በቀደመው ትውልድ ለሕይወታቸው ሳይሳሱ መስዋዕት የሆኑ የኢህአፓ አባላት የነበሩ ሴት ታጋዮች ነበሩ።ዛሬም ከመስዋዕትነት የተረፉት በተለያዩ ጊዜያት አልፎ አልፎ በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ሲናገሩ ቆይተዋል።ሰሞኑን በአገራችን ያለውን የለውጥ ተስፋ አስመልከቶ እነሆ ያወቱት መግለጫ፦
የታጋይ ሴቶች ድምፅ
እጅግ የተራዘመው የዲሞክራሲ ትግል ጥሪ የነፃነት ጮራ እያበራ መምጣቱ ተስፋ ይሰጣል።
እንደሚታወቀው ምርጥ ጀግኖችን የተነጠቅነው፣ በእስራትና በግርፋት የተሰቃየነው፣ ለስደትም የተዳረግነው በአገራችን ላይ
እንደዜጋ መብታችን ተከብሮ ሃሳባችንን ገልጸን ኮርተንና ተደስተን መኖር በመፈለጋችን ነው። “ያነበበ ያስነበበ፣ የፃፈ ያፃፈ፣
ያሰበ ያሳሰበ፣ የጠየቀ ያስጠየቀ፣ ወዘተ…” እንደወንጀለኛ እየተያዘ ወፌላላ ሲገረፍ፣ሲገደል፣ እሬሳው መንገድ ላይ ሲጣል፣
ማንነታችንን አዋርደው ኢሰብአዊ ድርጊት በመፈጸሙ እስከ ትጥቅ ትግል ፍልሚያ ደርሰን ነበር።
ቢሆንም የተመኘነው የህዝብ መንግስትና ዲሞክራሲ የህልም እንጀራ ሆነ፤ ትግላችንም ተራዘመ። ባላሰብነው መንገድም
የብሔር ፖለቲካ ከለላት፣ የእርስ በርስ ጥላቻና አለመተማመን ነገሰ፣ የአምባ ገነኖችም ግፍ ቄሮን ፋኖንና ዘርማን ወለደ።
ልጆቻችን አኮሩን። ኢትዮጵያን እንደገና ወለዷት። ታሪክም ራሷን ደገመች። እኛም ከሩቅ ሆነን ሲወድቁ እየወደቅን፣ ሲታሰሩ
እየከፋን፣ ሲሞቱ እያለቀስን፣ በምንችለው ሁሉ ጩኸት እያሰማን በመንፈስ አብረናቸው ነበርን። የዚህ ህዝብ የትግል ውጤት
ጠ/ ሚኒስትር አብይ አህመድን፥ ለማ መገርሳን፥ ገዱ አንዳርጋቸውንና የመሳሰሉትን ቁርጠኛ የኢትዮጵያ መሪዎችን አፈራ።
በተለይም ጠ/ ሚኒስትር አቢይ አህመድ ከስልጣን ርክክባቸው ጀምሮ ሴቶች በህብረተሰቦች ውስጥ ስላላቸው የተከበረ
አስተዋጽዖ ሊኖራቸውም ስለሚገባው ክብርና ተቀባይነት ከእናታቸውና ከሚስታቸው ምስጋና በላይ ለኢትዮጵያ ሴቶች
ባጠቃላይ ባሰሙት ንግግር ልባችን በጣም ተነክቷል ለዚህም ልናመሰግናቸውና ልንደግፋቸው እንወዳለን።
ስለዚህም ከዛሬዋ ቀን ጀምሮ የኢትዮጵያ እናቶች በልጆቻቸው ሬሳ ላይ አይቀመጡም፤ ደረታቸውንም አይደቁም።
ፊታቸውንም አይነጩም፤ አንጀታቸው ለረሃብ አይናቸው ለእንባ አይዳረግም። እኛ ታጋይ ሴቶች ይህን ባገራችን ላይ እያበበ
የመጣውን የለውጥ ኃይል ለዲሞክራሲ እስከታገለ ድረስ ከጎኑ በመቆም ድጋፋችንን እንሰጠዋለን፥ አብረነውም እንታገላለን።
በዚህም ትግል መላው አገር ወዳድ ዲሞክራሲያዊ ሴቶች አብረውን እንዲታገሉ ጥሪ እናቀርባለን።
በአገርና በውጭ አገር ያላችሁ የተቃዋሚ ቡድኖችም ይህን የተቀደሰ አሳብ በመጋራት ሴቶች በራሳቸው በነፃነት እንዲደራጁና
የራሳቸውንም ጥያቄ በማንሳት ራሳቸውንና ህብረተሰቡን እንዲያስተምሩ ባገራቸውም የፖለቲካ መስክ እንዲሳተፉ
በተቻላችሁ ሁሉ ድጋፍና ትብብር እንድታደርጉ ባገር ስም እንጠይቃለን። እንደዚሁም ይህን የጥፋት ዘመን አጥፍተን
የነገዋን የሰላም አገር ለመፍጠር ዜጎቿ ሁሉ እኩል እንዲሆኑ በውጭና በውስጥ ያሉ የተቀናቃኝ ሃይሎች የጋራ ውይይት
በማካሄድ የጋራ መፍትኄ እንዲያመጡ መንገድ ቢከፈት ቀና ጉዞ ይሆናል ብለን እናምናለን።
በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያችን የምትጠይቀው ማንኛውም አገር ወዳድ የሩቅ ተመልካች ሳይሆን ተጠራጣሪና አበጣሪ ከመሆን
ተቆጥቦ ይህ ትግል እስከ ወሰደን ዳርቻ ድረስ በአዲስ ሃይልና በአዲስ መንፈስ ተባብረን የህዝብን ሃያልነትና አሸናፊነት
ማሳየት ይኖርብናል። ትግሉ ተጀመረ እንጂ አላለቀም። መጪው ትውልድ የሚኮራባትን አዲሲቷን ኢትዮጵያ መረከብ
ይገባዋል። አገራችን ብዙ ጀግኖች ብታጣም ጀግና እንደ ውሃ ይፈልቅባታል።
ያሁኑ ትግል:
ይጠናቀቃል በድል፤
የዲሞክራሲ ስራ:
ይከናወናል በጋራ፤
ትግሉም ይቀጥላል፡
የደፈረሰው ይጠራል፤
ታጋይ ሴቶች፡
የነፃነት ችቦዎች።
ትግሉ ያሸንፋል!
ኢትዮጵያ ለዘላለም ትኑር!
Hiber radio Las Vegas ይህ ህብር ሬድዮ _የወቅታዊ መረጃ ምንጭ ነው። ህብር ሬድዮ በአቤኔዘር ኮሙኒኬሽን ሴንተር እየተዘጋጀ ከላስ ቬጋስ ከተማ፣ ዘወትር ዕሁድ በአካባቢው ሰዓት አቆጣጠር ከምሽቱ 6፤30 ሰዓት እስከ 8 ሰዓት በህብር ሬዲዮ ድህረ ገጽ ወይም በቀጥታ በስልክ ለማዳመጥ 5639993994 ወይም 563999-3988 ፣ 1641-793-8229 ወይም 1641-715-8596 በመረጡት ቁጥር መደወል ብቻ በቂ ነው ። በእንግሊዝ ለምትኖሩ በ01405770140 በስልክ ማዳመጥ ይቻላል። ዘወትር በድህረ ገጻችን፣ ከ googel app store Hiber Radio ወደ ስልክዎ በመጫን ካልሆነም በዘሐበሻ እንዲሁም በተጠቀሱት ስልኮች ማዳመጥ ይቻላል።