ጤና ይስጥልኝ ውድ ኢትዮጵያውያን
ዶክተር አብይ አህመድ አዲሱ የሀገራችን ጠቅላይ ሚንስትር መሆኑን ተከትሎ ከጋዜጠኛ ሰይፉ ፋንታሁን ጋር ቃለመጠይቅ ከሰጠሁበት ሰዓት ጀምሮ ብዙ ሚድያዎችና ግለሰቦች በጉዳዩ ዙሪያ ተጨማሪ ማብራሪያ እንድሰጥ ስለጠየቁኝ ይህን ጽሁፍ በፌስቡክ ገፄ ለመጫር ተገድጃለሁ። ምንም እንኳን አንድ ግለሰብ ሀገር የመምራትን ያህል ትልቅ ሀላፊነት ሲጣልበት ግዙፍ ፖለቲካዊ እንደምታ እንዳለው የሚታወቅ ቢሆንም ፤ እኔ ፖለቲካውን ለባለሙያዎቹ በመተው ስለ አዲሱ የሀገራችን መሪ ማንነትና ተክለ ስብእና ከማውቀው ላይ ጥቂት ነገሮች ለማካፈል እወዳለሁ።
ዶክተር አብይን የማውቀው ገና የ 11 አመት ታዳጊዎች ሳለን ነው። ከዚያን ጊዜ አንስቶ አብረን አድገን ፣ በኢትዮ-ኤርትራ ጦርነት እኔ ኪነት ስሰራ እሱ ደግሞ ኦፕሬተር ሁኖ ለስድስት አመታት ብዙ ውጣ ውረዶችን አልፈናል። በተለይ ከ19 83 ጀምሮ አብይን እንደ ጓደኛ ሳይሆን እንደ ታላቅ ወንድም ነው የማየው ብል ማካበድ አይሆንም። ወንድምም እህትም ስለሌለኝ ለቤተሰቤ እኔ ብቻ በመሆኔ ዶ/ር አብይ እና ኮረኔል አሸናፊ ኦሊ (ኢንጂቨን) ነብሱን ይማረውና ጌቱ (ኮሚታስ) የወንድምን ጣእም ያሳኙና በስራዬ ሲደግፉኝ
የነበሩ ወንድሞቼ ናቸው በተለይ ጌቱ (ኮሚታስ) በህይወት ኖሮ ይህን ቢያይ ምንኛ ደስ ባለኝ ነበር:: ከነዚህ ወድሞቼ ጋርና ከዶ/ር አብይ ጋር ብዙ የመከራ ግዜን አብረን አሳልፈናል:: በተለይ ዶ/ር አብይ ከገባበት እልህ አስጨራሽና ፈታኝ ጉዞ አላስፈላጊ ዋጋ እንዳይከፍል በሚል ስጋት ከፖለቲካ ራሱን እንዲያገል ደጋግሜ ወንድማዊ ምክሬን ለግሼው ነበር::
አብይ ከራሱ በላይ ሀገሩን በመውደዱ ፣ መንፈሳዊ ጥንካሬ በመላበሱና የሚመጣውን ሁሉ ለመቀበል እራሱን በማዘጋጀቱ ለዛሬ በቅቷል። በስራ ሂደት ብዙ ሁኔታዎችን በቅርበት ለማጤን እድል በማግኘቱና ልምድ በማካበቱ ፤ እንዲሁም ልዩ ልዩ መጽሀፍት በማንበብ ባደረጀው የእውቀት አቅም ምክንያት ፤ ወደፊትም ለሚገጥሙት ዘርፈ ብዙ ፈተናዎች እንደ እስከዛሬው ሁሉ በብልሃትና በቁርጠኛነት እንደሚወጣቸው አልጠራጠርም። ከዶ/ር አብይ ጋር ያለን ቤተሰባዊ ግንኙነትም አሁንም እንደ በፊቱ እንደቀጠለ ነው::
ከሁሉ በላይ ግን የኢትዮጵያ ህዝብ ከዳር እስከ ዳር ለሚያሰማው ድምጽ ተገቢውን ትኩረትና ምላሽ እንደሚሰጥ አተማመናለሁ። በተለይም ባለፉት ዓመታት የኢትዮጵያ ህዝብ በሀዘን ቆስሏል ፣ ለፍትህ ሲል ቀላይ የማይባል መስዋእትነት ከፍሏል። ከዚሁ ጋር ተያይዞ የሀገራችን ህልውና ጉዳይ እጅግ አሳሳቢ ሁኔታ ላይ መድረሱ ይታወቃል። ሆኖም ከራሱ በፊት ሀገሩን እንደሚያስቀድም የምመሰክርለት የሀገራችን መሪ ዶክተር አብይ ከገባንበት ቅርቃር አውጥቶ ወደ ሰላምና ፍቅር ጎዳና የሚሻግር ድልድይ እንደሚሆን ተስፋ አደርጋለሁ።
በዶክተር አብይ ዙሪያ ቃለመጠይቅ ለማድረግ የደወላችሁልኝ ሚድያዎች ከላይ የፃፍኩትን መልእክት እንድታሰራጩልኝ በትህትና እጠይቃለሁ።
ጌትሽ ማሞ
ኢትዮጵያ ለዘላለም ትኑር