Hiber Radio: “እንኳን በሳይበር የሚደረግ ጥቃት ይቅርና የወያኔ ተገንጣይ መንግስት እስር ቤትም ከዓላማችን አላሰናከለንም” – ከዘ-ሐበሻ የተሰጠ መግለጫ፣በሀከር ጥቃቱ የተሳተፉ የወያኔ ተላላኪዎችን ለማጋለጥ ተጨማሪ የባለሙያዎች ምርመራ ቀጥሏል

የዘሐበሻ ሎጎና ድህረ ገጹ ሀክ በተደረገበት ወቅት የሚታየው

በዘ-ሐበሻ ድህረ ገጽ ላይ ወያኔ በተደጋጋሚ በተለያዩ ጊዚያት የሳይበር ጥቃት አድራሻቸውን በተለያየ ቦታ ባስመዘገቡ የኢንተርኔት ወንጀል ተባባሪዎቹ ተደጋጋሚ ጥረት ሲያደርግ ቆይቶ በትላንትናው ዕለት ለተወሰኑ ሰኣታት የዘሐበሻ ድህረ ገጽ ላይ የሳይበር ጥቃት ተፈጽሞ ድህረ ገጹን ሐክ አድርገው የነበረ ቢሆንም የዘሐበሻ የአይቲ ባለሙያዎች ጥቃቱን ከመቀልበስ አልፈው በጥቃቱ የተሳተፉትንም ራሳቸውን ለመሸፈን ከደበቁበት ለማውጣትና ለማጋለጥ ከዚያም አልፎ የሕግ የበላይት ምን እንደሆነ ለማሳየት እየሰሩ መሆኑን ከድህረ ገጹ አዘጋጆች መካከል ዋና አዘጋጁ ጋዜጠኛ ሔኖክ አለማየሁ በተጨማሪ ገለጸ።

ከዘሐበሻ የወጣውን መግለጫ መሰረት በማድረግ ጋዜጠኛ ሔኖክ አለማየሁን በስልክ አነገግረን በሰጠን ተጨማሪ ማብራሪያ በተደጋጋሚ በተለይ በተለያዩ ስሞችና አድራሻዎች የሚላኩ ቫይረሶችን የአንባቢአን መረጃ በማስመሰል አንዳንዴም ሚታወቁ ሰዎችን እና ድርጅቶችን ስም በመስረቅ ሲያደርጉ መቆየታቸውን ገልጾ ያንን እየተከታተሉ ለአንባቢአን መግለጹ አስፈላጊ አይደለም ብለን ቆይተናል ብላል። በትላንቱ ጥቃት ሙሉ ለሙሉ ዘሐበሳን ለማፈንና ለማዳፈን የተወጠነ ሴራ መሆኑን ጠቅሶ ይህን መሰሉን ጥቃት የበለጠ ለማምከን የሚቻለው የወያኔ ጥቃት አድራሾችን ማንነት ለማወቅና ለማጋለጥ በተለይም በዚህ አሜሪካን አገር የሚኖሩትን በአገሪቱ ሕግ ስርዓት አልበኝነት ምን ሕጋዊ ዋጋ እንደሚያስከፍል ማሳየት ያስፈልጋል ሲል ገልጾ ወደፊት ተጨማሪ ዝርዝር መረጃ ለአንባቢዎች እንሰጣለን ብሏል። ዘሐበሻ ድህረ ገጽ የተለመደ ወቅታዊ መረጃም የማቅረብ ስራዋን አጠናክራ ቀጥላለች ብሏል።ከዘሐበሻ ወጣውን መግለጫ ተያይዞ ቀርቧል።

“እንኳን በሳይበር የሚደረግ ጥቃት ይቅርና የወያኔ ተገንጣይ መንግስት እስር ቤትም ከዓላማችን አላሰናከለንም” – ከዘ-ሐበሻ የተሰጠ መግለጫዘ-ሐበሻ ድረገጽ ከተመሰረተች 9 ዓመት ሆኗታል:: ባለፉት 9 ዓመታት በኢትዮጵያ ወቅታዊ ሁኔታዎችን መረጃ ከሚያቀብሉ የመረጃ መረቦች መካከል አንዷ በመሆን በአማራጭነት ሚድያነት አገልግላለች:: በየዕለቱ ድክመቶቻችን በማረም ከዘመኑ ቴክኖሎጂ ጋር በመራመድ አሁንም ተመራጭና ተአማኒ ሚዲያ ለመሆን ተግተን እየሰራን ነው::

እንደሚታወቀው የዘ-ሐበሻ አዘጋጆች የሚዲያን ሥራ የጀመሩት እዚህ ስደት ላይ ከወጡ በኋላ አይደለም:: በሃገር ቤት በኢትዮጵያ ነጻው ፕሬስ ውስጥ መስዋዕትነት የከፈሉ፣ የታሰሩ፣ የተገረፉና ብዙ መስዋዕትነት በከፈሉ ጋዜጠኞች የምትዘጋጅ ድረገጽ ናት::

ዘ-ሐበሻ ድረገጽ በተለይ ዕድሜያቸው ከ18 – 45 ዓመት ክልል ውስጥ በብዛት የምትጎበኝ፣ ወቅታዊ መረጃዎችንም በፍጥነት የምታደርስ መሆኗ የሕወሓትን መንግስት ሁሌም እንዳስደነገጠች ነው:: ባለፉት 9 ዓመታት በተለይ በእነዚህ ዕድሜ ክልሎች ባሉ ወገኖች ድረገጻችን በመጎብኘቷና በአብዛኛው 75% የሚሆነው የዘ-ሐበሻ ድረገጽ ጎብኚም ከኢትዮጵያ መሆኑ ያበሳጨው የሕወሓቱ መንግስት በርካታ ብሮችን በማፍሰስ ዘ-ሐበሻ የምታስተላልፈውን ነጻና ያልተገደበ መረጃ ለማፈን ብዙ ጥረቶችን አድርጓል:: ዘ-ሐበሻ ድረገጽን በሶስተኛ ወገን እንዲሸጥለት ከመጠየቅ አንስቶ ኮምፒውተሮቻችንን ከማጥቃት እስከ አዘጋጆቹ ቤተሰብ ድረስ ሄዶ የሕወሓት መንግስት ያላደረገው ያልሞከረው ነገር የለም:: አዘጋጆቹን በአካልና በንብረቶቻቸው ላይ ለማጥቃትም ብዙ ተሞክሮም ነበር::

ባለፉት 9 ዓመታት የደረሰብን ፈተና እንዲህ በትንሹ ተጽፎ የሚያልቅ ብቻ አይደለም:: ዘ-ሐበሻ ድረገጽን ሃክ ለማድረግ ብዙ ወጪዎችን የሚያፈሰው የሕወሓት መንግስት ከድረገጻችን በተጨማሪ ወደ አንድ ሚሊዮን የሚጠጋ ተከታይ ያለውን የፌስቡክ ገጻችንን ሃክ እስከማድረግ ደርሶ እንደነበር የቅርብ ጊዜ ትዝታችን ነው:: የፌስቡክ ገጻችንን ሃክ አድርገው የነበሩ የሕወሓት ተላላኪዎችም በሕግ የሚገባቸውን እርምጃ አግኝተዋል::

ይህን በሕወሓት መንግስት የሚደርሰውን የሳይበር ጥቃት ለማምለጥ ዘ-ሐበሻና አዘጋጆቿ በየ6 ወሩ ኮምፒውተሮቻቸውን ይቀያይሩ ነበር:: ብዙ ገንዘብ በማውጣትም የሳይበር ዘገበኛዎችን (ሴክዩሪቶዎችን) በመጫንም ጥቃቱን ስንከላከል ቆይተናል:: በዚህም መሃከል ግን ዘወትር ነጻ ሚዲያዎችን ለማፈን የማይተኛው የሕወሕት መንግስት እንደገና በዛሬው ዕለት ራሳቸውን “ጋዛ ሃከርስ” ብለው የሚጠሩ ሃከሮችን በመቅጠር የዋና አዘጋጁን ኢሜይል ሃክ በማድረግ እንዲሁም ድረገጹን ሃክ አድርገው በመቆጣጠር ለተወሰነ ሰዓታት ሲያውኩን ውለዋል::

የሕወሓት መንግስት የአዘጋጆቹን ኢሜይል ሃክ ቢያደርግ የሚያገኘው ምንም ምስጢራዊ መረጃ አይኖርም:: ዘ-ሐበሻ መረጃን ለሕዝብ ከማድረስ ውጭ ሌላ ምንም ዓይነት ተልዕኮ የሌላት በመሆኑ ምናልባት ወያኔዎች ኢሜሎቻችንን ቢበረብሩ የሚያገኙት ዞሮ ዞሮ በድረገጻችን ላይ በይፋ ተጽፈው የሚያገኟቸውን ጽሁፎች ብቻ ናቸውና ለልፋታቸውና ላጠፉት ገንዘብ ኪሳራቸው አስደስቶናል:: ድረገጻችንን ግን ሃክ ባደረጉትና ጥቃት በፈጸሙበት ቁጥር ግፋ ቢል እኛን የሚያስወጣን ገንዘብና መረጃ ልናደርሰበት የምንችልበትን ውድ ጊዜ ብቻ ነው::

ስለሆነም የሕወሓት መንግስት አንድ ሊገነበዘበው የሚገባው ትልቅ ነገር አለ:: የዘ-ሐበሻ አዘጋጆች በሃገር ቤት የስርዓቱን ማሰቃያ እስር ቤቶችንና ጨለማ ክፍሎችን እነማዕከላዊን፣ ከርቸሌን፣ 3ኛ ፖሊስ ጣቢያንና ሌሎችንም በመቅመስ የቆሙለትን ዓላማ ያጠነከሩ እንጂ በደረሰባቸው እስር የተፍረከረኩ አይደሉም:: ዛሬም በሳይበር ሕወሓት በሚያደርስብን ጥቃት ከአቋማችን ምንም ፍንክች እንደማያደርገን፣ እንደውም በተጠቃን ቁጥር እንደምንጠነክር እንዲገነዘቡት ለመግለጽ እንወዳለን:: ለዚህም ነው በመግቢያችን ላይ “እንኳን በሳይበር የሚደረግ ጥቃት የወያኔ ተገንጣይ መንግስት እስር ቤትም ከዓላማችን አላሰናከለንም” ያልነው::

ዕውነት ያሸንፋል!

የዘ-ሐበሻ ኤዲቶሪያል ቦርድ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *