(በጌታቸው ሽፈራው)
ማዕከላዊ እስረ ቤት የተኮላሸውን ብልቱን በችሎት ሱሪውን አውልቆ ያሳየው አስቻለው ደሴ ዛሬ ጥር 24/2010 ዓም ዐቃቤ ሕግ የሚያቀርብባቸውን ምስክር ለማዳመጥ በፌደራል ከፍተኛ ልደታ ምድብ 4ኛ ወንጀል ችሎት ተቀጥሮ ነበር።
ሁለት ምሰክሮች ፈረመው እንደቀሩ፣ እንዲሁም ሌሎች በአድራሻቸው ፖሊሰ ፈልጎ እንዳላገኛቸው ዐቃቤ ሕግ ለፍርድ ቤቱ ገልፆአል። የአስቻለው ቤተሰብ የሆነ በችሎት የታደመ ግለሰብ ፍርድ ቤቱን አስፈቅዶ አስቻለውን መጠየቅ እንዳልቻለ ገልፆአል።
1ኛ ተከሳሽ አስቻለው ደሴ የኃይማኖት አባቱ ሊጠይቁት ወደ ቂሊንጦ እስር ቤት ሲገቡ፣ የቂሊንጦ ጥበቃ ፖሊሶች ሻሻቸውን አስወልቀው እንዳስገቧቸውና ለምን እንዲህ አይነት ድርጊት ይፈፀማል ብሎ በመጠየቁ፣ በኃላፊዎቹ ተጠርቶ ወደ ጨለማ ቤት መወሰዱን ለፍርድ ቤቱ ገልፆአል። አስቻለው ደሴ አክሎም “ጨለማ ቤት ውስጥ 6 ቀን ራቁቴን፣ በካቴ ታስሬያለሁ” ሲል ለፍርድ ቤቱ ገልፆአል። ራቁቱን በካቴና ታስሮ ጨለማ ቤት በቆየበት ወቅት ውሃም ተከልክሎ እንደቆየ ለፍርድ ቤቱ አስረድቷል።
አሰቻለው ደሴ በአሁኑ ወቅትም ጨለማ ቤት ታሰሮ የሚገኝ ሲሆን ጨለማ ቤት የገባበትን ምክንያት እንዲገለፅለት ለቂሊንጦ እስር ቤት ኃላፊ እንዲሁም የቂሊንጦ ጥበቃ እና ደህንነት ኃላፊ ጥያቄ ቢያቀርብም መልስ እንዳላገኘ ገልፆአል።አስቻለው ደሴ ማዕከላዊ በተፈፀመበት ድብደባ ምክንያት በህመም ላይ የሚገኝ ሲሆን ለፍርድ ቤቱ አቤቱታ አቅርቧል። ከዚህም በተጨማሪ በማዕከላዊ እስር ቤት የሰብአዊ መብት ጥሰት የፈፀሙበትን መርማሪዎች እንዲከሰሱለት ለፍርድ ቤቱ ያቀረበ ሲሆን ፍርድ ቤቱም በዛሬው ቀን “እያየነው ነው” የሚል መልስ ሰጥቷል።
ህክምናውን በተመለከተ የቂሊንጦ ሀኪሞች የእስር ቤቱ ኃላፊዎች አስቻለው እንዲታከም እስካልፈቀዱ ድረስ ህክምና እንደማይሰጡት እንደገለፁለት ለችሎቱ አስረድቷል። አስቻለው “እኔ እንደማንኛውም ታራሚ ህክምና የማላገኝበት ምክንያት ምንድን ነው?” ሲል በችሎት ጥያቄ አቅርቧል።
በእነ አስቻለው ደሴ ላይ ዐቃቤ ሕግ አቀርባቸዋለሁ ብሎ ፈርመው የቀሩትን ሁለት ምስክሮች ፖሊስ አስሮ እንዲያቀርብ፣ እንዲሁም በአድራሻቸው አልተገኙም የተባሉትን አፈላልጎ እንዲያቀርብ ለየካቲት 19/2010 ዓም ተለዋጭ ቀጠሮ ተሰጥቷል።
(ዘገባውን ያደረሰችኝ ማህሌት ፋንታሁን ናት)
Hiber radio Las Vegas ይህ ህብር ሬድዮ _የወቅታዊ መረጃ ምንጭ ነው። ህብር ሬድዮ በአቤኔዘር ኮሙኒኬሽን ሴንተር እየተዘጋጀ ከላስ ቬጋስ ከተማ፣ ዘወትር ዕሁድ በአካባቢው ሰዓት አቆጣጠር ከምሽቱ 6፤30 ሰዓት እስከ 8 ሰዓት በህብር ሬዲዮ ድህረ ገጽ ወይም በቀጥታ በስልክ ለማዳመጥ 5639993994 ወይም 563999-3988 ወይም 712-432-8451 በመረጡት ቁጥር መደወል ብቻ በቂ ነው በእንግሊዝ ለምትኖሩ በ01405770140 በስልክ ማዳመጥ ይቻላል። ዘወትር በድህረ ገጻችን፣ ከ googel app store Hiber Radio ወደ ስልክዎ በመጫን ካልሆነም በዘሐበሻ እንዲሁም በተጠቀሱት ስልኮች ማዳመጥ ይቻላል።