በልዩ ልዩ አጋጣሚ የተለያየ ስምና ግብር ካላቸው ዕልፍ ሰዎች ጋር ተዋውቄያለሁ፤ በሕይወት መስተጋብር እንደሌላው ሰው ሁሉ፡፡
‹‹ዘመነ›› የሚባል ስም ያላቸው ሦስት የተለያዩ ሰዎችን አውቃለሁ፤ ሦስቱም ከተራራ የገዘፈ ታሪክና የታላቅ ስብዕና ባለቤቶች ናቸው፡፡ ከስሙ ይሁን ወይም አጋጣሚው የማውቃቸው ‹‹ዘመነዎች›› እንዲህ ናቸው፤ የእኔ ‹‹ዘመነዎች›› ዘመነ ካሤ፣ ዘመነ ምሕረትና ዘመነ ጌጤ ይባላሉ፡፡
የሕዝባቸው ብሶት ከማንም በላይ የገባቸው ናቸው፤ ከፊታቸው ከቀረበላቸው ሹመትና ሽልማት ይልቅ የዘመዶቻቸውን የመከራ ቀንበር መሸከም የመረጡ፣ የአንድ ትውልድ ፈርጦች! ስንት ሰው ነው ከፊቱ ያለውን ደስታና ፍስሃ ተጸይፎ ራሱን በመከራ ውስጥ ለሚገኝ የመንፈስ ደስታ የሚያጭ? እንዲህ ያለ ስብዕና መላበስ ዝም ብሎ አይገኝም፡፡ አርቆ ማሰብን፣ ማሰላሰልን፣ የሕዝብን ብሶት መስማትና ማዬት ከስጋዊ ጊዜያዊ ደስታ ይልቅ መንፈሳዊ ወኔን ይጠይቃል፤ ያኔ ነው ከፍ ወዳለ የላቀ ሰውነት የሚታደገው፡፡ ሦስቱም ዘመነዎች ይኼው ነው መገለጫቸው፤ በዚህ ሰዐት እነዚህ ዘመነዎች ለእኛ መኖር ራሳቸውን አደጋ ላይ የጣሉ ናቸው፡፡
ዘመነ ካሤ ከፊቱ በላይ በላዩ የሚመጣለትን ሹመትና ሽልማት እየተቀበለ ስጋውን በድሎት ሸፍኖ የውስጡን ጥያቄ እያፈነ ቢቆይ ኖሮ አሁን እንደመቀ መኮንን ከደረሱበት ቦታ ላይ መገኘት ለእርሱ ምንም አልነበረም፡፡ ግን ከግብዝነት ይልቅ ሰውነትን መረጠ፤ በናቡከደነፆር ቤት ከሚገኘው የቤተ መንግሥት እልፍኝ ድግስ ይልቅ ቆሎ መቆርጠም በቂ ነው አለ፤ የያዘውን ሹመት አየው- ተጸየፈው፡፡ የባሕር ዳር ያማሩ ዝምባባዎች፣ የጣና ሐይቅ ነፋስ፣ የሜጫ ማርና ወተት፣ የቆጋ መስኖ እሸት ዘመነን ወደ ኋላ እንዲመለስ አላደረጉትም፡፡ ሹምብጥ ያለው የተንጣለለ ቢሮው ኦና እንደሆነ በኅሊናው ተመለከተው፤ ኦና በሆነ ቢሮ ሊቀመጥ የሚችል ሰው የሆነ ሰው እንደማይኖር ሲገነዘብ ጊዜ አልፈጀበትም፡፡
ዘመነ ምሕረት በዩንቨርሲቲ ታሪክ አጥንቷል፤ በወያኔዎች ሹመት መጣለት- አስተማሪ ሆኖ ለተማሪዎቹ ታሪክን በተግባር ማስተማር እንዳለበት ወሰነ፡፡ ከታላላቅ ከተማዎች ይልቅ በበለሳና በደምቢያ ገጠራማ አካባቢዎች ተተኪዎችን ታሪክ አስተማረ፤ በቃል ሳይሆን በተግባር፡፡ ዘመነ ምሕረትን ታሪክ ምንድን ነው? ብሎ የሚጠይቅ ተማሪ የሚኖር አይመስለኝም፤ ለምን ቢባል ዘመነ ታሪክን እየሠራ ነውና የሚያሳያቸው፡፡ ከአቶ ማሙሸት አማረ ጋር በመሆን መኢአድን በመላው ኢትዮጵያ አቀጣጠሉት፡፡ በምርጫ 2007 ጊዜ ዘመነ እንዲህ አለ ‹‹ወያኔ ከሚባል ሌባ ኮሮጆ ጥበቃ አንቀመጥም፤ ለራሱ ሲል አያጭበርብር አሊያ ግን እንኳንስ እናቴ ሞታ እንዴውም አልቅስ አልቅስ ይለኛል›› ነው ያለው፡፡ ዘመነ ብዙ ጊዜ ሲናገር ሰምቼዋለሁ፤ ያኔ ያደረገው ታሪካዊ ንግግር ግን አፍ የሚያስከፍት ነበር፡፡ ዘመነ ተናግሮ ዝም የሚል ሰው አይደለም፤ ቃል መጠበቅና መታመን ከዘመነ በላይ ማን ይኖራል? አቤት ለዓላማ ያለው ጽናት! በዐማራነቱ ያልደረሰበት ችግር የለም፤ ግን አይበገርም፡፡ ከሕጻን ልጁ ፊት በመሣሪያ አፈሙዝ ተደብድቧል፤ በጉድጓድ ውስጥ ተጥሎ ዐይኑ ተሸፍኖ ሰካራም ትግሬዎች ተጸዳድተውበታል! እርሱ ግን በዚህ ሁሉ መካከል ሆኖ ስለሚበድሉት ሰዎች ከስብዕና በታች ስለመሆናቸው ያዝናል! ወደ ልዕለ ስብዕና መጠጋት እንዲህ ነው፡፡ ዘመነ የግድያ አዋጅ ወጥቶበት አገዛዙ በበለሳ፣ አርማጭሆ፣ ቋራና ወገራ ከአምስት ጊዜ በላይ እርሱን ለመግደል ጋንታ ጦር ልኳል፤ ከዚህ ሁሉ ግን በጀብደኝት አምልጧል፤ ብዙ በጣም ብዙ… አሁን ግን አደጋ ላይ ነው (በዝርዝር እመጣበታለሁ ሌላ ጊዜ)፡፡ ዘመነ ለዐማራ ሕዝብ የመከራ መስቀል መሸከም የማያደክመው ፍጥረት!
ዘመነ ጌጤም ከላይኞቹ ከሁለቱ ዘመነዎች የተለየ አይደለም፡፡ በተማረበት ትምህርት ተቀጥሮ መሥራት ወይም የወያኔ ሹመኛ መሆን ለእርሱ ምንም ናቸው፡፡ ጥሩ መሥሪያ ቤት መቀጠርም ሹመኛ መሆንም ሁሉም በየተራ ግብዣ መጥተውለት ነበር፤ ሁሉንም ናቃቸው፡፡ ለእርሱ ሕይወት የዐማራ ሕዝብ የገጠመውን ሰቆቃ አሽቀንጥሮ መጣል ነው፡፡ ለዚህም ከመኢአድ ጓዶች ጋር ተሰለፈ፡፡ አገዛዙ መኢአድን አፈረሰው፡፡ ዘመነ ለዐማራ ሕዝብ መብቱን እንዲያስከብር በሰላማዊ መንገድ ደከመኝ ሰለቸኝ ሳይል የወጣትነት እድሜውን ሰውቷል፡፡ ባለፈው የካቲት ወያኔዎች ጎንደር ላይ ከክንዱ ዱቤ ጋር አፍነው ወሰዷቸው – ትግሬዎች ወደ ማዕከላዊ፡፡ ይኼው ከየካቲት ጀምሮ በማዕከላዊ በስቅይት ላይ ነው- ዘመነ ጌጤ፡፡
እኔ የማውቃቸው ዘመነዎች እንደዚህ ያሉ ጀግኖች ናቸው፡፡ ነገሩ የስማቸው ትርጓሜ በራሱ የተሻለ እሳቤን የሚሻ ነው፤ ዘመነ- ሰለጠነ፣ መጠቀ፡፡ እነዚህ ጀግኖች የመጠቁት በቁሳዊ ሀብት አይደለም፤ በአስተሳሰብ ነው፡፡ ለሕዝብ መስዋት መሆን መዘመን ነው፡፡
የዐማራ ሕዝብ ትግል አሸናፊ ነው የምለው እንደነ ዘመነዎች ያሉ ጀግኖችን ስለማይ ነው፡፡
Hiber radio Las Vegas ይህ ህብር ሬድዮ _የወቅታዊ መረጃ ምንጭ ነው። ህብር ሬድዮ በአቤኔዘር ኮሙኒኬሽን ሴንተር እየተዘጋጀ ከላስ ቬጋስ ከተማ፣ ዘወትር ዕሁድ በአካባቢው ሰዓት አቆጣጠር ከምሽቱ 6፤30 ሰዓት እስከ 8 ሰዓት በህብር ሬዲዮ ድህረ ገጽ ወይም በቀጥታ በስልክ ለማዳመጥ 5639993994 ወይም 563999-3988 ወይም 712-432-8451 በመረጡት ቁጥር መደወል ብቻ በቂ ነው በእንግሊዝ ለምትኖሩ በ01405770140 በስልክ ማዳመጥ ይቻላል። ዘወትር በድህረ ገጻችን፣ ከ googel app store Hiber Radio ወደ ስልክዎ በመጫን ካልሆነም በዘሐበሻ እንዲሁም በተጠቀሱት ስልኮች ማዳመጥ ይቻላል።