(ሀብታሙ አሰፋ)
የኢትዮጵያውያን የተባበሩ የሲቪልና የማህበረሰብ ድርጅቶችና በመላው አሜሪካ የሚገኙ በተለይ በዴንቨር ያሉ ኢትዮጵአውያን ድርጅቶች ለወራት የታገሉበት ኤች አር 128 የህግ ረቂቅ ማክሰኞ አፕሪል 10 ለምክር ቤቱ ለድምጽ ይቀርባል ተብሎ ይጠበቃል።ታላቁ ቀጠሮ ነው።ዶ/ር አብይ <<በተመረጡበት>> ማግስት ለድምጽ ይቀርባል መባሉ ታላቅ ዜና ነው።ዶ/ር አብይ በጠቅላይ ሚንስትርነታቸው ሹመት ወቅት ያደረጉዋቸው ንግግሮች ዋናው ፍሬ ነገር ግድያ በቃ፣የሀሳብ ነጻነት ይከበር፣መደማመጥ፣ በጋራ መቆም የህግና የፍትህ የበላይነት ይኑር፣ ሙስናን ለስም በጸረ ሙስና ኮሚሽን ማስወገድ አይቻልም ነው።ይሄን በእርግጥ በተግባር ለመተርጎም ካሰቡ እነሆ ዋናው አጋዣቸው ኤች አር 128 ሊጸድቅ ነው። የተዘረፈ የአገር ሀብት፣በንጹሃን ደም የተጨማለቁ ባለስልጣናት የጉዞ እቀባ የሚጥል ነው። የዘረፉት ሀብት የሚታገድባቸው ይሆናል።ስለዚህ ዶ/ር አበይን <<ሕወሓት>>አያሰራውም እንጂ ለውጥ ለማምጣት ቆርጧል የሚሉ አያሌ ኢትዮጵያውያን እነሆ ጊዜው አሁን ነው ዶ/ር አብይ ደጋፊ የሚያገኙት እንደ ሀይለማርያም የሕወሓት አሽከር ከመሆን የሚገላግላቸው በትረ ሙሴ ኤች አር 128 ነው።ሲፋቁ ሕወሃት ከሆኑ ግን ይቃወሙትና ይለይላቸው።
በኢትዮጵያ ፍትሕ እንዲመጣ መሰረታዊ የዲሞክራሲ መብት መከበር ዲሞክራሲያዊ ስርዓት በዚያ አገር ላይ ለማምጣት የምንናፍቅ፣በወገኖቻችን ላይ ለመሬት እና ለስልጣን ሲባል በሕወሓት የተቀነባበረ የዘር ማጥፋት እንዲቆም ከፈለግን እነሆ የመጨረሻው መጀመሪያ የዚህ ሕግ መጽደቅ ነው። ይህ መሰረት ሳይጣል ለወገኔ እቆረቆራለሁ ማለት ዘበት ነው። ለአዲሱ ጠ/ሚ/ር ጊዜ ይሰጠው በሚል ሽፋን የገዳዮችን እድሜ የሚያራዝም አደገኛ ውሳኔ እንዳንወስን መተንቀቅ ይገባል።ጊዜ የሚሰጠው በተግባር እየሰራ ሲታይ ነው። ዋና ዋና ለውጥ መምታቱን የሚያሳዩ ተግባራት ደረጃ በደረጃ ሲፈጸሙ ስናይ ነው።ለዚህ ለውጥ የሚያግዘው ኤች አር 128 የመሰሉ የህግ ጉልበት ያላቸው ውሳኔዎች ያስፈልጋሉ።
አዲሱን ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አብይ አሕመድን ይሄን ሕግ ለማደናቀፍ ከሞከሩ የሹመታቸው ቀን ያደረጉት ንግግርና ተግባራቸው የማይገናኝ አብይ ከእነሱ ነው ከእኛ እያሉ ተስፋ የጣሉትንም አንጀታቸውን የሚቆርጥ ትልቅ ውሳኔ ነው።
ዛሬም በሺህ የሚቆጠሩ የህሊናና የፖለቲካ እስረኞች ከማዕከላዊ እስከ ባዶ ስድስት ከሚታወቁ እስከ ማይታወቁት እስር ቤቶች ከግለሰቦች ቪላ እስከ ጦር ካምፖች ግፍ እየተፈጸመባቸው ተረስተው ነጻነት ቀን እየጠበቁ ነው። አላግባብ የታሰሩ መፈታት የኤች አር 128 መዘግየት ምክንያት ሊሆን አይገባም።ያልተፈቱ ሺዎች መኖራቸው ብቻ ሳይሆን ዛሬም ከመግደልና ከማሰር አባዜ ያልተላቀቀውን ስርዓት አንድም ተጠያቂ የሚያደርግ ሀይል የለም። ኤች አር 128 ቢያንስ የተጠያቂነት መንገድ ይተርጋል ።ዶ/ር አብይን የሚደግፉ ለውጥ እንዲያመጡ ከመጓጓት ከሆነ የለውጥ አጋዥ የሆነውን ኤች አር 128 እንዲጸድቅ ዛሬም የተቻለውን ማሳሰብ መጠየቅ ማስታወስ ይገባል።ለውጥ የሚመጣው በተግባራዊ እርምጃ አስገዳጅነት ባለው ሕግ ጭምር እንጂ በወሬና በንግግር ብቻ አይደለም። ማነው ጎበዝ ደጋግሞ ንቁ ሲል የነበረው የመንቃት ዘመን ያድርግልን።
Hiber radio Las Vegas ይህ ህብር ሬድዮ _የወቅታዊ መረጃ ምንጭ ነው። ህብር ሬድዮ በአቤኔዘር ኮሙኒኬሽን ሴንተር እየተዘጋጀ ከላስ ቬጋስ ከተማ፣ ዘወትር ዕሁድ በአካባቢው ሰዓት አቆጣጠር ከምሽቱ 6፤30 ሰዓት እስከ 8 ሰዓት በህብር ሬዲዮ ድህረ ገጽ ወይም በቀጥታ በስልክ ለማዳመጥ 5639993994 ወይም 563999-3988 ፣ 1641-793-8229 ወይም 1641-715-8596 በመረጡት ቁጥር መደወል ብቻ በቂ ነው ። በእንግሊዝ ለምትኖሩ በ01405770140 በስልክ ማዳመጥ ይቻላል። ዘወትር በድህረ ገጻችን፣ ከ googel app store Hiber Radio ወደ ስልክዎ በመጫን ካልሆነም በዘሐበሻ እንዲሁም በተጠቀሱት ስልኮች ማዳመጥ ይቻላል።