አብን መከላከያ በአማራ ሕዝብ ላይ ትላንትና ዛሬ ያደረገውን ጭፍጨፋ ተከትሎ ጠንካራ መግልጫ ያወጣ ሲሆን የመግለጫው ሙሉ ቃለ ተከትሎ ቀርቧል።
የመከላከያ ሰራዊት በአማራ ላይ የሚያደርሰውን ግድያ በአስቸኳይ ሊያቆም ይገባል!
*****
መከላከያ ሰራዊት የአገርን ዳር ድንበር ከማስጠበቅ ዘሎ በየደረጃው ያሉ የአስተዳደር አካላት ባልጠየቁበትና አገራዊ ሰላምን የሚያናጋ አንዳችም ነገር ባልተፈጠረበት ሁኔታ በተደጋጋሚ ጊዜ በአማራ ሕዝብ ላይ በሚወስደው ሕገወጥና ጅምላ ጭፍጨፋና ግድያ ተቋሙ ላይ ዜጎች እምነት እንዲያጡ ሲያደርግ ቆይቷል።
የአማራ ሕዝብ የዘር ማጥፋት ወንጀል የፈፀመውን የሕወኃት አፋኝ ሥርዓት ገርስሶ አንፃራዊ የለውጥ ነፋስ እንዲመጣ ከፍተኛ መስዕዋትነትን ከፍሏል። ኢህአዴግን ከሕወኃታዊ አፋኝ መዋቅር ነፃ ለማውጣት ባደረገው ከፍተኛ ተጋድሎ መከላከያን ጨምሮ በሕወኃት ሳንባ ከሚተነፍሰው የፀጥታና ደኅንነት መዋቅር ጋር አንገት ለአንገት ተናንቋል። ያን ሁሉ ታሪካዊ ተጋድሎ ያደረገው ግን ዛሬም ራሳቸውን የለውጥ ኃይሎች ብለው በሚያሞካሹ አካላት እዝ ሥር ባለ የመከላከያ መዋቅር በአደባባይ በጥይት ለመገደል አልነበረም።
የአገር ዳር ድንበር ተጥሶ የኢትዮጵያ ሉዓላዊ ግዛት በሕወኃት ጋሻ ጃግሬ በሆነው የሱዳን ጦር ሲደፈር በዝምታ የተመለከተው መከላከያ የአማራ ሕዝብን ውስጣዊ አንድነትና ሰላም ለማናጋት የግጭት ነጋዴ የሆነን የአሸባሪው ሕወኃት ድርጅት ላይ ሕዝብ በመረጃና ተጨባጭ ማስረጃ ጭምር ያቀረበውን የይፈተሽልን ሰላማዊ ጥያቄ ንፁኃን አማራዎችን በጥይት ደብድቦ የፈፀመው ግድያ የፌዴራሉ መንግስት በተለይም የመከላከያ ሰራዊቱ ዛሬም ድረስ በአማራ ጥላቻ ስካር ላይ መሆኑን ያረጋገጠ ድርጊት ነው። በተለይ ደግሞ የራሱን ተሽከርካሪዎችና የመከላከያ ማሽነሪዎችን እንዳያንቀሳቅስ እገታ ሲፈፀምበት በዝምታ ያሳለፈ ተቋም መሆኑን ስንገዘብ የመከላከያ መዋቅሩ አማራ ላይ ያደረገው አሳፋሪ ተግባርን በከፍተኛ ጥርጣሬ እንድናየው ያስገድደናል።
ስለሆነም የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ(አብን)፦
1) የጦር ኃይሎች ጠቅላይ አዛዥ፣ የመከላከያ ሚኒስትሯና ኢታማዦር ሹሙ በተፈጠረው ጉዳይ ላይ ግልፅ ማብራሪያ እንዲሰጡን እንጠይቃለን።
2) የመከላከያ ሰራዊት በንፁኃን አማራዎች ላይ ግድያ እንዲፈፀም ትዕዛዝ የሰጡ አመራሮችና ወንጀሉን የፈፀሙ የሰራዊቱ አባላት በሕግ እንዲጠየቁ ይጠይቃል። በንፁኃን ዜጎች ላይ ለደረሰው ግድያም መንግስት ይቅርታ እንዲጠይቅና ለተጎጂ ቤተሰቦችም ካሳ እንዲከፍል እንጠይቃለን።
3) የመከላከያ ሰራዊት የክልሉ መንግስት ባልጠየቀበት ሁኔታ በተራ የደንብ ማስከበር ሥራ ከመሰማራት ተቆጥቦ ወደ ካምፑ እንዲሰባሰብና ሰላማዊ ሕዝብን ከማሸበር ድርጊቱም እንዲቆጠብ እንጠይቃለን።
4) የክልሉ መንግስት በተለይም የአማራ የፀጥታ ኃይሎች በሰላማዊ ሕዝባችን ላይ ከማናቸውም አካል የሚቃጣን ጥቃት እንዲከላከሉ እንጠይቃለን።
5) መላው አማራ ከተጎጂ ወገኖች ጋር እንዲሆንና ከመቼውም በላይ አንድነቱን እንዲያፀና፤ ራሱን የመከላከል ተፈጥሯዊ መብቱንም እንዲያስከብር እንጠይቃለን።
በመጨረሻም ለሰማዕት ቤተሰቦችና ለመላው አማራ ሕዝብ መጽናናትን እንመኛለን።
የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ
ጥር 01/2011 ዓ/ም
አዲስ አበባ፥ ሸዋ፣ ኢትዮጵያ