ከአጼ ሀይለስላሴ ዘመነ መንግስት ጀምሮ ከመብራት ሀይል መሐንዲስነት ጀምሮ በአገር ውስጥና በውጭ በተለያዩ ሀላፊነቶች ያገለገሉት በሽግግሩ ዘመን በከተማ ልማትና ኰንስትራክሽን ሚኒስቴር ሚንስትር የነበሩትና የጎንደር ልማት ማህበር(ጎልማ) የቀድሞ ፕሬዝዳንት ኢ/ር አራጋው ጥሩነህ ካሳ ባደረባቸው ሕመም በሕክምና ሲረዱ ቆይተው በተወለዱ በ77 ዓመታቸው ከዚህ ዓለም በሞት ተለይተዋል። ስርዓተ ቀብራቸው በአዲስ አበባ በቅድስት ስላሴ ካቴድራል ሚያዚያ 26 ቀን 2009 ዓ.ም. ጳጳሱን ጨምሮ ብጹአን አበው ሊቃነ ጳጳሳት እና ወዳጅ ዘመዶቻቸው በተገኙበት ሚያዚያ 26 ቀን 2009ዓ.ም በታላቅ ስነ ስርዓት ተፈጽሟል።
የኢ/ር አራጋው ጥሩነህ ካሳን ሙሉ የሕይወት ታሪክ ተከትሎ ቀርቧል ።ለቤተሰቦቻቸው ለወዳጅ ዘመድ መጽናናትን እንመኛለን።ባልደረባችን ታምሩ ገዳ የኢ/ር አራጋውን የሕይወት ታሪክ እንደሚከተለው አቅርቦታል።
የክቡር ኢንጂነር አራጋው ጥሩነህ ካሳ አጭር የሕይወት ታሪክ
ክቡር ኢንጂኔር አራጋው ጥሩነህ ካሣ ከእናታቸው ከ ወ/ሮ አያልነሽ ውቤ እና ከአባታቸው ከግራአዝማች ጥሩነህ ካሣ በቀድሞው በበጌምድር አና ሰሜን ጠቅላይ ግዛት ተብሎ ይጠራ በነበረው በደንቢያ ወረዳ ልዩ ሥሙ ሰቀልት መቋሚያ ማርያም በተባለች ደብር በ 1932 ዓ.ም ተወለዱ፡፡
እድሜያቸው ለትምሕርት እንደደረሰ በጎንደር ከተማ በሚገኘው በቂርቆስ ቤተክርስትያን መንፈሳዊ ትምህርት ተከታትለዋል፡፡ ከዚያም በመቀጠል ዘመናዊ ት/ቤት ገብተው
1) በጎንደር ከተማ በፃድቁ ዩሐንስ ት/ቤት እና በቀዳማዊ አፄ ኃ/ስላሴ የአንደኛ ደረጃ ትምህርታቸው አጠናቀዋል
2) የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን አዲስ አበባ በሚገኘው የመዳኒዓለም ባለአባት ት/ቤት አጠናቀዋል
3) የከፍተኛ ትምህርታቸውን በተመለከተ
3.1 በቀዳማዊ ኃ/ሥላሴ ዩኒቨርስቲ በሲቭል ኢንጅነሪንግ (BSC) በድግሪ ተመርቀዋል
3.2 በግሪክ ሀገር አቴንስ ከተማ በዶክሲስ ኢኒስቲቲዩት በከተማ ልማት በማስትሬት ድግሪ ተመርቀዋል
3.3 አሜሪካ በሚገኘው በታዋቂው ዩንቨርስቲ ኦፍ ፔንስልቫንያ ዋርተን ስኩል ኦፍ ኢኮኖሚክስ በኢኮኖሜትሪክስ በማስትሬት ድግሪ ተመርቀዋል
- II) የስራ አገልግሎት ዘመንን በተመለከተ
ክቡር ኢንጂነር አራጋው ጥሩነህ በረዥም የስራ ዘመን አገልግሎታቸው በሀገር ውስጥ እና በዓለም አቀፍ ደረጃ ያከናወኗቸው ከዚህ ቀጥሎ ተመልክቷል፡፡
1) በቀዳማዊ ኃ/ሥላሴ ዘመነ መንግስት በኢትዮጵያ መብራት ኃይል ባለስልጣን በመሃንዲስነት ተቀጥረው ለ5 ዓመት አገልግለዋል በዚህ የስራ ዘመንም
1.1 በደንቢ ዶሎ ከተማ ከሜጢ ወንዝ የኤሌክትሪክ ኃይል እንዲመነጭ አድርገዋል
2 1.2 የአዳማ ከተማ የመጠጥ ውሃ ስራን በዋና መሃነድዲስነት ሰርተው አስመርቀዋል፡፡ በዚህ ስራቸዉ ታጭተው የአለማያን ዉሃ ስራ ከፈረንሳይ መሃንዲሶች ተረክበዉ ግርማዊ ጃንሆይ በተገኙበት አስመርቀዋል፡፡
1.3 በአዋሽ ወንዝ በ2ኛው ኤሌክትሪክ ማመንጫ ግድብ ሥራ ላይ ተሳትፈዋል፡፡
2) በደርግ ዘመነ መንግስት
2.1 በአውራ ጎዳና ባለስልጣን የፕላን እና ፕሮግራም ኃላፊ ሆነው የ 25 ዓመት ሴክተር ስትራቴጂ ቀይሰው ከልዩ ልዩ የፋይናንስ ድርጅቶች በቂ መዋዕለ ንዋይ አስገኝተዋል
2.2 የአዲስ አበባ ውኃና ፍሳሽ ባለስልጣን ዋና ሥራ አስኪያጅ ሆነው የ 25 ዓመት ሴክተር ስትራተጂ ቅይሰው ከአውሮፓ ማህበር በቂ መዋዕለ ንዋይ አስገኝተዋል በተጨማሪም በለገዳዲ የመጠጥ ውሃ ግድብ ግንባታ ምክንያት ኢትዮጵያ በ Paris chamber of commerce ፍ/ቤት ላይ የሥራ ተቋራጩ በመሠረተው ክስ ብር 100 ሚሊዮን የተፈረደባትን ብቃት ያላቸውን የህግ ባለሙያዎች በመመደብና አስፈላጊ ማስረጃዎችን በሟሟላት ይግባኝ እንዲጠየቅ በማድረግ ፣ ብልሀትና ስልት የተሞላበት አመራር በመስጠት እና ተገቢውን ክትትል በማድረግ ይግባኙ ውጤታማ ሆኖ ፍርዱ ተሰርዞ ሀገራችን ልታወጣ የነበረውን ከፍተኛ ወጪ አድነዋል፡፡
2.3 በኢትዮጵያ ውሃ ሀብት ልማት ኰሚሽን ኰሚሽነር ሆነው 5 የባለስልጣን መ/ቤቶችን እና የአርባ ምንጭ የውሃ ቴክኖሎጂ ኢንስቲቱዩትን በአካዳሚክ ሴንትነት መርተዋል በተጨማሪም የቦርከና ፣ የዝዋይ ፣ የዋቢ ሸበሌ ፣ የአልዌሮ ግድቦችንና መስኖዎችን አስገንብተዋል፡፡
2.4 ለጎንደር ከተማ የመጠጥ ውሃ ግድብ አስገንብተው የህብረተሰቡን የውሃ ችግር ለመፍታት ከፍተኛ ጥረት አድርገዋል፡፡
2.5 ክቡር ኢንጅነር አራጋው ጥሩነህ መንግስት ለከፍተኛ ሀላፊነት አገራቸውን እንዲያገለግሉ ጥሪ አድርጎላቸው ከውጪ ሀገር ተመልሰው የኢትዮጵያ ሕንፃ ኮንስትራክሽን ሚንስቴር ሚንስትር ሆነው ሀገራቸውን አገልግለዋል፡፡
3) በኢህአዴግ ዘመነ መንግስት በሽግግር መንግስቱ ወቅት በከተማ ልማትና ኰንስትራክሽን ሚኒስቴር ሚንስትር
3 ሆነው አገልግለዋል፡፡
4) በዓለም አቀፍ ደረጃ
4.1 በዋርተን ስኩል ኦፍ ኢኮኖሚክስ በትምሁርታቸዉ ባመጡት ከፍተኛ ዉጤት ተመርጠው በዓለም ባንክ ኢኰኖሚስትነት አገልግለዋል፡፡
4.2 የተባበሩት መንግሥታት በኣፍሪካ ኢኰኖሚ ኮምሽን ከግብፅ እስከ ሳውዝ ኣፍሪካ የሚዘረጋውን መንገድ በኃላፊነት መርተዋል
4.3 በተባበሩት መንግሥታት የልማት ፕሮግራም በከፍተኛ የቴክኒክ አማካሪነት በታንዛንያ ዳሬ ሰላም ሰርተዋል፡፡
ከዚህ ረዥም ዘመን አገልግሎት በኋላ በ 1985 ዓ.ም በጡረታ ተገለዋል ነገር ግን
በነበራቸው የሥራ ፍላጎት እና ህብረተሰባቸውን ለማገልገል በነበራቸው ቁርጠኝነት
መንግስታዊ ያለሆኑ የዕርዳታ ድርጅቶች በመምራት ደከመኝ ሰለቸኝ ሳይሉ
ሀገራቸውን አገልግለዋል፡፡
በዚህ ጊዜም
1/ የጎንደር ልማት ማህበርን (ጎልማ) በፕሬዝዳንትነት መርተዋል
2/ ለመላ የጎንደር ዙሪያ ወረዳ ህብረተሰብ የገጠር መጠጥ ውሃ እና ሳኒቴሽን
እንዲሁም የአነስተኛ ማሳ መስኖዎችን ገንብተዋል፡፡
3/ በኦሮሚያ ክልል ለሙኪየ ወረዳ ህብረተሰብ የገጠር መጠጥ ውሃ እና ሳኒቴሽን አገልግሎት ገንብተው ህብረተሰቡ እንዲጠቀም አድርገዋል
4/ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስትያን ልማት እና ክርስትያናዊ ተራድኦ
ኰሚሽነርሆነው አገልግለዋል፡፡
4 ክቡር ኢንጅነር አራጋው ጥሩነህ ባለ ትዳር እና የ5 ሴት ልጆች አባት ሲሆኑ 5 የልጅ
ልጆችንም አፍርተዋል፡፡
ክቡር ኢንጅነር አራጋው ጥሩነህ በማህበራዊ ኑሮዋቸው ሰው አክባሪ ከሰው ጋር
ተግባቢ ብልህ ያካበቱትን ዕውቀትና ልምዳቸውን በሙሉ ፍቃደኝነት ለትውልድ
ያካፈሉ ታላቅ ሰው ነበሩ
ክቡር ኢንጅነር አራጋው ጥሩነህ በአደረባቸው ህመም ምክንያት በህክምና ሲረዱ
ቆይተው በ 77 ዓመታቸው ከዚህ ዓለም በሞት ተለይተዋል ፡፡ የቀብራቸው ስነስርዓትም በመንበረ ፀባዖት ቅድስት ስላሴ ካቴድራል ጳጳሱን ጨምሮ ብጹአን አበው ሊቃነ ጳጳሳት እና ወዳጅ ዘመዶቻቸው በተገኙበት ሚያዚያ 26 ቀን 2009ዓ.ም ተፈፅሟል ፡፡
እግዚአብሔር አምላክ ነፍሳቸውን በገነት ያስቀምጥልን አሜን!!