ከያሬድ ኃይለማርያም
መጋቢት 15፣ 2018
ዛሬ ጠዋት በኮማንድ ፓስቱ የታሰረውን የኦሮሚያ ክልል ፍትህ ቢሮ ቃል አቀባይ አቶ ታዬ ደንዳአን፤ የኢሰመጉ መርማሪ የነበርን ሰዎች የምናውቀው በአዲስ አበባ ዩንቨርሲት የሦስተኛ አመት ተማሪ በነበረበት ጊዜ ነው። በ1996 ወይም በፈረንጆቹ 2004 ዓ.ም በጥር ወር በስድስት ኪሎ ዩንቨርሲቲ ግቢ ውስጥ በተማሪዎች መካከል የተከሰተን ግጭት ተከትሎ የደንብ ልብስ የለበሱ የፖሊስ ኃይሎች በሌሊት የተማሪዎችን ማደሪያ ክፍሎች እያስከፈቱ ስድስት የኦሮሞ ተወላጅ የሆኑ ተማሪዎችን አስወጥተው ይደበድባሉ። ከዚያም ሁለት ተማሪዎችን ጨምረው ስምት የኦሮሞ ብሄር ተወላጅ የሆኑ ተማሪዎችን መርጠው ወደ ማዕከላዊ እስር ቤት በመወስድ ያስሯቸዋል። በቀጣዩ ቀን በግቢው ውስጥ የሚገኙ የኦሮሞ ብሄር ተማሪዎች ተሰባስበው ከዩንቨርሲቲው ፕሬዚደንት ቢሮ ፊት ለፊት ቆመው በሌሊት ታፍነው የተወሰዱ ወንድምና እህቶቻቸው ያለምንም ቅድመ ሁኔታ በአፋጣኝ እንዲፈቱ እጅግ ጨዋነትና ሕግ አክባሪነት በተሞላው መልኩ ይጠያቅሉ። ትንሽ ቆይቶም የዩንቨርሲቲው አስተዳደር የፖሊስ ኃይል ጣልቃ እንዲገባ ጥሪ በማድረጉ በሰላማዊ መንገድ ከፕሬዝዳንቱ ቢሮ ፊት ለፊት ቆመው ተቃውሟቸውን ያሰሙና የታሰሩት እንዲፈቱ ይጠይቁ የነበሩትን ተማሪዎች በፊደራል አድማ በታኝ ፖሊስ እንዲከበቡ ይደረጋል።
በወቅቱ በዩንቨሪሲቲው ውስጥ በምሽት ፕሮግራም የህግ ትምህርት እከታተል ስለነበር ይህን ሁኔታ በስፍራው ሆኜ የመታዘብ እድል ነበረኝ። በአድማ በታኝ ፖሊሶች የታገዙት የደህንነት ሰዎች እያንዳንዱን ተማሪ መታወቂያውን እንዲያሳይ በማድረግ የኦሮሞ ስም ያላቸው ብቻ እየተለዩ በተዘጋጁ የጭነተ መኪናዎች ላይ እንዲወጡ ሲደረግ ታዝቤያለ። በኋላም ወደ ኮልፌ ፖሊስ ማሰልጠኛ ካምፕ ተወስደዋል። ከሰልፈኛው መሃል የኦሮሞ ስም የሌላቸው ተማሪዎች እየተለዩ ግቢው ውስጥ እንዲቀሩ ሲደረግ በአይኔ ተመልክቻለሁ። ይህ አይነቱ አሳፋሪና አስነዋሪ የሆነ የዘር ማንነት ላይ ያነጣጠረ ጥቃት በማንም እና በየትም ስፍራ ቢፈጸም የሚወገዝ እርምጃ ቢሆንም በራሴ ወገኖች ላይ ሲፈጸም ባይኔ በብረቱ ቆሜ ማየቴ ግን ከልቤ ውስት ተሰንቅሮ የማይወጣ እጅግ የሚያም የጥቃት ስሜት ተሰምቶኛል።
ተማሪዎቹ ኮልፌ ፖሊስ ማሰልጠኛ ካምፕ ውስጥ እንደደረሱም ከታችና ከላይ የለበሷቸውን ልብሶች ከጉልበትና ከክርናቸው በላይ እንዲሰበስቡ ተደርጎ ኮሮኮንችና ጠጠር በተነጠፈበት መሬት ላይ በክርናቸውና በጉልበታቸው እየተንፏቀቁ እንዲንከባለሉና እንዲመላለሱ በመደረጉ ብዙዎቹ ለከባድ ጉዳት ተዳርገው ነበር። ከዚህም በላይ የከፋ የማሰቃየት ተግባራትም የተፈጸሙባቸው ሲሆን ደረቅ ዳቦ እየተወረወረላቸው በርሃብም እንዲቀጡም ተደርጓል።
ከታሰሩት እጅግ በርካታ ተማሪዎች መካከል ሁለት ሴት እና አሥራ ሁለት ወንድ ተማሪዎችም ተለይተው ወደ ማዕከላዊ እሥር ቤት ተወስደዋል። ከእነዚህ ተማሪዎች መካከል አንዱ የዛሬው የኦሮሚያ ክልል የፍትህ ቢሮ ቃል አቀባይ የሆነው የሕግ ባለሙያና ለህሊናው ያደረው ደፋሩ ታዮ ደንደኦ ነበር። ታዮ የተማሪዎቹም ተወካይ ሆኖ ስለ ተፈጠረው ጠቅላላ ሁኔታ የኢሰመጉ መርማሪዎች አናግረነው ነበር። በአጠቃላይ ከ329 በላይ ተማሪዎች ከዩንቨርሲቲ ተማሪነታቸው የታገዱ ሲሆን ከታሰሩትም መካከል 315 የሚሆኑትን ተለቀው በቀሩት ላይ ክስ ተመስርቶባቸው ነበር። ይህም በወቅቱ በመንግስቱ ሚዲያም ተገልጿል።
እነ ታዮ በሽብርተኝነት ተጠርጥረዋል በሚል ክስ ተመስርቶባቸው ለእስር ተዳርገዋል። ተገልጾ የማያልቅ ግፍም በማእከላዊ ዕስር ቤት ተፈጽሞባቸዋል። ለሶስት አመታትም ያለ መንም ፍትህ ሲሰቃዩ ከቆዩ በኋላ ታዮ ፍርድ ቤቱ በተጠረጠረበት ውንጀል ምንም በቂ ማስረጃ በአሳሪዎቹ በኩል መቅረብ ስላልቻለ በነጻ ለቆት ነበር። ይህ የወያኔ በትር ያልሰበረው ብርቱ ሰው ትምህርቱን በመቀጠል ሊመረቅ አራት ቀናት ሲቀርው በድጋሚ ተይዞ በሽብር ወንጀል ትጠረጠራለህ በሚል ብዙ እንግልት፣ ስቃይና እስርም ደርሶበታል። ለአስር አመታትም ታስሮ ከወጣ በኋላ ይህ የጽናት ተምሳሌት የሆነ ሰው ትምህርቱን ቀጥሎ ለመመረቅ ችሏል። ታዮ ልበ ንጹህና የፍቅር ተምሳሌትም ነው። እንዲህ ቁም ስቅሉን ባሳየው ሥርዓትና የወጣትነት እድሜውን በስቃይ ባሳለፈባት አገር ተማሮ አገሩን ጥሎ አልወጣም። በደል፣ እንግልት፣ ፍትህ ማጣትና ያለ ወንጀል እየታፈኑ በየማጎሪያ ቤቱ መማቀቅ በእሱ እንዲያበቃና የተጣመመውን ሥርዓት በማቃናት ለቀሩት የአገሩቱ ወጣቶች ተስፋ ሊሆን የመንግስት ተሿሚ በመሆን በፍትህ ዘርፍ ተሰማራ። ይህ ግፍና በደልን እያየ እንዳላየ ማለፍ የማይችለው ታዮ፤ የዛሬ 14 ዓመታት ግድም ተማሪ ሆኖ ለታሰሩ ጓደኞች ፍትህ በመጠየቁ ብቻ ሽብርተኛ ተብሎ ከአስር አመታት በላይ በእስር የተጉላላው ሰው ዛሬም ሥርዓቱ በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ስም የጫነበትን ገደብ ወደጎን በመተው በሞያሌ በመከላከያ ሰራዊት አባላት በግፍ ለተረሸኑት ወገኖቹ ድምጹን ያሰማ ደፋር የፍትህ ሰው ነው።
ይህች አገር ቀን እንዲወጣላት ስንት የታዩን አይነት ሰዎች ለመስዋትነት ማቅረብ ይኖርባት ይሆን? የአገዛዝ ሥርዓቱስ የሚጠረቃው ስንት ታዮዎችን በልቶ ይሆን?
በታዮና በተቀሩት የኦሮሞ ተማሪዎች ላይ የደረሱትን ግፎችና በደሎች በተመለከተ በወቅጡ እኔም እሰራበት የነበረው የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ጉባዔ (ኢሰመጉ) ካወጣቸው በርካታ መግለጫዎች መካከል አንዱን ከዚህ በታች ያለውን ማስፈንጠሪያ በመጫን ሊያነቡት ይችላሉ።
“A Human Rights Violation Committed Against Oromo Students of Addis Ababa University”, 74th Special Report 10 February 2004, https://www.ehrco.org/wp-conte…/uploads/2016/…/special74.pdf
https://www.ehrco.org/wp-content/uploads/2016/04/special74.pdf
የታዬ ደንዳአን ጉዳይ እንደገና እንዳስታውስ ላደረገኝ የቀድሞ ሥራ ባልደረባዮ ወንድማገኝ ጋሹ ምስጋናዮ ከፍ ያለ ነው።
ፍትህ ለታዮ ደንዳኦና ለቀሩት ግፉአን!
Hiber radio Las Vegas ይህ ህብር ሬድዮ _የወቅታዊ መረጃ ምንጭ ነው። ህብር ሬድዮ በአቤኔዘር ኮሙኒኬሽን ሴንተር እየተዘጋጀ ከላስ ቬጋስ ከተማ፣ ዘወትር ዕሁድ በአካባቢው ሰዓት አቆጣጠር ከምሽቱ 6፤30 ሰዓት እስከ 8 ሰዓት በህብር ሬዲዮ ድህረ ገጽ ወይም በቀጥታ በስልክ ለማዳመጥ 5639993994 ወይም 563999-3988 ፣ 1641-793-8229 ወይም 1641-715-8596 በመረጡት ቁጥር መደወል ብቻ በቂ ነው ። በእንግሊዝ ለምትኖሩ በ01405770140 በስልክ ማዳመጥ ይቻላል። ዘወትር በድህረ ገጻችን፣ ከ googel app store Hiber Radio ወደ ስልክዎ በመጫን ካልሆነም በዘሐበሻ እንዲሁም በተጠቀሱት ስልኮች ማዳመጥ ይቻላል።