Hiber Radio: የዋልድባ ገዳም መነኮሳት በ‹‹ሽብር ወንጀል›› ተከሰሱ

ከዋልድባ መነኮሳት በከፊል የሚያሳይ ፎቶ ከፋይል

ጋዜጠኛ ጌታቸው ሽፈራው የቀድሞው የሰማያዊ ፓርቲ ላሳን የነበረው የነገረ ኢትዮጵያ ዋና አዘጋጅ ሆኖ በሙያው እውነተኛ ዘገባዎችን ያቀርብ ነበር። በሙያው ሳቢያ ሀሳቡን በነጻነት በመግለጹ የአንድ ዓመት ከስድስት ወራት በላይ የግፍ እሰር አሳልፎ በቅርቡ ከእስር ቤት ወጥቷል። ዛሬም <<ደቦቃ>> ባለው የፌስ ቡክ ገጹ ላይ የፍርድ ቤት ዘገባዎችን እያቀረበ ሲሆን ወደፊትም ልዩ ልዩ ጦማሮችን የመጻፍና የማስተናገድ ሀሳብ እንዳለው ከገጹ መረዳት ይቻላል ። ከእስር ማግስት ግን እስረኛ ወገኖቹን ብቻ ሳይሆን የተነሳለትን ሙያዊ ግብ ወደ ጎን ሳያደርግ ዛሬም እውነትን ይዘግባል። በዚህ አጋጣሚ ጋዜጠኛ ጌታቸው ሽፈራውን እንኳን ከጠባቡ እስር ቤት ወደ ታላቁ እስር ቤት(ዞን 9) ተመለስክ፣ እንኳንም ድምጽህን ሰማን ለማለት እንወዳለን። ስለ ነጻነትና ነጻ ስለመሆን የሚታሰሩ ተመልሰው ወደዚያው ነጻነት ወንጀል ፣ሀሳብን በነጻ መግለጽ የሚያሳስር፣ የሚያስገድልበት አገር ላይ እየኖሩ ሁኔታዎች ሳይለወጡ በምን ሒሳብ ነው <<እንኳን ደስ ያለህ >>የሚባለው ? ለሁሉም የጋዜጠኛ ጌታቸው ሽፈራውን የፍርድ ቤት ዘገባ እነሆ፦

(በጌታቸው ሺፈራው)

ጎንደር ከተማ በነበረው ህዝባዊ ንቅናቄ ወቅት ተሳትፈዋል ተብለው መንግስት ይፈልጋቸው የነበሩ ግለሰቦችን መንግስት እንዳይዛቸው አግዘዋል የተባሉ ሁለት የዋልድባ ገዳም መነኮሳት በ‹‹ሽብር ወንጀል›› ተከሰዋል፡፡ የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ መድብ 4ኛ ወንጀል ችሎት ዛሬ ሰኔ 20/2009 ዓ.ም በዋለው ችሎት በእነ ተሻገር ወ/ሚካኤል ላቀው ክስ መዝገብ ስር የተከሰሱ 35 ግለሰቦች ክስ በንባብ ያሰማ ሲሆን ከተከሳሾቹ መካከል ሁለቱ፤ አባ ገ/እየሱስ ኪ/ማርያም ካሴ (4ኛ ተከሳሽ) እንዲሁም አባ ገ/ስላሴ ወ/ሀይማኖት (5ኛ ተከሳሽ) የዋልድባ ገዳም መነኮሳት ናቸው፡፡በክስ መዝገቡ ስር ያሉት ተከሳሾች 6 ክሶች የተመሰረተባቸው ሲሆን 1ኛ ክስ ከ1ኛ-5ኛ ተከሳሾች፣ 2ኛ ክስ ከ6ኛ ተከሳሾች -17ኛ እና 33ኛ ተከሳሽ ላይ፣ 3ኛ ክስ ከ18-20ኛ ተከሳሾች፣ 4ኛ 21ኛ እና 22ኛ ተከሳሾች፣ 5ኛ ክስ ከ23- 32ና 35ኛ ተከሳሾች፣ 6ኛ ክስ በ34ኛ ተከሳሽ ላይ ቀርቧል፡፡ ከቀረቡት ክሶች መካከል ከ5ኛ ክስ ውጭ ያሉት ክሶች በ1996 የወጣውን የወንጀለኛ መቅጫ ህግ አንቀፅ 32/1/(ሀ)(ለ) (38) እና በፀረ ሽብር አዋጁ ቁጥር 652/2001 አንቀፅ 4 ስር የተደነገገውን በመተላለፍ ከእነ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ፣ ዶ/ር ታደሰ ብሩ፣ አስማረ ብሩ፣ ግርማቸው (ቅዱስ)፣ ኢሳት ጋዜጠኞችና ሌሎች ግለሰቦች በመገናኘትና ገንዘብ በመቀበል በሰሜን ጎንደር ዞን በወገራ፣ በደንቢያ፣ በአርማጭሆ፣ ደቡብ ጎንደር፣ ባህር ዳር እና ቤንሻንጉል መተከል ዞን አካባቢዎች ለሚገኙ ታጣቂዎች መሳሪያ፣ ጥይትና  ቁሳቁስ  አቀብለዋል ሲል ክስ አቅርቦባቸዋል፡፡ ከዚህም በተጫማሪ ለታጣቂዎችና ውጭ ሀገር ይገኛሉ ለተባሉት የአርበኞች ግንቦት ሰባት አመራሮች ሲያቀብሉ ነበር በሚል በማሴር፣ በመደራጀትና ሽብር ለመፈፀም ሙከራ ክስ አቅርቧል፡፡

5ኛ ክስ በፀረ ሽብር አዋጁ ቁጥር 652/2001 አንቀፅ 7(1) ስር የተደነገገውን በመተላለፍ ገንዘብ በማስላክ፣ መሳሪያ በመግዛት፣ ቁሳቁስና መረጃዎችን ለታጣቂዎቹ በማድረስና ለአመራሮቹና ለታጣቂዎች መረጃ በማድረስ በማንኛውም የሽብር ወንጀል ተሳትፈዋል ሲል ክስ መስርቷል፡፡

6ኛ ክስ በ34ኛ ተከሳሽ ላይ የቀረበ ሲሆን በሰሜንና ደቡብ ጎንደር ዞን እንዲሁም ባህር ዳር አካባቢ ለሚገኙ ታጣቂዎች ስልጠና ሰጥቷል በሚል ተከሷል፡፡ 21ኛ  እና 22ኛ ተከሳሾች ቤንሻንጉል ክልል መተከል ውስጥ ሲንቀሳቀሱ ነበር ተብሎ ክስ የቀረበባቸው ሲሆን ቀሪዎቹ ተከሳሾች በሰሜን ጎንደር፣ ደቡብ ጎንደርና ባህር ዳር ከተማ በነበረው ህዝባዊ ንቅናቄ ተሳታፊ እንደነበሩ ክሱ ላይ ቀርቧል፡፡ ተከሳሾቹ ከአሁን ቀደም ሌላ ክስ ከቀረበባቸው ንግስት ይርጋ እና አታላይ ዛፌ እንዲሁም አርማጭሆና ወልቃይት አካበቢ የነበሩ ታጣቂዎችን ይመበራ ነበር ከተባለው ጎቤ መልኬ ጋርም ግንኙነት ነበራቸው የሚል የክስ ዝርዝር ቀርቦባቸዋል፡፡ በዚህ የክስ መዝገብ ስር የተጠቀሱት ግለሰቦች፡-

1ኛ. ተሻገር ወ/ሚካኤል ላቀው

2ኛ. ነጋ ዘላለም መንግስቴ

3ኛ. ተስፋሁን ማንዴ ሰላምሰው

4ኛ. አባ ገ/እየሱስ ኪ/ማርያም ካሴ

5ኛ. አባ ገ/ስላሴ ወ/ሀይማኖት

6ኛ. ሰኢድ ኑርሁሴን ኑርሰይድ

7ኛ. በለጠ አዱኛ መንግስቱ

8ኛ. ተስፋሚካኤል  አበበ ላቀው

9ኛ. እንዳለው ፍቃዴ አበበ

10ኛ. ስለሽ ግርማይ ነጋሽ

11ኛ. ይታይ ክብረት አታላይ

12ኛ. አዛናው ሲሳይ ገዛኸኝ

13ኛ. ዮሃንስ አየሁ ዘለቀ

14ኛ. አለማየሁ መኳንንት ካሴ

15ኛ. አሸናፊ ዮሃንስ ዘሪሁን

16ኛ. እዮኤል  በሪሁን ይማም

17ኛ. ዓለምሰገድ ዋኛው በሪሁን

18ኛ. አበበ አበጀ ሽመልስ

19ኛ. መንግስቴ ተስፋሁን አረጋ

20ኛ. ሰለሞን ፀኃይ እንግዳ

21ኛ. አዝመራው ተሰማ አዕምሮ

22ኛ. ነበቡሽ ደሳለኝ መንግስቴ

23ኛ. ታደሰ ይግዛው ገብሬ

24ኛ. ቢራራ ልጃዓለም አብርሃም

25ኛ. አብርሃም ድረስ አለሙ

26ኛ. አማረ ገ/ሚካኤል ገ/ስላሴ

27ኛ. ሲሳይ ተስፋ ደሴ

28ኛ. አራጋው እንዳለ አሰፋ

29ኛ. ፍቅሬ ግርማይ ምትኩ

30ኛ. ደጀኔ ደምሴ ወርቅነህ

31ኛ. ሙላቱ ፍስሃ ገብሩ

32ኛ. ማርሸት አሰፋ ባዬ

33ኛ. ክንድሽህ ሀጎስ ታዬ

34ኛ. መንግስቴ አማረ ያዜ

35ኛ. ተስፋሁን ሙሌ መኮንን፣ ሲሆኑ የክስ መቃወሚያ ለማቅረብ ለሀምሌ 11/2009 ዓ.ም ተቀጥረዋል፡፡

Hiber radio Las Vegas ይህ ህብር ሬድዮ _የወቅታዊ መረጃ ምንጭ ነው። ህብር ሬድዮ በአቤኔዘር ኮሙኒኬሽን ሴንተር እየተዘጋጀ  ከላስ ቬጋስ ከተማ፣ ዘወትር ዕሁድ በአካባቢው ሰዓት አቆጣጠር ከምሽቱ 630 ሰዓት እስከ 8 ሰዓት በህብር ሬዲዮ ድህረ ገጽ ወይም በቀጥታ በስልክ ለማዳመጥ 5639993994 ወይም 563999-3988 ወይም 712-432-8451 በመረጡት ቁጥር መደወል ብቻ በቂ ነው በእንግሊዝ ለምትኖሩ 01405770140 በስልክ ማዳመጥ ይቻላል። ዘወትር በድህረ ገጻችን፣ googel app store Hiber Radio ወደ ስልክዎ በመጫን ካልሆነም በዘሐበሻ እንዲሁም በተጠቀሱት ስልኮች ማዳመጥ ይቻላል።

 

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *