ታዋቂው ድምጻዊ ቴዲ አፍሮ በባህር ዳር ስታዲየም ከአቦጊዳ ባንድ ጋር ኮንሰርቱን ጥር 12 ቀን 20110 ዓ.ም. ለማቅረብ ፈቃድ ማግኘቱን ገልጾ በውሳኔው መደሰቱን ይፋ አደረገ። የፈቃድ ሁኔታውንም አስመልክቶ እንደጠቀሰው የአማራ ክልላዊ መንግስት፣ለባሕር ዳር ከተማ አስተዳደር ጽ/ቤትና ጉዳዩ ለሚመለከታቸው አካላት ለቀረበላቸው የፈቃድ ጥያቄ ያለ አንዳች ማጉላላት መፍቀዳቸውንና ለዝግጅት ወደ ውቧ የቱሪስት ከተማ ባህር ዳር ከመላው የአገሪቱ ክፍል የሙዚቃ አፍቃሪዎች እና ቱሪስቶች ለማቅረብ ማቀዱን ገልጿል።
የአማራ ክልል የሕዝብ ግንኙነት ሀላፊ አቶ ንጉሱ ጥላሁን በበኩሉ እውቁ አርቲስት ቴዎድሮስ ካሳሁን ጥር 12 ቀን 2010 ዓ.ም. በክልሉ መዲና ባህር ዳር <<ኢትዮጵያ ወደ ፍቅር >> በሚል ርዕስ ኮንሰርቱን እንደሚያቀርብና ኮንሰርቱም ስለ ሰላም፣ስለ ፍቅር፣ስለ አንድነት፣ስለ አብሮነት እና ስለ ኢትዮጵያዊነት የሚቀነቀንበት ሞሆኑን ጠቅሰው የክልሉ መንግስትና የባህር ዳር ከተማ አስተዳደር የአርቲስቱን ጥአቄ በታላቅ አክብሮት ተቀብለውታል ብለዋል።
ድምጻዊ ቴዎድሮሰወ ካሳሁን ኢትዮጵአ የተሰኘውን አልበሙ ከማውጣቱ በፊትም ሆነ በሁዋላ በአገር ቤት ለበዓል ዋዜማ በአዲስ አበባ በሚሊኒየም አዳራሽ ሊያቀርብ የነበረው የሙዚቃ ኮንሰርት በተደጋጋሚ መከልከልን ተከትሎ በአገሩ ቤት በተለያዩ ከተሞች አስከትሎ ሊያቀርብ የነበረው ኮንሰርት ሳይካሄድ የቀረ ሲሆን ሌላው ቀርቶ ማር እስከ ጧፍ የተሰኘውና በፍቅር እስከ መቃብር ላይ መሰረት አድርጎ ለሰራው ዜማ ኪሊፕና የአልበሙ ምርቃት በአዲስ አበባ ሒልተን ሆቴል በግል ወጪው የጠራው ዝግጅት መከልከሉ ላይ ቅሬታውን መግለጹ ይታወሳል።
በቅርቡ በአማራ ክልል ም/ር ቤት የክልሉ መገናና ብዙሃን የስራ ሪፖርት በቀረበበት ወቅት አቶ መርሐጽድቅ የተባሉ የም/ቤት አባል የቴዲ አፍሮ ዜማዎች መታገድ በሕገ መንግስቱ የተከለከለውን ቅድመ ምርመራ (ሳንሱር) ተግባራዊ የሚያደርግ ነው ሲሉ ተቃውሞ ማቅረባቸውን ጠቅሰን መዘገባችን ይታወሳል።
የድምጻዊ ቴዲ አፍሮ የባህር ዳሩን ኮንሰርት አስመልክቶ ያወጣው መግለጫና የአማራ ክልል በበኩሉ ስለ ኮንሰርቱ ያወጣው ተያይዞ ቀርቧል። የድምጻዊ ቴዲ አፍሮ መልዕክት
ኢትዮጵያ ወደ ፍቅር “የመጀመሪያው ኮንሰርት በባሕር ዳር
ቅዳሜ ጥር 12 ቀን በአማራ ክልላዊ መንግሥት ዋና ከተማ በሆነችው በውቧ ባሕር ዳር ከተማ ከ80 ሺሕ ሕዝብ በላይ ማስተናገድ በሚችለው በታላቁ ብሄራዊ ስታዲየም ከአቡጊዳ ባንድ ጋር የሙዚቃ ዝግጅቴን እንዳቀርብ ለአማራ ክልላዊ መንግስት፣ ለባሕር ዳር ከተማ አስተዳደር ጽ/ቤትና ጉዳዩ ለሚመለከታቸው አካላት ጥያቄያችንን አቅርበን የነበረ ሲሆን ፤ ጥያቄያችንን የተመለከቱት ሁሉም አካላት ያለ አንዳች ቢሮክራሲና እንግልት በጠየቅነው ቦታና ዕለት የሙዚቃ ድግሳችንን ለቱሪስት መስህቧ ባሕር ዳር ከተማና አካባቢዋ ነዋሪዎች፣ ከመላው የአገራችን ክፍል ለሚመጡት የሙዚቃ አፍቃሪዎችና አለም አቀፍ ቱሪስቶች ማቅረብ እንድንችል የፈቀዱልን በመሆኑ ታላቅ ደስታ ተሰምቶናል።
እኔም ወደ ሙዚቃው አለም ከገባሁበት በተለይም የመጀመሪዬ አልበሜ ከሆነችው አቡጊዳ ጀምሮ በቅርብ እስካሳተምኩት 5ኛው አለበሜ “ኢትዮጵያ” ድረስ ከፍተኛ ፍቅር የለገሰኝን የሙዚቃ አፍቃሪ ለማስደሰት ከአቡጊዳ ባንድ ጋር ከፍተኛ ዝግጅት እያደረግን ስንሆን፤ ቅዳሜ ጥር 12 ቀን ለመገናኘት ያብቃን እላለሁ።
ከሁሉ አስቀድሞ ይህ ሁሉ ይሆን ዘንድ ፈቃዱ የሆነውን ቅዱስ እግዚአብሄርን ክብር መስጋና ይድረሰው እያልኩ ፤ ለጥያቄያችን አወንታዊ መልስ በመስጠትና ጥር 12 ቀን የምናቀርበው የሙዚቃ ኮንሰርት የተሳካ እንዲሆን ከፍተኛ ድጋፍ ላደረጉልን፡
ለአማራ ክልላዊ መንግስት
ለባህር ዳር ከተማ አስተዳደር ምክር ቤት
በዚህ ሂደት ውስጥ ከፍተኛ ርብርብ ላደረጋችሁት ለባሕር ዳር ከተማና አካባባዋ ወጣቶች ከፍተኛ ምስጋናችንን እናቀርባለን።
እንደ እግዚአብሄር ፈቃድ ይህ የሙዚቃ ዝግጅታችን በሌሎችም የአገራችን ከተሞች የሚቀጥል ሲሆን ጊዜው ሲፈቅድ ዝግጅታችንን የምናቀርብባቸውን ቦታዎችና ቀኑን እናሳውቃለን።
ባሕር ዳር ጥር 12 ቀን በታላቁ ብሔራዊ ስታዲዬም በሰላም ያገናኘን !
ቴዎድሮስ ካሳሁን (ቴዲ አፍሮ)
የአማራ ክልል የሕዝብ ግንኙነት ሀላፊ መልዕክት
ጥር 3 ቀን 2010 ዓ.ም
================
እንደምን ሰነበታችሁ ?
እውቁ አርቲስት ቴዎድሮስ ካሳሁን /ቴዴ አፍሮ/በጥምቀት ማግስት ጥር 12 ቀን 2010 ዓ.ም በክልላችን መዲና ውቢቷ ባህር ዳር ከተማ ግዙፉ ስታዲየም ” ኢትዮጵያ ወደ ፍቅር ” በሚል ርዕስ የሙዚቃ ኮንስርት ለማዘጋጀት ወደ ባህር ዳር ሊያቀና ነው።
ኮንሰርቱ ስለ ሰላም ፣ስለ ፍቅር፣ስለአንድነት ፣ስለ አብሮነት እና ስለ የኢትዮጵያዊት የሚቀነቀንበት ሲሆን በክልላችን ልንሰራቸው ካቀድናው የህዝብ ለህዝብ ስራዎች አንዱ ሰለሆነ የክልላችን መንግስት እና የባህር ዳር ከተማ አስተዳደር የአርቲስቱን ጥያቄ በታላቅ አክብሮት ተቀብለውታል።
የውቢቷ ባህር ዳር ከተማ እና አካባቢዋ ነዋሪዎች ኮንሰርቱ የተሳካ ይሆን ዘንድ የሚጠበቅባቸውን ሁሉ እንደሚያደርጉ ሙሉ እምነታችን ሲሆን በክልላችን የተለያዩ አካባቢዎች መሰል የአንድነት ፣ የሰላም እና የፍቅር መድረኮችን በመፍጠር አገራዊ አንድነታችንን ለማጠናከር የምንሰራቸውን ስራዎች ከህዝባችን ጋር በመሆን አጠናክረን የምንቀጥል መሆናችንን እንገልፃለን።