ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ብዙ ንግግራቸው ላይ በአፅንኦት<< መደመር >> የሚለውን ቃል ይጠቀማሉ :: ባጠቃላይ ሚኒስትሩ ንግግራቸው ሁሉ የሚያሰባስብ፣ የሚያፋቅር ፣ አንድነትን የሚያስተጋባ:፣ተስፋ የሚሰጥ በመሆኑ ኢትዮጵያን እየለወጡዋት ነው:: ከንንግግራቸው ጋር በተግባር የሚያሳዩት ሁሉ ከጨለማና ሕዝብን ከለያየ ከከፋፈለ በጥቂቶች ተገዝቶ ተዋርዶ ከኖረበት ዘመን ወደ ብርሀንና የተስፋ ዘመን እያሸጋገሩት ነው:: አንዱ የጠቅላይ ሚኒስትሩ መርሆ <<መደመር >> ነው’::
ኢትዮጵያን ታላቅ አድርጓት እስከዛሬ በማንም በምንም ሳትደፈር እዚህ ያደረሳት መደመር ነው:: ኢትዮጵያውያን በባህል፣ በቋንቋ፣ በሀይማኖት ያሸበረቀ የድልና የትግል ታሪክ ተጎናጽፈው የደፈራቸውን ሁሉ ያሸነፉት በመደመራቸው ነው:: እንደሰው በውስጣቸው ልዩነት ኖሮ አልፎ አልፎ ቢጋጩም እንደ አንድ ሕዝብ አንድ አገር ተደምረው አሸንፈው ኢትዮጵያ የምትባል አገር አቆዩን :: በመደመር ያላመኑትና ይህንን እድል ያላገኙት ብዙ የአፍሪካ አገሮች ቅኝ ገዢዎች በሰጧቸው ድንበር ውስጥ ተከፋፍለው ለአገራቸውም ስም ሰጥተው በዚያ ስም ብሔራዊ ስሜት ለመገንባት የሞከሩት ባለፉት ሰባ ዓመታት ውስጥ ነው:: ኢትዮጵያ ግን ኢትዮጵያ ተብላ የኖረችው ከሁለት ሺህ አመታት በላይ ነው:: እንደ ዘመኑ ኢትዮጵያዊነት የተለየ ትርጉም የተለየ አስተዳደር ይኑረው እንጂ ኢትዮጵያዊነት የኖረ የነበረ ስሜትና ዜግነት ነው ::ይህም የሆነው በመደመራችን ነው :: ዛሬ አዲሱ ትውልድ በተለያዩ ርዕዮተ ዓለሞች ተደናግሮ ጥቂቶች ባራመዱት የግራ አስተሳሰብ አገርና ብሔርን ለያይቶ በመመልከት ሕዝብን ለመከፋፈል ሲሞከር በመደመር ፋንታ ተቀነስን ::
በእኔ የውትድርና ዘመን የምናውቀው መደመር ብቻ ነበር :: ቁዋንቃ ባህል ሀይማኖት ሳይከፋፍለን እንደ ሰው ባህርይ ጉድለቶች ብናሳይም በአገር ጉዳይ ላይ ግን ሁል ጊዜ እንደተደመርን ነበር ::
የኤርትራ መገንጠል እንቅስቃሴ ሲወለድ መቀነስ ጀመርን :: በመቀነሳችን ምክንያት ብዙ ሕዝብ አለቀ። ሰላም አጣን። ኢትዮጵያ አካሏ ጎደለ:: መደመርን አውግዘው መቀነስን ለመረጡ ለነሱም አልበጀም። የመደመርን አስተሳሰብ በጥሞናና በሰላም ያላራመደ ህዝብ ወደጦርነት ይሄዳል:: የሚደመረው በሀይል ሳይሆን በፍቅር በውይይት በመቻቻል መሆኑን መረዳት የተሳነው የደርግ መንግሥት ኢትዮጵያ እንድትቀነስ ሁኔታውን አመቻቸ:: በመደመር የማያምነው እንደውም መቀነስን ዓላማው አድርጎ የመጣው የወያኔ መንግስት አገርን ከማስገንጠል አልፎ ሌላው ኢትዮጵያ ከድምር በታች ሆኖ ተከፋፍሎ እንዲኖር የአገዛዙ ፖሊሲ አደረገ :: ኢትዮጵያ በደቡባዊ እፍሪካ ሀገሮች የቅኝ አገዛዝ አስተዳር ያወጀው ( Bantustanization ) ባንቱስታናይዜሽን በውኃላም በደቡብ አፍሪካ የተተገበረው የአፓርታይድ ፖሊሲ ዓይነት ኢትዮጵያ ታወጀባት:: ሕዝብ ተከለለ :: ወያኔ እራሱን ከሌላው ኢትዮጵያ ቀነሰ:: መደመር ለአገዛዙ አደገኛ ስለሆነ ጥቂቶች እንዲገዙ ሌሎች ደግሞ ተከፋፍለው ተገዥ እንዲሆኑ 27 ዓመት የመቀነስ ፖሊሲ ሲያራምድ ኖረ :: ለመግዛት እንዲያመች የአገራችን ታሪክ ጎደፈ፣ተጣመመ ፣ አዲስ ታሪክ ተፈጠረ። ብዙ ሕዝብ ተሰቃየ፣ታሠረ፣ ተገደለ፣ ተለያየ። አገሩን ለቆ በምድረ ሰሀራ ፣በሜዲቴራኔያን ባህር፣ በቀይ ባህር ፣በየመን፣በአረብ አገሮች ምድረ በዳ እና በሲናይ በረሀ አለቀ። ታረደ፣ሰውነቱ እየተቀደደ ኩላሊት መነገጃ ሆነ ::
መደመር ሲዋረድ መቀነስ ሲነግስ ማንንም አልጠቀመም ። ጥቂቶች የተጠቀሙ መስሏቸው ነበር:: መደመር ሲያሸንፍ ኢትዮጵያዊነት አሸነፈ :: በጠ/ሚ አብይ አማካኝነት የመደመር ታሪካችን እየታደሰ ነው :: ስንደመር የአድዋ ነብር፣ የመቅደላ አምበሳ ሆነን ዳር ድንበራችንንና አንድነታችንን ጠብቀን እንኖራለን:: ስንደመር እንፋቀራል። ስንደመር ያለንን እንካፈላለን፡፡ ስንደመር እንከባበራለን። ስንደመር የቋንቋ፣ የሀይማኖት፣ የባህል ልዩነቶች የጥንካሬና የአንድነት ምንጮች እንጂ አይቀንሱንም :: ስለዚህ የጠ/ሚ አብይን መልዕክት በተግባር ለማዋል ለአመራሩም ድጋፍ ለመስጠት መነጋገር መወያየት እንጀምር :: መደመር ሀይል ነው :: ሰሞኑን የሚወጣው ሕዝባዊ ሰልፍ የመደመር ተሀድሶ፣ የአንድነት ሀይል አሸናፊ መሆኑን የሚያበስር ታላቅ ሰልፍና መልዕክት ይሁን :: ስንደመር በማንም በምንም አንሸንፍም :: ሊቀንሱን ፣ ሊያደክሙን፣ ሊበታትኑን፣ሊያፋጁን የሚሞክሩ ሁሉ የታሪክ አተላዎች ሆነው ይቀራሉ :: መደመር ያሸንፋል ::
Hiber radio Las Vegas ይህ ህብር ሬድዮ _የወቅታዊ መረጃ ምንጭ ነው። ህብር ሬድዮ በአቤኔዘር ኮሙኒኬሽን ሴንተር እየተዘጋጀ ከላስ ቬጋስ ከተማ፣ ዘወትር ዕሁድ በአካባቢው ሰዓት አቆጣጠር ከምሽቱ 6፤30 ሰዓት እስከ 8 ሰዓት በህብር ሬዲዮ ድህረ ገጽ ወይም በቀጥታ በስልክ ለማዳመጥ 5639993994 ወይም 563999-3988 ፣ 1641-793-8229 ወይም 1641-715-8596 በመረጡት ቁጥር መደወል ብቻ በቂ ነው ። በእንግሊዝ ለምትኖሩ በ01405770140 በስልክ ማዳመጥ ይቻላል። ዘወትር በድህረ ገጻችን፣ ከ googel app store Hiber Radio ወደ ስልክዎ በመጫን ካልሆነም በዘሐበሻ እንዲሁም በተጠቀሱት ስልኮች ማዳመጥ ይቻላል።