ዛሬ ግንቦት 2/2010 ዓም ከሁሉም የእስር ቤቱ ማማዎች መሳርያዎች ወደ እስረኛው ተጠምደው እንዳረፈዱ ለማወቅ ተችሏል
ሚያዝያ 30/2010 ዓም ቀጠሮ የነበራቸው በእነ መቶ አለቃ ማስረሻ ክስ መዝገብ 38ቱ ተከሳሾች ችሎት ከተረበሸ በኋላ ቂሊንጦ ዞን 5 የታሰሩት ተከሳሾች ድብደባ ተፈፅሞባቸዋል
ከ38 ተከሳሾች መካከል 11ተከሳሾች ከፍርድ ቤት እንደተመለሱ ጨለማ ቤት ገብተዋል። ፍፁም ጌታቸውን ጨምሮ ፍርድ ቤት ላይ ጥያቄ ያነሱት ተደብድበዋል። የአጥፉ አበራ እጅ ጉዳት ደርሶበት በፋሻ እንደተጠቀለለ ታውቋል
የቂሊንጦ እስር ቤት ከ38ቱ ተከሳሾች መካከል ነፃ ከተባሉት 8 እስረኞች ውጭ ሌሎቹን ዛሬ ግንቦት 2/2010 ዓም ወደ ዝዋይ እጭናለሁ በማለቱ የዞን 1 እስረኞች “ወደ ዝዋት አይሄዱም” ብለው በመቃወማቸው ውጥረት ነግሶ እንዳረፈደ ለማወቅ ተችሏል። በዚህም መሰረት ከሁሉም የእስር ቤቱ ማማዎች ወደ እስረኛው መሳርያ ተጠምዶ አርፍዷል። የቤተሰብ ጥየቃም ተከልክሎ የነበር ሲሆን የጀመረው ከጠዋቱ አራት ሰዓት በኋላ ነው።
የ38ቱ ተከሳሽ እስረኞች ከፍርድ ቤት ከተመለሱ በኋላ የርሃብ አድማ እንዳደረጉ ተገልፆአል። እስካሁንም ምግብ አልበሉም። የቂሊንጦ እስር ቤት ከአሁን ቀደምም 22 ተከሳሾችን ወደ ዝዋይ በመውሰድ ጠዋት ጠዋት ራቁታቸውን አሸዋ ላይ አስተኝቶ፣ ላያቸው ላይ ውሃ በመድፋት የግርፋትና ማሰቃየት ተግባር እንደፈፀመባቸው በችሎት መናገራቸው ይታወሳል። እስር ቤቱ ተከሳሾች ወደ ዝዋይ እጭናለሁ ሲል አለመግባባት የተፈጠረውም ከአሁን ቀደን በእስረኞች ላይ ከተፈፀመው የማሰቃየት ተግባር አንፃር ነው ተብሏል።
የቂሊንጦ እስር ቤት ባልታወቀ ምክንያት ከተለያዩ የእስር ቤቱ ዞኖች ታስረው የነበሩ የፖለቲካ እስረኞችን ወደ ዞን አንድ እንዳዛወራቸው ታውቋል። በአሁኑ ወቅት ቂሊንጦ ዞን 1 ውስጥ ከ270 እስከ 300 ያህል የፖለቲካ እስረኞች በእስር ላይ ይገኛሉ።
ይህ በእንዲህ እንዳለ ባለፈው ማክሰኞ የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 19ኛ ወንጀል ችሎት ዛሬ በጊዜያዊነት በ4ወንጀል ባስቻለው ችሎት በቅሊንጦ ቃጠሎን ተከትሎ ከተከሰሱት መካከል እነ መ/አ ማስረሻ ሰጤ፣ዶ/ር ፍቅሩማሩን ጨምሮ የተወሰኑ ተከሳሾችን የሽብር ክሱን በወንጀለኛ መቅጫ ሕጉ እንዲታይና ወንጀሉን ተከላከሉ ሲል የወሰነ ሲሆን የተወሰኑ ተከሳሾችን በነጻ ለቋል።ተከሳሾች ብይኑን በመቃወማቸው በእስረኞች ላይ በፍርድ ቤት ፖሊሶቹ መሳሪያ አቀባብለው አፈሙዝ በማዞራቸው የተከሳሽ ቤተሰቦች በዋይታ ሐዘናቸውን መግለጻቸውን የመረጃ ምንጮቹን ጠቅሶ ጋዜጠኛ ጌታቸው ሽፈራውን ጠቅሰን መዘገባችን ይታወሳል።
በቂሊንጦ ቃጠሎ ሰበብ የተከሰሱት ዛሬ በችሎቱ በተፈጠረ ችግር በርካታ አፈሙዝ ዞሮባቸዋል። በተከሳሾቹ ላይ ጥይት ሲቀባበልባቸው፣ አፈሙዝ ሲዞርባቸው ያዩ የተከሳሾች ቤተሰቦች ዋይታ አሰምተዋል። አልቅሰዋል። ያለው ዘገባ አንዲት ዮናታን ተስፋዬ ሲያፅናናቸው የነበሩ እናት “እኔ ልቅደም፣ እኔን ቀድሞ ይግደለኝ” እያሉ ለተከሳሽ ልጃቸው ሲያለቅሱ እንደነበር ተዘግቧል።
ከዚህ ቀደም እስረኞቹ ከዚህ ቀደም ለኢትዮጵያ ሕዝብ፣ለዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶች፣በአገር ውስጥና በውጭ ለሚገኙ መገናኛ ብዙሃናት በሸዋ ሮቢት የቅሊንጦን ቃጠሎ ተከትሎ ሲቃወሙ የነበሩ እስረኞች ዐይናቸው እያየ ተገድለው እሳት መጨመራቸውን፣ሊያመልጡ ነው በሚል ሆን ተብሎ የተፈጸመውን ግድያ ማታቸውን አጋልጠዋል።ድርጊቱን የፈጸሙና ዛሬም በእስር ቤቱ በሀላፊነት ላይ ባሉ የእስር ቤቱ ሀላፊዎችን አሳልፎ ላለመስጠት በሸዋ ሮቢት አማራና ጉራጌ ብሔር ተወላጅ የሆኑትን ግንቦት ሰባት ኦሮሞ የሆኑትን ኦነግ ሙስሊሞችን ከአሸባሪዎች ጋር የወገኑ ሲሉ ከፍተኛ ግፍ እንደፈፀሙባቸው በዝርዝር ይፋ አድርገዋል።የአገዛዙ የሰብዓዊ መብት ኮሚሽንም ያወጣውን የተድበሰበሰ ሪፖርትና አጥፊዎች እንዳይቀጡ ለመሸፋፈን የተደረገውን ሙከራ አውግዘዋል። ዐቃቢ ሕግ ሀሰተኛ ምስክሮችን እያሰለጠነባቸው ማስስከሩን ገልጸው ነበር።
Hiber radio Las Vegas ይህ ህብር ሬድዮ _የወቅታዊ መረጃ ምንጭ ነው። ህብር ሬድዮ በአቤኔዘር ኮሙኒኬሽን ሴንተር እየተዘጋጀ ከላስ ቬጋስ ከተማ፣ ዘወትር ዕሁድ በአካባቢው ሰዓት አቆጣጠር ከምሽቱ 6፤30 ሰዓት እስከ 8 ሰዓት በህብር ሬዲዮ ድህረ ገጽ ወይም በቀጥታ በስልክ ለማዳመጥ 5639993994 ወይም 563999-3988 ፣ 1641-793-8229 ወይም 1641-715-8596 በመረጡት ቁጥር መደወል ብቻ በቂ ነው ። በእንግሊዝ ለምትኖሩ በ01405770140 በስልክ ማዳመጥ ይቻላል። ዘወትር በድህረ ገጻችን፣ ከ googel app store Hiber Radio ወደ ስልክዎ በመጫን ካልሆነም በዘሐበሻ እንዲሁም በተጠቀሱት ስልኮች ማዳመጥ ይቻላል።