውልድ ስርዓቱ ካልተለወጠ በስተቀር፤ ትግሉን አያቆምም። የህወሓቶች/ኢህአደጎች ትኩረት በስልጣን ስካርና በኪራይ ሰብሳቢነት ስግብግብነት የተበከለ ስለሆነ፤ ሌላው ቀርቶ በራሳቸው አገዛዝ ዘመን የተወለደውን አዲስ ትውልድ ራእይ፤ እምነት፤ ፍላጎትና ቆራጥነት አላወቁትም።

ገዢው ፓርቲ ቢያውቅበት፤ ወጣቱ ትውልድ መስዋእት ሆኖ የሚጠይቃቸው ለውጦች የሚከተሉት መሆናቸው ነው፤

2 አንድ፤ ህወሓቶች/ኢህአዴጎች አስቸኳዩን አዋጅ ስበው፤ ያሰሯቸውን የፖለቲካ እስረኞች ፈትተው፤ ግድያውንና ሌላውን አፈና አቁመው፤ ለእውነተኛ ሰላም ቁርጠኛ ሆነው የፖለቲካ ድርድርና የፖለቲካ ስልጣን ሽግግር ውይይት ማድረግ ተቀዳሜንት አለው፤

ሁለት፤ ህወሓቶች/ኢህአዴጎች ይህን ለማድረግ ፈቃደኛ ካልሆኑ የሕዝቡን አመጽ ማስፋፋት እና ይኼን ስኬታማ ለማድረግ በልዩ ልዩ ቦታዎች የሚካሄደውን ሕዝባዊ አመጽ ማገናኘት፤ ማቆራኘትና አቅጣጫ መስጠት ነው። እነዚህ አማራጮች ቀላል ናቸው የሚል ግምት የለኝም። ከባድ ናቸው። ፍትህ በቀላሉ ስኬታማ ስለማይሆን ብዙ እልቂትና ብዙ ጥፋት እንደሚኖር አስቀድሞ ማወቅና መተንብይ ይቻላል።

ዋናው ሰብሳቢ እሴት ዲሞክራሲ ብቻ አይደለም። አገር ከሌለ ዲሞክራሲ አይታሰብም። ዋናው መሰረት በኢትዮጵያ ግዛታዊ አንድነት፤ ዘላቂ ጥቅም፤ ሉዐላዊነትና በመላው ሕዝቧ እውነተኛ እኩልነት ላይ ምንም ድርድር አለማድረግ ነው። ይህን ለማድረግ ፍትህ አስፈላጊ መሆኑ የሚያከራክር አይደለም። የጎንደር ወጣት ትውልድ “የኦሮሞው ደም ደማችን ነው” ብሎ የኦሮሞው ወጣት ትውልድ በተመሳሳይ ያስተጋባውን አንርሳ። ስርዓቱን ያሸበረው ይህ ለጋራ አገር የጋራ ጩኸት ነው እላለሁ። አሁንም በተናጠል የሚደረጉ ጥረቶች የህወሓቶችን/ኢህአዴጎችን እድሜ እንደሚያራዝሙ መገንዘብ ወሳኝ ሆኗል።

2.መስፈርቱ ፍትህ ነው ስል ምን ማለቴ ነው?

በሕዝቡ፤ በተለይ በወጣቱ ትውልድ ጥያቄ መስፈርት ሲገመገም የሹም ሽሩ ውጤት ተመሳሳይ እንደሚሆን አስቀድሞ ለመተንበይ ይቻላል። ለዚህ ነው፤ የጠቅላይ ሚንስትሩን አዲስ ካቢኔት “የቀውስ ተከላካይ ካቢኔ” ብሎ ለመጥራት ይቻላል የምለው። ይህ ካቢኔ በየቀኑ ለሚገረፈው፤ ለሚታሰረው፤ ለሚሰወረውና ለሚገደለው የኦሮሞ፤ የዐማራ፤ የአፋር፤ የሲዳማ፤ የኦጋዴን፤ የጋምቤላ፤ የኦሞ ሸለቆ ወዘተ ወጣት ትውልድ ምን ትርጉም አለው? በእኔ ግምት ማህበረሰባዊ ጥቅምና ትርጉም የለውም። ይህ አገዛዝ ለራሱም ህልውና ቢሆን መጀመሪያ የኢትዮያን ሕዝብ ይቅርታ ቢጠይቅ “ብልሃተኛ አመራር” ያሰኘዋል። ይቅርታ ቢጠይቅና ጦርነቱን ቢያቆም ለእርቅና ለሰላም መንገድ ሊከፍት ይችላል። ይህን የምልበት ዋና ምክንያት አንድ ነው። ከሕዝብ ጋር የተጣላ አገዛዝ መጀመሪያ መታረቅና መስማማት ያለበት ከሕዝብ ጋር ነው። የሕዝቡ ጥላቻ ከግለሰቦች ጋር አይደለም፤ ከማንም ብሄር ጋር አይደለም። የኦሮሞው ሕዝብ ከትገራዩ ሕዝብ ጋር ጠላትነት የለውም። የዐማራው ሕዝብ የኦሮሞን ወይንም የትግራዩን ሕዝብ ወይንም የአፋሩን ሕዝብ ተጣልቶ ወደ ጦርነት አልሄደም። ጦርነቱን የሚያካሂደው ገዢው ፓርቲ ነው። ባለፉት አስራ አንድ ወራት፤ የማንም ብሄር በሌላው ላይ ጦርነት እና እልቂት አልፈጸመም፤ ወደፊትም አይፈጽምም። ቅራኔው በሰፊው የኢትዮጵያ ሕዝብና በጠባብ ብሄርተኛውና በምዝበራ በተበከለው፤ በቃኝን በማያውቀው፤ በንጹሃን ደም በተቀባው ህወሓትና አባሮቹ መካከል ነው። ይህ ቅራኔ በሹም ሽር ሊፈታ አይችልም። የተሾሙት ግለሰቦች መጠንቀቅ ያለባቸው ባልሰሩት ወንጀል እንዳይከሰሱ፤ የልጅ ልጆቻቸውን በአጥፊነት እንዳበከሉ ጭምር ነው። በአጼ ኃይለ ሥላሴና በደርግ ባለሥልጣናት ላይ የደረሰውን ማስታወስ ይጠቅማል።

ስለሆነም፤ ጠቅላይ ሚንስትሩና አባሮቻቸው መጀመሪያ መመለስ ያለባቸውን ጥያቄ አልመለሱትም። የአስተዳደር ጉድለትና ሙስና እንዳለ ከተናገሩ ቆይተዋል። የአሁኑ ሹም ሽር ከላይና ከስሩ በኪራይ ሰብሳቢነት፤ በሕዝብ ጭፍጨፋና ጭቆና የበሰበሰውን ስርዓት ምንም ሳይነካ፤ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አውጆ አሁንም ብዙ መቶ ወጣቶችን የሚጨፈጭፈውን፤ ብዙ ሽህዎቹን የሚያስረውን፤ ከራሱ ውጭ ለማሰብ የተሳነውን፤ ሕዝብ የጠላውን፤ በህወሓት የበላይነት የሚገዛውን ፓርቲ፤ ስርዐትና መንግሥት ለተከታታይ አመታት ለማጠናከር የተደረገ ሙከራ ነው። ሕዝቡ ይኼን የፖለቲካ ቁማር ደጋግሞ ስላየው የአሁኑንም ሹም ሽር “ጉልቻ ቢቀያየር ወጥ አያጣፍጥም እያለ” እያፌዘ በማለፍ ላይ ይታያል። በትእግሱቱ  የሚታወቀው የኢትዮጵያ ሕዝብ ካለፉት ሃያ አምስት ዓመታት ጭካኔ የተማረው ነገር ቢኖር ይህ ትእግስት ማክተም አለበት የሚል ነው። ልጅ ወይንም ዘመድ ወይንም ወዳጅ ያልሞተበት እና ያልታሰረበት ቤተሰብ ፈልጎ ለማግኘት አይቻልም። የህወሓቶችን ስድብ፤ ባለጌነት፤ ጠባብ ዘረኝነት፤ ቂመኝነት፤ ከፋፋይነት፤ አገር አጥፊነት፤ ጉረኛነት፤ ትእቢተኛነት፤ ዘራፊነት፤ ጨካኝነት ወዘተ ያልቀመሰ ኢትዮጵያዊ የለም። ስለሌም፤ ከአሁን በኋላ በትእግስት እንለፈው የሚል ኢትዮጵያዊ የሚኖር  አይመስለኝም። ሕዝቡ ብልህ ስለሆነ የሚታገልበትን ሁኔት መምረጡ በውጭ ለምንኖረው ከፍተኛ ትምህርት እየሰጠን ነው።

3.የህወሓቶች/ኢህአዴጎች የመጨረሻ ግብ (End Game) ምንድን ነው?

እየገደሉ ሰላም! እያፈኑ ሰላም! መሬትና ቤት እየነጠቁ የአገር እርጋታ! እየመዘበሩ እድገት! ጠብ ጫሪነትና ራስን አገልጋይነት ነው። የአሁኑ ሹም ሽር የመጨረሻ ግብ ምን ይሆን? ብየ ራሴን ስጠይቅ የማገኘው መልስ አንድ ብቻ ነው። የህወሓትን/ኢህአዴግን እድሜ ለማራዘም ነው። ግለሰቦቹ ምርጫ አላቸው፤ ስራውን አንፈልግም ሊሉ ይችላሉ። ሆኖም፤ የተሾሙት ግለሰቦች ጥፋት ነው አልልም። እነዚህ ግለሰቦች ቅንነት፤ ችሎታና ፈቃደኛነት ቢኖራቸውም እንዲያገለገሉ ቃል ኪዳን የገቡት የኢትዮጵያን ሕዝብ የፍትህ ፍላጎት ስኬታማ ለማድረግ አይደለም፤ ገዢውን ፓርቲና ስርዓቱን ለማገልገል ነው። በደርግም ጊዜ ተሹመው ያገለገሉትን የደርግን ስርዓት እንደነበረ ታሪክ ይመሰክራል። የአሁኑ አገዛዝ ከደርግም ሆነ ከሌላ አልተማረም።

ለምሳሌ፤ እነዚህ አዲስ ሹሞች አስቸኳዩን አዋጅ ለመሳብ አይችሉም። እነዚህ ግለሰቦች ግድያውና አፈናው እንዲቆም ለማድረግ አይችሉም። እነዚህ ግለሰቦች የስልጣን ድርድር ይደረግ ብለው ለመከራከር አይችሉም። እነዚህ ግለሰቦች የመጀመሪያው ስራችን ሕዝቡን ይቅርታ መጠየቅ ነው ሊሉ አይችሉም። አንድ ተመልካች እንደ ተናገረው፤ “ወያኔ የብሔረሰብ ደርጅት መሆኑ ብቻ ሳይሆን ላለፉት ሁለት ዐሥርት ዓመታት መላ ኢትዮጵያን ተቆጣጥሮ ይህ ነው የማይባል ሀብት ያጋበሰ፣ ግዙፍ የቢዝነስ ኢምፓየር የገነባ፣ የኢትዮጵያን የመከላካያና የጸጥታ ተቋማት ሙሉ በሙሉ በእጁ ያደረገ፣ ከወያኔ ጋር ተጠጋግቶ በአንድ ጀንበር ሀብት ያፈራና ወያኔን ለመጠበቅ የማያመነታ ከበርቴ ቡድን ከጎኑ ያሰለፈ ግፈኛ ቡድን በመሆኑ እንዲህ በቀላሉ ይንኮታኮታል ብለንም አናምንም፡፡ ይህ ጸረ ሕዝብ ቡድን የሀብቱና የምቾቱ ምንጭ የሆነውን ሥልጣኑን ለማስጠበቅ ሲል የማይፈነቅለው ድንጋይ እንደሌለ የተገደሉት፣ የተሰደዱትና በገፍ የታሰሩት ወገኖቻችን፣ እንዲሁም በቅርቡ ያወጣው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በቂ ማስረጃዎች ናቸው፡፡ ወደፊትም ቢሆን ሥልጣኑን ለማስጠበቅ ወገኖቻችን ይገድላል፣ ያስራል፣ ያሳድዳል፡፡” እነዚህ አዲስ ሹማምንት መስዋእት የሆነውን ትውልድ አናስታውስ፤ የምንሰራው አደጋውን ያባብሰዋል ለማለት አይችሉም። በፖለቲካ ስልጣን ያካበቱት ኃብት እንዲነካ አይፈልጉም። በአፋር፤ በጋምቤላ፤ በኦሮምያ፤ በዐማራና ሌሎች ክልሎች የነዋሪውን መሬትና ሌላ የተፈጥሮ ኃብት ነጥቀው ለራሳቸውና ለቤተሰቦቻቸው ጥቅም ማዋላቸው አላሳፈራቸውም። ስህተት ነው ብለው የተቀበሉበት ወቅት የለም። ጭፍን ጭካኔ አብሮ የሄደውና የሚሄደው ጭፍን ከሆነ ምዝበራ ጋር ነው እላለሁ።

በመሬት ላይ የሚካሄደው እልቂትና ትግል በምንም አይቆምም የምለው ለዚህ ነው። ምንም እንኳን የመገናኛ ብዙሃን ቢዘጋም ሕዝቡ የሚያገኘውን መረጃ ለማስተላለፍ የሚችልበት ዘዴዎች አልተቋረጡም። እያንዳንዱ ታጋይ ጋዜጠኛ ሆኗል ለማለት ይቻላል። እያንዳንዱ መንደር የጎበዝ አለቃዎችን እየፈጠረ ነው ለማለት ይቻላል። ይህ ታሪካዊ እምቢተኛነት በታንክና ብሄሊኮፕተር ማስፈራሪያ ሊቆም አይችልም። ይህን የማይቆም ሁኔታ አሃዞችን በመጠቀም ለመፈተሽ ይቻላል። አሁንም በገፍ መስዋእት የሚሆነው የሁለት ግዙፍ ብሄሮች አባላት ወጣት ትውልድ ነው። “A majority of the arrests were made from the Oromo and Amhara regions – the centre of demonstrations – which make up 60 percent of the country’s population.” ይህ ስፋት ያለው ሕዝባዊ እንቅስቃሴ ሌሎች ወዳጆችና አጋሮች እያፈራ ነው። ለምሳሌ፤ በኢትዮጵያዊነቱ የሚኮራው፤ ጀግናው የአፋር ሕዝብ ዝግጁነቱንና ቆራጥነቱን አብስሮናል። የአፋሩ መሪ ሃምፈሪ አሊ-ሚራ ለኢሳት በሰጡት ቃለ መጠይቅ፤ የአፋር ሕዝብ የሌሎቹን ታጋይና ቆራጥ ወንድሞች/እህቶቹን ፈለግ ተከትሎ የሕዝባዊ እንቅስቃሴው አጋር እንደሚሆን አስምረውበታል። በሲዳማም ተመሳሳይ እንቅስቃሴ እንደተጀመረ ሰምተናል። የኦሮሞውና የዐማራው ሕዝባዊ እንቅስቃሴ በምንም ሊቆም አይችልም የምለው ለዚህ ነው። ተራው ድሃ ወታደር፤ ተራው ድሃ የኢህአዴግ አባል፤ ተራው ዝቅተኛ ደሞዝ የሚያገኝ የመንግሥት ሰራተኛ ወዘተ ማድረግ ያለበት ከሕዝቡ ጎን መቆም ነው። ገዢው ፓርቲ አንድ መቶ አስራ ሁለት ሚሊየን ሕዝብ ሊጨፈጭፍ አይችልም፤ መግቢያና መውጫ ቀዳዳ አይኖረውም።

ህወሓቶች/ኢህአዴጎች ለአገሪቱ መሰረታዊ ችግሮች የሰጡት መልስ ሁኔታውን አባብሶታል እንጅ መውጫ ቀዳዳ ሊፈጥር አልቻለም። የገዢው ፓርቲ ቃል አቀባይ ከአስቸኳዩ አዋጁ በሗላ የሰብአዊ መብቶች ሁኔታ መባባሱን አምኗል። ቢያንስ እንዲህ ብሏል። “Some 11,607 individuals have so far been detained in six prisons, of which 347 are female, in connection with the state of emergency declared in the country,” official Taddesse Hordofa said in a televised statement on Saturday. በሌላ መድረክ የተሰማው ቁጥር ከዚህ ስድስት ጊዜ ከፍ ይላል፤ ከ60,000 በላይ የሚገመት የኦሮሞና የዐማራ ወጣት በልዩ ልዩ እስር ቤቶች ታጉሯል። ከዚህ ውጭ በማይታወቅበት መንገድ የሚገደለው፤ የሚታሰረውና የሚሰወረው ወጣት ቁጥር ብዙ ሺህ እንደሚገመት ይነገራል። ገዢው ፓርቲ ግፉን የሚያቆመው ስንት ወጣት ከገደለ፤ ስንት ወጣት ካሰረ፤ ስንት ወጣት እንዲሰወር ካደረገ በኋላ ይሆን? ብየ እራሴን ስጠይቅ፤ የማገኘው መልስ አሰቃቂ ነው። ካለፈው ታሪክ የምናገኘው መልስ ቁጥሩ ገደብ የለውም የሚል ነው። አንድ “መንግሥት ተብየ” ቡድን በራሱ ሕዝብ ላይ የሞት ፍርድ ሲፈርድ ህወሓት/ኢህአዴግ የመጀመሪያው ሳይሆን አይቀርም።

በአጭሩ፤ አዲሱ ሹም ሽር በገፍ የሚሞተውን፤ የሚታሰረውን፤ እንዲሰወር የሚደረገውን የወጣቱን ትውልድ እና በለቅሶ ላይ የሚገኙትን እናቶች፤ አባቶች፤ እህትና ወንድሞች፤ ወዳጆች አሰቃቂ ሁኔታ አይለውጠውም።

4.ሕዝቡ፤ በተለይ ወጣቱ ትውልድ ምን ጠይቆ ነበር? ምን መልስ ተሰጠው?

የተሰጠው መልስ “ገዢህን ፓርቲ ተቀበል” የሚል ጭፍንና ጨካኝ የሆነ መልስ ነው። ይህ መልስ የአስቸኳዩን አዋጅ የባሰ አፋኝና ገዳይ ያደርገዋል። የጠቅላይ ሚንስትር ኃይለማሪያም ቡድን አገሪቱን በበላይነት ለሚያሽከረክረው የህወሓቶች የስለላ፤ የአፈና፤ የአልሞ ተኳሽ፤ በጠቅላላ ለህወሓቶች የመከላከያ ኃይል የበለጠ ስልጣን ይሰጣል። ይህን ማየት ያለብን በውጭ ከምንኖረው ስደተኞችና ተቃዋሚዎች አንጻር፤ ከፈረንጆች ጥቅም አንጻር ሳይሆን ከወጣቱ ትውልድ ጥያቄና መስዋእትነት አንጻር ነው። ኢላማ ከሆነው ከዐማራው፤ ከኮንሶው፤ ከአፋሩ፤ ከኦሮሞውና ሌላው አንቅስቃሴ አንጻር ነው።

ለማጠቃለል፤ 1. ለአንድ ዓመት ሲካሄድ የቆየው የሕዝብ እምቢተኛነትና ያስከተለው ቀውስ ሊታይ የሚገባው ከኢትዮጵያ ዘላቂነት፤ ከነጻነት፤ ከፍትህ፤ ከሕግ የበላይነት፤ ከሰብአዊ መብቶች መከበር፤ ከእውነተኛ እኩልነት፤ የሕዝብን ምሬት ከማዳመጥ ወይንም ካለማዳመጥ፤ ከዲሞክራሳዊ ስርዓት ክፍተቶች እና ለእነዚህ ፍላጎቶች ጉድለት መንስኤ ከሆኑት ከማንነት፤ ከመሬት ነጠቃ፤ ከኪራይ ሰብሳቢነት፤ ከአስተዳደር ብልግና፤ ከስራ አጥነት፤ ከጥገኝነት ጥያቄዎች አንጻሮች ነው። መስዋእት የሆነው በብዙ ሽህ የሚገመት ወጣት ትውልድ እና የእንዚህ ሰማእታት ወላጆች፤ ዘመዶች የተመኙትና የፈለጉት ገዢው ፓርቲ ራሱን ገምግቦ “የማውቅልህ ብቸኛ ወዳጅህ እኔ ብቻ ነኝ፤ እኔ የሾምኳቸውን ግለሰቦች እንደ ገጸ በረከት ተቀበል” የሚል መልእክት ለመስማት አይደለም። ይኼማ ለሃያ አምስት ዓመታት ተሞክሮ አለሰራም። የሕዝብን ምሬት እና ንዴት ለማዳመጥ የማይፈልግ አገዛዝ የሚፈጥረው የባሰ መዘዝ ነው። ይኼን በበለጠ የሚያውቀው ወጣቱ ትውልድ መሆኑን መቀበል ግዴታችን ነው። በተናጠል የምናደርገው ጩኸት የሚያስጠቃውም ይህን ቆራት ትውልድ ለው።

  1. በኦሮምያ ሆነ በዐማራ፤ በጋምቤላ ሆነ በኮንሶ፤ በአፋር ሆነ በትግራይ፤ በኦሞ ሸለቆ ሆነ በአዋሽ ሸለቆ ወዘተርፈ ሕዝብ የሚፈልገው ብሶቱን የሚያዳምጠው፤ ለሕዝብ ተገዢና ታዛዢ የሆነ መንግሥት ነው። በሕዝብና ለሕዝብ የቆመ መንግሥት የፖሊሲና የመዋቅር ለውጦችን ሳያመናታ ያካሂዳል። ለውጥን አይፈራም። ለውጥን ስለማይፈራ ከሕዝብ የሚፈራው አንድም ነገር የለም። ህወሓቶች/ኢህአዴጎች ከማንም በላይ የሚፈሩት ሕዝብን ነው።
  2. የፖሊሲና የመዋቅር ተግዳሮቶች በሹም ሽር ሊፈቱ ይችሉ ቢሆን ኖሮ የአጼ ኃይለ ሥላሴና የደርግ መንግሥታት ይቆዩ ነበር። እንዲያውም፤ የእነዚህ መንግሥታት የባለሥልጣናት ስርጭት የኢትዮጵያን ሕዝብ ስርጭት ያንጸባርቅ ነበር። በነበረው የሰው ኃይል መጠን ሲመዘን እነዚህ መንግሥታት የብዙ የታወቁ ባለሞያዎች ተጠቃሚ ነበሩ። አሁን “ቴክኖክራት” የሚለው መስፈርት አዲስና ያልተመለደ የሚመስል ትሩግም ተሰጥቶታል። አንድ ግለሰብ ቴክኖክራትም ቢሆን አዛዡና የበላዩ ህወሓት እንደሚሆን የሚጠራጠር ኢትዮጵያዊ ያለ አይመስለኝም። አዲስ ቋንቋ ተጠቅሞ ሕዝብን ለማታለል የሚቻል አይመስለኝም። እነዚህ አዲስ የቴክኖክራት ሹማምንት፤ የበላይ ትእዛዝ አስፈጻሚ መሆናቸው ስለማይቀር ህወሓቶች/ኢህአዴጎች በሚፈጽሙት ወንጀል ተባባሪ እንደሚሆኑ መገንዘብ ይኖርባቸዋል። “እኔ ከደሙ ንጹህ ነኝ፤ ምክንያቱም ቴክኖክራት ስለሆንኩ” ሊሉ አይችሉም።
  3. አንዳንድ ተመልካቾች የአሁኑን የጠቅላይ ሚንስትር ኃይለማሪያም ደሳለኝን ካቢኔ ከበፊቶቹ ለየት የሚያደርገው ምንድን ነው? ይሉና የካቢኔው “ስርጭት ለኦሮሞው ሕዝብ ውክልና የቁጥር ብዛት የሚሰጥ መሆኑ ነው” የሚል መልስ ያቀርባሉ። እርግጥ፤ ዘጠኝ የኦሮሞ ብሄር አባላት አሉበት። ለምሳሌ፤ ህወሕት/ኢህአዴግ የውጭ ጉዳይ ሚንስትሩን ቦታ ለተባበሩት መንግሥታት የጤና ድርጅት ተወዳዳሪ የሆነውን የህወሓት ቀኝ እጅ “ዶር ቴዎድሮስ አድሃኖምን” በመተካት በማህል አገር ለተወለደው የትግራዩ ብሄር አባል ወርቅነህ ገበየሁ አበርክተውታል። የብሄር መለያ መስፈርት መሆን የለበትም የሚል መርህ ቢኖር ኖሮ ይህ ሹመት አያከራክርም። ኢትዮጵያ የምትፈልገው የችሎታ መስፈርት እንጅ የጎጥ፤ የብሄር፤ የኃይማኖት፤ የፓርቲ አባልነት መስፈርት አይደለም። ይኼ በችሎታ ብቻ ስራ የማግኘት መስፈርት ወደ ጎን የተተወው በደርግ ዘመን ነው። ከዚያ ወዲህ፤ በባሰ ሁኔታ፤ ሹመት በችሎታ ሳይሆን በብሄር፤ በፓርቲ ታማኝነት ሆኗል። ኃብትም የሚገኘው በችሎታ አይደለም። አፈ ጮሌው የትግራይ ብሄር አባሉና ለህወሓት ታማኝነት የነበረው ጌታቸው ረዳ፤ የመገናኛ ሚንስትር ሆኖ ያገለገለው ግለሰብ ተሰናብቶ በምትኩ የኦሮሞ ብሄር አባል የሆነው ዶር ነገሪ ሌንጮ ተሹሟል። ይህ ግለሰብ ችሎታ እንዳለው የሚከራከር የለም። ሆኖም፤ እነዚህ አዲስ ሹሞች በኦሮሞውና በዐማራው ሕዝብ ላይ በተካሄደው እልቂት “ከደሙ ንጹህ ናቸው ወይንስ አይደሉም” የሚለውን መሰረታዊ ጥያቄ ወደ ጎን ትተን ምን አዲስ ነገር ያመጣሉ፤ ራሳቸውን ለውጠው የህወሓትን/ኢህአዴግን የተሳሳተና ጸረ-ሕዝብ፤ ጸረ-ነጻነት፤ ጸረ-ፍትህ እና ጸረ-ዲሞክራሲ ፖሊሲ ለመለወጥ ድፍረትና አንደበት አላቸው ወይንስ የላቸውም? ብለን መጠየቅ ግዴታችን ነው። በእኔ ግምት አይችሉም። የተሾሙት ስርዓቱን እንዲለውጡ ሳይሆን የህወሓት/ኢህአዴግን እድሜ ለማራዘም፤ የገጠሙትን ችግሮች ተባብረው እንዲጠግኑ ነው። ስርዓቱ እንዲለወጥ ከጠየቁ ሌላ ሹም ሽር ይደረጋል።

የችሎታ መስፈርት እንዳለ ሆኖ፤ በብሄር ስርጭት ሲታይ የደርግን መንግሥት የሚበልጥ የለም፤ ስርጭቱ አላዳነውም። የደርግ አገዛዝ ከሁሉም በላይ ሁሉንም ብሄሮችና ኃይማኖቶች ያስተናግድ እንደ ነበር ታሪክ ይመሰክራል። ጀኔራል አማን አንዶምን ሹሞ ገድሏል። ጀኔራል ተፈሪ በንቲን ሹም ገድሏል ወዘተርፈ።  የኢትዮጵያ ሕዝብ ችግር ብሄር ወይንም ኃይማኖት አይደለም። ስርዓት ነው። በጣም መጠንቀቅ ያለብን የሌለ የኃይማኖት ልዩነት እያጋነን አገሪቱን ወደ ሌላ የባሰ አደጋ እንዳናሸጋግራት ነው። የኢትዮጵያ ችግር የጠባብ ብሄርተኛው የህወሓት ስርዓት ነው፤ የብሄርና የኃይማኖት ልዩነት አይደለም።

እኛስ ምን ማድረግ አለብን?

ከእኛ ብዙ ይጠበቃል፤

መጀመሪያ የፖለቲካ ድንቁርናን እናስወግድ፤ ለምሳሌ፤ እርስ በርስ አለመተማመንን፤ የብሄርና የኃይማኖት ልዩነቶችን ማጋነንን፤

የኢትዮጵያን ዘላቂነት፤ የመላው ሕዝቧን ነጻነትና እውነተኛ እኩልነት የምንፈልግ ግለሰቦችና ስብስቦች በተቀዳሚ ተግባር ማድረግ ያለብን የህወሓቶችን የከፋፋይ ተንኮሎች አለማስተጋባት ነው። ኦሮሞውን ከዐማራው፤ አፋሩንና ሌላውን ከትግሬው ወዘተርፈ ለማጋጨትና ለማጣላት ቀን ከሌት የሚሰራው ወያኔ ነው፤ ይህን ክፍፍል የሚያስተጋባ ግለሰብ ወይንም ቡድን ሁሉ ከወያኔ ሊለይ አይችልም። ወያኔዎች ከሚሰሩት የመከፋፈል ስራ በባሰ ደረጃ ይህን የከፋፍለህ ግዛው የፖለቲካ ባህልና ስራ በረቀቀ ደረጃ፤ ለምሳሌ በፌስ ቡክ፤ በዩቱብና ሌላ የምናካሂደው ራሳችን ነን። በምንም የማይለያይ ሕዝብ እንዲለያይ፤ እርስ በርሱ እንዲጠራጠር ካደረግን የምንደግፈው የህወሓት/ኢህአዴግን አፋኝና ጨቋኝ ስርዓት ዘላቂነት ነው። በብሄር ክፍፍል የተጠመደውን የህወሓት ወጥመድ ልንሰብረው የምንችለው ከብሄር እና ከኃይማኖት በላይ በኢትዮጵያዊነት እና በሁሉም ኢትዮጵያዊያን መብትና ክብር ዙሪያ ለመናገር፤ ለመመካከርና ለመናበብ ስንችል ነው። ማንኛውም ፍትህ የሚፈልግ ግለሰብና ቡድን ጎንደሬውና ኦሮሞው ደፍሮ የተናገረውን “የኦሮሞ ደም ደማችን ነው፤ የጎንደሬው ደም ደማችን ነው” የሚለውን መርህ ስናስተጋባ ነው፤

ፍትህን የምንፈልግ ሁሉ በሕዝብ ብሶት የምናደርገውን የፖለቲካ ወይንም የስልጣን ወይንም የኃይማኖት ንግድ ማቆም አለብን። የሕዝብ አንድነት አስፈላጊ መሆኑ አያከራክርም። ሆኖም፤ የሕዝብ አንድነት ስኬታማ ሊሆን የሚችለው ኢትዮጵያ የምትባል የጋራ አገር አለችን ለማለት ስንደፍር ነው። ሕዝብ በአየር ላይ አይኖርም፤ የሚኖረውና የሚታገለው በመሬት ላይ ነው። የኦሮሞው፤ የዐማራው፤ የአፋሩ፤ የጉራጌው፤ የወላይታው፤ የኦጋዴን ሶማሌው፤ የአኟኩ፤ የትግራዩ ወዘተ ሕዝብ በጋራ ታግሎና መስዋእት ሆኖ ያቆያትን አገር እናፍርስ የሚል ኢትዮጵያዊ ያለ አይመስለኝም። ከሌለ ሕዝባዊ ትግሉ ብሄራዊ (አገራዊ) እንጅ ጎጣዊ ሊሆን አይችልም። ጎጣዊ ነው ካልን አሸናፊ የሚሆነው ህወሓት ነው፤

ፍትህን የምንፈልግ ከሆነ በየቦታው፤ በየሜዳው የሚዛመተውን የፖለቲካ ሃሰት “ውሸት እንደሆነ መጋለጡ ላይቀር፤ እውነቱን ተናግሮ ከመሸበት ማደር” በሚለው ብሂል ለመለወጥ መድፈርና ማጋለጥ ይኖርብናል። ምክንያቱም፤ የማይለያየውን ሕዝብ የሚያለያዩ ክፍሎች ዘመቻ በማካሄድ ላይ ናቸው። ይህ ዘመቻ የውጭ መንግሥታትንም ይጨምራል፤

ፍትህ የምንፈልግ ከሆንን- አብዛኛዎቻችን እንፈልጋለን- እኛም ውጭ የምንኖረው መስዋእትነትን ማስተናገድ አለብን፤

ፍትህን የምንፈልግ ከሆነ፤ መተባበርን መርሆ ለማድረግ መቁረጥ አለብን፤ መጠላለፍን ማቆም አለብን፤ ፍትህን የምንፈልግ ከሆነ አሁንም በህወሓት/ኢህአዴግ መርሆዎችና አጀንዳ መመራትን ማቆም ይኖርብናል። የሕዝብ አጀንዳ ግልጽ ነው፤ ውጭ ያለነው ግን ግልጽ አይደለንም፤ ግልጽ እንሁን፤

6 ፍትህን የምንፈልግ ከሆነ ቅንጦትን ወደ ጎን ትተን ካለችን ቀንሰን ለሚታገሉት፤ በእስር ቤቶ ለታጎሩት፤ ልጆቻቸውን ላጡት ወዘተርፈ መለገስ አለብን። ከገቢያችን አስር በመቶ ለመስጠት የምንወስነው መቸ ነው?

ፍትህን የምንፈልግ ከሆነ ዐማራውና ኦሮሞው የሚያደርገውን የኢኮኖሚ እገባ ፈለግ ተከትለን እኛም እገባውን ማስፋፋት ይኖርብናል:: ሕዝብ እየተጨፈጨፈ፤ አሁንም አንድ እግራችን አዲስ አበባ ሌላው ውጭ በሆነ ሂደት የትም አንደርስም፤ የምንልከውን ገንዘብ በሰላሳ በመቶ ብንቀንስ ምን እንሆናለን?

ፍትህን የምንፈልግ ከሆነ እርጋታ አለመኖርን ለጊዜው መቀበል አለብን፤ በእርጋታ ስም ብዙ ወጣት ትውልድ እየተጨፈጨፈ መሆኑን መረዳት ያስፈልጋል፤ ይህን በያካባቢያችን ለፈረንጆች ማስረዳት ግዴታችን ነው፤

ፍትህን የምንፈልግ ከሆነ የተቃዋሚ ፓርቲዎች ለአንድ ብሄራዊ ዓላማ እንዲሰሩ ማስጨነቅ፤ መጎትጎት፤ መማለድ፤ ጫና ማድረግ አለብን። እኛ ስራችን ሳንሰራ አሜሪካኖችን፤ እንግሊዞችን፤ አውሮፓዊያንን ለመውቀስ አንችልም፤

ፍትህን የምንፈልግ ከሆነ ችግሮቻችንና ተስፋዎቻችን በግልጽ፤ ሕዝብ በሚገባው ቋንቋ መናገርና መጻፍ አለብን፤ ፍርሃትን ማስወገድ አለብን፤

ለምሳሌ፤ የሽግግር መንግሥት ያስፈልጋ ስንል ምን ማለታችን ነው? ማንን ያካትታል፤ በምን መስፈርት? ለስንት ጊዜ፤ ምን ለመስራት? ምን አይነት ተቋሞችን ያፈርሳል፤ ምን አይነቶችን ለሽግግሩ እንዲጠቅሙ ያደርጋል? ሽግግሩ ህወሓት/ኢህአዴግን ይጨምራል ወይንስ ያገላል? ካለፈው የቂም በቀል ታሪካችን ምን እንማራለን? ወዘተርፈ፤ እና

ፍትህን የምንፈልግ ከሆነ ፈረንጆችን ከመማጸናችን በፊት እርስ በርሳችን መታረቅና መስማማት አለብን። ኢትዮጵያን ከመፈራረ፤ ሕዝቧን ከእርስ በርስ እልቂት ለማዳን የምንችለው ራሳችን ነን፤ ፈረንጆች አይደሉም። ሆነውም አያውቁም።

ህብር ሬድዮን በህብር ሬዲዮ ድህረ ገጽ ወይም በቀጥታ በስልክ ለማዳመጥ 712 -432-8451 መደወል ብቻ በቂ ነው በእንግሊዝ ለምትኖሩ በ01405770140 በስልክ ማዳመጥ ይቻላል። ዘወትር በድህረ ገጻችን፣ ከ googel app store Hiber Radio ወደ ስልክዎ በመጫን ካልሆነም በዘሐበሻ እንዲሁም በተጠቀሱት ስልኮች ማዳመጥ ይቻላል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *