በጌታቸው ሽፈራው
ሻምበል አበበ ጎሹ ኃይሌ የወልቃይት ተወላጅ ሲሆን የ42ኛ ክፍለ ጦር አባል ነው። ነሃሴ 24/2009 ዓም በአመራሮቹ ትዕዛዝ ለእስር ተዳረገ። እስከ ህዳር 7/2010 ዓም አዘዞ ካምፕ ውስጥ ታስሮ ቆይቷል።
በመሃል የመከላከያ ሰዎች መስከረም 26/2010 ዓም ቃል እንደተቀበሉት መዝገቡ ላይ ተገልፆአል። ከህዳር 7/2010 ዓም በኋላ ወደ አብርሃ ጅራ ፖሊስ ጣቢያ ተልኮ እስከ ዛሬ መጋቢት 6/2010 ዓም ፍርድ ቤት ቀርቦ አያውቅም። ከዛሬ በቀር አንድም ቀን ፍርድ ቤት ቀርቦ አያውቅም!
ሕገ መንግስቱ አንድ ተጠርጣሪ በተያዘ በ48 ሰዓት ውስጥ ፍርድ ቤት መቅረብ እንዳለበት ይገልፃል። “ሕገ መንግስታዊ ስርዓቱን ለመጠበቅ እሰራለሁ” የሚለው፣ ኮማንድ ፖስቱን አሳውጆ እቆጣጠረዋለሁ ( ሕገመንግስታዊ መብቶች በደንብ መጣሳቸውን ለማስፈፀም) የሚለው መከላከያ ሰራዊት ግን ያሰረውን ሻምበል አበበን እስከ ነሃሴ 26/2009 ዓም ባለው ጊዜ ውስጥ በ48 ሰዓት ውስጥ ፍርድ ቤት ማቅረብ ሲገባው፣ 48 ሰዓቱ ብቻ ሳይሆን 2009 አመትን አሳልፎ፣ ከ4,776 ሰዓታት በኋላ መጋቢት 6/2010 ዓም ለመጀመርያ ጊዜ ፍርድ ቤት እንዲቀርብ ሆኗል።
“ፍርድ ቤት ስለቀረብኩ እግዚያብሔርን አመሰግናለሁ” ብሏል፣ ከመከላከያ እስር ወጥቶ የአማራ ብሔራዊ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ጎንደር ምድብ የቀረበው የመከላከያ አባል።
ፍርድ ቤቱም ተከሳሽ የቆየው በፖሊስ እጅ ቢሆን ስለ አያያዙ ማብራሪያ መጠየቅ ይቻል እንደነበር፣ ነገር ግን ይዞት የቆየው መከላከያ በመሆኑ መጠየቅ እንደማይቻል በመግለፅ ወደ ጎንደር ማረሚያ ቤት እንዲዛወር ትዕዛዝ ሰጥቷል።
” ኢትዮጵያ ውስጥ የሕግ የበላይነት ሳይሆን የመሳርያ የበላይነት ነው ያለው” ብሎ ለመከራከር ይህ ዋና አስረጅ ነበር። መከራከር አያስፈልግም እንጅ! ተለምዷልና!
Hiber radio Las Vegas ይህ ህብር ሬድዮ _የወቅታዊ መረጃ ምንጭ ነው። ህብር ሬድዮ በአቤኔዘር ኮሙኒኬሽን ሴንተር እየተዘጋጀ ከላስ ቬጋስ ከተማ፣ ዘወትር ዕሁድ በአካባቢው ሰዓት አቆጣጠር ከምሽቱ 6፤30 ሰዓት እስከ 8 ሰዓት በህብር ሬዲዮ ድህረ ገጽ ወይም በቀጥታ በስልክ ለማዳመጥ 5639993994 ወይም 563999-3988 ፣ 1641-793-8229 ወይም 1641-715-8596 በመረጡት ቁጥር መደወል ብቻ በቂ ነው ። በእንግሊዝ ለምትኖሩ በ01405770140 በስልክ ማዳመጥ ይቻላል። ዘወትር በድህረ ገጻችን፣ ከ googel app store Hiber Radio ወደ ስልክዎ በመጫን ካልሆነም በዘሐበሻ እንዲሁም በተጠቀሱት ስልኮች ማዳመጥ ይቻላል።