Hiber Radio: የሽግግር መንግስት ስለማቋቋም የቀረበ ዝክረ ሃሳብ /ሊያነቡት የሚገባ በጦማሪ ስዩም ተሾመ የቀረበ

 የሽግግር መንግስት ስለማቋቋም የቀረበ ዝክረ ሃሳብ

በስዩም ተሾመ

መግቢያ

ሀገራችን ያለችበት የፖለቲካ ቀውስ ለበጎ ወይም ለመጥፎ ክስተቶች ምቹ አጋጣሚ ፈጥሯል። በአንድ በኩል፣ በተወሰነ አከባቢ የተከሰተ ግጭትና አለመረጋጋት ባልተጠበቀ መልኩ በብዙ ሰዎች ሕይወትና ንብረት ላይ ጉዳት ያስለትላል። በሌላ በኩል፣ የሀገሪቱን ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች በዘላቂነት ለመቅረፍ የሚያስችል ሥር-ነቀል ለውጥና መሻሻል ለማድረግ እንደ ምቹ አጋጣሚ ሊወሰድ ይችላል። ባለፉት ሁለት አስርት አመታት በተግባር እንደታየው የህወሓት/ኢህአዴግ መንግስት ከተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች የሚነሳውን የመብት፥ ነፃነትና ፍትሃዊ ተጠቃሚነት ጥያቄ በኃይል ከማፈንና ከማዳፈን በዘለለ ዘላቂ መፍትሄ ለመስጠት ጥረት ሲያደርግ አይስተዋልም። የሕዝብን ጥያቄ በኃይልና ጉልበት ለመቆጣጠር የሚደረግ ማንኛውም ጥረት ሁኔታዎችን ይበልጥ እያባባሰ ዛሬ ላይ ደርሰናል። ሁኔታዎች በዚሁ ከቀጠሉ ሀገሪቱ ወደ ለየለት የእርስ በእርስ ግጭትና ጦርነት መግባቷ አይቀሬ ነው። ስለዚህ የሕዝብን ጥያቄ ተቀብሎ ማስተናገድ የተሳነው የፖለቲካ ቡድን በሀገር ላይ የመጨረሻ ውድቀት፣ በሕዝብ ላይ የባሰ ዕልቂት ከማስከተሉ በፊት ሁላችንም ችግሩን ለመፍታት መረባረብ አለብን። በዚህ ፅሁፍ የሀገራችን ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች በዘላቂነት ለመፍታት ያስችላል ያልኩትን የመፍትሄ ሃሳብ አቅርቤያለሁ። ሁላችሁም በጉዳዩ ላይ ተጨማሪ ሃሳብና አስተያየት በመስጠት ዝክረ ሃሳቡን ይበልጥ ማዳበርና በተቀናጀ መልኩ ተግባራዊ ማድረግ ይቻላል። በዚህ መሰረት፣ ሀገርና ሕዝብን ከለየለት የእርስ በእርስ ጦርነትና ግጭት እንታደጋለን ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ።

1 የዜጎች ጥያቄ እና የመንግስት ጭቆና

በተለያዩ የሀገሪቱ አከባቢዎች ለሚታዩት የፖለቲካ ግጭቶችና አለመረጋጋቶች በስተጀርባ ያለው የዴሞክራሲ ጥያቄ ነው። በተለያየ ቦታና ግዜ ከሕዝብ የሚነሱት በጥቅሉ የመብት፥ ነፃነትና ፍትሃዊ ተጠቃሚነት ጥያቄዎች ናቸው። ለእነዚህ ጥያቄዎች ዘላቂ መፍትሄ መስጠት የሚቻለው በእኩልነት መርህ ላይ የተመሰረተ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት መዘርጋት ሲቻል ነው። በእርግጥ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት የሁሉንም መብት፥ ነፃነትና ተጠቃሚነት በአንድ ግዜ ማረጋገጥ አያስችልም። ነገር ግን፣ የስርዓቱ መሰረታዊ ዓላማና ፋይዳ ሁሉም ዜጎች “እኩል” መብትና ነፃነት፣ እንዲሁም ፍትሃዊ ተጠቃሚነት እንዲኖራቸው ማስቻል ነው። በመሆኑም የዜጎች ጥያቄ እና የዴሞክራሲያዊ መንግስት ፋይዳ አንድና ተመሳሳይ ሲሆን እሱም “እኩልነት” ነው።

ዴሞክራሲያዊ መንግስት ከተለያዩ የሕብረተሰብ ክፍሎች ለሚነሱ የመብት፥ ነፃነትና ፍትሃዊ ተጠቃሚነት ጥያቄዎች ተገቢ ምላሽ ለመስጠት የሚያስችል መዋቅር፥ ተቋማት እና አሰራር ይዘረጋል። በዚህ መሰረት የመንግስት መዋቅር፥ ተቋማትና የአሰራር ሂደት በእኩልነት መርህ ላይ የተመሰረቱ ይሆናል። በሌላ በኩል፣ የዜጎች ጥያቄ ደግሞ “እኩል መብት፥ ነፃነትና ፍትሃዊ ተጠቃሚነት ሊኖረን ይገባል” በሚል እሳቤ ላይ የተመሰረተ ነው። ስለዚህ መንግስት በሚመራበት መርህ እና ዜጎች በሚያነሱት ጥያቄ መካከል ልዩነት የለም። በመሆኑም በደሞክራሲያዊ ስርዓት ውስጥ የዜጎች ፖለቲካዊ ጥያቄ ለግጭትና አለመረጋጋት መንስዔ ሊሆን አይችልም።

በየትኛውም የፖለቲካ ማህብረሰብ ዘንድ የዜጎች ጥያቄ “እኩል መብት፥ ነፃነትና ፍትሃዊ ተጠቃሚነት” የሚለው ነው። በዚህ መልኩ ዜጎች የሚነሱት የእኩልነት ጥያቄ ለግጭትና አለመረጋጋት መንስዔ የሚሆነው በእኩልነት መርህ ላይ ያልተመሰረተ መንግስታዊ ስርዓት ሲኖር ነው። በእኩልነት መርህ ላይ ያልተመሰረተ መንግስታዊ ስርዓት መሰረታዊ ዓላማና ፋይዳ የአንድ ወገን የበላይነትና ተጠቃሚነትን ማረጋገጥ ነው። በመሆኑም የመንግስት መዋቅር፥ ተቋማት እና አሰራር የአንድ ወገን የበላይነትና ተጠቃሚነትን የሚያረጋግጥ፣ ለዚህም የዜጎችን ዴሞክራሲያዊ ጥያቄ በኃይል የሚያፍንና የሚያዳፍን ጨቋኝና አምባገነን ይሆናል።

የአምባገነናዊ መንግስት አወቃቀር፥ ተቋማትና የተግባር መርህና አሰራር የዜጎችን ዴሞክራሲ ጥያቄ ተቀብሎ ለማስተናገድ አያስችሉም። ምክንያቱም የዜጎች ጥያቄ ከመንግስታዊ ስርዓቱ ዓላማና የተግባር መርህ ጋር ይጋጫል። የአምባገነናዊ ስርዓት መሰረታዊ ዓላማ የአንድ ወገን የበላይነትና ተጠቃሚነትን ማረጋገጥ ሲሆን ተግባራዊ እንቅስቃሴው የሚመራው በፍርሃት

መርህና መመሪያ ነው። የአንድ ወገን የበላይነት፣ ተጠቃሚነትና ፍርሃትን ለማረጋገጥ የሚደረግ ነገር በሙሉ የብዙሃኑን መብት፥ ነፃነትና ፍትሃዊ ተጠቃሚነት ይፃረራል። በአንፃሩ የብዙሃኑን መብት፥ ነፃነትና ፍትሃዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የሚደረግ ማንኛውም ነገር የአንድ ወገን የበላይነት፥ ተጠቃሚነትና ፍርሃትን ያስወግዳል።

እንደ ማንኛውም የፖለቲካ ማህብረሰብ የሀገራችን ዜጎች የሚያነሱት የመብት፥ ነፃነትና ፍትሃዊ ተጠቃሚነት ጥያቄ ነው። በተለይ ባለፉት ሦስት አመታት ሀገሪቱ ወደ ፖለቲካዊ ግጭትና አለመረጋጋት ውስጥ የገባቸው እነዚህ ጥያቄዎች ተገቢ ምላሽ ስላልተሰጣቸው ነው። ይህ የሆነበት መሰረታዊ ምክንያት ደግሞ በስልጣን ላይ ያለው መንግስት ከተለያዩ የሕብረተሰብ ክፍሎች የሚነሱ የመብት፥ ነፃነትና ፍትሃዊ ተጠቃሚነት ጥያቄዎችን ተቀብሎ ለማስተናገድ የሚያስችል መዋቅር፥ ተቋማትና አሰራር ስለሌለው ነው። ምክንያቱም የኢህአዴግ መንግስት የአንድ ወገን የበላይነትና ተጠቃሚነትን በማረጋገጥ ላይ የተመሰረተና በፍርሃት መርህና መመሪያ የሚመራ ጨቋኝና አምባገነን ነው።

በመሰረቱ ዜጎች የሚያነሷቸው የመብት፥ ነፃነትና ፍትሃዊ ተጠቃሚነት ጥያቄዎች ወደ ፖለቲካዊ ግጭትና አለመረጋጋት የሚያመሩት መንግስታዊ ስርዓቱ በእኩልነት መርህ ያልተመሰረተ ከሆነና ከሆነ ብቻ ነው። ምክንያቱም በእኩልነት መርህ ላይ የተመሰረተ መንግስታዊ ስርዓት ከተለያዩ የሕብረተሰብ ክፍሎች የሚነሱ የመብት፥ ነፃነትና ፍትሃዊ ተጠቃሚነት ጥያቄዎችን ተቀብሎ ለማስተናገድና ተገቢ ምላሽ ለመስጠት የሚያስችል መዋቅር፥ ተቋማትና የአሰራር ሂደቶች ይኖሩታል። አምባገነናዊ ስርዓት ግን ከብዙሃኑ መብትና ፍትሃዊ ተጠቃሚነት ይልቅ የጥቂቶችን የበላይነትና ተጠቃሚነት የሚያረጋግጥ፣ የነፃነት ጥያቄን በፍርሃት ቆፈን ለማፈን ጥረት ያደርጋል።

የአምባገነናዊ መንግስት መሰረታዊ ባህሪ፥ ፋይዳና የተግባር መርህ ከብዙሃኑ የሕብረተሰብ ክፍል ፍላጎት፥ ምርጫና ጥያቄ አንፃር ተፃራሪ ነው። በመሆኑም እያንዳንዱ የዜጎች ፖለቲካዊ እንቅስቃሴ ለመንግስታዊ ስርዓቱ ስጋትና አደጋ ነው። በሌላ በኩል፣ እያንዳንዱ የመንግስት እንቅስቃሴ የዜጎችን መብትና እኩልነት የሚፃረር ነው። በመሆኑም እያንዳንዱ ፖለቲካዊ እንቅስቃሴ በመንግስትና ዜጎች መካከል ግጭትና አለመግባባት ያስከትላል። ከግዜ ወደ ግዜ ፖለቲካዊ ግጭትና አለመረጋጋት እየተስፋፋ ይሄዳል። አሁን ያለው ፖለቲካዊ ቀውስ በዜጎች የእኩልነት ጥያቄ እና በመንግስት አምባገነናዊ ጭቆና መካከል በተፈጠረ ግጭት ምክንያት የተከሰተ ነው።

ከላይ በተገለፀው መሰረት፣ አሁን በሀገራችን የሚስተዋለው የፖለቲካ ቀውስ መንስዔው በዜጎች የእኩልነት ጥያቄ እና በመንግስት አምባገነናዊ ጭቆና መካከል የተፈጠረው ግጭት ነው። የችግሩ መንስዔ አንድ እንደመሆኑ መፍትሄውም አንድና ተመሳሳይ ነው። በዜጎች እና መንግስት መካከል ያለው ግጭት የችግሩ መንስዔ ከሆነ መፍትሄው በሁለቱ መካከል ያለውን ግጭት ማስቀረት ነው። ግጭቱን ማስቀረት የሚቻለው የብዙሃኑን መብትና ፍትሃዊ ተጠቃሚነት ማረጋገጥ ሲቻል ነው። የብዙሃኑን መብትና ፍትሃዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ደግሞ በእኩልነት መርህ ላይ የተመሰረተ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት መዘርጋት የግድ አስፈላጊ ነው።

ዴሞክራሲያዊ ስርዓት በመዘርጋት የብዙሃኑን መብትና ፍትሃዊ ተጠቃሚነት ማረጋገጥ የሚቻለው በአንድ ወገን የበላይነትና ተጠቃሚነት ላይ የተመሰረተ አምባገነናዊ ስርዓትን ማስወገድ ሲቻል ነው። በአጠቃላይ ለዜጎች የዴሞክራሲ ጥያቄ ተገቢ ምላሽ ለመስጠት እና/ወይም በዜጎች ላይ የሚፈፀመውን ጭቆና ለማስቀረት፣ በዚህም በዜጎችና መንግስት መካከል ያለውን ልዩነትና ግጭት ለማስወገድ፣ የመንግስት ተግባራዊ እንቅስቃሴ በሙሉ በእኩልነት መርህ የሚመራ ሊሆን ይገባል። ለዚህ ደግሞ ሕገ-መንግስቱን መሰረት በማድረግ የሚወጡ የሕግ አዋጆች፥ ደንቦችና መመሪያዎች በሙሉ በእኩልነት መርህ ላይ የተመሰረቱ መሆን አለባቸው።

2 መንግስት እና ሕገ መንግስት 

በመሰረቱ የመንግስት ተግባርና አንቅስቃሴ በዘፈቀደ የሚከናወን አይደለም። ማንኛውም ዓይነት ተግባርና እንቅስቃሴ ሕጋዊ መሰረት ከሌለው ተፈፃሚ ሊሆን አይችልም። በአጠቃላይ ማንኛውም ዓይነት የመንግስት እንቅስቃሴ ሕገ-መንግስቱን የሚቃረን መሆን የለበትም። ሕገ መንግስት የሀገሪቱ የበላይ ሕግ እንደመሆኑ ማንኛውም ሕግ፥ ደንብ፥ መመሪያ፣ ልማዳዊ አሰራር፣ እንዲሁም የመንግስት አካል ወይም ባለስልጣን ውሳኔ ሕገ-መንግስቱን የሚቃረን ከሆነ ተፈፃሚነት አይኖረውም። ከዚህ በተጨማሪ፣ ማንኛውም ዜጋ፥ የመንግስት አካላት፥ የፖለቲካ ድርጅቶች፥ ሌሎች ማህበራት እንዲሁም ባለስልጣኖቻቸው ሕገ መንግስቱን የማስከበርና ለሕገ መንግስቱ ተገዢ የመሆን ኃላፊነት አለባቸው።

በዚህ መሰረት፣ በመንግስት አካልት የሚረቀቁ፥ የሚፀድቁና ተግባራዊ የሚደረጉ ሕጎች፥ ደንቦች ወይም መመሪያዎች፣ እንዲሁም አሰራሮችና ውሳኔዎች ሕገ-መንግስቱን የሚቃረኑ ከሆነ ተፈፃሚ አይሆኑም። ስለዚህ በሕገ-መንግስቱ የተደነገጉ የዜጎች ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶችና ነፃነቶችን የሚቃረኑ ሕጎች፥ ደንቦች፥ መመሪያዎች፥ አሰራሮች፥ ውሳኔዎች ወይም ሌሎች ተግባራት በዜጎች፥ በመንግስት አካላት፥ በፖለቲካ ድርጅቶች እና ሌሎች ማህበራት ዘንድ ተቀባይነት ሆነ ተፈፃሚነት ሊኖራቸው አይችልም።

ነገር ግን፣ ባለፉት አስር አመታት በተግባር እንደታየው፣ በፀረ-ሽብር አዋጁ አማካኝነት በሺህ የሚቆጠሩ ዜጎች ተከስሰዋል፥ ታስረዋል፥ ተፈርዶባቸዋል፣ ለስቃይ፥ ስደት፥ የአክል ጉዳትና ሞት ተዳርገዋል። በመሆኑም የኢህአዴግ መንግስት በሕገ-መንግስቱ የተደነገጉ መብቶችና ነፃነቶችን የሚቃረኑ ሕጎች፥ ደንቦች፥ መመሪያዎች፥ አሰራሮች፥ ውሳኔዎች ወይም ሌሎች ተግባራት ፈፅሟል። በፀረ-ሽብር አዋጁ አማካኝነት በገዳም ከሚኖሩ መነኩሴዎች እስከ የእስልምና ሃይማኖት መሪዎችን በአሸባሪነት ከስሷል፤ በመንግስት ሥራና አሰራር ላይ ግልፅነትና ተጠያቂነት እንዲሰፍን ወይም የዜጎች መብትና ነፃነት እንዲከበር የጠየቁ ጋዜጠኞች፥ የመብት ተሟጋቾች፥ ፖለቲከኞችን፥ ምሁራን፥…ወዘተ በፀረ-ሽብር አዋጁ ተከስሰው ለእስርና ስደት ተዳርገዋል፣ በእስር ቤት አስከፊ ስቃይና መከራ ደርሶባቸዋል። በዚህ መሰረት፣ በፀረ-ሽብር አዋጁ አማካኝነት ብቻ የሕገ-መንግስቱ የበላይነት ሙሉ በሙሉ ተንዷል።

በኢፊዲሪ ሕገ መንግስት አንቀፅ (9) መሰረት፣ “ሕገ መንግስቱ የሀገሪቱ የበላይ ሕግ እንደሆነና ማንኛውም ሕግ፥ ደንብ፥ መመሪያ፣ ልማዳዊ አሰራር፣ እንዲሁም የመንግስት አካል ወይም ባለስልጣን ውሳኔ ሕገ-መንግስቱን የሚቃረን ከሆነ ተፈፃሚነት አይኖረውም” ይላል። በእርግጥ የፀረ-ሽብር ሕጉ በሀገሪቱ ዜጎች፥ የፖለቲካ ድርጅቶች፣ ሚዲያዎች፣ ሲቪል ማህበራት እና ሌሎች የሕብረተሰብ ክፍሎች ዘንድ ተቀባይነት የለውም። ምክንያቱም ማንኛውም የሕብረተሰብ ክፍል በራሱ ላይ በደልና ጭቆና ለመፈፀም የሚያገለግል የሕግ አዋጅን አይቀበልም። ነገር ግን፣ የፀረ-ሽብር አዋጁ ላለፉት ዘጠኝ አመታት በሕግ አውጪዎች፥ ሕግ ተርጓሚዎችና ሕግ አስፈፃሚዎች ዘንድ ተቀባይነት አግኝቶ ተግባራዊ ተደርጓል። ሕገ-መንግስታዊ መሰረት ከሌለው የኢህአዴግ መንግስት የፀረ-ሽብር አዋጁን ማርቀቅ፥ ማፅደቅ ሆነ ተግባራዊ ማድረግ አይችልም። ስለዚህ የኢፊዲሪ ሕገ-መንግስት ራሱን የሚቃረኑ ሕጎችን፥ ደንቦችን፥ መመሪያዎችን፥ አሰራሮችን ወይም ውሳኔዎችን ተግባራዊ እንዲሆኑ የሚያስችል መርህ በውስጡ አካትቷል። በመሆኑም ሕገ መንግስቱ ራሱን በራሱ ይጥሳል።

ሕገ መንግስቱ ራሱን በራሱ የሚቃረንበት መሰረታዊ ምክንያት በሕገ መንግስቱ አንቀፅ (8) ላይ የተደነገገው “የሕዝብ ሉዓላዊነት” የሚለው መርህ ነው። በዚህ አንቀፅ “የኢትዮጲያ ብሔሮች፥ ብሔረሰቦች፥ ሕዝቦች የኢትዮጲያ ሉዓላዊ ስልጣን ባለቤቶች ናቸው” በማለት ይደነግጋል። ነገር ግን፣ ይህ ሕገ መንግስታዊ መርህ፤ አንደኛ፡- ከመንግስት አመሰራረት ሂደት፥ ከነፃነት፥ ሉዓላዊነትና ማህበራዊ-ውል ፅንሰ-ሃሳቦች ጋር ይጋጫል፣ ሁለተኛ፡- ከተቀሩት የሕገ-መንግስቱ መሰረታዊ መርሆች፣ የዜጎች ዴሞክራሲያዊ መብቶችና ነፃነቶች፣ ሌሎች የሕገ-መንግስቱ ድንጋጌዎች፥ የብሔራዊ ፖሊሲ መርሆችና ዓላማዎች ጋር ይጋጫል፥ ይጥሳል፥ ይገድባል።

በመሰረቱ የሉዓላዊ ስልጣን ባለቤት የሆነ አካል ባለመብት ብቻ ሳይሆን የበላይ ባለስልጣን ጭምር ነው። የሉዓላዊ ስልጣን ባለቤት የሆነ አካል በሀገሪቱ ሕዝብና መንግስት ላይ የስልጣን የበላይነት ይኖረዋል። ስለዚህ፣ የሀገሪቱ መንግስት ተጠሪነቱ ለዚህ አካል ይሆናል። በኢፊዲሪ ሕገ-መንግስት ሦስተኛ ምዕራፍ ስር የዜጎች ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶችና ነፃነቶች በግልፅ ተዘርዝረዋል። ሆኖም ግን፣ በአንቀፅ (8) መሰረት፣ የሀገሪቱ ዜጎች የሉዓላዊ ስልጣን ባለቤት አይደሉም። ስለዚህ የኢትዮጲያ ዜጎች መብታቸውን የመጠየቅ መብት ወይም ስልጣን የላቸውም። በሌላ በኩል፣ የኢትዮጲያ ብሔሮች፥ ብሔረሰቦች፥ ሕዝቦች በሕገ-መንግስቱ መሰረት የተሰጣቸውን ሉዓላዊ ስልጣን በቀጥታ መጠቀም ሆነ መጠየቅ አይችሉም።

የዜጎች ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ (ተፈጥሯዊና ፖለቲካዊ) መብቶች በሕገ-መንግስቱ የተዘረዘሩ ቢሆንም ሕገ-መንግስታዊ መብታቸው እንዲከበር የመጠየቅ ስልጣን የላቸውም። የኢትዮጲያ ብሔሮች፥ ብሔረሰቦች፥ ሕዝቦች የሉዓላዊ ስልጣን ባለቤት ቢሆኑም መብታቸውን በራሳቸው መጠየቅ ሆነ መጠቀም አይችሉም። ዜጎች ደግሞ በቡድን ተደራጅተው የብሔሮች፥ ብሔረሰቦች፥ ሕዝቦች መብትና ተጠቃሚነት እንዲከበር የመጠየቅ ሉዓላዊ መብትና ስልጣን የላቸውም። በዚህ መሰረት፣ የኢትዮጲያ ዜጎች የማይጠይቁት መብት ሲኖራቸው የኢትዮጲያ ብሔሮች፥ ብሔረሰቦች፥ ሕዝቦች ደግሞ የማይጠቀሙበት የስልጣን አላቸው።

የኢትዮጵያ ሕዝብ (ዜጎች) የሉዓላዊ ስልጣን ባለቤትነት ስለሌላቸው በሕገ-መንግስቱ የተደነገጉ ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶችና ነፃነቶችን የመጠየቅ፥ የማስከበር፥ የማሻሻል፥ የመቀየር፥… የፖለቲካ ስልጣን የላቸውም። ስለዚህ በሕገ-መንግስቱ የተደነገጉ መብቶችና ነፃነቶችን ተግባራዊ ማድረግ ወይም መጠቀም አይችሉም። የኢትዮጲያ ብሔሮች፥ ብሔረሰቦች፥ ሕዝቦች የሉዓላዊ ስልጣን ባለቤቶች ቢሆኑም በሕገ-መንግስቱ የተደነገጉ ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶችን ለመጠየቅ፥ ለመጣስ፥ ለማክበር፥ ለማስከበር፥ ለማሻሻል፥ ለመቀየር፥… የሚያስችል ተፈጥሯዊ ባህሪ የላቸውም። ስለዚህ እንደ ሰው ሉዓላዊነታቸውን፥ የስልጣን የበላይነታቸውን ተግባራዊ ማድረግ ወይም በተግባር ማረጋገጥ አይችሉም። በመሆኑም የኢትዮጲያ ዜጎች በሀገራቸውና መንግስታቸው ላይ ሉዓላዊ መብትና ስልጣን፣ የሰልጣን ባለቤትነትና የበላይነት የላቸውም። በአንፃሩ የኢትዮጲያ ብሔሮች፥ ብሔረሰቦች፥ ሕዝቦች በሕገ-መንግስቱ በተሰጣቸው ሉዓላዊ ስልጣን መሰረት በራሳቸው ምንም ማድረግ አይችሉም፤ የራሳቸውን ሆነ የዜጎችን መብት አይጥሱም፥ አያከብሩም፥ አያስከብሩም፥…ወዘተ።

በሕገ-መንግስቱ አንቀፅ(8) መሰረት “የሕዝብ ሉዓላዊነት” በሚለው መርህ ምክንያት የተቀሩት የሕገ-መንግስቱ መሰረታዊ መርሆች፣ የዜጎች ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶችና ነፃነቶች፣ እንዲሁም ሌሎች ድንጋጌዎች፥ ብሔራዊ ፖሊሲዎችና ዓላማዎች በሙሉ ፋይዳ-ቢስ ሆነዋል። ባለፉት አስር አመታት ይህን የተሳሳተ ሕገ-መንግስታዊ መርህ መሰረት በማድረግ የተለያዩ አዋጆች፥ መመሪያዎች፥ አሰራሮች እና ውሳኔዎች ተግባራዊ ተደርገዋል። ከእነዚህ ውስጥ፤ የፀረ-ሽብር አዋጅ፣ የመረጃ ነፃነትና ሚዲያ አዋጅ፣ የበጎ አድራጎት ድርጅቶችና ማህበራት ሕብረት መመሪያ፣ የኮምፒውተር ነክ ወንጀሎች አዋጅ፣ የብሔራዊ መረጃና ደህንነት መስሪያ ቤት እና የመረጃ መረብ ደህንነት ኤጀንሲ በዜጎች ላይ የሚያደርጉት ጥብቅ ክትትልና ቁጥጥር፣ እንዲሁም የኢትዮጲያ ቴሌኮምኒኬሽን ኮርፖሬሽን በተደጋጋሚ የኢንተርኔት አገልግሎትን ማቋረጥ እና የመሳሰሉትን መጥቀስ ይቻላል።

በዚህ መሰረት፣ በተሳሳተ መርህ ላይ የተመሰረቱ አዋጆች፥ መመሪያዎች፥ አሰራሮችና የባለስልጣናት ውሳኔዎች በሕገ መንግስቱ የተደነገጉ መሰረታዊ መብቶችና ነፃነቶችን፥ የመንግስት አወቃቀርና ኃላፊነትን፣ እንዲሁም ብሔራዊ ዓላማዎች እና ሌሎች ድንጋጌዎችን የሚቃረኑ ናቸው። በመሆኑም ሕገ-መንግስቱ ራሱን በራሱ እንዲቃረን፥ እንዲጥስና እንዲያፈርስ አድርገውታል። ከዚህ በተጨማሪ፣ እነዚህ የሕግ ማዕቀፎች በሀገሪቱ ውስጥ የተለየ ሃሳብና አመለካከት የሚያስተናግዱ ነፃና ገለልተኛ ሚዲያዎች እንዲጠፉ፣ የሙያና ሲቪል ማህበራት የሚጠበቅባቸውን ሚናና ኃላፊነት በአግባቡ እንዳይወጡ፣ የተቃዋሚ ፖለቲካ ፓርቲ መሪዎችና አባላትን፥ ጋዜጠኞችና የመብት ተሟጋቾች ለእስር፥ ስደት፥ እንግልትና ሞት የተዳረጉት ከላይ በተጠቀሱት አፍራሽ አዋጆች፥ መመሪያዎች፥ አሰራሮችና ውሳኔዎች ምክንያት ነው። በዚህ ምክንያት ሕገ-መንግስታዊ ስርዓቱ ራሱን በራሱ አፍርሷል፣ የዴሞክራሲ መዋቅርና ተቋማት ሙሉ በሙሉ ፈርሰዋል።

3 እድገት እና ተሃድሶ

3.1 የኢኮኖሚ እድገት

የሀገሪቱ ኢኮኖሚ ፈጣን እድገት እንዲያስመዘግብ እና ፍትሃዊ የሀብት ክፍፍል እንዲኖር ለማስቻል በዓለም አቀፍ ገበያ ተወዳዳሪ የሆኑ የቢዝነስ ተቋማትን መፍጠር፥ ማሳደግና ማስፋፋት ያስፈልጋል። ለዚህ ደግሞ የሀገር ውስጥና የውጪ ባለሃብቶች በተለያዩ የሥራ መስኮች እንዲሰማሩ በማድረግ አዳዲስ የሥራ ፈጠራዎችና የቢዝነስ እንቅስቃሴዎች ሊኖሩ ይገባል። ሆኖም ግን፣ በሀገር አቀፍ ደረጃ በኢትዮጲያ ያለው የሥራ ፈጠራና የቢዝነስ እንቅስቃሴ በጣም ደካማ ነው። ለዚህ ደግሞ በጉምሩክና ታክስ አስተዳደር፣ በመሬት፥ ብድርና የውጪ-ምንዛሬ አቅርቦት፣ በኢንቨስትመንት ማበረታቻና ድጋፍ አሰጣጥ ረገድ የሚስተዋሉ ክፍተቶች፣ አድሏዊና ብልሹ አሰራሮች በምክንያትነት ይጠቀሳሉ።

ለምሳሌ በተባበሩት መንግስታት1፥ የዓለም ባንክ2 እና አንዳንድ ምሁራን3 በዘርፉ የሚንቀሳቀሱ የቢዝነስ ፈጣሪዎችን (entrepreneurs) ዋቢ በማድረግ በሰሯቸው ጥናቶች ለዘርፉ እድገት ዋና ማነቆ የሆነው ችግር አንድና ተመሳሳይ መሆኑን አረጋግጠዋል። በኢትዮጲያ የኢንዱስትሪ ዘርፍ ለአዳዲስ ቢዝነሶች እድገትና መስፋፋት ማነቆ የሆነው ችግር፤ አንደኛ፡- አዳዲስና አነስተኛ የግል ቢዝነስ ተቋማት በመሬት፥ ብድርና የውጪ ምንዛሬ አቅርቦት ረገድ አስፈላጊው ድጋፍና ማበረታቻ አይደረግላቸውም፣ ሁለተኛ፡- እነዚሁ የግል ቢዝነስ ተቋማት የተሻለ የመሬት፥ ብድርና የውጪ ምንዛሬ አቅርቦት፣ እንዲሁም የላቀ ድጋፍና ማበረታቻ ከሚደረግላቸው የመንግስት ድርጅቶች (State-owned enterprises)፥ የኢንዶውመንት ድርጅቶች (party-affiliated endowments) እና አንዳንድ የውጪ ድርጅቶች ጋር ፍትሃዊ ባልሆነ የገበያ ውድድር ውስጥ መግባታቸው እንደሆነ ከላይ የተጠቀሱት የጥናት ውጤቶች አረጋግጠዋል። በሌላ በኩል፣ እ.አ.አ. በ2009 ዓ.ም በዓለም ባንክ የተሰራ ጥናት፣ ከላይ የተጠቀሱት ለአዳዲስና አነስተኛ የግል ቢዝነስ ተቋማት እድገት ማነቆ የሆኑ ችግሮች ለመንግስት እና ኢንዶውመንት ድርጅቶች አሳሳቢ አለመሆናቸውን ይገልፃል4።

ከላይ በተጠቀሱት የጥናት ውጤቶች መሰረት፣ በግል የቢዝነስ ተቋማት እና በመንግስትና ኢንዶውመንት ድርጅቶች መካከል መሰረታዊ የሆነ ልዩነት መኖሩን መገንዘብ ይቻላል። “Tilman A. (2010)” የተባለ ጀርመናዊ የስነ-ምጣኔ ምሁር “Industrial policy in Ethiopia*5” በሚል ርዕስ ባካሄዱት ጥናት በግል የቢዝነስ ድርጅቶች እና በመንግስትና ኢንዶውመንት ድርጅቶች መካከል የሚስተዋለው ልዩነት በዋናነት የፖለቲካዊ ስርዓቱ ውጤት እንደሆነ ይገልፃል። እንደ እሱ አገላለፅ፣ ኢትዮጲያ ውስጥ ፖለቲካ እና ቢዝነሱ እርስ-በእርሱ የተጠላለፈ ነው፡-

“…business and politics are still strongly entwined in Ethiopia. State-owned enterprises (SOEs) still dominate many manufacturing industries and service sectors, and party-affiliated endowments have taken many of the business opportunities left for private engagement. To date Ethiopia is clearly anything but a predatory state whose government pillages the economy.  …Power constellations may change, those who have vested interests in SOEs and endowment-owned enterprises may gain political influence, and political power shifts may force political leaders to compromise on their development agenda.”  Tilman A. (2010): Industrial policy in Ethiopia / Tilman Altenburg. – Bonn : DIE, 2010. − (Discussion Paper / Deutsches Institut für Entwicklungspolitik ; 2/2010) ISBN 978-3-88985-477-3

ከላይ በተገለፀው መሰረት፣ የመንግስት ድርጅቶች የማምረቻና አገልግሎት ኢንዱስትሪውን በበላይነት የተቆጣጠሩ ሲሆን የኢንዶውመንት ድርጅቶቹ ለግል ድርጅቶች የሚሆነውን ዘርፍ ተቀራምተውታል። እስካሁን ድረስ በስልጣን ላይ ያለው መንግስት ኪራይ ሰብሳቢ እና ጥገኛ ከመሆኑም በላይ የፖለቲካ ለውጥ በሚኖርበት ግዜ የመንግስትና ኢንዶውመንት ድርጅቶቹን የፖለቲካ ተፅዕኖ ለመፍጠር እንደሚጠቀምባቸው ይገልፃል። በዚህ መሰረት፣ የመንግስትና ኢንዶውመንት ድርጅቶች ለግል ቢዝነስ ተቋማት እድገትና ማስፋፋት ማነቆ ከመሆናቸው በተጨማሪ በፖለቲካዊ ስርዓቱ ላይ ለውጥና መሻሻል እንዳይመጣ እንቅፋት ናቸው።

በሀገራችን ኢኮኖሚና ፖለቲካ መካከል የሚስተዋለው መጠላለፍ በዋናነት የህወሓትን የበላይነት ከማረጋገጥ ጋራ የተያያዘ ነው። ከዚህ አንፃር የመንግስት እና ኢንዶውመንት ድርጅቶች በሀገሪቱ ፖለቲካ ላይ እያሳደሩት ያለው ተፅዕኖ መመልከት ይቻላል። ለምሳሌ ከሶማሌ ክልል ለተፈናቀሉ የኦሮሚያ ክልል ነዋሪዎች በ700 የመልዕክት አድራሻ የተጀመረው የድጋፍ ማሰባሰቢያ እንዲቋረጥ የተደረገው በአብዲ አሊ አቤቱታና በዶ/ር ደብረፂዮን ገ/ሚካኤል ትዕዛዝ ነው። በተመሳሳይ የኢንተርኔት አገልግሎት ከአዲስ አበባ በስተቀር በመላው ሀገሪቱ እንዲቋረጥ የተደረገው በዶ/ር ደብረፂዮን ትዕዛዝ ስለመሆኑ ጥርጥር የለውም። የብረታብረትና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን እና የመከላከያ ኮንስትራክሽን በዋናነት በህወሓት ጄኔራሎች የሚመሩ ናቸው። የብሔራዊ መረጃና ደህንነት መስሪያ ቤት እና የመረጃ መረብ ደህንነት ኤጀንሲ ሙሉ በሙሉ በህወሓት አባላትና ደጋፊዎች የሚመሩ ናቸው።

እነዚህን የመንግስት ድርጅቶችና ኤጀንሲዎች የሚመሩት ከፍተኛ የህወሓት አባላትና አመራሮች 40 ቢሊዮን ዶላር ካፒታል ካለው “EFFORT” ጋር ቀጥተኛ እና/ወይም ተዘዋዋሪ የሆነ የጥቅም ትስስር አላቸው። ስለዚህ ለአዳዲስና ጀማሪ የሆኑ አነስተኛና መካከለኛ የግል ቢዝነስ ተቋማትን ምቹ ሁኔታ መፍጠር የሚቻለው የመንግስት እና ኢንዶውመንት ድርጅቶች በኢንዱስትሪ ዘርፉ ላይ የሚያሳድሩትን ተፅዕኖ በመቀነስ እና/ወይም በመግታት ነው። ነገር ግን፣ በዚህ ረገድ የሚወሰድ ማንኛውም ዓይነት እርምጃ በአንድም ሆነ በሌላ መልኩ የህወሓትን የበላይነት ከመግታት ጋር የተያያዘ ነው። ምክንያቱም የመንግስት ድርጅቶች በዋናነት የህወሓትን የስልጣን የበላይነት ለማስቀጠል የሚያገለግሉ ሲሆን የኢንዶውመንት ድርጅቶቹ ድግሞ በዋናነት የህወሓትን የኢኮኖሚ የበላይነትና ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ ናቸው። በመሆኑም የሀገሪቱን ኢንዱስትሪ እድገትና ተወዳዳሪነት ለማረጋገጥ የሚወሰደው ማንኛውም ዓይነት እርምጃ የህወሓትን የበላይነት ከማስወገድ ጋር በቀጥታ የተያያዘ ነው።

3.2 የፖለቲካ አመራር ወጥመድ 

ከላይ በተጠቀሰው መሰረት፣ በሀገሪቱ ኢኮኖሚ ላይ የሚስተዋሉ ችግሮችን በዘላቂነት ለመፍታት በቅድሚያ በመንግስታዊ ስርዓቱ ላይ ስር-ነቀል ለውጥ መምጣት አለበት። በመንግስት አስተዳደርና የተቋማት ሥራና አሰራርን በማሻሻል ግልፅነትና ተጠያቂነትን ማስፈንና የመልካም አስተዳደር ችግሮችን መቅረፍ፣ በዚህም ለዜጎች ቀልጣፋና ጥራት ያለው አገልግሎት ማቅረብና ፍትሃዊ ተጠቃሚነትን ማረጋገጥ ይቻላል። ይህን ለማድረግ ግን በቅድሚያ ብቃት፥ ተነሳሽነትና ቁርጠኝነት ያለው የፖለቲካ አመራር ያስፈልጋል።

ደሃ ሀገራት ለማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮቻቸው ዘላቂ መፍትሄ ከመስጠት የሚያግዳቸው መሰረታዊ ችግር የፖለቲካ አመራር ወጥመድ (Political Leadership Trap) ነው። በበለፀጉ ሀገራት ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮችን ለመፍታት የሚያስችል የዳበረ የዕውቀትና ልምድ በተለያዩ የሕብረተሰብ ክፍሎች ዘንድ ይገኛል። ከዚህ በተጨማሪ፣ አስፈላጊው ብቃትና ክህሎት የሌላቸው የፖለቲካ መሪዎችን በዴሞክራሲያዊ ምርጫ አማካኝነት በቀላሉ ከስልጣን ማስወገድ ይቻላል።

አንደ ኢትዮጲያ ያሉ ሀገራት መሪዎች አንዴ በፖለቲካ አመራር ወጥመድ ከተጠለፉ ግን ሥር-የሰደዱ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮችን ለመፍታት የሚያስችል ተነሳሽነትና ቁርጠኝነት አይኖራቸውም። ነገር ግን፣ እነዚህን አመራሮች በቀላሉ ከስልጣን ማስወገድና አስፈላጊው ብቃት፥ ተነሳሽነትና ቁርጠኝነት ባለው አዲስ አመራር ለመተካት የሚያስችል ዴሞክራሲያዊ ምርጫ የለም። ስለዚህ የፖለቲካ አመራሩ ስልጣን በሕዝብ ምርጫና በግዜ ያልተገደበ ከሆነ ሥራና አሰራሩ ግልፅነትና ተጠያቂነት ሊኖረው አይችልም።

በመሰረቱ በአመራር ወጥመድ የተጠለፉ አመራሮች የሥራቸውን ውጤታማነት የሚመዝኑት በራሳቸው ውስጣዊ እርካታ (Internal Satisfaction) አይደለም። ከዚያ ይልቅ፣ የሥራቸውን ውጤትና ውጤታማነት የሚመዝኑት በሌሎች ሰዎች ዘንድ በፈጠሩት ደስታ ወይም በውጫዊ እርካታ (External Gratification) ነው። ፕሮፌሰር “Bill George” የተባሉ የዘርፉ ምሁር “Why Leaders Lose Their Way” በሚል ርዕስ ፅሁፍ የሥራቸውን ውጤትና ውጤታማነት በውጫዊ እርካታ የሚመዝኑ መሪዎች እንዴት በአመራር ወጥመድ እንደሚጠለፉ ይገልፃሉ፡-

“When leaders focus on external gratification instead of inner satisfaction, they lose their grounding. Often they reject the honest critic who speaks truth to power. Instead, they surround themselves with sycophants who tell them what they want to hear. Over time, they are unable to engage in honest dialogue; others learn not to confront them with reality.” Why Leaders Lose their Way

በሥራቸው ውስጣዉ እርካታ (Internal Satisfaction) የሚያገኙ መሪዎች የተሳሳተ ውሳኔ ከወሰኑ ወይም ዝቅተኛ የሆነ አፈፃፀም ካስመዘገቡ እውነቱ በሕዝቡ ዘንድ ቢታወቅም-ባይታወቅም እንደ አመራር በአፈፃፀማቸው እርካታ አያገኙም። የሥራቸውን ውጤታማነት በውጫዊ እርካታ (External Gratification) የሚመዝኑ መሪዎች የተሳሳተ ውሳኔ ከወሰኑ ወይም ዝቅተኛ አፈፃፀም ካስመዘገቡ እውነቱ እስካልታወቀ ድረስ በሥራቸው ይረካሉ። ስለዚህ የተሳሳቱ ውሳኔዎችን ትክክል እንደሆኑ ወይም የጎላ ተፅዕኖ እንደሌላቸው አድርጎ በማቅረብ፣ እንዲሁም ዝቅተኛ የሆነን አፈፃፀም በሪፖርት ላይ የተሻለ አስመስሎ ለማቅረብ ጥረት ያደርጋሉ።

ከራሳቸው ይልቅ ሌሎች ሰዎችን በማስደሰት (External Gratification) ላይ የሚያተኩሩ ባለስልጣናት ለትችትና ነቀፌታ በሥራቸው ደስተኛ እንዳይሆኑ ያደርጋቸዋል። በመሆኑም፣ በቀጣይ ስህተት-አልባ የሆነ ሥራ ለመስራት (perfectionism) ጥረት ያደርጋሉ። ሆኖም ግን፣ ስህተት-አልባ የሆነ ሥራ ለመስራት የሚደረግ ጥረት ድክመቶች ተለይተው እንዳይታወቁ ያደርጋል። ፕሮፌሰር “Bill George” ለዚህ ዓይነት የአመራር ሥነ-ልቦና ችግር የተጋለጡ ባለስልጣናት ብቃትና ክህሎት እንዳላቸው ለማሳየት በሚያደርጉት ጥረት ተደጋጋሚ ስህተቶችን እንደሚሰሩ፣ ስህተትን በሌላ ስህተት ለማስተካከል እንደሚጥሩ፣ በዚህም ለከፍተኛ ውድቀት እንደሚዳርጉ ይገልፃሉ።

“…..To prove they aren’t impostors, they drive so hard for perfection that they are incapable of acknowledging their failures. When confronted by them, they convince themselves and others that these problems are neither their fault nor their responsibility. …At this stage leaders are vulnerable to making big mistakes, such as violating the law or putting their organizations’ existence at risk. Their distortions convince them they are doing nothing wrong, or they rationalize that their deviations are acceptable to achieve a greater good.” Why Leaders Lose their Way

በዚህ መሰረት፣ በፖለቲካ አመራር ወጥመድ የተጠለፉ መሪዎች አስፈላጊው ብቃት፥ ተነሳሽነትና ቁርጠኝነት ስለሌላቸው የለውጥና መሻሻል እንቅፋት ናቸው። ከዚህ በተጨማሪ፣ ሥራና አሰራራቸው ግልፅነትና ተጠያቂነት ስለሌለው በሚከተሉት አፍራሽ ተግባራት ውስጥ ይሰማራሉ። ለምሳሌ፡- ተዓማኒነት የጎደላቸው ውይይቶች (a lack of honest conversations)፣ ከልክ ያለፈ የፖለቲካ ጨዋታ (too much political game playing)፣ እርስ-በእርስ መረጃ ያለመለዋወጥ (silo thinking)፣ የክትትልና ባለቤትነት ስሜት ማጣት (lack of ownership and follow-through) እና መጥፎ ባህሪያትን መታገስ (tolerating bad behaviors)።

የሀገሪቱን ልማትና እድገት፣ የህዝቡን ሰላምና ደህንነት በዘላቂነት ለማረጋገጥ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት መገንባት፣ ለዚህ ደግሞ ሕገ መንግስታዊ ስርዓቱን ማሻሻል የግድ አስፈላጊ ነው። በዚህ መሰረት የሀገራችንን ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊች ችግሮች ደረጃ በደረጃ ለመፍታት አስፈላጊው ብቃት፥ ተነሳሽነትና ቁርጠኝነት ያላቸው የፖለቲካ መሪዎች ያስፈልጋሉ። ነገር ግን፣ ከላይ ለመግለፅ እንደተሞከረው፣ በተለያየ ደረጃ የሚገኙ የኢህአዴግ መንግስት ባለስልጣናት በአብዛኛው በአመራር ወጥመድ የተጠለፉ ናቸው።

በአመራር ወጥመድ የተጠለፉ ባለስልጣናት ከብዘሃኑ የሕብረተሰብ ክፍል የሚነሱ የመብት፥ ነፃነትና ፍትሃዊ ተጠቃሚነት ጥያቄዎችን በአግባቡ ለመረዳትና ተገቢ ምላሽ ለመስጠት የሚያስችል አቅም የላቸውም። በመሆኑም የሀገሪቱን ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ችግሮች በዘላቂነት ለመቅረፍ የሚደረገው ጥረት መጀመር ያለበት በአመራር ወጥመድ የተጠለፉ የፖለቲካ መሪዎችን መለየትና ከአመራር ሰጪነት ማንሳት ነው። ምክንያቱም በአመራር ወጥመድ ተጠልፈው የወደቁ የፖለቲካ መሪዎች እንቅስቃሴ ሙሉ በሙሉ ፀረ-ለውጥና አፍራሽ ነው።

በዚህ መሰረት፣ የኢህአዴግ መንግስት ወይም የኢህአዴግ አባል ድርጅቶች የዜጎች መብትና ነፃነት የተከበረበት ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ለመዘርጋት የመጀመሪያው ተግባር በአመራር ወጥመድ የተጠለፉ አመራሮችን መለየትና ከአመራርነት ሰጪነት ማስወገድ ነው። ከዚህ በመቀጠል በፖለቲካዊ ስርዓቱ የሚስተዋሉ መሰረታዊ ችግሮችን በዝርዝር መረዳት የሚችሉ የሙያ ብቃትና የአመራር ክህሎት ያላቸው፣ ከፖለቲካ ስልጣንና የግል ጥቅም ጥማት ይልቅ በሕዝብ አገልጋይነት መርህ የሚመሩ ሀገር ወዳድ ምሁራን፥ የፖለቲካ መሪዎች፥ ጋዜጠኞች፥ የመብት ተሟጋቾች፥ የሀገር ሽማግሌዎች፥ የሃይማኖት መሪዎች እና ሌሎች የሕብረተሰብ ክፍሎች መሪዎች የሚሳተፉበት የምክክር መድረክ ማቋቋም ያስፈልጋል። ሁሉም የሕብረተሰብ ክፍሎች ከዚህ በፊት፥ አሁንና ወደፊት ስላለው ነባራዊ ሁኔታ በነፃነት ሃሳብና አስተያየት የሚሰጡባቸው የውይይትና ምክክር መድረኮች ማዘጋጀት። ከእነዚህ መድረኮች የተሰበሰበውን የሕዝብ አስተያየት እንደ ግብዓት በመውሰድና በዚህ ፅሁፍ የተገለፀውን ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ሁኔታ መሰረት በማድረግ ለሁለት ዓመት የሚቆይ የሽግግር መንግስት መቋቋም አለበት።

4 የሕገ መንግስት ማሻሻያ እና የሽግግር መንግስት

4.1 ሕገ መንግስቱን ስለማሻሻል

በክፍል አንድ እንደተገለፀው ከተለያዩ የሕብረተሰብ ክፍሎች የሚነሳው የዴሞክራሲ ጥያቄ ነው። ሀገሪቱ ከገባችበት የፖለቲካ ቀውስ እንድትወጣና ፈጣን የኢኮኖሚ እድገትና ፍትሃዊ የሃብት ክፍፍል ለማረጋገጥ ዴሞክራሲዊ ስርዓት መዘርጋት የግድ አስፈላጊ ነው። ለዚህ ደግሞ የፈረሰውን የዴሞክራሲ መዋቅርና ተቋማት መልሶ መገንባት ያስፈልጋል። ዴሞክራሲያዊ ስርዓት መገንባት የሚቻለው የሕግ የበላይነትን ማረጋገጥ ሲቻል ነው። የሕግ የበላይነት የሚረጋገጠው፤ በሕገ መንግስቱ የተደነገጉ መሰረታዊ መብቶችና ነፃነቶች በማስከበር፣ የመንግስት ግልፅነትና ተጠያቂነት በማረጋገጥና በመንግስትና ሃይማኖት መለያየት፣ በዚህም የሕገ መንግስቱን ማክበርና ማስከበር ሲቻል ነው። በዚህ መሰረት፣ የሕገ-መንግስቱን የበላይነት ለማረጋገጥ ሁለት መሰረታዊ ለውጦች ያስፍለጋሉ። እነሱም፣ አንደኛ፡- በሕገ መንግስቱ ውስጥ ያለውን የተሳሳተ መርህ ማስተካከል፣ ሁለተኛ፡- በዚህ የተሳሳተ መርህ መሰረት የወጡ አፍራሽ አዋጆች፥ መመሪያዎች፥ አሰራሮችና ውሳኔዎች ማሻሻል ወይም ማስወገድ ናቸው።

በኢፊዲሪ ሕገ መንግስት ውስጥ ለአፍራሽ ሕጎች፥ መመሪያዎች፥ አሰራሮችና ውሳኔዎች መነሻ የሆነው በአንቀፅ (8) ላይ የተጠቀሰው “የሕዝብ ሉዓላዊነት” የሚለው መርህ ነው። በመሆኑም “የኢትዮጲያ ብሔሮች፥ ብሔረሰቦች፥ ሕዝቦች የኢትዮጲያ ሉዓላዊ ስልጣን ባለቤቶች ናቸው” የሚለው መርህ “ኢትዮጲያዊያን የኢትዮጲያ ሉዓላዊ ስልጣን ባለቤቶች ናቸው” ተብሎ መስተካከል አለበት። ይህን ማድረግ እስካልተቻለ ድረስ፤ አንደኛ፡- መንግስታዊ ስርዓቱ ከሀገርና መንግስት አመሰራረት ሂደት፥ ከነፃነት፥ ሉዓላዊነትና ማህበራዊ-ውል (Social contract) ፅንሰ-ሃሳቦች ጋር ይጋጫል፣ ሁለተኛ፡- ይህ መርህ ከተቀሩት የሕገ-መንግስቱ መሰረታዊ መርሆች፣ የዜጎች ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶችና ነፃነቶች፣ እንዲሁም የሕገ መንግስቱን ብሔራዊ ፖሊሲ ዓላማዎችና ሌሎች ድንጋጌዎች ጋር ይቃረናል።

በዚህ መሰረት፣ የተሳሳተው መርህ በተጠቀሰው መልኩ ካልተሻሻለ በስተቀር ራሱን የሚቃረኑ አፍራሽ ሕጎች፥ ደንቦች፥ መመሪያዎች፥ አሰራሮችና ውሳኔዎች መነሻ ሆኖ ይቀጥላል። በመሆኑም ሕገ መንግስቱ ራሱን በራሱ ያፈርሳል ወይም ለዴሞክራሲያዊ ስርዓት መሰረት የሆኑ መዋቅሮች፥ ተቋማትና አሰራሮች እንዳይዘረጉ እንቅፋት ይሆናል። ዜጎች የኢትዮጲያ የሉዓላዊ ስልጣን ባለቤቶች ከሆኑ በሀገሪቱ ላይ ባለቤትነት፣ በመንግስት ላይ የስልጣን የበላይነት ይኖራቸዋል። ይህ ሲሆን ዜጎች በሕገ መንግስቱ ከተደነገጉ ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች በተጨማሪ ሕገ መንግስቱን በራሱ የማስከበር ስልጣንና ኃላፊነት ይኖራቸዋል። በአጠቃላይ የተሳሳተውን ሕገ-መንግስታዊ መርህ በማስተካከል፤ የዜጎችን ሰብዓዊ እና ዴሞክራሲያዊ መብቶች እንዲያከብር፣ ሥራና አሰራሩ ግልፅነትና ተጠያቂነት እንዲኖረው፣ የሃይማኖት ነፃነት እንዲከበር፣ በዚህም የእያንዳንዱና የሁሉም ዜጎች መብት፥ ነፃነትና ፍትሃዊ ተጠቃሚነት እንዲረጋገጥ ማድረግ ይችላል።

የዜጎች ፖለቲካዊ መብትና ነፃነት ሲከበር የሕገ መንግስቱ የበላይነት ይረጋገጣል። በዚህ መልኩ፣ የሕግ የበላይነትን በማረጋገጥ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት መገንባት ይቻላል። ይህን ለማድረግ ግን የሚከተሉትን የዴሞክራሲ ተቋማት መፍጠርና ማስፋፋት ያስፈልጋል።እነሱም፡- ነፃና ገለልተኛ ሚዲያዎች፣ ማህብረሰቡን በንቃት የሚያሳትፉ የሰቪል ማህበራት እና ጠንካራ የተቃዋሚ

ፖለቲካ ፓርቲዎች። ነገር ግን፣ እነዚህን የዴሞክራሲ ተቋማት መልሶ ለመገንባት፤ የፀረ-ሽብር አዋጅ፣ የመረጃ ነፃነትና ሚዲያ አዋጅ፣ የበጎ አድራጎት ድርጅቶችና ማህበራት ሕብረት መመሪያ፣ የኮምፒውተር ነክ ወንጀሎች አዋጅ፣ የብሔራዊ መረጃና ደህንነት መስሪያ ቤት እና የመረጃ መረብ ደህንነት ኤጀንሲ በዜጎች ላይ የሚያካሂዱት ክትትልና ቁጥጥር፣ በኢንተርኔት አገልግሎትና በሌሎች የግንኙነት አውታሮች ላይ የሚታየው መስተጓጎል እና የመሳሰሉትን አፋኝ ሕጎችና የጭቆና ተግባራት ከነጭራሹ መወገድ አለባቸው።

ነገር ግን፣ እነዚህን አፍራሽ አዋጆች፥ መመሪያዎች፥ አሰራሮችና ውሳኔዎች በዘላቂነት ለማስወገድ ወይም ለማሻሻል ሕገ መንግስታዊ መሰረት ያስፈልጋል። ለዚህ ደግሞ ለእነዚህ አፍራሽ ሕጎች መነሻ የሆነውን የተሳሳተ ሕገ መንግስታዊ መርህ ማስተካከል ያስፈልጋል። ይህን ማድረግ እስካልተቻለ ድረስ ሕገ መንግስቱን የሚቃረኑ አዋጆች፥ መመሪያዎች፥ አሰራሮችና ውሳኔዎችን ማስወገድ፥ ማሻሻል፥ ማስቀረት አይቻልም። በመሆኑም የዴሞክራሲ ተቋማትን መገንባትና ማጠናከር፣ በዚህም የዜጎችን እኩልነትና ፍትሃዊ ተጠቃሚነት የተረጋገጠበት ዴሞክራሲያዊ ስርዓት መዘርጋት አይቻልም።

በአጠቃላይ በዜጎች ላይ ለሚደርሰው በደልና ጭቆና መሰረታዊ ምክንያት በተሳሳተ መርህ ላይ የተመሰረተው ሕገ መንግስት ነው። ሕገ መንግስቱ ዜጎችን በሀገራቸው ላይ ያላቸውን ባለቤትነት፣ በመንግስት ላይ ያላቸውን የስልጣን የበላይነት ይገፍፋል። በዚህ መሰረት ሕገ መንግስቱን የሚቃረኑ አፋኝ ሕጎች፥ መመሪያዎች፥ አሰራሮችና ውሳኔዎች በመንግስት አካላት ተግባራዊ እንዲደረጉ አስችሏል። በእነዚህ አፋኝ ሕጎች ምክንያት ዜጎች የሚደርስባቸውን በደልና ጭቆና በመቃወም አደባባይ ሲወጡ ከመንግስት ጋር አጋጭቷቸዋል። በዚህ መሰረት፣ ሕገ መንግስቱ በተለያዩ የሀገሪቱ አከባቢዎች ለተከሰተው የፖለቲካ ግጭትና አለመረጋጋት መንስዔ ነው። ምክንያቱም፣ አንደኛ፡- የሀገሪቱን ዜጎች ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብታቸውን የማስከበር መብት፥ ሉዓላዊ ስልጣን ገፍፏቸዋል፣ ሁለተኛ፡- መንግስት የዜጎችን ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች የማክበርና የማስከበር ግዴታውን እንዳይወጣ ምክንያት ሆኗል። ሕገ-መንግስቱ ካልተሻሻለ በስተቀር የሀገሪቱን የፖለቲካ ችግር ለመፍታት የሚደረገው ጥረት የዜሮ-ድምር ጨዋታ ነው።

4.2 የሽግግር መንግስት ስለማቋቋም

በመሰረቱ የችግሩ መንስዔ በሆነው ሕገ መንግስት መሰረት የሚደረግ ማንኛውም ዓይነት ለውጥ ዘላቂ መፍትሄ አያመጣም። በተሳሳተ መንገድ የሚጓዝ ሰው እርምጃው ቢፈጥን፥ ቢዘገይ ወይም ቢቆም ከአሰበበት ቦታ አይደርስም። ምክንያቱም ችግሩ ያለው በሚሄድበት መንገድና አቅጣጫ እንጂ በእርምጃው ፍጥነትና መዘግየት አይደለም። በተመሳሳይ በሀገራችን ለተከሰተው የፖለቲካ ቀውስ መሰረታዊው ምክንያት የምንከተለው ፖለቲካዊ ስርዓት ነው። ፖለቲካዊ ስርዓቱ የሚመራበት ሕገ መንግስት ካልተሻሻለ በስተቀር የሀገሪቱን ችግር በዘላቂነት ለመቅረፍ የሚስችል ሁለንተናዊ ለውጥና መሻሻል ማድረግ አይቻልም።

ችግሩ ሳይፈጠር በፊት መከላከል፣ ከተፈጠረ በኋላም መፍትሄ መስጠት ስለተሳናቸው ነገሮች ተባብሰው አሁን ካሉበት ደረጃ እንዲደርሱ ያደረጉ ሕግ አውጪ፥ ሕግ ተርጓሚ እና ሕግ አስፈፃሚ አካላት ሀገሪቱ የገጠሟትን ኢኮኖሚያዊ፥ ፖለቲካዊና ማህበራዊ ችግሮች በአግባቡ ለመገንዘብ፥ የመፍትሄ አቅጣጫ ለማስቀመጥና ይህን ተግባራዊ ለማድረግ የሚያስችል የፖለቲካ ብቃትና ተነሳሽነት የላቸውም። ከዚህ በተጨማሪ፣ ሁሉም የመንግስት አካላት ሀገሪቱ ለገባችበት የፖለቲካ ቀውስ በአንድም ሆነ በሌላ መልኩ ተጠያቂ እንደመሆናቸው መጠን በብዙሃኑ የሕብረተሰብ ክፍል ዘንድ ቅቡልነትና ተዓማኒነት የላቸውም። በመሆኑም የሀገሪቱን ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች ለመቅረፍ አስፈላጊ የሆነውንና ባለፉት አስር አመታት በራሳቸው ያፈረሱትን የዴሞክራሲ መዋቅር፥ ተቋማትና አሰራር መልሰው ለመገንባት የሚያስችል አቅም ሊኖራቸው አይችልም።

በሀገራችን የተከሰተውን ፖለቲካዊ ቀውስ በዘላቂነት ለመፍታት የሚቻለው በፅኑ መሰረት ላይ በተገነባ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ነው። ይህን ደግሞ ማድረግ የሚቻለው የሽግግር መንግስት በማቋቋም ነው። የችግሩ መሰረታዊ ምክንያት በሆነው ሕገ መንግስት መሰረት ባለስልጣናትን መቀያየር “ጉልቻ ቢቀያየር ወጥ አያጣፍጥም!” የሚባለው ዓይነት ነው። የዜጎችን ሉዓላዊ መብትና ስልጣን ገፍፎ ለብሔሮች በመስጠት ላይ የተመሰረተው መንግስታዊ ስርዓት የግለሰቦችን መብትና እኩልነት ማረጋገጥ አይችልም። ከዚህ በተጨማሪ፣ የህወሓት/ኢህአዴግ አመራሮችና ልሂቃን በፖለቲካ አመራር ወጥመድ ተጠልፈው ወድቀዋል። በመሆኑም፣ የሕገ መንግስቱን ሆነ የሚመሩት መንግስት መሰረታዊ ችግር በራሳቸው መገንዘብና ዘላቂ መፍትሄ መስጠት አይችሉም። ስለዚህ የሀገራችንን ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች በዘላቂነት ለመፍታት የሽግግር መንግስት መቋቋም አለበት።

ስለ ሕገ መንግስቱ ማሻሻያ ሆነ ስለ ሽግግር መንግስቱ አስፈላጊነት ከህወሓት/ኢህአዴግ መንግስት አመራሮችና ደጋፊዎች ገንቢ ሃሳብና አስተያየት መጠበቅ አያስፈልግም። ይህን የመገንዘብ አቅምና ብቃት ቢኖራቸው ኖሮ ሀገራችን አሁን ካለችበት ቅጥን-ቅጡ የጠፋ የፖለቲካ ቀውስ ውስጥ አትወድቅም ነበር። ስለዚህ የሽግግር መንግስቱን ለማቋቋምና በዜጎች ነፃነትና እኩልነት መርህ ላይ የተመሰረተ መንግስታዊ ስርዓት ለመዘርጋት በሚደረገው እንቅስቃሴ የህወሓት/ኢህአዴግን ፍቃደኝነትና ይሁኝታ መጠየቅ ሆነ መጠበቅ አስፈላጊ አይደለም።

ማጣቀሻዎች

1*UNCTAD (United Nations Conference on Trade and Development) (2004): An investment guide to Ethiopia: opportunities and conditions, Geneva, March

2*World Bank (2007a): Ethiopia: accelerating equitable growth: country economic memorandum, Washington, DC

3*Zerihun, A. (2008): Industrialisation policy and industrial development strategy in Ethiopia, in: T. Assefa (ed.), Digest of Ethiopia’s national policies, strategies and programs, Addis Ababa: Forum for Social Studies, 239−281

4*World Bank (2009): Ethiopia: towards the competitive frontier: strategies for improving Ethiopia’s investment climate, Washington, DC

5* Tilman A. (2010): Industrial policy in Ethiopia / Tilman Altenburg. – Bonn : DIE, 2010. − (Discussion Paper / Deutsches Institut für Entwicklungspolitik ; 2/2010) ISBN 978-3-88985-477-3

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *