Hiber Radio: ለህሊና እስረኞች ጥብቅና በመቆሙ የተጠቃው ጠበቃ ተማም አባቡልጉ ዛሬም ይናገራል ( ልዩ ቃለ ምልልስ ከጅረት መጽሔት ጋር)

ጅረት መጽሔት የጥር 27 ቀን 2009 እትም የፊት ገጽ

ይህ ፁሑፍ በጥር 27ቀን 2009ዓ.ም በጅረት መጽሔት የወጣ ሲኾን ምንም ለውጥ ሳይደረግለት ለማኅበራዊ ሚዲያ ተጠቃሚዎች እንዲህ ተሰናድቷል

  • ኮማንድ ፖስቱ መጀመሪያ ህገወጥ ድርጅት ነው፡፡
  • አሁን የጊዜ ጉዳይ ነው እንጂ ህዝቡ የሀገሪቱ ባለቤት ይሆናል፡፡
  • የኢትዮጵያ ህዝብ ፍላጎትና የህወሃት አላማ አብረው አይሄዱም

 

የዛሬ የመጽሔት እንግዳችን ታዋቂው የህግ ባለሙያ ጠበቃ ተማም አባቡልጉ በአቃቢ ህግነት በ1987ዓ.ም ከአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ በመጀመሪያ ድግሪ በህግ ተመርቀዋል፡፡ ከተመረቁበት ጀምሮ እስከ 1992ዓ.ም ድረስ በአቃቢ ሕግ፣ በነገረ ፈጅነት፣ በህግ አማካሪነት ሠርተዋል፡፡ ከ1992ዓ.ም ጀምሮ ከ15 -16 ዓመት ያክል በዚሁ ሙያ ቆይተዋል፡፡ ከአንድ ዓመት በፊት “ህግ በመጣስ” በሚል በጥብቅና ሙያቸው እንዳይሰሩ ታግደዋል፡፡

ከእንግዳችን ጋር በዛሬው ውይይታችን በፍርድ ቤት ስለተወሰነባቸው ቀዳማይ እና ደኃራዊ እግድ፤ አሁን ስላሉበት ነባራዊ ሁኔታ፤ ስለአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ እንዲሁም አነጋጋሪ ስለሆነው ስለዶናልድ ትራንፕ መመረጥ እንዲሁም ስለተለያዩ ሀገራዊ ጉዳዮች ከጋዜጠኛ ሀብታሙ ምናለ ጋር ሰፋ ያለ ቆይታ አድርገዋል፡፡

ጥያቄ፡- የጥብቅና መብትህን በፍርድ ቤት በፊት ለአንድ ዓመት ከሰባት ወር ታግደሃል፡፡ አንባቢዎቻችንም እንዲያውቁት ምክንያቱን ብትገልጽልኝ

ጠበቃ ተማም፡- ዋናው ኬዙ ሁለት ክስ ነው፡፡ አንደኛው ክስ ባልና ሚስት መሃል ሽምግልና ተቀምጠህ ስታበቃ ‹‹ጠበቃ ሆነሃል የሚል ነው አንድ ዓመት ከሰባት ወር የተቀጣሁት ያለምንም ማስረጃ ነው፡፡ ሽምግልናው ላይ እንዳልነበርኩ አስመስክሪያለሁ ውክልናዬ ሽምግልና ላይ እስከ መገኘት ጭምር ነው የሚለው ጉዳዩን በሽምግልና መጨረስ ይላል፡፡ ከሳሼንና የከሳሼን አባትና አጎት ቃል ብቻ ሰምተው ነው የፈረዱብኝ፡፡ ሽምግልናው ላይ ብገኝ እንኳን ወንጀል አይደለም፤ የሚያስጠይቅ አይደለም፤ ውክልናዬ በሽምግልና እስከ መጨረስ፤ በሽምግልና ላይ መገኘት ይላል፡፡ ብገኝ እንኳን ጥፋት አልነበረም፡፡ የተቀጣሁት እኮ ዝቅተኛ ሆኖ አይደልም ‹‹ተማም አባቡልጉ ላለፉት 16 ዓመታት አንድም ክስ አልተከሰሰም›› ይላል፡፡ የእነ አቡበከርን፣ የእነ አብርሃ ደስታን ክስ ስይዝ ነው ክስ መምጣት የጀመረው ቀጥሎ ሌላ ክስ መጣ በውስጡ አራት፣ አምስት ክስ አለበት::

ጥያቄ፡- የማን ጠበቃ ሆነህ ነው? ክስ የተከሰስከው ምንስ አድርገሃል ተብለህ?

ጠበቃ ተማም፡- የእነሀብታሙ አያሌው የ4ቱ ፖለቲከኞች ጠበቃ ሁኜ በሄድኩበት ጊዜ ሁሉንም ነገር አሟልቼ ሰውዬው አብርሃ ደስታን ሊጠራልኝ ሄዶ ነው ‹‹ሻይ እንጠጣ›› ብለሃል ተብዬ ነው ክሱ ላይ ምስክር ሆኖ የቀረበው ሰውዬው ብቻ ነው ሌላ የቀረበ የለም፡፡ ሰውዬው ቀረበ ‹‹ብሎሃል?›› ‹‹አዎ ብሎኛል!›› ‹‹ምንድን ነው ከአንተ የሚፈልገው ተማም?››፤ ‹‹ከእኛ ምንም ፈልጎ አያውቅም፤ ሁሉን ነገር አሟልቶ ነው የሚመጣው፤ ውሉ አለው ልጠራለት ሄጃለሁ አለ፡፡›› ጉቦ አልተደረገም፤ ካልተደረገ ደግሞ ወንጀልም አይደለም፡፡ በሎሚ መጽሔት ላይ የሰጠኹት ቃል ደግሞ በኢትዮጵያ የፀረ- ሽብር ህግና የአሜሪካ የሽብር አዋጅ ላይ ያለውን ልዩነት ነው የገለጽኩት የእኛው ተስፋፍቶ የወጣ ነው፡፡ የእኛ Bill of Attender ነው፡፡ ኢትዮጵያውያንን ከሀገራቸው ነጥሎ የሚያስቀር መሆኑን ነው የህግ ትንታኔ የሰጠሁት፤ የፀረ ሽብር አዋጁ ህጋዊ አይደለም ህገ-መንግስቱን ይቃረናል፡፡ ብያለሁ እላለሁ አሁንም መቃወሚያዬን አቅርቤያለሁ ለምን መሰለህ መቃወሚያዬን አቅርቤያለሁ በእነ አቡበከር ላይ በእነ ሀብታሙ አያሌው ላይም አቅርቤዋለሁ በሌሎቹ ላይም አቀርበዋለሁ ለምን በየትኛውም ሀገር 48 አንቀጽ ያለው የሽብር አዋጅ የለም፡፡ ሀገር ማስተዳደደሪያ አይደልም እኮ ለልዩ ሁኔታ የሚወጣ ነው የፀረ ሽብር አዋጅ እኛ ጋር ግን እየተዳደርንበት ነው ሌላው ‹‹የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ህዝቡ እንዳይሰማ አድርገኻል›› ነው፡፡ ህዝቡ እንዳይሰማ ባደርግስ ኢቲቪ የእኛ ሀብት ነው የእኛ ሀብት ለሁሉም ግልጋሎት መዋል ሲገባው ኢህአዴግ ለብቻ ይዞ ይጠቀምበታል፡፡ በሀገራችን ወንጀል ነው ይሄ እራሱ ለሁሉም ነው የተቋቋመው ለግልህ ይዘህ ማድረግ የለብህም፡፡

ጥያቄ፡- ድጋሚ መቀጣትህን ታውቅ ነበር?

ጠበቃ ተማም፡- ቀድሜ ያወኩት ነገር የለም:: ታህሳስ 24 ቀን 2009 ዓ.ም ነበር እገዳዬ ስላለቀ ፍቃዴን አድሱልኝ ስል ሰዎቹ የሚያደርጉትን ግራ ተጋብተው ‹‹አቶ ተማም ተጨምሮብሃል›› አሉኝ እንግዲህ ፋይሌን መንግሥት አለ ብዬ ነው እነሱ ጋር ያስቀመጥኩት፤ ቤቴ ወስጄ አላስቀምጠውም፤ ማን ነው የጨመረብኝ መቼስ ተነገረኝ ስል ‹‹አይ ተጨምሮብሃል 6 ወር መንግሥት በከሰሰህ ክስ›› ተባልኩኝ 6 ወሬን ጨምሬ መጣሁ፡፡ ህገ- ወጥነቱ አንደኛ አልተለጠፈም፤ ሁለተኛ አልተነገረኝም፤ ሶስተኛ በህጉ መሰረት ከ6 ወር በኃላ አይወሰንም የሚል አለ፡፡ በእዚህ ጉዳይ ከእዚህኛው በፊት ነው መሃል ላይ እልባት ማግኘት የነበረበት ቀርቷል፤ ብለን ነው የነበረው እውነቱን ለመናገር ይግባኝ አላልኩበትም፣ አልልበትም፤ ለእኔ መነገር ግን ግዴታ አለበት፡፡ ‹‹ፍቃድ አድሱልኝ›› ስል ‹‹‹ተጨምሮብሃል›› የተባልኩት ከአመት በኃላ ይሄኛው ከተወሰነ በኃላ ነው የተወሰነውን እኔ አላውቅም፡፡

ጥያቄ፡- ይግባኝ ለመጠየቅ ጥረት አድርገሃል?

ጠበቃ ተማም፡- ቢነገረኝ ነው ይግባኝ የምጠይቀው በእዛኛው ይግባኝ አልጠየኩም ለምን እጠይቃለሁ፤ በየጊዜው የምንፅፈው ውሸት አይደለም ‹‹ፍርድ ቤት ነጻና ገለልተኛ አይደለም›› ህሊና ያለው ሰው የህግ ባለሙያ አይደለም፡፡ ያለማስረጃ ክስ የማይሆነውን ጉዳይ ክስ ነው ብሎ ተቀብሎ ሊፈርድ የመጨረሻ ውሳኔ ነው የተወሰነብኝ ‹‹የኢትዮጵያ ቴሌቪዥንን ህዝቡ እንዳያይ አድርጓል›› እንዴት ነው የዲስፒሊን ችግር የሚሆነው ወንጀል ከሆነ ወንጀል ይሆናል፡፡ በነገራችን ላይ ‹‹ከፖሊስ ጋር አይተባበርም›› ይላል፡፡ ከፖሊስ ጋር የመተባበር ግዴታ የለብኝም፤ ፖሊስ ደንበኞቼን እንዳይደበድባቸው ነው መከላከል ያለብኝ ይሄ ከፖሊስ ጋር አለመተባበር አይደለም ሌላው ከፖሊሱ ጋር ሻይ እንጠጣ ማለት ምንድን ነው ነውሩ ኢትዮጵያዊነት ነው::

ጥያቄ፡- በቀጣይነት ምን ልታደርግ አስበሃል? ብዙ አመት ነው የተቀጣኸው

ጠበቃ ተማም፡- ብዙ አመት ነው የተቀጣሁት እነ ኤልያስ እነ አናንያ ምን አጥፍተው ነው ምንም እኮ አላጠፉም! በመጀመሪያ እንደ እዚህ አይነት ነገሮችን ስለማውቅ እኔ እንደውም ለኢትዮጵያ ነው የምፀልየው ኢትዮጵያ ውስጥ የሚሰሩ ግፎች የመጨረሻችን የእንባ ሀገር እያደረጋት ነው ይሄን ሀገር ወደሌላ አደጋ ውስጥ አትውሰድብን ብለን ነው የምንፀልየው ሰው በግፍ የሚገደልበት ሀገር ነው ከ500 በላይ ወገኖቼ ተገለውብኛል፡፡ በአማራና በኦሮሚያ እነዚህ ሁሉ እኮ ወንድሞቻችን ናቸው በእሬቻ ሰዎች ተገለዋል ያን ያደረጉ ሰዎች አልተጠየቁም ፍትህ አላገኙም፡፡ እነዚህ ሁሉ ተፈፅመዋል እነዚህ ሁሉ ቤተሰብ አላቸው እኔ ቤተሰብ አለኝ የእኔ ቤተሰብ ይራባል እነዛ ግን ልጆቻቸውን ያጡ አሉ ስለዚህ የሁላችንም ፍትህ አንድ ላይ ይበየናል ብዬ ነው የምጠብቀው

ጥያቄ፡- ስለዚህ ወደ ቀጣይ ነገር አትሄድም?

ጠበቃ ተማም፡- ወደየት ትሄዳለህ ሀገሩ እኮ የእኛ አይደለም! ሀገሩ የአንተ፣ መንግሥቱ የአንተ ሲሆን፣ ሥርዓቱ የአንተ ሲሆን ደረጃውን ጠብቀህ ትሄዳለህ፡፡ አሁን ያለው ውሸትና የማስመሰል ሥራ ነው፡፡ ሆን ብለህ ኢትዮጵያውያንን ለሀገር የሚያስቡ ሰዎችን ከጨዋታ ውጪ የማድረግ፤ አቅም የማሳጣት ነው፡፡ የኢትዮጵያ ህዝብ ፍላጎትና የህወሃት አላማ አብረው አይሄዱም አሁን የህወሃት(ኢህአዴግ) ፍላጎት የኢትዮጵያንን ህዝብ ፍላጎት በመጋፋት ጭምር ነው ሊቀጥል የሚፈልገው ከኢትዮጵያ ህዝብ ጋር በመሆን የቆሙ ሰዎች በሙሉ የእዚህ ሥርዓት ጠላት ተደርገው ነው የሚወሰዱት በማሰር፣ በመግደል ፣ ገንዘብ፣ በማሳጣት፣ በማሳደድ ሀብታሙ አያሌው ላይ የሆነው ተመልከት የተናገረው ለህዝብ ነው፡፡ በመጀመሪያ ኢህአዴግ ነበር፤ አካሄዱ ትክክል እንዳልሆነ አወቀ፤ ከኢትዮጵያ ህዝብ ጎን እሰለፋለሁ ብሎ አቅጣጫውን ቀየረ፤ ጠላት ተደርጎ ተያዘ፡፡ የኢትዮጵያ ህዝብ ነጻ ሲወጣ አብረን ነፃ እንወጣለን፡፡ በሀገራችን ነው የምንኖረው በሀገራችን መሥራት መብት ማንም ይሰጠናል ማንም ይነፍገናል ብለን አናስብም፡፡ ሀገር ከልጆችህ፣ ከቤተሰብ በላይ ነው ይሄም ትልቅ ነገር ነው በእርግጥ ካልሰራህ ከፍተኛ የኢኮኖሚ ችግር ያጋጥመሃል ግን በእዚህ አይነት ውስጥ አልፈናል፡፡ አንደኛ ጊዜው አልፏል ሁለተኛ ይሄ ሆን ተብሎ የተደረገ ስለሆነ በህግ መሄድ እራስን ማታለል ነው የሚመስለኝ

ጥያቄ፡- የአንተ የግል ጉዳይ እዚህ ጋር እንቋጨውና ኮማንድ ፖስት ብለው አውጀዋል በሰለጠነው አለም አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ነው ይሄን እንዴት እናጣጥመው?

ጠበቃ ተማም፡- ኮማንድ ፖስቱ ማለት አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ማለት አይደለም!፤ ኮማንድ ፖስቱ ማለት የእዝ አካል ማለት ነው፡፡ ኮማንድ ፖስት ተብሎ አይቋቋም፣ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የመሬት መንቀጥቀጥ፣ የጎርፍ አደጋ፣ ሀገር ስትወረር ይታወጃል፡፡ ህዝብ መብት ሲጠይቅ ግን አይታወጅም፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ አማራና ኦሮሞ መብቴን ተነጠኩ ብለው ነው የጠየቀው፤ በእዛ ጊዜ የሚደረገው ምንድን ነው መልስ መስጠት ነው፡፡ ካልቻለ ደግሞ ሥልጣን መልቀቅ ነው እንጂ ኮማንድ ፖስቱ ማወጅ አይደለም፡፡

ጥያቄ፡- ኮማንድ ፖስቱ ሲታወጅና፤ ከታወጀ ጀምሮ እስካሁን ባለው ሁኔታ ምን ተገነዘብክ?

ጠበቃ ተማም፡- እጆቻቸውን ነው የፈቱት በነገራችን ላይ አስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ምንም ማለት አየደለም የሽብር አዋጁ የገነዘውን የህዝቡን መብት ኮማንድ ፖስቱ የሬሳ ሳጥን ውስጥ ከቶ ነው ሚስማር የመታበት ትንሽ የቀረችዋን መብት ነው የዘጓት በየትኛው የወንጀል መርህ መስማትን ወንጀል የሚያደርገው ህግ የለም የሰዎች አስተሳሰብ ነው እውነቱን ለመነጋገር ህግ ነው ብለህ ማመን በህግ መቀለድ ነው፡፡ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ህግ ነው አልለውም፡፡ ህግም ከህገ- መንግሥቱም አንጻር መሄድ አለበት፤ ሰዋዊም መሆን አለበት፤ ምክንያታዊ መሆን አለበት፤ ተገቢ አስተሳሰብ (logical) ሎጂካል መሆን አለበት፡፡ መስማት ለምንድን ነው ወንጀል ሊሆን የሚችለው መናገር ወንጀል ሊሆን ይችላል፤ ስም ማጥፋት ስላለበት ነው ኮማንድ ፖስቱ ስሰማ ምንም አልመሰለኝም ‹‹የኢትዮጵያ ህዝብ ከፍርሃት ቆፈን ወጥቷል›› ወደ ፍርሃት ቆፈን ለመመለስ ነው፡፡ የኢትዮጵያ ህዝብ ስነልቦናን በፍርሃት ለመመለስ የተጠቀሙት ቃል ነው ሌላ ምንም የለውም፡፡

ጥያቄ፡- ኮማንድ ፖስቱ ግን እንደ ህግ ባለሙያ ስታየው አስፈላጊ ነው?

ጠበቃ ተማም፡- ኮማንድ ፖስቱ መጀመሪያ ህገወጥ ድርጅት ነው፡፡ በእርግጠኝነት ኢ-ህገ መንግሥትታዊ ነው፡፡ በህገ መንግሥት አንቀጽ 93 ላይ ኮማንድ ፖስቱ ይታወጃል አይልም!፡፡ በሰላም፣ በጦርነት ጊዜ፣ ሀገሪቷን የማስተዳደር ሥልጣን የሚንስትሮች ምክር ቤት ነው ይላል፡፡ ህገ መንግሥቱ 93 ላይ ኮማንድ ፖስቱ ይቋቋማል አይልም፡፡ ይሄ ኮማንድ ፖስቱ ኦሮሚያ ውስጥ የኦሮሚያን መንግሥት አፍርሶ ሀገሪቷን ያስተዳድር ነበር እኮ ስለዚህ በህግ አልተቋቋመም፡፡ መጀመሪያ በህግ ሳይቋቋም ስልጣን ማስተላለፍ መፈንቅለ መንግሥት ነው፡፡ የተደረገው በህገ-መንግሥት የተቋቋመ መንግሥት ላይ በእነ ብአዴን፣ ደኢህዴን፣ ኦህዴድ ላይ መፈንቅለ መንግሥት አደርጎ የህወሃት የወታደራዊና የደህንነት ክንፉ ስልጣን የያዘበት ነው፡፡ በህገ መንግሥቱ የሌለ ህገ-ወጥ አካል ነው ህጋዊ ለመሆን እኮ ENABLing Law ይባላል፡፡ በህግ መቋቋሚያ አዋጅ መኖር አለበት:: የመቋቋሚያ አዋጅ ያቋቋመው ይሄ አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ነው፡፡ ስለዚህ ህገ- ወጥ ነው፡፡ የኢትዮጵያ ህገ መንግሥት አንቀጽ 9 ንዑስ 3 የሚለው ‹‹በሌላ መልኩ ስልጣን መያዝ አይቻልም››ይላል፡፡ ሀገሪቷን የሚመሩት የሚሾሙት እነሱ ናቸው ጠቅላይ ሚንስቴር ኃይለማርያም ደሳለኝ ያስጠይቃቸዋል፡፡ ለምን በህገ-መንግሥት የሌለ ቡድን ሽፋን ነው የሰጡት የኢህአዴግን ህገወጥነት የሚያሳይ ነው፡፡ ይሄን ያደረጉ ሰዎች ህገ- መንግሥን በመናድ ነው መከሰስ ያለባቸው ህገ መንግሥቱ ውስጥ የሌለ ቡድን ማቋቋም በኢትዮጵያ ህገ መንግሥት አይቻልም፡፡ አንድም ቦታ ፈልግ ኮማንድ ፖስት የሚባል የለም፡፡ በሰላም ጊዜ፣ በጦርነት፣በአደጋ ጊዜ በአስቸኳይ ጊዜ ሀገሪቱን የማስተዳደር ሥልጣን የሚንስትሮች ምክር ቤት ነው፡፡ ሚንስትሮች ምክር ቤት ተሰባስቦ እኔ ተገልብጫለሁ ከአሁን በኃላ ሌላ ቡድን ተቋቋሟል ሀገሪቱን ያሰተዳድራል ማለቱ ህገ-ወጥ ነው፡፡ ሀገሪቷ ውስጥ ሁለት መንግሥት የመኖር ሁኔታ ነው ያሳየን አንዱ ማስክ እየፈለገ ነው ዶክተሮችን፣ ፕሮፌሰሮችን መንግሥት አመጣ፡፡ ካባ ለማልበስ ነው የተሞከረው አንዱ ከአንዱ ጋር አልተቀናጀም አሁን እነዚህ የተሾሙት ለኮማንድ ፖስቱ ነው ማለት ነው፡፡ እንደ ደርግ ወታደራዊ አገዛዝ ነው ‹‹እከሌን እከሌን አስገብተናል እንደሚባለው›› አሁንም ‹‹እከሌን እከሌን አስገብተናል›› ለምሳሌ አቶ ወርቅነህ ገበየው ‹‹የኮማንድ ፖስቱ ውጭ ጉዳይ ኃላፊ ተብሎ ነበር መሾም የነበረበት ካልሆነ ሌላ መንግሥት ነው የኾነው ሁለት መንግሥት ነው ያለው ነው የሚባለው በነገራችን ላይ ለምንም ነገር ደንታ ያላቸው አይመስለኝም፡፡ ለህገ መንግስቱም ደንታ የላቸውም፡፡

ጥያቄ፡- ኮማንድ ፖስት ሲታወጅኦህዴድ፣ ብአዴን መጠንከር ወይም የመብት ጥያቄን ህወሃት ላይ ማስነሳታቸው ተከትሎ እነዚህን ለማብረድ ታስቦ ይሆናል?

ጠበቃ ተማም፡- ለእዚህ ነው እሱን መፈንቅለ መንግሥት ያደረገ ነው የምለው ‹‹ኮማንድ ፖስቱ የህወሃት ወታደራዊ ክንፍ ነው፡፡›› በእነሱ እጅ እሳት ለመያዝ የተቋቋመው ኢህአዴግ የሚለውን ካባ የለበሰው ጥምረት ውስጥ ጥያቄ ሲያቀርቡበት እንደ ለእኔ ያዙልኝ ብሎ ነበር የሰጣቸው እነ ኦሮሞን ያዙልኝ ብሎ ነበር የሰጣቸው ኃላ ህዝቡም አልቀበልም አለ እነዚህ ሰዎች የመብት ጥያቄ ማንሳት ጀመሩ እነዚህን አስወግዶ የሰጣቸውን ሀገር መልሶ የወሰደበት ነው ወታደራዊ ክንፉ ስለዚህ እንደዛ ልትል ትችላለህ እነዚህ የኦህዴድ የመብት ጥያቄ እንደ ድሮ አናገለግልም ባይነት የህዝብ ወገንተኝነት ማሳየት የፈጠረው ነው ሊባል ይችላል፡፡

ጥያቄ፡- ስለዚህ እነዚህ አጋሮቹ ወደ ህዝብ እየተቀላቀሉ ያሉበት ሁኔታ ነው ያለው ማለት እንችላለን?

ጠበቃ ተማም፡- እንዴ አዎ! በእዚህ እኮ ነው ህዝቡ 2 ለ 0 እየመራ ነው ያለው የምንለው ህዝቡ አሁን የመብት የጥያቄውን መልሰው ደብድበውት ህዝቡ ‹‹የመብት ጥያቄውን አላደረኩም! በቃ ስህተት ነው!›› ካለ ወደ መጀመሪያው ተመልሰው የሚቀጥሉ ከሆነ ህዝቡ ተሸነፈ ማለት ነው፡፡ ህወሃት በድብቅ ያደርግ የነበረውን ፊት ለፊት አውጥቶ በወታደራዊ ማድረጉ ለህዝቡ ድል ነው ብዬ ነው የማምነው

ጥያቄ፡- በተቃራኒው ተቃዋሚ ፓርቲዎች ደግሞ በመፈረካከስ ላይ ይገኛሉ፤ ምንስ ይጠበቃል?

ጠበቃ ተማም፡- በመጀመሪያ ደረጃ አንድ በመሆን ከኢህአዴግ ፊት ሊቆሙ ይገባል፡፡ ኢህአዴግን ‹‹አስቸኳይ ጊዜ አዋጅህን ሻር›› ማለት አለባቸው፡፡ ሳያማክራቸው ነው ያወጣው በሌላ ሀገር ተቃዋሚዎች ተነግሯቸው ነው የሚወጣው ፓርቲዎች በአንድነት ከህዝባቸው ጋር መቆም አለባቸው፡፡ ጥያቄዎቻቸውን በጋራ ማቅረብ አለባቸው፡፡ ኢህአዴግን ማጀቢያ መሆን የለባቸውም በህግ ስለመኖራቸው በኢህአዴግ ፍላጎት አለመሆኑን ማሳየት አለባቸው፡፡

ጥያቄ፡- ፓርቲዎች ምን ማድረግ አለባቸው?

ጠበቃ ተማም፡- በአንድ ላይ መሆን፤ ካልሆነም መፍረስ መድብለ ፓርቲ የለም ብለው የኢህአዴግን ጭንብል ማውለቅ አለባቸው፡፡ ተስማምተው መድብለ ፓርቲ እንዳቋቋሙት ሁሉ ተስማምተው ማፍረስ፤ ነጻና ገለልተኛ ፍርድ ቤት፣ምርጫ ቦርድ በሌለበት ፍትሓዊ ምርጫ የለም! ስለዚህ የኢህአዴግ ማስፈፀሚያ ላለመሆን መወሰን አለባቸው፡፡ ኢህአዴግን ለመለወጥ ማስገደድ ያስፈልጋል፡፡ ኢትዮጵያ አሁን የነጻነት መንገድ ላይ አይደለችም እንደውም በእዚህ አካሄድ ከ1000 ዓመት በኃላ እንኳን ወደ ዴሞክራሲ አንደርስም ምክንያቱም ከዴሞክራሲ ቀኝ ኃላ ዞረን በሌላአቅጣጫ እየሄድን ስላለን በእዚህ ቀጥ ብለን ብንሄድ ወደ ባሰ አምባገነንነት ነው የምንሄደው ወደ ባሰ አምባገነንነት በሂደት የምንደርስበት ነገር የለም ስለዚህ አጠቃላይ ለውጥ ነው የሚያስፈልገው

ጥያቄ፡- አዋጁ ለህዝቡም፣ ለመንግሥትም የሚሰጠው ጥቅም ምንድን ነው?

ጠበቃ ተማም፡- ለህዝቡ እኮ አይደለም የወጣው፡፡ ህዝቡ የሚያገኘው ጉዳት ብቻ ነው ህዝቡ መብቱንም አያገኝም፡፡ ከፍርሃቱ እየነቃ ነበር ወደ ፍርሃቱ ይመለሳል! ኢህአዴግ ህዝቡን አስፈራርቶ እንደ መጀመሪያው ይቀጥላል መልሱ ካልተመለሰለት የሚኖረው እንዴት ነው እንደ ፍልስጤምና እስራኤል በመሳሪያ ኃይል አንዱ አንዱን እያስገበረ መኖር የኢትዮጵያ ህዝብ ፍልስጤማዊ ሆኖ ኢህአዴግ እስራኤላዊ ሆኖ ተገዳጁ ሆኖ ነው TPLf (Eprdf) የህዝብ ተቀባይነት እንደሌለው አረጋግጧል፡፡ በመሳሪያ ኃይል ተጠቅሞ ህዝቡን አስከብሮ መኖር የፈለገበት ሁኔታ መኖሩ ነው የሚታየው

ጥያቄ፡- ኮማንድ ፖስቱ ከእዚህ በኃላ ምን አይነት ሄደቶች ይኖራሉ?

ጠበቃ ተማም፡- ጨዋታው ያለው በህወሃትና በኢትዮጵያ ህዝብ መካከል ነው፡፡ በኢትዮጵያ ህዝብ በአንድ በኩል እና የህወሃት ኢህአዴግ በአንድ በኩል ነው ትግሉ እየተደረገ ያለው አሁን ስታይ ኢህአዴግ የህዝብ ሚና ወገን የሆኑትን እነ ዶ/ር መራራን እና ወጣቶችን እያሰረ ነው መጨረሻ ላይ ማን ያሸንፋል ነው ህወሃት ያሸንፋል የኢትዮጵያ ህዝብ ያሸንፋል ነው አሁን ጨዋታውን የኢትዮጵያ ህዝብ እየመራ ነው፡፡ ከእዚህ በኃላ ደግሞ እንዳየነው ህዝቡ ተሸንፎ አያውቅም ያለምንም ጥርጥር ይሄ ጨዋታ በኢትዮጵያ ህዝብ አሸናፊነት እንደሚጠናቀቅ ባለሙሉ ተስፋ ነኝ!

ጥያቄ፡- አሁን ኮማንድ ፖስቱ ምናልባት ይቀጥላልም አይቀጥልም የሚል ነገር አለ

ጠበቃ ተማም፡- ይቀጥላሉ! እንጂ ለምንድን ነው የማይቀጥሉት ህዝቡን ፀጥ ረጭ አድርገው ነው ማኖር የሚፈልጉት፤ የእንግሊዝ የጸረ ሽብር አዋጅ ሲወጣ በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅነት ነው፡፡ የእኛ እስካሁን አለ 48 አንቀጽ አለው ይሄንንም ሰፋ ሰፋ አደርጎታል፡፡ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ 32 አንቀጽ አሉት ስለዚህ በ2012 የውሸት ምርጫ ድረስ ያስኬዱታል ማለት ነው፡፡ ስለዚህ ህዝቡን ፀጥ ማሰኘቱ ሰላም አስገኝቶለታል ብለው ስለሚያስቡ ነው፡፡

ጥያቄ፡- ታሰረው የሚወጡ ልጆች ሲወጡ ምን አይነት መንፈስ የሚኖራቸው ይመስልሃል

ጠበቃ ተማም፡- የንዴት፣ የቁጭት፣ በሀገርህ የመጠቃት፣ አቅምና ጠባቂ የማጣት፣ የመበደል ስሜት ነው የሚሰማቸው እንኳን እነሱ እኔም የቁጭት ስሜት ነው የሚሰማኝ ምክንያቱም አንድ ህዝብ የእራስህ መንግሥት በማጣት የተደራጀ ኃይል የጥቃት ሰለባ ስትሆን ቁጭት ነው የሚሰማህ ከእዚህ ውጪ ሊሆን አይችልም፡፡

ጥያቄ፡- የኮማንድ ፖስቱ ሥጋት የለብህም?

ጠበቃ ተማም፡- ‹‹ስጋት የለብኝም!›› ኮማንድ ፖስቱ እራሱ የሥጋት ውጤት ነው ህወሃት ሰግቶ ያደረገው የመጨረሻ መወራጫው ነው፡፡ ከህዝብ ጋር ባለው ትግል ህዝብን በቁጥጥር ስር ለማዋል ነው፡፡ እንደውም ልፋታችንን ቀንሰውታል፡፡ እነዚህ ሁሉ ሲደረጉ ነው የነበሩት በኢትዮጵያ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ከ1967ዓ.ም ጀምሮ አልተነሳም ኢህአዴግ ሲመጣ እሱኑኑ እኮ ነው የቀጠለው ሰው ያለአግባብ ይታሰራል፤ ከኮማንድ ፖስቱ በፊትም አይደለም እንዴ 500 ሰዎች ኦሮሚያ የተገደሉት በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ወቅት እንኳን በህገ-መንግሥቱ አንቀጽ 25 ላይ የእኩልነት መብት መንካት እና የጭካኔ አያያዝ ተከልክሏል፡፡ በእርግጠኝነት በኢትዮጵያ ውስጥ ከእዛ በፊት ጭካኔያዊ አያያዝ ነበር፡፡ በኃላም ቀጥሏል ስለዚህ እውነቱን ለመናገር መታሰር አይደለም መገደል አይደለም እኔ ከታሰርኩ ፣አንተ ታሰርክ ከበደ ታሰረ ምን ለውጥ አለው ይሄ እኮ የሚያሳይህ መጀመሪያ የኢትዮጵያ ህዝብ ቦክቶ ይኖር ነበር፡፡ እምቢ አለው መልሰህ ትፈራኛለህ አለው ግብግብ ላይ ነው ያሉት በቃ ህዝቡን አሳምኖ መግዛት አልቻሉም፡፡ ህዝቡን መብቱን ሊሰጡት አልቻሉም፡፡ ስለዚህ ፈርተህ ትኖራለህ ነው ያው ወታደሮቹን ሰው ላይ ማዝመት ነው በ1997ዓ.ም ዘምቷል፡፡ ስለዚህ እኔ ይሄ ሀገር የማን ነው? የሚል ጥያቄን ያወጣው እኛ ላይ የሚዘምተው ወታደር የማን ነው? ወታደር ድንበር ነው የሚጠብቀው እኛ ላይ የሚዘምት ወታደር የህዝብ ኃይል ይበልጣል የወታደር ኃይል እሱን የምናየው ነው የሚሆነው አንዱ አስተማሪያችን ታሪክ ነውና ከታሪክ እንደምናውቀው ህዝብ ተሸንፎ አያውቅም የኢትዮጵያ ህዝብ ደግሞ መርሳት የሌለብን ነገር በ1966ዓ.ም አብዮት አካባቢ ብዙዎች እንሚሉት አይደለም የኢትዮጵያ ህዝብ ፈሪ ህዝብ አይደለም ጀግና ህዝብ ነው፡፡

ጥያቄ፡- የኢትዮጵያስ ቀጣይ መጻኢ ምን ይመስላል?

ጠበቃ ተማም፡- ብሩህ ነገር ነው የሚታየኝ ለምንድን ነው የሚሆነው የኢትጵያ ህዝብ አሁን ፊት ለፊት ወጥቷል፡፡ ህዝቡ ማንነቱን፣ አንድነቱን፣ በጋራ ካልሆነ መብቱን እንደማያገኝ አውቋል፡፡ የጫላ መብት የገብረ እግዚአብሔር መብት ሳይከበር እንደማይከበር አውቋል፡፡ የመብትና የልዩ መብት ልዩነትን አውቋል፡፡ አምባገነኖች የእኔ ነህ ብለው የሚሰጡህ መብትና አንተ በዜግነትህ የምታገኘው መብት ልዩነቱን አውቋል፡፡ ስለዚህ ሚናውን ስለለየ የኢትዮጵያ ህዝብ ሀገሪቱ የውሸት ሳይሆን የእውነት የእሱ መሆኑን አውቋል፡፡ ሉዓላዊ የሥልጣን አካል ድሮ ከነገሥታቱ ሲወድቅ ህዝቡ መውሰድ ነበረበት ደርግ ወሰደበት፤ ከደርግ ኢህአዴግ ወሰደባቸው ስለዚህ ህዝቡ የሥልጣን ባለቤት አልሆነም የሀገሪቱ እድል በእራሱ መወሰን እንዳለበት ህዝቡ ገብቶታል፡፡ አሁን የጊዜ ጉዳይ ነው እንጂ ህዝቡ የሀገሪቱ ባለቤት ይሆናል፡፡ እና እኔ የሚታየኝ ብሩህ ተስፋ ነው ኢትዮጵያ የህግ የበላይነት የተከበረባት፤ የዜጎቿ መብት የተረጋገጠባት፤ ዴሞክራሲ የሰፈነባት፤ በኢኮኖሚ የበለፀገች፤ ህዝቦቿ ተከባብረው የሚኖሩባት ሀገር በቅርብ ቀን አንተ ትብስ፤ አንቺ ትብስ የሚባልባት ሀገር ለመሆን 11ኛው ሰዓት ላይ ነው ያለችው

ጥያቄ፡- ይሄን ማን ሊመራው ይችላል?

ጠበቃ ተማም፡- የኢትዮጵያ ህዝብ ራሱ

ጥያቄ፡- ካለመሪ?

ጠበቃ ተማም፡- የኢትዮጵያ ህዝብ ራሱ መሪ ያበጃል! እኔ የማምንበት አንድ ነገር አለ ኢትዮጵያ ጥሎ የማይጥላት የእራሷ አምላክ አላት እንደሚለው ዜመኛው በእርግጠኝነት የምናገረው የኢትዮጵያ ህዝብ በመውደቅ ላይ አይደለም እየመራ ነው ያለው አምባገነኖችን አስፈራርቶ ጭምብላቸውን ገላልጦ ፊት ለፊት እንዲወጡ ነው እያደረገ ያለው የኢትዮጵያ ህዝብ በድል እየመራ ነው፡፡

ጥያቄ፡- ጠ/ሚንስቴር ኃ/ ማርያም ደሳለኝ ኮማንድ ፖስት በመቋቋሙ ድል እንዳስመዘገቡ በአድናቆትም ነጮቹ እንደጨበጧቸው ነግረውናል

ጠበቃ ተማም፡- ብርታት በወታደራዊ አስተዳደር መምራት ከሆነ ወረራ ነው፡፡ የእነሱ ጳጳስ ማኪያቬሊ እራሱ ወታደርህን ደብቅ ነው የሚለው በህግ መግዛት አቅቶህ በወታደር መግዛት የትም ሀገር ጥንካሬ ሆኖ አያውቅም ፈረንጆቹ ህዝባችሁን ደፈጠጣችሁ በቁጥጥር ስር አደረጋችሁ ብለው ነው ጨበጡን ብለው ያወሩት በኢትዮጵያ አምባገነን መንግሥታት ታሪክ ውስጥ አምባገኖችም ነበሩ፡፡ እንደእዚህ አይነት አሳፋሪ ንግግር አዳምጬ አላውቅም መባልም የለበትም፡፡ አንድ ሰው ከግብፅ የመጣ ታሰሯል? በእዚህ ጉዳይ ማንም የታሰረ የለም ማነው የታሰረው? እነ ዳንኤል ሺበሺ፣ መራራ ጉዲና፣ ኦሮሞዎች ናቸው ተሰብስበው የታሰሩት፤ መንደር ሥራ ፈተው የሚውሉ ልጆች ናቸው የታሰሩት፡፡ መንግሥት ሥራ መስጠት ሲገባው ሥራም ሳይሰጥ ቆይቶ ነው ሰብስቦ እያሰረ ያለው፤ መብት የጠየቁትን አሸነፍን ፈረንጆች ጨበጡን ብለህ ታወራለህ? ያሳፍራል፡፡

ጥያቄ፡- እጃችንን ጨበጡ ያሉት ሀገራቸው ላይ በዴሞክራሲ ከፍ ብለው የሚታዩ ሀገራት ናቸው

ጠበቃ ተማም፡- ዴሞክራት ሀገራትማ እነሱን እንደ አሻንጉሊት አድርገው የሚጠቀሙባቸው ናቸው፡፡ ተመልክተህ እንደሆነ ስለውጭ ሰው ነው የሚያወራው እነ አሜሪካን ከሶማሌ ጋር ከተዋጋህላቸው ‹‹ምርጥ ነህ!›› ይሉሃል፡፡ ገንዘብ ይሰጡሃል ይደግፉሃል፡፡ እነሱም ይሄን ያውቃሉ አሁን እነትራንፕ መጥተዋል ትራንፕ የነቃ ሰው ነው፡፡ ሽብርተኞችን የሚፈጥሩት አምባገነኖች መሆኑን ተረድቷል፡፡ ከአሁን በኃላ ለሽብርተኞች ብሎ የሚሰጣቸው ገንዘብ አይኖርም፡፡ ሽብርተኞችን እየፈጠሩ ቢዝነስ እንደሚሰሩ አውቋል፡፡ ነጋዴም ስለሆነ ገንዘብ ላይሰጥ ይችላል፡፡

ጥያቄ፡- የትራንፕ መመረጥ ኢህአዴግን ያስደስተዋል? ያስከፋዋል?

ጠበቃ ተማም፡- የትራንፕ መመረጥ እኔን አስደስቶኛል፡፡ አሜሪካኖች ካስደሰታቸው መምረጣቸው ትክክል ነው፡፡ ትራንፕ የንግድ ሰው ስለሆነ የመጣበትም መንገድ ጠንካራ ስለሆነ ሰውዬውም ትልቅ ነገሮችን የሚረዱ ናቸው ብዬ ስለማስብ ኢህአዴግን ያስከፋዋል ብዬ ነው የማስበው፡፡ በቀላሉ የሚያታልሉት አይደለም፡፡ትራንፕ ብር አይሰጣቸውም የዲፕሎማሲያዊ ድጋፍ አይሰጣቸውም እጃቸውን አይጨብጥም፡፡ በእርግጥ እናንተ ምን አይነት ‹‹ጎበዝ ናችሁ! ህዝባችሁን ስለመታቸሁ!›› አይላቸውም ብር እሰጣችኃለሁ አይላቸውም፡፡ ስለዚህ ኢህአዴግን አያስደስተውም፡፡ እኛን ግን አስደስቶናል በእዚህ አጋጣሚ ትራንፕም አምባገነኖች የአሜሪካን መሪዎችን ሞኝ አድርገው እንደሚወስዱ ማወቅ ያለበት ይመስለኛል፡፡ ለአፍሪካና ለአረብ አምባገነኖች ዲፕሎማሲያዊ ድጋፍ እንደማይሰጥና የአሜሪካንን ህዝብ ገንዘብ ለአሜሪካኖች እንደሚያውል እጁንም ከእኛ ላይ እንደሚያነሳ በነገራችን ላይ እንደ እነ አብርሃም ሊንከን የባሪያዎችን ነፃነት በማምጣት ነው፡፡ የተደነቀው አሁን ደግሞ ባርነት ያለው አፍሪካ ውስጥ ነው፡፡ ትራንፕ የአፍሪካንን ህዝብ ከባርነት በማውጣት ክህዝቡ ጋር በመቆም ካልሆነ ደግሞ አምባገነኖችን ባለመርዳት እንደ እነ አብርሃም ሊንከን አሜሪካንን እንዳቋቋሙት ጆርጅ ዋሽንግተን ታሪክ ሊሰራ ይችላል ብዬ ነው የማስበው

ጥያቄ፡- ብታገኘው ምን ትለዋለህ?

ጠበቃ ተማም፡- ባገኘው ‹‹ታሪክ ሥራ እለዋለሁ!›› በፊትህ ያለው ታሪክ በአሜሪካ ውስጥ አይደለም ያለው አሜሪካን ትልቅ የሚያደርግ አንተንም እንደ ሌሎቹ ትልልቅ ሰዎች ትልቅ የሚያደርግ የአፍሪካንን አምባገነን ባለመርዳት የአፍሪካ ህዝብን ከመደገፍ የአፍሪካን ህዝብ ከእራሱ ገዢዎች ባርነት በመውጣት ስለሆነ ‹‹ታሪክ ሥራ እለዋለሁ!›› በእርግጠኝነት ደግሞ ትራንፕም ነገሮችን የሚረዳ ስለሚሆን ያን እንደሚያደርግ እርግጠኛ ነኝ!

ጥያቄ፡- ስለኢትዮጵያስ ምን ትለዋለህ?

ጠበቃ ተማም፡- እኛ አሁን ያለንበት ሁኔታ የአሜሪካን ጥቁሮች ከ1865 በፊት የነበረውን በነበረው ጊዜ እንደነበረው አይነት እንደሆነ እነግረዋለሁ፡፡ የኢትዮጵያ ህዝብ በሀገሩ መሪዎች ቅኝ እየተገዛ መሆኑን እነግረዋለሁ የኢትዮጵያ ህዝብ ደግሞ ተባብሮ በውጭ ኃይል ቅኝ ያልተገዙ ሆነው አሁን ግን በዘመናዊ ቅኝ አገዛዝ የተደራጁ ኃይሎች እየገዙት መሆኑን፤ የኢትዮጵያ ህዝብ ቅኝ ገዢዎችን አዋርዶ እንደመለሰ ሁሉ እነዚህንም አዋርዶ እንደሚመልስ በእዚህ ውስጥ የአሜሪካኖች ሚና ከህዝቡ ጋር መቆም ካልሆነ ከህዝቡ ጋር የዘላለም ቂም ማትረፍ እንደሆነ አነግረዋለሁ ስለዚህ መስመርህን አስተካክል እለዋለሁ ማለት ነው፡፡

ጥያቄ፡- ማስተላለፍ የምትፈልገው መልእክት?

ጠበቃ ተማም፡- ‹‹ዞሮ ዞሮ ግፍ መልስ አለው፤ ውጤት አለው፡፡ ነገሮች በተወጠሩ መጠን ነው ወጣሪውን የሚገፉት ስለዚህ ነገሩን እያከረሩ ያሉ አካላት ከእዚህ አቋማቸው ቢታቀቡና የኢትዮጵያን ህዝብ እንደሀገር፣ እንደህዝብ ይቅርና እንደሰው እንዲመለከቱት፤ የኢትዮጵያ ህዝብ ተዋርዶ አይቀርም! ከእዚህ ውርደት ይወጣል፤ የእዛን ጊዜ ደግሞ ሒሳብ መተሳሰብ ይኖራል፤ ያ እንዳይሆን እንዳይፈጠር አቅም አለን የሚሉ አካላት ህዝቡ ላይ የሚያደርጉትን በደል ለእራሳችሁ ብላችሁ ገታ አደርጉ፤ መሸነፋችሁ አይቀርም ትሸነፋላችሁ፤ ስትሸነፉም ደግሞ ያደረጋችሁትን በህግ ትጠየቃላችሁ፤ የህግ ባለሙያዎች መቼም ጠበቃ መሆናችን አይቀርም ስለዚህ ወንጀሎቻችሁን አታብዙ ነው የምለው

ጥያቄ፡- ስለሰጠኸን ቃለ መጠይቅ ከልብ አመሰግናለሁ

ጠበቃ ተማም፡- እኔም አመሰግናለሁ

Hiber radio Las Vegas ይህ ህብር ሬድዮ _የወቅታዊ መረጃ ምንጭ ነው። ህብር ሬድዮ በአቤኔዘር ኮሙኒኬሽን ሴንተር እየተዘጋጀ  ከላስ ቬጋስ ከተማ፣ ዘወትር ዕሁድ በአካባቢው ሰዓት አቆጣጠር ከምሽቱ 630 ሰዓት እስከ 8 ሰዓት በህብር ሬዲዮ ድህረ ገጽ ወይም በቀጥታ በስልክ ለማዳመጥ 5639993994 ወይም 563999-3988 ወይም 712-432-8451 በመረጡት ቁጥር መደወል ብቻ በቂ ነው በእንግሊዝ ለምትኖሩ 01405770140 በስልክ ማዳመጥ ይቻላል። ዘወትር በድህረ ገጻችን፣ googel app store Hiber Radio ወደ ስልክዎ በመጫን ካልሆነም በዘሐበሻ እንዲሁም በተጠቀሱት ስልኮች ማዳመጥ ይቻላል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *