አቶ ኤርሚያስ ለገሰ ሕዝቡ በይስሙላው ምርጫ ድምጽ መስጫ ላይ ለስርዓቱ ያለውን ተቃውሞ እንዲገልጽበት ጥሪ አስተላለፉ፣የተቃዋሚ ታዛቢዎች ለፓርቲያቸው የተሰጠውን ድምጽ መቁጠር ብቻ ሳይሆን የተበላሹትን ገዢው ፓርቲ እንዳይጠቀምባቸው ተከላከሉ ሲሉ አስጠነቀቁ

 

Ermias-Legesse_006(ሕብር ሬዲዮ -ላስቬጋስ )አስቀድሞ ውጤቱ የታወቀውና የህዝቡ ድምጽ የማይከበርበት ኢህአዴግ ለራሱ የፈለገውን ድምጽ የሚወስድበት የይስሙላ ምርጫ እለት አማራጭ ጠፍቶ ወደ ምርጫ ጣቢያው ለመሄድ የተገደደ እና ገዢውን ፓርቲም ሆነ ተቃዋሚን የማይመርጡ በተለይም የታቃዋሚ ምንም ዕጩ የሊለባቸውም ሆነ ቢኖሩም ታዛቢ እንዳይገኝ የተደረገባቸው ቦታዎች ህዝቡ ወት በሆነ መንገድ በድምጽ መስጫው ወረቀት ላይ በምስጢር ተቃውሞውን እንዲገልጽ አቶ ኤርሚአስ ለገሰ የቀድሞው የአገዛዙ የኮሚኒኬሽን ሚኒስትር ዴኤታና የመለስ ቱርፋቶች ደራሲ ገለጹ።

አቶ ኤርሚያስ ለገሰ የተግባር ሳምንት ብለው በምርጫው ዋዜማ ባወጡት ጽሑፍ በዚህ ወቅት በምርጫው ዕለት ሊከወኑ የሚችሉ ጉዳዮችን ዘርዝረው ለሕዝቡና ለተቃዋሚ መሪዎች ጥሪ አስተላልፈዋል። በዚህ ጽሁፋቸው ተቃዋሚዎች በሁሉም ዕጮዎቻቸው ባሉበት ቦታዎች ታዛቢ እንዲያስቀምጡ እና በምርጫ 2002 የተቃዋሚ ታዛቢዎች እንዳደረጉት ሳይሆን ለፓርቲያቸው የተሸጠውን ድምጽ ብቻ ሳይሆን የተበላሹትን ለብቻ ቆጥረው ለይተው ድምጽ አልባ እንዲሆኑ የማስደረግ እና በፍጥነት ለፓርቲያቸው ሪፖርት የማድርግ ግዴታቸውን እንዲወጡ ጠይቀዋል። ያ ካልሆነ ገዢው ፓርቲ ከዚህ ቀደም እንዳደረገው የተበላሺትን ወረቀቶች ድምጽ አልባ እንዳይሆኑ በማስደረግ ለራሱ ይጠቀምባቸዋል ብለዋል።

በድምጽ መስጫው ላይ የሚደረጉ ተቃውሞዎችን ወጥ እንዲሆኑ ማድረግ አስፈላጊ መሆኑን የጠቆሙት የቅድሞ የአገዛዙ የኮሚኒኬሽን ሚኒስትር ዴኤታ ወደ ምርጫ ጣቢያ መሄድ የህልውና ጉዳይ ሆኖበት ስርዓቱን መምረጥ የማይፈልገው ሌላው ቀርቶ የራሱ የድርጅት አባል ሆነው ለስራ ዋስትና ሲሉ የሚመርጡ ያላቸውን የውስጥ ተቃውሞ በምስጢር ድምጽ በሚሰጥበት የድምጽ መስጫ ወረቀት ላይ ተቃውሞን በመጻፍ ለስርዓቱ ያለን ተቃውሞ መግለጫ ብቸኛና ለደህንነት የማያሰጋ መሆኑን ገልጸዋል።

የተቃውሞው መልዕክቶች ወጥ እንዲሆኑ ማድረግ ላይ ስምምነት ከተፈጠረ ለዚሁ የሚሆን ዘዴ መቀየስ አስፈላጊነቱን የጠቆሙት አቶ ኤርሚያስ የሙስሊሙ ማህበረሰብ <<ፍትህ>> የሚለውን ወይም ጨረቃን መሳልና ሌሎችንም የተስማማባቸውን ክርስቲያኑም በሊቢያ መስዋዕት የሆኑትን ለማሰብ መስቀል አሊአም ሌላ በጋራ በመጠቀም ተቃውሞን መግለጽ ሲሆን ከዚህ ውጭ ለውጥ በኢትዮጵአ በትጥቅ ትግል ነው የሚመጣው ብለው የሚአምኑም በተመሳሳይ ወጥ በሆነ መንገድ በምስጢር ሀሳባቸውን በመግለጽ የውስጥ ተቃውሟቸውን ለማሳየት የይስሙላውን ምርጫ ይጠቀሙበት ሲሉ በጽሁፋቸው ገልጸዋል።

<<ምርጫው አስቀድሞ ያለቀና ነጻ አለመሆኑን ሕዝበ ተረድቷል>> ያሉት አቶ ኤርሚያስ ዋጋ የሚያስከፍለው ነገር ግን ጉልህ የተቃውሞ ማሳያ መንገድ ያሉትንም በጽሁፋቸው ጠቅሰው ያም ወደ ምርጫ ጣቢያው ዝር አለማለት በተለይ ይህ የተቃዋሚ ታዛቢዎች በሌሎበት አካባቢ ትርጉም ያለው የተቃውሞ ማሳያ ሊሆን እንደሚችል ገልጸዋል። መሰረታዊ የዲሞክራሲና የሰብኣዊ መብት በተገፈፈበት የሲቪል ተቋማት በተሽመደመዱበት ፣ የገዢውን ፓርቲ ፕሮፖጋንዳ የሚያሰራጩ ሚዲያዎች ብቻ ባሉበት፣የብዕር አርበኞችና የሀይማኖት ነጻነት ታጋዮች በአሸባሪው ጸረ ሽብር አዋጁ በተከሰሱበት ፣ገዢውን ፓርቲ በተወሰነ መልኩ ሊገዳደሩ የሚችሉ የፖለቲካ ፓርቲዎች በፖለቲካ ውሳኔ ተላልፈው በተሰጡበት የምርጫ ካርድ ተሸክሞ ወደ ምርጫ ጣቢያ መሄድ የሞራል ጥያቄ ማስነሳቱ አይቀርም ብለዋል።

አቶ ኢርሚያስ በመጪው ዕሁድ ለምርጫ ህ/ሰቡ ምን ፈልጌ ነው ድምጽ ምሰጠው ? ምን ለማትረፍ? የተጠቀሱት መሰረታዊ ችግሮች በኔ ድምጽ ይፈታሉ ብሎ እያንዳንዱ እራሱን ሊጠይቅ የሚገባበት ሳምንት ነው ብለዋል። በአዲስ አበባ በምርጫ 2002 የሆነውን በማሳያነት አጣቅሰው ለምርጫ ከተመዘገበው ውስጥ 43.8 በመቶ ብቻ ለምርጫ ሲወጣ የቀረው ለምርጫ ባለመውጣት ተቃውሞውን አሳይቷል ሲሉ የፕ/ር መስፍን ወልደማሪያምን ጥናትን መሰረት ያደረገውን <<ስልጣን ፣ባህልና አገዛዝ፣ ፖለቲካና ምርጫ>> የሚለውን መጽሐፍ አብይ ማስረጃዎች ጠቅሰዋል። ለምርጫ አለመውጣት በገጠራማ አካባቢዎች እንደ አፋር፣ሱማሊ ክልል፣ጋምቤላ፣ቤንሻንጉል እና ትግራይን በመሳሰሉ አካባቢዎች አስቀድሞ ኮሮጆ ተሞልቶ ስለሚያልቅ ትርጉም እንደሌለው ገልጸዋል።

አቶ ኤርሚያስ ለገሰ የመለስ ቱርፋቶች ባለቤት አልባ ከተማ በሚል መጽሐፋቸው ውስጥ ኢህአዴግ በምርጫ 2002 የሕዝብ ድምጽ እንዴት እንደዘረፈ እና ምርቻውም አስቀድሞ የተበላ ዕቁብ እንደነበር ጠቅሰው የጻፉትን መሰረት አድርገን ለሕብር ሬዲዮ በሰጡን ቃለ መጠይቅ የዘንድሮውም ምርቻ ከተበላ ዕቁብነት የማይዘልና በስልታን ላይ ያለው ስርዓት በምርጫ ይወድቃል ብለው እንደማያምኑ ነገር ግን በሰላማዊ መንገድ እንታገላለን የሚሉትንም እንደማይቃወሙ መግለጻቸው ይታወሳል።

(ህብር ሬዲዮን ዘወትር ከህብርና በዘሐበሻ ድህረ ገጽ በተጨማሪ በማንኛውም ቀን በስልክ ለማዳመጥ 7124328451 ይደውሉ)

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *