ሀገራችን ውስብስብ በሆኑ ማህበራዊ፥ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች እንዳሉባት እርግጥ ነው። እነዚህ ውስብስብና እርስ-በእርስ የተጠላለፉ ችግሮች በዘላቂነት ለመፍታት በጥናትና ዕውቀት ላይ የተመሰረተ መፍትሄ መስጠት ያስፈልጋል። ለዚህ ደግሞ ተነሳሽነትና ቁርጠኝነት ያለው የፖለቲካ አመራር ሊኖር ይገባል። ችግሩ ሲፈጠር በነበረው ወይም ችግሩን በፈጠረው የፖለቲካ አስተዳደርና አመራር፤ የመንግስትን አስተዳደርና የተቋማት አሰራር ማሻሻል፥ ግልፅነትና ተጠያቂነትን ማስፈን፣ የመልካም አስተዳደር ችግሮችን መቅረፍ፣ ቀልጣፋና ጥራት ያለው አገልግሎት መስጠት፥ የብዙሃኑን ተጠቃሚነት ማረጋገጥ፣… በአጠቃላይ የሀገሪቱን ማህበራዊ፥ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች በዘላቂነት መቅረፍ አይቻልም።
በዚህ መሰረት፣ ሀገራችን ከገባችበት ፖለቲካዊ ቀውስና አለመረጋጋት እንድትወጣ፣ በዜጎች ሕይወት፥ አካልና ንብረት ላይ እየደረሰ ያለውን ጥቃትና ጉዳት ለማስቀረትና የሁሉም መብት፥ ነፃነትና ፍትሃዊ ተጠቃሚነት ለማስከበር በፖለቲካዊ ስርዓቱ ላይ ስር-ነቀል ለውጥ መደረግ አለበት። ይህን እውን ለማድረግ ደግሞ በቅድሚያ በፖለቲካ ስርዓቱ ውስጥ የሚስተዋሉ መዋቅራዊ ችግሮችን (structural problems) በግልፅ መለየት ያስፈልጋል። ስለዚህ የሀገራችን ፖለቲካዊ ስርዓት ያሉበት መዋቅራዊ ችግሮች ምንድን ናቸው?
በሕገ-መንግስቱ አተገባበር ላይ የሚስተዋሉ ችግሮችን በተለያዩ ፅሁፎች ለማቅረብ ሞክሬያለሁ። የዚህ ፅሁፍ ትኩረት በሕገ-መንግስቱ የተሳሳቱ መርሆች፥ ድንጋጌዎች እና የመንግስት አወቃቀር ላይ ነው። በዚህ መሰረት፣ ሦስት አንቀፆችን መነሻ በማድረግ ሕገ-መንግስቱ፤ ለዜጎች ፀረ-እኩልነት እና ፀረ-ነፃነት፣
1ኛ) ሕገ-መንግስቱ ለዜጎች “ፀረ-እኩልነት” ነው!
ሕገ-መንግስቱ በአምስት መሰረታዊ መርሆች ላይ የተመሰረተ ነው። ከአምስቱ መሰረታዊ መርሆች ውስጥ የመጀመሪያው አንቀፅ 8 ላይ የተጠቀሰው “የሕዝብ ሉዓላዊነት” የሚለው መርህ ነው። በዚህ አንቀፅ መሰረት “የኢትዮጲያ ብሔሮች፥ ብሔረሰቦች፥ ሕዝቦች የኢትዮጲያ ሉዓላዊ ስልጣን ባለቤቶች ናቸው” ይላል። በዚህ መሰረት፣ የሀገሪቱ ዜጎች የሉዓላዊ ስልጣን ባለቤትነት የላቸውም። በመሆኑም በሕገ-መንግስቱ የተደነገጉ ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶችና ነፃነቶችን የመጠየቅ፥ የማስከበር፥ የማሻሻል፥ የመቀየር፥… ሉዓላዊ ስልጣን የላቸውም። ስለዚህ ዜጎች ሰብዓዊና ዴሞክራሲየዊ መብቶችና ነፃነቶችን መጠየቅ ሆነ መጠቀም አይችሉም።
በተቃራኒው የኢትዮጲያ ብሔሮች፥ ብሔረሰቦች፥ ሕዝቦች የሉዓላዊ ስልጣን ባለቤቶች ቢሆኑም በሕገ-መንግስቱ የተደነገጉ ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶችን ለመጠየቅ፥ ለመጣስ፥ ለማክበር፥ ለማስከበር፥ ለማሻሻል፥ ለመቀየር፥… የሚያስችል ተፈጥሯዊ አቅም የላቸውም። ስለዚህ ሉዓላዊነታቸውን፥ የስልጣን የበላይነታቸውን ተግባራዊ ማድረግ ሆነ መጠቀም አይችሉም።
በሕገ-መንግስቱ መሰረት፣ የኢትዮጲያ ዜጎች በሀገራቸውና መንግስታቸው ላይ ሉዓላዊ መብትና ስልጣን፣ የሰልጣን ባለቤትነትና የበላይነት የላቸውም። በአንፃሩ የኢትዮጲያ ብሔሮች፥ ብሔረሰቦች፥ ሕዝቦች በሕገ-መንግስቱ በተሰጣቸው ሉዓላዊ ስልጣን መሰረት በራሳቸው ምንም ማድረግ አይችሉም፤ የራሳቸውን ሆነ የዜጎችን መብት አይጥሱም፥ አያከብሩም፥ አያስከብሩም፥…ወዘተ። ኢትዮጲያዊያን በሀገራቸውና መንግስታቸው ላይ ሉዓላዊ መብትና ስልጣን (sovereign power) የላቸውም። የአንድ ሀገር ዜጎች ሉዓላዊ መብትና ስልጣን ከሌላቸው በሀገሪቱ ላይ ባለቤትነት፣ በመንግስት ላይ የበላይነት ሊኖራቸው አይችልም። ስለዚህ ሕገ-መንግስቱ ለዜጎች ፀረ-እኩልነት ነው!
2ኛ) ሕገ-መንግስቱ ለሀገር “ፀረ-አንድነት” ነው!
ሀገርና መንግስት የሚመሰረተው በወደፊት አብሮነት እና አንድነት ነው። በሕገ-መንግስቱ አንቀፅ 39 መሰረት አሁን ያለው መንግስታዊ ስርዓት ከወደፊት አብሮነት ይልቅ መለያየትን፣ ከአንድነት ይልቅ ልዩነትን በማስፋትና ማስረፅ ላይ የተመሰረተ ነው። በመሆኑም ሀገር ከሚመሰረትበት ፅንሰ-ሃሳብ ፍፁም ተቃራኒ ከመሆኑም በላይ በተለያዩ የሕብረተሰብ ክፍሎች መካከል ያለመተማመንና ጥርጣሬ መንፈስ የሚያሰርፅ ነው።
ለምሳሌ በሕገ-መንግስቱ አንቀፅ 39(1) መሰረት፣ ነገ የትኛውም ብሔር፥ ብሔረሰብ፥ ሕዝብ ከተቀሩት የኢትዮጲያ ብሔሮች፥ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች የመገንጠል መብቱ በማናቸውም መልኩ ያለ ገደብ የተጠበቀ ነው። ይህ አንቀፅ “ትላንት ላይ አንድነት አልነበረንም፣ ዛሬ ላይ በልዩነት አለን፣ ነገ ላይ መለያየት እንችላለን” በሚል እሳቤ ላይ የተመሰረተ ነው። በመሆኑም ዛሬ ላይ አብረን እያለን ነገ ላይ ለመለያየት መንገድ ቀይሰናል።
በመሰረቱ በመለያየት መርህ ላይ የተመሰረተ መንግስታዊ ስርዓት ለሀገር አንድነትና ሉዓላዊነት ከፍተኛ ስጋት (threat) ነው። ምክንያቱም ከትላንቱ ታሪክ ጥሩውን እያደበዘዘ መጥፎውን የሚያጎላ፣ ዛሬ ላይ ከሀገራዊ አንድነት ይልቅ የብሔር ልዩነትን የሚያቀነቅን፣ ነገ ላይ ከአብሮነት ይልቅ የመለያየት መንገድ የቀየሰ የፖለቲካ ስርዓት የሀገር ፍቅርና ክብር ከዜጎች ውስጥ ተሟጥጦ እንዲጠፋ ያደርጋል።
የትላንቱን መጥፎ ታሪክ እየሰበክን፣ ዛሬ ላይ ልዩነትን እያጎላን፣ ነገ ላይ ለመለያየት መንገዱን ቀይሰን የወደፊት አብሮነት ሊኖረን አይቻለንም። የወደፊት አብሮነት ከሌለን ዛሬ ላይ አንድነት የለንም። ዛሬ ላይ አንድነት ከሌለን ነገ ላይ አብሮነት አይኖረንም። ዜጎች ለሀገራቸው ፍቅርና ክብር አይኖራቸውም። ይህ የአብሮነት መንፈስን በመሸርሸር የሀገር አንድነት፥ ፍቅርና የዜግነት ክብር ከዜጎች ልብ ውስጥ ተፍቆ እንዲጠፋ ያደርጋል። ስለዚህ ሕገ-መንግስቱ ለሀገር ፀረ-አንድነት ነው!
3ኛ) ሕገ-መንግስቱ ለሕዝብ “ፀረ-ሰላም” ነው!
በዚህ ረገድ የመንግስትን አወቃቀር የሚደነግገውን የሕገ-መንግስቱን አንቀፅ 49 እንደ ማሳያ መጥቀስ ይቻላል። በንዑስ አንቀፅ 2 ላይ የአዲስ አበባ ከተማ መስተዳደር ራሱን በራሱ የማስተዳደር ሙሉ ስልጣን እንዳለው ይጠቅሳል። ቀጥሎ ባለው ንዕስ አንቀፅ 3 ግን “የአዲስ አበባ ከተማ መስተዳደር ተጠሪነቱ ለፌደራሉ መንግስት ይሆናል” ይላል። የአዲስ አበባ ከተማ ራሱን በራሱ የማስተዳደር ሙሉ ስልጣን ካለው የከተማው መስተዳደር ተጠሪነቱ ለአዲስ አበባ ከተማ ምክር ቤት መሆን አለበት። ከዚህ በተጨማሪ፣ አዲስ አበባ ከተማ የፌደራል መንግስት እና የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት “ርዕሰ ከተማ” ናት። በመሆኑም የፌደራሉ መንግስት በአዲስ አበባ ከተማ ላይ ከኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት የተለየ መብትና ስልጣን ሊኖረው አይችልም። ስለዚህ የከተማ መስተዳደሩ ተጠሪነት ለፌደራል መንግስት ብቻ የሚሆንበት አግባብ የለም።
ከዚያ ይልቅ፣ የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪ በሕገ-መንግስቱ መሰረት በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የራሱ መቀመጫ አለው። ከዚህ በተጨማሪ፣ እንደ ማንኛውም ክልል የራሱ የሆነ ምክር ቤት አለው። ስለዚህ የከተማ መስተዳደሩ ተጠሪነቱ የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪዎች ራስን በራስ የማስተዳደር መብታቸውን ተጠቅመው ለመረጡት የከተማ ምክር ቤት መሆን አለበት። የኦሮሚያ ክልል መስተዳደር ተጠሪነቱ ለኦሮሚያ ምክር ቤት (ጨፌ) ነው። የአማራ ክልል መስተዳደር ተጠሪነቱ ለአማራ ክልል ምክር ቤት ነው። የፌደራሉ መንግስት ተጠሪነቱ ለፌደራሉ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ነው። በተመሳሳይ የአዲስ አበባ ከተማ መስተዳደር ተጠሪነቱ በከተማ ነዋሪዎች ለተመረጠ የከተማው ምክር ቤት መሆን አለበት።
ይህ ባለመሆኑ ምክንያት፤ አንደኛ፡- የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪዎች ራስን በራስ የማስተዳደር መብትና ስልጣን ተገፍፏል፣ ሁለተኛ፡- የፌደራሉ መንግስት በከተማዋ ላይ የማይገባውን ስልጣን ተሰጥቶታል፣ ሦስተኛ፡- ይህን የማይገባ ስልጣን በመጠቀም፣ በኦሮሚያ ክልል እና በአዲስ አበባ መስተዳደር መካከል የተቀናጀ የአገልግሎት አቅርቦት፣ የተፈጥሮ ሃብት አጠቃቀም እና አስተዳደራዊ ግንኙነት እንዳይኖር አድርጓል፣ በአንቀፅ 49(5) መሰረት የኦሮሚያ ክልል በአዲስ አበባ ላይ ያለውን ልዩ ጥቅም እንዳይከበር እንቅፋት ሆኗል። በዚህ መሰረት፣ የከተማዋ ነዋሪዎች እና የኦሮሚያ ክልል ሕዝብ ጥቅምና ተጠቃሚነት እንዳይረጋገጥ አድርጓል። የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪዎች የተለያዩ አገልግሎቶች አቅርቦትን አስተጓጉሏል፣ በመኖሪያ ቤትና በትራንስፖርት አገልግሎት እጥረት ተንገላተዋል። ለግንባታ በሚል ሰበብ ነዋሪዎች ከመኖሪያ ቤታቸው ተፈናቅለው መንገድ ላይ ወድቀዋል፣ ለጤና መታወክና ለውሃ ወለድ ወረርሽኝ በሽታ ተጋልጠዋል።
በመሰረቱ መሬት፤ አንደኛ፡- በሀገራችን ዋንኛ የሃብት ምንጭ የብሔሮች፣ ብሄረሰቦችና ሕዝቦች ፍትሃዊ ተጠቃሚነት ማረጋገጫ ነው። ሁለተኛ፡- በሀገራችን ሁኔታ መሬት ከማንነት ጋር የተያያዘ ስለሆነ ብሔር ብሄረሰቦች የማንነት መገለጫዎቻቸውን ማሳደግ የሚችሉት ከመሬት ያለመነቀል ዋስትና ሲያገኙ ነው። ሆኖም ግን፣ በአዲስ አበባ ዙሪያ የሚገኙ የኦሮሞ አርሶ አደሮች ያለ በቂ ካሳ ክፍያ ከመሬታቸው በግፍ ተፈናቅለዋል።
ከዚህ በተጨማሪ፣ ከተማዋ በሚወጣው የተበከለ አየርና ፍሳሽ፣ እንዲሁም ደረቅ ቆሻሻ ምክንያት በማህብረሰቡ ጤንነትና የአከባቢ ደህንነት ላይ ከፍተኛ ጉዳት አድርሷል። ይህ ሁሉ የሆነው በፌደራሉ መንግስት ጣልቃ-ገብነት ምክንያት ነው። ከአዲስ አበባ ማስተር ፕላን ጋር ተያይዞ ከ2006 ዓ.ም ጀምሮ በኦሮሚያ ክልል የተነሳው አመፅና ተቃውሞ፣ በንፁሃን ሕይወትና ንብረት ላይ የደረሰው ጉዳት በሙሉ በፌደራሉ መንግስት ጣልቃ ገብነት ነው። ለጣልቃ ገብነቱ መንስዔ ደግሞ ሕገ-መንግስቱ ነው። ስለዚህ ሕገ-መንግስቱ ለሕዝብ ፀረ-ሰላም ነው!
በአጠቃላይ ሕገ-መንግስቱ የተመሰረተው፤ ለዜጎች ፀረ-እኩልነት፣ ለሀገር ፀረ-አንድነት፣ ለሕዝቦች ፀረ-ሰላም በሆነ ፅንሰ-ሃሳብ ላይ ነው። በዚህ ሕገ-መንግስት መሰረት ላለፉት አመታት የዜጎች መብት፥ የሀገር አንድነት፥ የሕዝብ ሰላም አልተከበረም። ይህን ሕገ-መንግስት ይዞ ስለ ዜጎች መብትና ነፃነት፣ ስለ ሀገር አንድነትና ሉዓላዊነት፣ ስለ ሕዝብ ሰላምና ደህንነት ማውራት፥ መናገር፥ መደስኮር፥ … ከቶ እንዴት ይቻላል? ይህን ሕገ-መንግስት ይዞ ጉዞ “የዘንጀሮ መንገድ ቢከተሉት ገደል” የሚሉት ዓይነት ነው!
Hiber radio Las Vegas ይህ ህብር ሬድዮ _የወቅታዊ መረጃ ምንጭ ነው። ህብር ሬድዮ በአቤኔዘር ኮሙኒኬሽን ሴንተር እየተዘጋጀ ከላስ ቬጋስ ከተማ፣ ዘወትር ዕሁድ በአካባቢው ሰዓት አቆጣጠር ከምሽቱ 6፤30 ሰዓት እስከ 8 ሰዓት በህብር ሬዲዮ ድህረ ገጽ ወይም በቀጥታ በስልክ ለማዳመጥ 5639993994 ወይም 563999-3988 ወይም 712-432-8451 በመረጡት ቁጥር መደወል ብቻ በቂ ነው በእንግሊዝ ለምትኖሩ በ01405770140 በስልክ ማዳመጥ ይቻላል። ዘወትር በድህረ ገጻችን፣ ከ googel app store Hiber Radio ወደ ስልክዎ በመጫን ካልሆነም በዘሐበሻ እንዲሁም በተጠቀሱት ስልኮች ማዳመጥ ይቻላል።