Hiber Radio: ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋና አንዷለም አራጌን ጨምሮ የፖለቲካ እስረኞች እንደሚፈቱ ተገለጸ

(ህብር ሬዲዮ) ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ እና አንዷለም አራጌን ጨምሮ በእስር ላይ የሚገኙ የፖለቲካና የህሊና እስረኞች መካከል አገዛዙ 746 ታራሚዎችና ተጠርታሪዎች በይቅርታና ክሳቸው ተቋርጦ እንደሚፈቱ በሚቆጣጠራቸው መገናኛ ብዙሃን አማካይነት  ይፋ አደረገ ።

ከጋዜጠኛ እስክንድር ነጋና  ከቀድሞው አንድነት ፓርቲ ሕጋዊ አመራሮች አንዱ አንዷለም አራጌ ሌላ የትኞቹ የፖለቲካና የህሊና እስረኞች ይካተቱ አይካተቱ የታወቀ ባይሆንም አንዳንዶች በመፈንቅለ መንግስት በሚል የአገዛዙ ክስና የግፍ ፍርድ  ሳቢያ ታስረው በስቃይ ላይ ያሉት እነ ጄኔራል ተፈራ ማሞ፣ጄ/ል አሳምነው ጽጌ፣ወ/ሮ እማዋይሽ አለሙና ሌሎችም ተካተዋል ቢሉም ማረጋጋገጥ አልተቻለም።

የአገዛዙ ልዩ ልዩ መገናኛ ብዙሃን ተቀባብለው እንደዘገቡት ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ እንደገለጸው የኢህአዴግ ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ የሰጠውን ቀደም ያለ ውሳኔ ተከትሎ በፌደራል ደረጃ ቀደም ብሌ በሽብር የፈጠራ ክስ ሳቢያ፣በሐይማኖት ሳቢያ እና አክራሪነት ባለው ሌላ ሀሰተኛ ክስ  ሳቢያ ተፈረደባቸውን ጨምሮ በእስር ቤቴች የሚገኙ 417 እስረኞች በይቅርታ እንዲለቀቁ ተወስኗል ይላል። ከእነዚህ የግፍ እስረኞች መካከል 298 በፌደራል ማረሚያ ቤት የሚገኙ እና 119 በአማራ ክልል ማረሚያ ቤቶች የሚገኙ ናቸው በይቅርታ እንዲለቀቁ ሲል በዝርዝር ገልጿል። ኮ/ል ደመቀ ዘውዱ በዚህ ዝርዝር ይኑሩ አይኑሩ ማወቅ አልተቻለም።

የቀሩት እስረኞች በተመሳሳይ የፈጠራ ክስ ሳቢያ ከታሰሩት መካከል የ329 እስረኞች ክሳቸው እንዲቋረጥ መወሰኑንም የወጣው ዘገባ ይጠቅሳል።

ቀደም ሲል ከፖለቲካ እስረኞች ዶ/ር መረራ ጉዲና ብቻ የተፈቱ ሲሆን የጤናቸው ሁኔታ አጠራጣሪ የሆነው አቶ በቀለ ገርባ በዚህ ዝርዝር ለመኖራቸው የተገለጸ ነገር የለም።

ጠቅላይ ዐቃቤ ሕጉ ዛሬ እነ እስክንድር ነጋን ጨምሮ 746 ይፈታሉ ይበል እንጂ ቀደም ሲል ሕገ መንግስቱን ለመናድ ያሰቡና በዚያ ሳቢያ የተከሰሱ እንደማይለቀቁ የተናገሩ ቢሆንም የሕዝቡ ተቃውሞ እያየለ መምጣትና ስርዓቱ የእስረኛን ጉዳይ ጊዜ ለመግዣ የሚጠቀምበት መሆኑ በይፋ በሚነገርበት ወቅት የእስረኞቹ ይፈታሉ ዜናን ብዙዎች በመልካምነት ተቀብለዋል።

 

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *