Hiber Radio: ማንም ጤነኛ የሆነ ሰው እየሰጠመ ባለ ጀልባ ላይ አይሳፈርም፤ በተለይ ለአማራና ኦሮሞ የፓርላማ አባላት!

በአቻምየለህ ታምሩ

እንደሚታወቀ በአማራና ኦሮሞ መከራ ላይ ድሎቱን ያደላደለው የፋሽስት ወያኔ አገዛዝ የትግራይ ወታደሮችን እያሰማራ አማራንና ኦሮሞን በይፋ መጨፍጨፍ ከጀመረ ሶስት አመታትን አስቆጥሯል። ሕዝባችን እስካሁን ድረስ ባካሄደው ፍትሐዊና ሰላማዊ ትግል በሺዎች የሚቆጠሩ ንጽሐን ኢትዮጵያውያንን ለትግራይ ወታደሮች ገብሯል።

ባሁኑ ሰዓት በሺዎች የሚቆጠሩ ንጹሐንን በግፍ የረሸነው ፋሽስት ወያኔ ተጨማሪ ሺዎችን በእሩምታ ለመጨፍጨፍና ለመረሸን የፓርላማ አባላቱ ከጎኑ እንዲሰለፉና ይፋዊ ፍቃድ እንዲሰጡት ቀጠሮ ይዟል።

ዛሬ ላይ በደረስንበት የሕዝብ ትግል ደረጃ ፋሽስት ወያኔ እየሰጠመ ያለ ጀልባ ሆኗል። ማንም ጤነኛ የሆነ ሰው እየሰጠመ ባለ ጀልባ ላይ አይሳፈርም። እየሰጠመ ያለው ጀልባ ፋሽስት ወያኔ በፓርላማ ስም ሕዝብን ለመጨፍጨፍ ፍቃድ ቢያገኝ እያንዳንዱ የፓርላማ አባል ነገ በታሪክና በሕግ ፊት ተጠያቂ ከመሆን አይድንም።

ፋሽስት ወያኔ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን በፓርላማ አስጸድቆ ሕዝባችንን ወደመጨፍጨፍ ቢገባ ወያኔ ተወግዶ አገርና መንግሥት ሲኖረን ተጠያቂ የሚደረገው ፋሽስት ወያኔ ብቻ ሳይሆን ወያኔ እንዲጨፈጭፍ በፓርላማ ይፋዊ ፍቃድ የሰጡት የፓርላማ አባላት ሁሉ ናቸው። በደርግ ላይ ወያኔ ያቀረበችውን ክስ ያዬ በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ስም ወያኔ ሕዝብን እንዲጨፈጭፍ ድምጽ አይሰጥም። ይህ ዛሬ ወያኔ ሕዝብ እንዲጨፈጭፍ የፓርላማ አባላት ፍቃድ እንዲሰጡት ለፓርላማ የሚቀርበው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ነገ ፋሽስት ወያኔን ብቻ ሳይሆን እያንዳንዱ የፓርላማ አባል በወንጀል፣ በትውልድና በታሪክ ተጠያቂ የሚደረግበት ዶሴ መሆኑን ፋሽስት ወያኔ ራሱ በደርግ ላይ ከመሰረተው ክስ ጋር አዛምዶ ማየቱ በቂ ነው።

ወያኔ ደርግን የከሰሰው «የጊዜያዊ ወታደራዊ አስተዳደር ደርግ» በሚል ስም ደርግ መስከረም 2 ቀን 1967 ዓ.ም. ባስነረገው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅና በአዋጁ ስም መንግሥቱ ኃይለ ማርያም በፈጸመው ግፍና ግድያ ነው። እንደሚታወቀው ደርግ የ120 አካባቢ የበታች መኮንኖች ሸንጎ ነው። መስከረም 2 ቀን 1967 ዓ.ም. ጊዜያዊ ወታደራዊ «መንግሥት» የሆነው ደርግ 120 የደርግና አባላትን ይዞ በደርግ ስም በመሰየም ነው። መንግሥቱ ኃይለ ማርያም መስከረም 2 ቀን 1967 ዓ.ም. ያወጣውን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የደነገገውም «የጊዜያዊ ወታደራዊ አስተዳደር ደርግ አዋጅ» ብሎ የ120ው የደርግ አባላት አዋጅ አድርጎ ነው። ይህንን ያወቀው ፋሽስት ወያኔም በደርግ ላይ ክስ ሲመሰርት በመንግሥቱ ኃይለ መርያም ወንጀል ተጠያቂ ያደረገው መንግሥቱ ኃይለ ማርያምን ብቻ ሳይሆን ጊዜያዊ ወታደራዊ አስተዳደር ብለው «መንግሥት» የሆኑትን 120ውን የደርግ አባላት ሁሉ በእኩል ወንጀል ነው።

መንግሥቱ ኃይለማርያም በ120ዎቹ የደርግ አባላት ስም መስከረም 2 ቀን 1967 ዓ.ም. ያወጣው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አሁን ወያኔ በፓርላማ እንዲጸድቅ ከሚፈልገው አዋጅ ጋር አንድ አይነት ነው። መንግሥቱ ኃይለ ማርይም መስከረም 2፣ 1967 ዓ.ም. ባወጀው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅና አዋጁን ተከትሎ በተፈጸመው ግፍና ግድያ ተጠያቂ የሆነው መንግሥቱ ኃይለ ማርያም ብቻ ሳይሆን 120ዎቹም የደርግ አባላት ሁሉ ከመንግሥቱ ኃይለ ማርያም እኩል አዋጁ ተከትሎ በተካሄደው ግፍና ግድያ ተጠያቂ የሚሆኑ ከሆነ የወያኔን የአስቸኳይ ጊዜ የሚያጸድቁት እያንዳንዱ የፓርላማ አባል [በራሳቸው ፈርደው ካጸደቁት ማለቴ ነው] ወያኔ በአስቸኳይ ጊዜያዊ አዋጁ ስም በሚፈጽመው ግፍና ግድያ ተጠያቂ የማይደረግበት ምክንያት ያለም። ባጭሩ ወያኔ ሕዝብ ሊጨፈጭፍበት ያወጣውን አዋጅ በፓርላማ የሚያስጸድቀው እያንዳንዱን የፓርላማ አባል በግፍና ግድያ ወንጀል ተጠያቂ ለማድረግ ነው።

ስለሆነም እያንዳንዱ የፓርላማ አባል፤ በተለይ ደግሞ በወያኔ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ target የተደረገውን አማራና ኦሮሞ እንወክላለን የሚሉ ሁሉ ትናንትና የደርግ አባላት በተከሰሱበት የግፍና የግድና አዋጅ በጋራ ላለመጠየቅ ራሳቸውን ነጻ ማውጣት አለባቸው። ተስፋ የቆረጠው ወያኔ ሕዝብን ያለ ምህረት ለመጨፍጨፍ ያወጣው የግድያ አዋጅ አጽዳቂ ላለመሆንና ነገን ከልጆቹና ከወገኖቹ ጋር አብሮ ለመኖር የሚያስብ ሁሉ አስቸኳይ ጊዜ አዋጁ እንዲጸድቅ ድምጽ ሲሰጥ ነገ አይቀሬው ለውጥ ሲመጣ በወንጀል የሚጠየቅበትን መዝገብ እየፈረመ እንደሆነ ማሰብ ይኖርበታል። ይህ ደግሞ ዛሬ ግማሽ ሕይወቱ ወደ ሞት የተለወጠው ወያኔ መወገዱ ሳይታለም የተፈታ ስለሆነ አይቀሬ ነው።

መወገዱ አይቀሬ ከሆነ አገዛዝ ጋር በገዳይነት ላለመወንጀልና ነገ ነጻ ዜጋ ሆኖ በሰላም ለመኖር የሚያስብ የፓርላማ አባል ሁሉ በወንጀል የሚጠየቅበትን የወያኔ የአስቸኳይ አዋጅ ከማጽደቅ ራሱን መጠበቅ ይኖርበታል። ነገ ወያኔ ከተወገደ በኋላ ዛሬ በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ በግፍ እየወደቁ ያሉት ሰማዕታት ፍትህ ሲያገኙና ወንጀለኞች ለፍርድ ሲቀርቡ «ሳላምንበት ነው ድምጽ የሰጠሁት» ፤ «ተገድጄ ነው የፈረምሁት» የሚለው አይሰራም። ይህ ሰበብ ለ120ው የደርግ አባላትም አልሰራም። መንግሥቱ ባወጀው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ እንኳን በሕይወት የነበሩቱ የሞቱትም ከመከሰስ አልዳኑም። እያንዳንዱ የፓርላማ አባል ወያኔ ሊወድቅ አይችልም፤ ስለሆነም በወንጀል ልጠየቅ አልችልም ከሚል አዚም መላቀቅ አለበት። ዘላለም ሕዝብ እየጨፈጨፈ የሚኖር አገዛዝ የለምና ትውልዶች ሁሉ እየታገሉት ያለው ፋሽስት ወያኔም ሕዝብ እየጨፈጨፈ ሊኖር አይችልምና መወገዱ አይቀሬ ነው፤ ሕዝብ የገደሉና ያስገደሉ ግፈኞችንም እጃቸው የኋሊት በመጫኛ ታስሮ በእውነተኛ ዳኛ ፊት ይቀርባሉ። የወያኔን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ለማጽደው የተዘጋጀ የፓርላማ አባል ሁሉ በግፍ ክብረ ወሰን እንደተቀዳጀው ወያኔ በደም ተጨማልቆ እጁ የኋሊት በመጫኛ ታስሮ ለፍርድ እንዳይቀርብ ወንጀለኛ የሚያደርገውን የወያኔን የመጨፍጨፊያ አዋጅ ውድቅ ያድርግ።

እያንዳንዱ የደርግ አባል ያውም ባላጸደቀበት ሁኔታ መንግሥቱ ኃይለ ማርያም በደርግ ስም መስከረም 2 ቀን 1967 ዓ.ም. ባወጣው አዋጅ ከመንግሥቱ ኃይለ ማርያም እኩል ተጠያቂ ሆኖ ወያኔን በፓርላማ ግደል ብሎ እጅ በማውጣት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ እንዲጸድቅ ርዳታ የሰጠ ማንኛውም የምክር ቤት አባል አዋጁን ተከትሎ ወያኔ በሚያካሂደው ጭፍጨፋ ተጠያቂ የማይሆንበት አንዳች አመክንዮ የለም። እያንዳንዱ የፓርላማ አባል የወያኔን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ለማጽደቅ እጅ ሲያወጣ ነገ በወንጀል የሚከሰስበትን ዶሴ እየፈረመ እንደሆነ ይወቅ። ፋሽስት ወያኔ ነገ አይኖርም፤ ነገ ለመኖር የሚሻ ነገ በወጀል ላለመጠየቅ ዛሬ የወያኔን አዋጅ የግድያ አዋጅ ውድቅ በማድረግ ለነገ ራሱን ይጠብቅ።

ብልህ በሞኝ ስህተት ይማራል እንዲሉ፤ በተለይ የአማራና የኦሮሞ የፓርላማ አባላት መንግሥቱ ኃይለ ማርያም እንዳሻው ገድሎ በወያኔ ዘመን በወንጀል ተጠያቂ እንዲሆኑና እድሜያቸውን ሙሉ ማጎሪያ ቤት ገብተው እንዲማቃቁ እንደተደረጉት የደርግ አባላት ሁሉ በወንጀል ተጠያቂ እንዳይሆኑ ወያኔ በስማቸው ሕዝብ ለመጨፍጨፍ ካወጣው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ራሳቸውን አርቀው ወያኔ በሚያካሂደው ጭፍጨፋ ተጠያቂ እንዳይሆኑ ከደርግ አባላት ስህተት መማር ይኖርባቸዋል። የፓርላማ አባላቱ ይህንን የሚያደርጉት ስለእያንዳንዳችን ሲሉ ብቻ ሳይሆን ስለራሳቸው የነገ ሕይወትም ነውና ነገ በወንጀል ተጠያቂ የሚያደርጋቸውን የወያኔ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ውድቅ ማድረግ ይኖርባቸዋል። ነገን ለመኖር የሚያስብ ግማሽ ሕይወቱ ወደ ሞት ተለውጦ እውር ድንብሩን እየሄደ ካለ ፋሽታዊ አገዛዝ ጋር አብሮ ወንጀል አይሰራምና!

Hiber radio Las Vegas ይህ ህብር ሬድዮ _የወቅታዊ መረጃ ምንጭ ነው። ህብር ሬድዮ በአቤኔዘር ኮሙኒኬሽን ሴንተር እየተዘጋጀ  ከላስ ቬጋስ ከተማ፣ ዘወትር ዕሁድ በአካባቢው ሰዓት አቆጣጠር ከምሽቱ 630 ሰዓት እስከሰዓት በህብር ሬዲዮ ድህረ ገጽ ወይም በቀጥታ በስልክ ለማዳመጥ  5639993994 ወይም 563999-3988 1641-793-8229 ወይም 1641-715-8596  በመረጡት ቁጥር መደወል ብቻ በቂ ነው በእንግሊዝ ለምትኖሩ 01405770140 በስልክ ማዳመጥ ይቻላል። ዘወትር በድህረ ገጻችን፣ googel app store Hiber Radio ወደ ስልክዎ በመጫን ካልሆነም በዘሐበሻ እንዲሁም በተጠቀሱት ስልኮች ማዳመጥ ይቻላል።

 

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *