ሸንቁጥ አየለ
ህዉሃት በ1983/84 ዓም ኦነግን ይዛ ቀሪዉን የኢትዮጵያ ህዝብ አግልላ ምናምንቴ ህገ መንግስት እና ኢትዮጵያዉያንን የሚያባላ ክልል ያጸደቀች ጊዜ ብዙ ኢትዮጵያዉያንን እና አለም አቀፍ ማህበረሰብን ማታለል ችላ ነበር:: በድጋሚም በ1997 ዓም ምርጫ ብዙሃኑ ኢትዮጵያዊ ለዉጥ ፈልጎ ቅንጅትን ሲመርጥ ሶስት ጣምራ ስትራቴጂዎችን ተጠቅማ ህዝባዊዉን ሀይል ከጫዋታ ዉጭ እንዲሆን አድርጋዉ ነበር::ይሄዉም የቀኝ ክንፍ አክራሪ ሀይሎች መጡብህ የሚል ማስደንበሪያ: የጉልበት ስልት እና ቅንጅቱን እራሱን ገብቶ የመከፋፈል ስትራቴጂዎችን በማጣመር ቅንጅቱን ከጥቅም ዉጭ ማድረግ ችላ ነበር::
አሁንም ህዉሃት ህዝባዊ ተቃዉሞ ለሁለት አመታት ሲንጣት ቢከርምም ለሶስተኛ ጊዜ የተዋጣለት ድርሰት ጽፋ የድል አክሊሉን እራሷ ላይ መጫን ችላለች:: የዚህ ድርሰት ዋና የሴራ ማጠንጠኛ ደግሞ ከዚህ ቀደሞቹ አካሄድ የተለዬ ገጽታ እንዲኖረዉ የተደረገዉ በሚከተሉት ነጥቦች ላይ ነዉ::
1ኛ. ኢህአዴግ ዉስጥ ክፍፍል ተነስቷል የሚል ፕሮፖጋንዳ በደንብ እንዲስፋፋ ተደረገ::በዚህም ኦህዴድ እና ብአዴን ከህዉሃት ጋር ትግል ዉስጥ ገብተዋል የሚል ትርክት ተቀባይነት እንዲያገኝ ተደረገ::በዋናነትም የኦሮሞ ብሄረተኛ ተቃዋሚዎችን እንዲሁም የአማራ ብሄረተኛ ተቃዋሚዎችን በማፈላለግ ከኦህዴድ ጋር እና ከብአዴን ጋር እንዲቆሙ ብሎም ህዉሃትን እንዲቃዉሙ ብዙ የተንኮል ስራዎች እና የፕርፖጋንዳ ስራዎች ተሰርተዋል::የኦሮሞ ብሄረተኞችን እነ ጀዋርን ሳይቀር ወደ ኦህዴድ ደጋፊነት እንዲያዘነብሉ ማድረግ የሚያስችል የድርሰት ሴራዉ እንዲጦፍ ተደረገ::
2ኛ. ከዚህም በማስቀጠል ህዉሃት/ኢህአዴግ በአራቱ የግንባር ፓርቲዎች መሃከል የጦፈ የስልጣን ፉክክር እየተደረገ እንደሆነ ለማስመሰል በርካታ ድራማዎችን ሰራች::በተለይም የወያኔ ቅጥረኛ ይሁኑ ወይም ተቃዋሚ ይሁኑ ምንንነታቸዉ በማይለይ አክቲቪስት እና ጋዜጠኞች ሾልኮ የደረሰኝ መረጃ በሚል ቀደዳ (grapevine communication) አባይ ጸሃዬ እና አቢይ ተቧቀሱ: ደመቀ እና ደብረጺዮን ተደባደቡ: ቲም ለማ እና ገዱ ግንባር ፈጠሩ በሚል ትርክት በለዉጥ ጥማት የሚንገበገበዉን ኢትዮጵያዊ ብዙሃን ትኩረት ወደ ህዉሃት ድራማ ትርክት እንዲሳብ አደረጉት::
3ኛ. ለማ መገርሳ እና ገዱ አንዳርጋቸዉ በባህርዳር አለ ህዉሃት እዉቅና የተገናኙ እንዲመስል በርካት የሹልክታ ተግባቦት (grapevine communication) ትርክቶች በማህበራዊ ድረገጽ እና ተቃዋሚ በሚመስሉ ዌብ ሳይቶች ላይ ሰፊ ቀደዳ እንዲደረግባቸዉ ተደረገ:: ይባስ ብሎም አቦይ ስብሃት ብአዴኖችን ሰብስቦ ለምን ከኦህዴዶች ጋር መከራችሁ ብሎ አስጠነቀቃቸዉ የሚል ትርክት ከባህርዳር የብአዴን ካድሬዎች እንዲሰራጭ ተደረገ:: ድራማዉን በደንብ ለማጦፍም ኢትዮጵያዊነት ሲሰበክ ለመስማት የሚቋምጠዉን ሰዉ የሚያማልል “ኢትዮጵያዊነት ሱሴ” የሚል ትርክት በስፋት እንዲሰማ ተደረገ:: በዚህም ወያኔ የአንድነት ሀሳብ አቀንቃኝ ነኝ የሚሉ ተቃዋሚዎችን ሀሳብ ሳይቀር መስረቅ ቻለች:: በሚገርም እና ለማመን በሚያስቸግር ፍጥነት ኢትዮጵያ የሚል ቃል ሲጠራ ጆሮዉን ያሳክከዉ የነበረዉ ጀዋር ሳይቀር ኢትዮጵያዊነት ሱሴ የሚለዉ ትርክት ደጋፊ እንዲሆን የቲም ለማ ሀይል እያሸነፈ ነዉ: የህዉሃት ጉልበቱ እየተንቀጠቀጠ ነዉ የሚል አንደምታዎች መሰራጨት ጀመሩ::
4ኛ. ለማመን በሚገርም ፍጥነት ለማ መገርሳ እና አቢይ ቦታ እንዲቀያየሩ እና አቢይ የኦህዴድ ሊቀመንበር እንዲሆን ሲደረግ ወያኔ ከኋላ ሆና ድራማዉን ብትቆምርም ይሄ የአቢይ እና የለማ ቦታ ልዉዉጥ የጀግንነት እና የብልሃት ትርክት እንዲላበስ ወደ ተቃዋሚ ጎራዉ እንዲስፋፋ ተደረገ::በዚህም የቀድሞዉ የኢህአዴድግ ሚኒስቴር የነበረዉ እና ወያኔን ብዙ አመታት ያገለገለዉ ኤርምያስ ለገሰ የኢሳት የኦህዴድ ድምጽ እንዲሆን እና እነ አቢይን እንዲያጀግን አስተማማኝ ስራ ተሰራ::ኢሳት ኢህአዴግን የከፋፈለ መስሎት በዋናነት የወያኔን ድራማ ማስፈጸሚያ ሚዲያ ሆኖ ቁጭ አለ::ኢሳት ይባስ ብሎ የኦህዴድ አጀጋኝ እና የእነ አቢይ አማካሪ ሆኖ ሲቀርብ ወያኔ ለጻፈዉ ድራማ ዋና ተባባሪ መሆኑን ያስተዋለዉ አይመስልም::ወያኔን ጎዳሁ ብሎ ወያኔን የመጥቀም ስራዉ አሁንም ተጠናክሮ ቀጥሏል::
ከጥቂት አመታት በፊት ስዬ አብርሃ የሚባልን የወያኔ አራጅ የአንድነት ፓርቲ መሪ ለማድረግ ዋናዉን ስራ የሰሩት የተቃዋሚ ሚዲያዎች ናቸዉ:: ገፊ ምክንያታቸዉም ስዬ አብርሃ የወያኔን ጦር ጠንቅቆ ስለሚያዉቀዉ ለዉጡን በፍጥነት የሚመራ ሀይል ይሆናል በማለት ነበር:: ሆኖም ስዬ አብርሃ የሰራዉ አንድ የተዋጣለት ስራ ቢኖር የአንድነት ፓርቲን አፈራርሶ መሄዱ ነበር:: አሁን ደግሞ የህዉሃት የጎንዮሽ አማካሪ መሆኑ ብቻ ነዉ:: አሁንም አቢይን የሚያቆለጳጵሱት ተቃዋሚ ሚዲያዎች ዋና ትንታኔአቸዉ አቢይ ደህንነቱን እና ጦሩን ያዉቀዋል የሚል የተደናገረ ተጠይቅ ጭምር ነዉ:: አንዳንዶች አሁን በልባቸዉ የሚሉት ነገር ምንድን ነዉ? አቢይ ኦሮሞ ነዉ: ስዬ ደግሞ ትግሬ ነዉ::ስለዚህ አቢይ እንደ ስዬ ህዝቡን ሊከዳ አይችልም ይላሉ::ይሄ አይነቱ አስተሳሰብ ዋናዉ ህዉሃቶች የሚፈልጉት እና ሰዎች በጎሳ ገመድ ብቻ ተንጠላትለዉ የፖለቲካ ትንታኔዎችን በጎሳ ህሳቤ ላይ ሲቀምሩ ወያኔዎቹ ደግሞ አሽከሮቻቸዉን በደንብ መዘወር እንዲችሉ እንደሚያደርጋቸዉ ያወቃሉ::
5ኛ. አሁን በጠቅላይ ሚኒስቴር ሹመቱ ላይ ህዉሃት በአቢይ ደስተኛ እንዳልሆነ ለማስመሰልም ቀደም ብሎ ጀምሮ የሹልክታ ተግባቦት (grapevine communication) ትርክቶች በማህበራዊ ድረገጽ እና ተቃዋሚ በሚመስሉ ዌብ ሳይቶች ላይ ሰፊ ቀደዳ እንዲደረግባቸዉ ሆኗል::በማጠናቀቂያዉም የድራማዉ አፈጻጸም እዉነት እንዲመስል ተደርጎ ተከዉኗል:: ደመቀ መኮንን የሚባለዉ እንስሳ እራሱን ከዉድድሩ አገለለ በዚህም ኦህዴድ እና ብአዴን በጋራ ወያኔን ለመታገል ቀድመዉ ቃል ስለተገባቡ ብአዴኖች ድምጻቸዉን ለአቢይ ሰጡ የሚል ትርክት የሴራዉ አካል ሆነ:: ይሄ ብቻ ሳይሆን ደመቀ መኮንንም ለማጀገን እንዲሁም የብ አዴንን ክብር ጠብቀዉ ከኦህ ዴድ ጋር የጠበቀ ፍቅር ናቸዉ ለማስባል ብሎም በብዙሃኑ የአማራ እና የኦሮሞ ተወካዮች የተመረጠ ጠቅላይ ሚኒስቴር ነዉ ለማስባል አቢይ በዋናነት በኦህዴድ እና በብአዴን ድጋፍ እንዳለፈ እንዲመስል ድራማዉ አግባባዊ ትረካዉን አስቀምጧል::ይሄም የብዙሃኑን ልብ ማሳመን ችሏል::ለጉድ ይግረማችሁ ብለዉ ህዉሃቶች የደቡብንም ድጋፍ እንዳያጡ የድራማዉን ሴራ በደንብ ያጦፉበት ክፍል ደግሞ መሳጭ ነዉ::ህዉሃት ካለዉ 45 ድምጽ ሁለቱን ብቻ ለደብረጺዮን ሰጠ::ቀሪዉን ግን ለደቡቡ ሰዉ ለሺፈራዉ ሺጉጤ ሰጠ ብለዉን ቁጭ::ምድረ እንኩሮም መሬት ጠባዉ ደብረጺዮንን የተበቀለዉ እየመሰለዉ ደብረጺዮን ሁለት ድምጽ ብቻ አገኘ እያለ ጭፈራ ላይ አተኩሯል::
እዉነታዉ ምንድን ነዉ?
አሁን በመሬት ላይ የወያኔ አፈና ቀጥሏል::ባህርዳር ላይ በሰላማዊ መንገድ ለመታገል ፓርቲ እንመሰርታለን ያሉ ወጣቶች በጅምላ ታፍነዉ እስር ቤት ተወርዉረዋል::ከፈተኛ ድብደባ እና አፈና እየተከናወነባቸዉ ነዉ::በአማራ ክልል በየቀኑ ሰዎች እየተገደሉ እና እየታሰሩ ነዉ::ኦሮሚያ ዉስጥ በዚህ ሁለት ቀን ዉስጥ እንኳን በርካታ የወረዳ አመራሮች: የፖሊስ አባላት እና በርካታ ወጣቶች በእስር እየተጋዙ ነዉ::በርካታ ወጣቶችም እየተገደሉ እንደሆነ ይሰማል::እነ ተመስገን እና እነ እስክንድር ከበርካታ ጀግኖች ጋር ባንዲራ ሰቀላችሁ: መገባበዝ አትችሉም ተብለዉ በጅምላ ታፍነዉ ወደ እስር የተወረወሩት አሁንም በወያኔ ቀጭን ትዕዛዝ ነዉ::
በእስር ቤት ካለዉ ተቃዋሚ አሁንም 95% የሚሆነዉ በወህኒ እየማቀቀ ነዉ:: በየአካባቢዉ የተነሱ የዲሞክራሲ እና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች አንዱም እንኳን አልተፈታም:: ሆኖም ወያኔዎች እና አስመሳይ ተቃዋሚዎች የተቃዉሞዉን አቅጣጫ እኛ የመረጥንልህን ጠቅላይ ሚኒስቴር ትግሬ ሳይሆን ከዚህ ብሄር በመሆኑ ተነስተህ አጨብጭብ የሚል አንደምታ እየሰበኩ ነዉ:: የኢትዮጵያ ህዝብ ጥያቄ የኦሮሞ ጠቅላይ ሚኒስቴር: የአማራ ጠቅላይ ሚኒስቴር: የትግሬ ጠቅላይ ሚኒስቴር የሚል አይደለም::የኢትዮጵያ ህዝብ ጥያቄ በዋንኛነት የዲሞክራሲ አስተሳሰብ እና መርህ እዉን የሚሆበት ስርዓት እና በህግ የበላይነት የሚመራ ተቋማት እዉን ሆኖ ማዬት ነዉ::ይሄን ደግሞ ገማሁ: በሰበስኩ: በወንጀል ተጨማለቅሁ: በሙስና ከረፋሁ ብሎ እራሱን ደጋግሞ በህዝብ ፊት ባዋረደዉ ኢህአዴግ ተግባራዊ ማድረግ አይቻልም:: እንቶኔም ሄደ እንቶኔም ተተካ ሁሉም የገማዉ ስርዓት አካል እና አባል ነዉና::
የወያኔ ጊዜአዊ ድል ግን ምንድን ነዉ?
1-በኢትዮጵያ ማህበረሰብ ዘንድ:- ወያኔ ከፍተኛ ጊዜአዊ ድል ተጎናጽፏል::የወያኔ የማህበራዊ ሚዲያ እና የዌብሳይት ሰራዊት እንዲሁም ዋና ተቃዋሚ ነን የሚሉት ሳይቀር ለአቢይ ጊዜ መስጠት እንደሚገባ እየወተወቱ ነዉ::ለዉጥ በአንድ ለሊት እዉን አይሆንም: ለአቢይ ጊዜ ይሰጠዉ እና እንዬዉ የሚል ቅስቀሳ እየጦፈ ነዉ::ወያኔ ከዚህ የተሻለ ወርቃማ ሀሳብ እዉን ሆኖ ማዬት አትፈልግም::
2-በአለም አቀፍ ማህበረሰብ ዘንድ ወያኔ/ኢህኣዴግ ደንበኛ ነጥብ አስቆጥራለች::የምዕራባዉያን ሚዲያዎች በኢትዮጵያ ዉስጥ ከፍተኛ ለዉጥ እየተከናወነ ነዉ ሲሉ እየዘገቡ ነዉ::አሁን በአሜሪካ መንግስት ተረቆ ሊጸድቅ ያለዉን ጸረ ወያኔ ህግም ዉድቅ ለማስደረግ ጥሩ ሰበብ አግኝታለች::
3-በተቃዋሚዎች ዘንድ:- በጎሳ ስሌት የተበሻቀጠዉ የተቃዋሚዎች አስተሳሰብ ኦሮሞ ተሾመ: አማራ ተሾመ : ትግሬ ወረደ ከሚል አስተሳሰብ ሊዘል እንደማይችል ህዉሃት ስሌቱን አግኝታዋለች::አሁን በኦሮሞ ተቃዋሚዎች በኩል ወያኔ ታላቅ እፎይታ ታገኛለች::ለአቢይም የእንኳን ደስ ያለህ መግለጫ ከእነ ጀዋር እየጎረፈለት ነዉ:: እንዲሁም የትግሬ ፖለቲከኞችን ተንኮል አምርረዉ የሚጠሉ የአማራ ፖለቲከኞች እና የአንድነት ፖለቲካ ጽንሰ ሀሳብ አራማጆች ለጊዜዉ አቢይ በመሆኑ ደስታቸዉ ወደር ያጣዉ የህዉሃት ትግሬ ሀይል ከወንበሩ ላይ ገለል ያለ ስለመሰላቸዉ ነዉ::በዚህም ይሄ ሁሉ ሀይል አቢይን እንኳን ደህና መጣህ የሚል መግለጫ እያጎረፈለት ነዉ::ይሄ እዉነታ ግን ምን ያህል ጊዜ እንደሚቆይ እናያለን::ህዉሃት አሁንም ከወንበሩ ጀርባ እንዳደፈጠ ማስተዋል የሚጀምሩበት ቀን ግን እሩቅ ላይሆን ይችላል::
4-ዲያስፖራዉ:- ብዙሃኑ የኢትዮጵያ ዲያስፖራ በማንኛዉም አይነት የሚዲያ ሀሳብ የሚወሰድ ሀይል ነዉ::በተለይም አንድ ሀሳብ በሚዲያዎች ጮሆ ከተተረከ በዉጭ ሀገር የሚንከራተተዉ ኢትዮጵያዊ ነገሮችን በቅርበት የሚመረምርበት እድሉ ጠባብ ስለሆነ የሚዲያ ትርክቶችን መልሶ ከማስተጋባት ዉጭ ምርጫ የለዉም::በኢትዮጵያ ናፍቆት የሚንገበገበዉ አብዛኛዉ ዲያስፖራ አንድ ምኞት ብቻ አለዉ::ኢትዮጵያ ድና ማዬት:: እናም ኢትዮጵያን የሚታደግ ለመሰለዉ ነገር ሁሉ ድጋፉን ከመስጠት በተለይም ደግሞ በሚዲያ የተራገበን ሀሳብ ከመደገፍ ወደኋላ አይልም::አሁን ለጊዜዉ የህዉሃት የሚዲያ ሰራዊት በተቃዋሚ መሰልነት: በኦህዴድነት: በብአዴንነንት : በኢሳት በኩል እና በእነጀዋር ሚዲያ በኩል በተሰራጨዉ ኢህአዴግ ዉስጥ ክፍፍል አለ ብሎም ኦህዴድ እና ብአዴን ተጋግዘዉ አሸንፈዉ ወጡ በሚለዉ የተዛባ መረጃ የተምታታዉ ዲያስፖራ ዛሬ የአቢይ ደጋፊ በመሆን ለአቢይ የእንኳን ደስ አለህ መግለጫዉን እያዘነበለት ነዉ::ስለዚህም የዲያስፖራዉን ድጋፍ ወያኔ በሰራችዉ ድራማ አግንታለች ማለት ነዉ::
- ኦህዴድ ከህዉሃት የተለዬ ነዉ::ብአዴን ከህዉሃት ተጣልቷል የሚልዉ ትርክት ለወያኔ እድሜ እጅግ ጠቃሚዉ ነዉ::በዚህም የኦሮሞን ተቃዋሚ እና የአማራን ተቃዋሚ በኦህዴድ እና በብአዴን ዙሪያ ለማሰባሰብ እና በደንብ ለመጥባት ምቹ ሁኔታ ተፈጥረዉላታል::ኢህአዴግ/ህዉሃት ህልዉናዉ አንድ መሆኑን እና በጋራ የጋራ መደብ የተሳሰሩ የፖለቲካ ሀይል መሆናቸዉን የሚረሳ እና ኢህ አዴግ እንደ አንድ ሀይል የጸረ ኢትዮጵያዊነት ዋና ተዋናይ መሆኑን የካደ ተቃዋሚን ማግኘትን የመሰለ ወርቃማ እድልን ወያኔ ተጎናጽፋለች::
ዋናዉ ጥያቄ:- የኢትዮጵያ ህዝብ የለዉጥ ጥያቄዉ ቆመ ማለት ይቻላል ወይ?
ከላይ እንደተባለዉ አቢይን ለመሰዬም በድራማዉ የሴራ ጥልቀት የተነሳ ጊዜአዊ ዝምታ እና እረፍት ለወያኔ ይፈጠርላታል:: ሆኖም አቢያ አንዳችም መሰረታዊ ለዉጥ ማምጣት የሚያስችለዉ ሁኔታ የለም::ህዉሃት ከወንበሩ ጀርባ አድፍጣለች እና::የህዉሃት/ኢህአዴግ መሰረታዊ ፖሊሲም ቀጣይ ይሆናል:: ስለሆነም የኢትዮጵያ ህዝብ የለዉጥ ጥያቄ አይቆምም::
ትግሉም አይቆምም::ሆኖም ሌላ ቅርጽ እና መልክ እየያዘ መምጣቱ አይቀርም::ልፍስፍሶች: ከወያኔ ጋር የተነካኩ እና በወያኔ ተራ የድራማ ሴራ የሚወናበዱ ተቃዋሚዎችም በሂደት በህዝባዊ አይን ስር መግባታቸዉ የታመነ ነዉ::ዋናዉ ህዝባዊ ማዕበል እና የጠመንጃ ትግል ገና ይወለዳል እንጅ የትግል ሂደቱ አይቆምም:: ለዉጡ ግን እንዲህ በቀላሉ የሚሆን አይደለም::
ከወያኔ ጋር የተነካኩትን ብቻ ሳይሆን በወያኔ ሀሳብ የሚያነክሱትን ሀይሎች ሁሉ ጠርጎ የሚበላ ህዝባዊ ቁጣ ከትጥቅ ትግል ይወለዳል::ለዚህም ዋናዉ ገፊ ሀሳብ አቢይም ሆነ ከአቢይ ጀርባ ያደፈጠዉ ህዉሃት የኢትዮጵያን ህዝብ የለዉጥ ጥያቄ የሚመልስ አንዳችም ነገር ማድረግ ስለማይችል ነዉ::ህዝባዊዉ ቁጣ ግን ወያኔ/ኢህአዴግን ብቻ ሳይሆን የሚበላዉ በወያኔ/ኢህዴግ ሀሳብ የሚያነክሱትን ሁላ ይሆናል::