(ህብር ራዲዮ)በህወሓት መሪዎች መካከል ቆየውን የስልጣን ሽኩቻ ከፖለቲካ አመራሩ አልፎ በወታደሩ ውስጥም መግባቱ ተደጋግሞ ሲዘገብ የነበረውን በሚአጋልጥ መልኩ የአቶ መለስና የባለቤታቸው ታማኝ የነበሩት ጄኔራል ሳሞራ የኑስ 17 ኣመት ስልጣን ላይ ቆይተዋል ከስልታን መነሳታቸውን እደግፋለሁ በማለት የቀድሞ የሰራዊቱ አዛዥ ሌ/ጄ/ጻድቃን ገ/ተንሳይ በሰጡት ቃለ መጠይቅ ይፋ አደረጉ።
በህወሓት ማዕከላዊ ኮሚቴ ስብሰባ ተደጋጋሚ የስልጣን ሽኩቻ ሲያደርጉ የቆዩት የእነ አዜብና የዶ/ር ደብረጺዮን ቡድን መጨረሻ ወ/ሮ አዜብ ታግደው አስከትሎም ከኤፈርት ዋና መሪነታቸው ከተነሱ በሁዋላ ቀጣዩ ጄ/ል ሳሞራ እንደሚሆኑ ተደጋግሞ ተዘገበ ሲሆን የዛሬው የሌ/ል/ጄ ጻድቃን ለሪፖርተር የሰጡት ቃለ መጠይቅ በእርግጥ የጄኔራሉ ከስልጣን መነሳታቸውን ያስረገጠ ሆኗል። ህብር ሬዲዮ የሰሞኑን ወታደራዊ ሹመት አስመልክቶ ከብ/ጄ/ ሀይሉ ጎንፋ ጋር ባደረግነው ቃለ መጠይቅ ላይ የሶስት ም/ኤታ/ማዦር ሹመትና አራተኛው ጄኔራል በሶማሌና በኦሮሞ መካከል ለተነሳውና የበርካታ ንጹሃንን ሕይወት ቀጥፎ ሚሊዮን ለሚጠጉ ሰዎች መፈናቀል ምክንያት የሆኑት የሌ/ጄ/ል አብርሃ ወ/ማርያም መሾም ስርኣቱ ለፍርድ መቅረብ ያለባቸው ገዳዮችን እየሾመ በአፈናው ለመቀጠል መወሰኑን ገልጸዋል።
የሌ/ጄ/ል ጻድቃን የዛሬው ቃለ መጠይቅ የጄ/ል ሳሞራን ከስልጣን መነሳት የማይቀር መሆኑን ፍንጭ የሰጠ ሲሆን አስቀድሞ ሰሞኑን ከተሾሙት አራት ጄኔራሎች አንዱ አብርሃ ወ/ማርያም ይተኳቸዋል የሚል የአንዳንድ ወገኖች ግምት መሰማት ጀምሯል።የሰሞነ ሱመተ በሰራዊቱ የአንደ የትግራይ ቡድን የበላይነት የበለጠ የሚያጠናክር መሆኑን ለህብር ገለጹ ሲሆን ጻድቃን በበኩላቸው ለውጥ አለ ብለው ለመናገር ሞክረዋል።
የሌ/ጄ/ል ጻድቃን ገ/ተንሳይን ለሪፖርተር የሰጡትን ቃለ መጠይቅ እነሆ
የሕወሓቱ መከላከያ ቁንጮ ሳሞራ የኑስ
የጄኔራሎች ሹመትና አንድምታው
7 February 2018
ዮሐንስ አንበርብር
ፕሬዚዳንት ሙላቱ ተሾመ (ዶ/ር) በርዕሰ ብሔርነት ከተሾሙ አንስቶ ከፈጸሟቸው ተግባራት በጉልህ የሚታወቀው፣ ባለፉት ዓመታት ለከፍተኛ ጄኔራል መኮንኖች በየዓመቱ ሲሰጡ የነበረው የማዕረግ ሹመት ነው፡፡
ፕሬዚዳንቱ በ2005 ዓ.ም. ለ35 ጄኔራሎች ሹመት ከሰጡ በኋላ በ2006 ዓ.ም. ለ37፣ በ2008 ዓ.ም. ለስድስት፣ በ2009 ዓ.ም. ደግሞ ለ38 ጄኔራሎች ሹመት ሰጥተዋል፡፡ ዓርብ ጥር 25 ቀን 2010 ዓ.ም. ደግሞ ለ61 የሠራዊቱ ከፍተኛ መኮንኖች የጄኔራል መኮንነት ማዕረጎችን ሰጥተዋል፡፡
በጠቅላይ ሚኒስትሩ አቅራቢነት በፕሬዚዳንቱ የተሰጠው ሹመት ለ40 ኮሎኔሎች የብርጋዴር ጄኔራልነት ማዕረግ አስገኝቷል፡፡ 14 ብርጋዴር ጄኔራሎች የሜጀር ጄኔራልነት ማዕረግ የተሰጣቸው ሲሆን፣ ሦስት ሜጄር ጄኔራል የነበሩ ደግሞ የሌተና ጄኔራልነት ማዕረግ አግኝተዋል፡፡
በዚህ ሹመት ያልተጠበቀው ፕሬዚዳንቱ ለአራት ሌተና ጄኔራሎች የሰጡት ሹመት ነው፡፡ በጠቅላይ ሚኒስትሩ አቅራቢነት ፕሬዚዳንቱ በሰጡት ያልተጠበቀ ሹመት ሌተና ጄኔራል ሰዓረ መኮንን፣ ሌተናል ጄኔራል አብርሃ ወልደ ማርያም፣ ሌተና ጄኔራል አደም መሐመድና ሌተና ጄኔራል ብርሃኑ ጁላ የጄኔራል ማዕረግ ሲሰጣቸው፣ እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ የአገሪቱ ብቸኛ ጄኔራል ከሆኑት ጠቅላይ ኤታ ማጆር ሹም ጄኔራል ሳሞራ ዮኑስ ጋር በአሁኑ ወቅት አምስት ሙሉ ጄኔራሎች አሉ፡፡
ፕሬዚዳንቱ የማዕረግ ዕድገት ከሰጡ በኋላ በማግሥቱ ደግሞ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ ጄኔራል ሰዓረ መኮንን፣ ጄኔራል አደም መሐመድና ጄኔራል ብርሃኑ ጁላን የምክትል ጠቅላይ ኤታ ማጆር ሹም ኃላፊነት ሰጥተዋቸዋል፡፡
የሹመቱ አንድምታ
የመከላከያ ሚኒስቴርን የ2005 ዓ.ም. የሥራ አፈጻጸም ሪፖርት ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በወቅቱ ያቀረቡት የመከላከያ ሚኒስትሩ አቶ ሲራጅ ፈጌሳ፣ በትጥቅ ትግሉ የተሳተፉ ታጋዮች በመደበኛው ሠራዊት ውስጥ እንዲቀጥሉ በመደረጉ ምክንያት መከላከያ ሠራዊቱ የአገሪቱን ብሔር ብሔረሰቦች ተዋጽኦ ለረዥም ዓመታት ሳይጠብቅ በመቆየቱ፣ በሕገ መንግሥቱ መሠረት የሠራዊቱን የብሔር ተዋጽኦ የማመጣጠን ተግባር ትኩረት ተሰጥቶት በመሥራት ላይ መሆኑን ተናግረው ነበር፡፡
በወቅቱ ባቀረቡት ሪፖርት የትግራይ ብሔር የሠራዊቱ አባላት ለዓመታት የቆየ አብላጫነት ቀድሞ እንዲቀነስ መደረጉን ተናግረው ነበር፡፡ በዚሁ መሠረት እስከ 2004 ዓ.ም. መጨረሻ ድረስ በተደረገው የማመጣጠን ሥራ የአማራ ብሔር የሠራዊቱ አባላት ቁጥር 30,343 በመሆን የአንደኛነት ደረጃ መያዙን፣ የኦሮሞ ብሔር የሠራዊቱ አባላት ቁጥር ደግሞ 25,205 በመሆን በሁለተኛ ደረጃ መሆናቸውንና በሦስተኛ ደረጃነት ደግሞ የደቡብ ብሔሮችና ብሔረሰቦች የሆኑ የሠራዊቱ አባላት 22,842 መሆናቸውን ገልጸው ነበር፡፡ የትግራይ ብሔር ተወላጅ የሆኑ የሠራዊቱ አባላት ደግሞ ወደ 18,580 እንዲወርድ ተደርጎ በአራተኛ ደረጃ ላይ እንደሚገኝ በወቅቱ ተዘግቦ ነበር፡፡
የብሔር ተዋጽኦውን የማመጣጠን ሥራ እንደሚቀጥል በወቅቱ የተናገሩት ሚኒስትሩ፣ በተለይ ከፍተኛ የሠራዊቱ አመራሮችን ተዋጽኦ የማመጣጠን ተግባር በቀጣይ ዓመታት የሠራዊቱን ብቃት እንዳያዳክም ጥንቃቄ ተደርጎ እንዲከናወን ትኩረት መሰጠቱን ገልጸው ነበር፡፡
በዚህም ምክንያት ይመስላል ፕሬዚዳንት ሙላቱ ላለፉት አራት ተከታታይ ዓመታት ለከፍተኛ የሠራዊቱ አመራር መኮንኖች ከፍተኛ ማዕረግ ሲሰጡ የቆዩት፡፡
የሰሞኑን የሹመት አንድምታን አስመልክቶ ሪፖርተር ያነጋገራቸው የሠራዊቱ የቀድሞ ጠቅላይ ኤታ ማጆር ሹም ሌተና ጄኔራል ፃድቃን ገብረ ትንሳዔ የሰሞኑ የጄኔራሎች ሹመት ፖለቲካዊ አንድምታ እንዳለው ይገምታሉ፡፡ ሌተና ጄኔራል ፃድቃን እስካሁን ድረስ እንቆቅልሽ ሆኖባቸው ምክንያቱን ሳያውቁ ከኤታ ማጆር ሹም ኃላፊነታቸው በ1993 ዓ.ም. ተነስተው ከሠራዊቱም የተሰናበቱ ናቸው፡፡ በአሁኑ ወቅት በግል የማማከር ሥራና በንግድ ላይ የተሰማሩ ሲሆን፣ ደቡብ ሱዳን ከሱዳን ነፃነቷን ካገኘች በኋላ በስምጥ ሸለቆ ተዋጊነት (ጎሬላ) የተደራጀውን የደቡብ ሱዳን መንግሥት ሠራዊትን በመደበኛ ሠራዊትነት እንዲያዋቅሩ በእንግሊዝ ዓለም አቀፍ የልማት ትብብር ቀጣሪነት፣ ከሌሎች ባልደረቦቻቸው ጋር ሠራዊቱን የማዋቀር ኃላፊነት የተወጡ ናቸው፡፡ ፕሬዚዳንቱ ባለፈው ሳምንት የሰጡትን ሹመት በተመለከተ፣ ‹‹የዘገየ ካልሆነ በስተቀር ተገቢ ዕርምጃ ነው፤›› ብለውታል፡፡ መንግሥታት እንዲህ መሰል በርካታ ሹመት በአንድ ጊዜ ሲሰጡ የራሱ ፖለቲካዊ መነሻ እንዳለው የተናገሩት ሌተና ጄኔራል ፃድቃን፣ የፖለቲካ ምክንያቱን ወይም የሹመቱ ፖለቲካዊ ግብ ምን እንደሆነ በይፋ ባለመነገሩ ከግምት የዘለለ ምንም ማለት እንደማይችሉ ገልጸዋል፡፡ አማራጩ የብሔር ተዋጽኦን ማስተካከል ነው ይላሉ፡፡
‹‹ሠራዊቱ ለበርካታ ዓመታት በትግራይ ብሔር የበላይነት ውስጥ የቆየ በመሆኑ ቅሬታ ይሰማበታል፡፡ ይህ መነሳቱና መስተካከል አለበት መባሉ ለእኔ ተገቢ ነው፤›› ሲሉ ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡
በሰሞኑ ሹመት ከኮሎኔል ማዕረግ ወደ ብርጋዴር ጄኔራልነት ያደጉትን አንዳንዶቹን በአጋጣሚ በኢትዮጵያ ኤርትራ ጦርነት ወቅት እንደሚያውቋቸው፣ የተቀሩትን ደግሞ ከዝርዝሩ እንደተመለከቷቸውና ከትግራይ ብሔር ውጪ ያሉት የተካተቱበት መሆኑ፣ የሹመቱ ዓላማ ብሔር ማመጣጠን የሚያስብል መሆኑን እንዲረዱ እንዳስቻላቸው ተናግረዋል፡፡
‹‹የሹመቱ ፖለቲካዊ ግብ እንደገመትኩት ከሆነ የዘገየ ነገር ግን ተገቢ ዕርምጃ ነው፡፡ የአገር ሰላምና አንድነት ላይ ከሚያበረክተው አስተዋጽኦ አንፃር ካየነውም የጎላ ድርሻ ይኖረዋል፤›› የሚል እምነታቸውን ገልጸዋል፡፡
ምክትል ጠቅላይ ኤታ ማጆር ሹሞች?
በኢትዮጵያ አገር መከላከያ ሠራዊት ውስጥ ከጠቅላይ ኤታ ማጆር ሹሙ ውጪ በምክትል ጠቅላይ ኤታ ማጆር ሹምነት መዋቅርም ሆነ ምደባ ባለፉት 27 ዓመታት አልታየም፡፡ በጉዳዩ ላይ ሪፖርተር ያነጋገራቸው አንድ ከፍተኛ የሕግ ባለሙያ፣ የምክትል ጠቅላይ ኤታ ማጆር ሹምነት ሠራዊቱ ከተቋቋመበት አዋጅ አንፃር በመመልከት በሕጉ ያልተደገፈ መሆኑን ይናገራሉ፡፡
የቀድሞውም ሆነ በ2005 ዓ.ም. የተሻሻለው የሠራዊቱ ማቋቋሚያ አዋጅ ቁጥር 809 ይህንን የምክትል ጠቅላይ ኤታ ማጆር ሹም ኃላፊነት በተመለከተ የሚለው ነገር እንደሌለ፣ በዚህ ሥልጣን የተሾሙት ጄኔራሎች ተግባራዊ ኃላፊነትም እንደማይታወቅ ይገልጻሉ፡፡ ከዚህ በኋላ ማሻሻያ አዋጅ ሊመጣ ይችል ይሆናል፣ ካልሆነ ግን በዚህ ኃላፊነት ማን ምን ማድረግ እንዳለበት ለሠራዊቱም ለሕዝቡም ምናልባትም ለተሿሚዎቹ ግልጽ ባለመሆኑ፣ የተግባርና ኃላፊነት መጣረስ ሊፈጥር ይችላል የሚል ሥጋት እንዳላቸው የሕግ ባለሙያው አስረድተዋል፡፡
የሠለጠኑ አገሮች ልምድ ከአንድ በላይ የጠቅላይ ኤታ ማጆር ሹም ኃላፊነት መኖሩን፣ እነዚህም በኤታ ማጆር ሹሞች የጋራ ምክር ቤት አባላት እንደሆኑ ያሳያል፡፡ የኤታ ማጆር ሹሞች የጋራ ምክር ቤት ሊቀመንበር አንድ ጠቅላይ ኤታ ማጆር ሹም ብቻ ባላቸው አገሮች ውስጥ እንደተለመደው በደኅንነት ጉዳዮች የአገሪቱ ፕሬዚዳንት አማካሪ ነው፡፡ በእንግሊዝም ኤታ ማጆር ሹሞች የጋራ ኮሚቴ ሲኖር፣ የኮሚቴው ሰብሳቢ የአገሪቱን ጦር አጠቃላይ እንቅስቃሴ የመምራት ኃላፊነት ሲኖርበት የመንግሥት የደኅንነት አማካሪ ነው፡፡
ሰሞኑን በተደረገው የሦስት ምክትል ጠቅላይ ኤታ ማጆር ሹሞች ምደባ ላይ የተጠየቁት ሌተና ጄኔራል ፃድቃን በሌሎች አገሮች የተለመደና ግልጽ ኃላፊነት የወጣለት ሥልጣን መሆኑን ተናግረዋል፡፡ በኢትዮጵያ ይህ የኃላፊነት ስያሜ ሳይሰጥ ቢቆይም ሥራው ግን ይሠራ እንደነበር ገልጸዋል፡፡ ይህንን በመረዳትም የምክትል ኤታ ማጆር ሹሞቹ ኃላፊነት በግልጽ ተለይቶ ይገለጻል የሚል እምነት አላቸው፡፡
ጠቅላይ ኤታ ማጆር ሹም
ይህንን ሰሞነኛ ሹመት በተመለከተ የተለያዩ አስተያየቶች ከማኅበረሰቡ በመደመጥ ላይ ናቸው፡፡ ሹመቱ የብሔር ተዋጽኦን ለማመጣጠን ያለመ ነው ከሚለው አንስቶ፣ የአገሪቱ ጠቅላይ ኤታ ማጆር ሹም የሆኑትን ጄኔራል ሳሞራ የኑስ ለመተካት ያለመ ስለመሆኑም በስፋት ይነገራል፡፡
ይህንን አስመልክቶ የተጠየቁት ሌተና ጄነራል ፃድቃን የሰሞኑ ሹመት ዓላማ፣ ‹‹ጊዜያቸውን የጨረሱትን ለመተካት ይመስላል፡፡ በተጨማሪም የአገሪቱን ፖለቲካዊ ሁኔታ መነሻ ያደረገ ነው ብዬ እገምታለሁ፤›› ብለዋል፡፡
የሠራዊቱ ማቋቋሚያ አዋጅ አንቀጽ አሥር ላይ፣ ‹‹ማንኛውም የሠራዊት አባል መኮንን ከሆነ በኋላ ቢያንስ ለአሥር ዓመታት አገልግሎት ይሰጣል፡፡ ሆኖም ጄኔራል መኮንኖች ከሆኑ ከ55 ዓመት በላይ ሊያገለግሉ አይችሉም፤››ይላል፡፡ ጄኔራል መኮንኖች ማለት ከብርጋዴር ጄኔራል እስከ ሙሉ ጄኔራል ያለውን ይመለከታል፡፡
ይሁን እንጂ አላስፈላጊ በሚሆንበት ጊዜ የአገልግሎት ዘመን ሊራዘም እንደሚችል ይኸው አዋጅ ይደነግጋል፡፡
በዚሁ መሠረትም የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኤታ ማጆር ሹምን የአገልግሎት ዘመን ማራዘም የሚመለከት ከሆነ፣ የጦር ኃይሎች ጠቅላይ አዛዥ ለሆኑት ለአገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ቀርቦ ከተፈቀደ ከአምስት ዓመት ላልበለጠ ጊዜ ሊራዘም እንደሚችል ይደነግጋል፡፡
የሰሞኑ ሹመት ዓላማ ጊዜያቸውን ያጠናቀቁ የሠራዊቱ አመራሮችን ለመተካት ነው ብለው እንደሚገምቱ የተናገሩት ሌተና ጄኔራል ፃድቃን፣ ‹‹በሥልጣን ላይ ያሉትን ጠቅላይ ኤታ ማጆር ሹም ለመተካት ስለመሆኑ የማውቀው ነገር የለም፡፡ ከሆነም ትክክለኛ ዕርምጃ ነው፤›› ብለዋል፡፡ ምክንያታቸውንም ሲናገሩ፣ ‹‹ሥልጣን ላይ ያሉት ጠቅላይ ኤታ ማጆር ሹም ከ17 ዓመታት በላይ ቆይተዋል፡፡ ዘገየ ካልሆነ በስተቀር ተገቢ ዕርምጃ ነው፤›› ብለዋል፡፡ ሙሉ ጄኔራልነት የተሾሙትን ሠራዊቱ ውስጥ በነበሩበት ጊዜ በቅርበት እንደሚያውቋቸው ጠቁመዋል፡፡
ከላይ ያለው የሪፖርተር ዘገባ ከመውጣቱ በፊት ስለ ሰሞኑ ወታደራዊ ሹመት ብ/ጄ/ል ሐይሉ ጎንፋ ከህብር ሬዲዮ ጋር አደረጉት ወቅታዊ ቃለ መጠይቅ በርከት ያሉወሳኝ ጉዳዮችን አንስተዋል። ያድምጡት