Hiber Radio: ልክ ያጣው የእነ ገብረ እግዚያብሔር እብሪት ከማዕከላዊ እስከ ካንጋሮው ፍርድ ቤት

በጋዜጠኛ ጌታቸው ሽፈራው

አስቻለው ደሴ የፌደራል ፖሊስ አባል ነበር። አማራ በሰበብ በሚታሰርበትና በሚከሰስበት ግንቦት 7 አባል ነህ ተብሎ ታሰረ። የተለመደውና የሌለው የ”ሽብር” ክስ ተመስርቶበታል። የታሰረው ደግሞ የአማራ ወጣቶች ዘራቸውን እንዳይተኩ ከሚኮላሹበት ማዕከላዊ ወንጀል ምርመራ ነው። እንደሌሎቹ ወንድሞቹ አስቻለው ደሴንም ብልቱ ላይ ሁለት ሊትር ሀይላንድ ውሃ አንጠልጥለው ዘሩን እንዳይተካ አድርገውታል። ጆሮውንም ጎድተውታል። ለዚህ ሁሉ ቁስሉ ምንም አይነት የህክምና እርዳታ አላገኘም። በክሱና በማንነቱ ምክንያት ህክምና ተከልክሏል። ጥጋበኞች ላቆሰሉት፣ ለጎዱት አካልና መንፈሱ ምንም አይነት ህክምና አላገኘም።

የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 4ኛ ወንጀል ችሎት ቀርቦ ማዕከላዊ የደረሰበትን አሰቃቂ በደል በቃል ሊገልፅ ሲል “በፅሑፍ አቅርብ” ተባለ። አስቻለው ደሴ ግን የተፈፀመበትን ቢያንስ በችሎቱ የታደሙት ወገኖቹ ያዩለት ዘንድ ሱሪውን አውልቆ “የኢትዮጵያ ህዝብ ይፍረደኝ” አለ። ችሎቱን የታደሙት አነቡ፣ ከአስቻለው በምሬት እየተናገረ በችሎት የነበሩት በተለይም የሴቶች ሲቃም አጀበው። በፅሑፍ አቅርብ ያሉት ዳኞች፣ ያጀቡት ፖሊሶች በአስቻለው የሰቆቃ ድምፅ ፀጥ አሉ። ይሰማ የነበረው የእሱ የሰቆቃ ጩኸትና የታዳሚዎች ሲቃ ብቻ ነበር።

አስቻለው ደሴ ይህን ሰቆቃ ተናግሮ ወደ ቂሊንጦ ሲመለስ፣ ሌላ ቅጣት ነበር የጠበቀው። ከቃጠሎው በኋላ በግዳጅ በእስረኛ ጉልበት ወደተሰራው ዞን 5 ተቀየረ። ዞን 5 ጥብቅ ቁጥጥርና አፈና ያለበት እስር ቤት ነው። የቂሊንጦ እስር ቤት ኃላፊዎች ምንም በማያገባቸው አስቻለውን ጨምሮ በርካቶችን ፍርድ ቤት በሚናገሩት ይደበድቧቸዋል። ወደ ጨለማ ቤት ይልኳቸዋል። የአሳሪዎቹ እብሪት ግን በዚህ ግን አላበቃም።

የአስቻለው ቤተሰብ የሆኑ ቄስ ይህን መከረኛ ወጣት ለመጠየቅ ከአማራ ክልል ወደ ቂሊንጦ ይሄዳሉ። እስር ቤቱ በር ላይ ግን ያልጠበቁት ይገጥማቸዋል። ጥምጣማቸውን ካላወለቁ ወደ እስር ቤቱ እንደማይገቡ ይነገራቸዋል። ቄሱ ቢለምኑ የሰማቸው አላገኙም። አሳሪዎቹ የቄስ ማንነትንም ወደ ኋላ ያያሉ፣ በመጡበት አካባቢ ይመዝኗቸዋል፣ ያዋርዷቸዋል፣የእስረኛውን ማንነት ጋርም ያያይዙታል።

ቄሱ ሰቆቃ የደረሰበትን አስቻለውን ለመጠየቅ ሲሉ ቆባቸውን አውልቀው ገቡ። የተፈፀመባቸውን አስፀያፊ ተግባርም ለአስቻለው አጫወቱት። አስቻለው ለምን እንዲህ ይበድሉናል ብሎ በምሬት ሲናገር ከጎኑ የቆመው ጥበቃ ፖሊስ እየሰማ ነበር። ይህም ወንጀል ሆኖ ለእነ ገብረ እግዚያብሔር ተነገራቸው። ገብረ እግዚያብሔር የተባለ ፖሊስ እግዚያብሔርን የማይፈራ ከቂሊንጦ “ኃላፊዎች” መካከል አንዱ ነው። ቄሱ ቆባቸውን አውልቀው እንዲገቡ መገደዳቸው ሳይበቃ፣ ይህ መደረግ አልነበረበትም አለ ተብሎ አስቻለውን አስደብድቦ ጨለማ ቤት እንዲገባ አድርጓል። ያ ሁሉ በደል የተፈፀመበት አስቻለው በቤተሰቦቹ እንዳይጠየቅ ተከልክሏል። ማዕከላዊ በተፈፀመበት ድብደባ ቁስሉ ሳይጠግግና ህክምና ሳያገኝ አሁንም እየተደበደበ ነው። የእነ ገብረ እግዚያብሔር እብሪት ልክ አጥቷል!

Hiber radio Las Vegas ይህ ህብር ሬድዮ _የወቅታዊ መረጃ ምንጭ ነው። ህብር ሬድዮ በአቤኔዘር ኮሙኒኬሽን ሴንተር እየተዘጋጀ  ከላስ ቬጋስ ከተማ፣ ዘወትር ዕሁድ በአካባቢው ሰዓት አቆጣጠር ከምሽቱ 630 ሰዓት እስከሰዓት በህብር ሬዲዮ ድህረ ገጽ ወይም በቀጥታ በስልክ ለማዳመጥ  5639993994 ወይም 563999-3988 ወይም 712-432-8451 በመረጡት ቁጥር መደወል ብቻ በቂ ነው በእንግሊዝ ለምትኖሩ 01405770140 በስልክ ማዳመጥ ይቻላል። ዘወትር በድህረ ገጻችን፣ googel app store Hiber Radio ወደ ስልክዎ በመጫን ካልሆነም በዘሐበሻ እንዲሁም በተጠቀሱት ስልኮች ማዳመጥ ይቻላል።

 

 

 

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *