የሕወሓት እና የአዴፓ የቃላት ጦርነት ፣መዘዙ…
የኢሕአዲግ መስራች ድርጅቶች የሆኑት ህዝባዊ ወያኔ ሓርነት ትግራይ(ሕወሓት) እና የአማራ ዲሞክራሲ
ፓርቲ (አዴፓ) ከከባድ መሳሪያ ፍልሚያ ያልተናነሰ ፣ ሙት እና ቁስለኛ ያል ያልተለቀመበት ፣ያልተቆጠረበት ፣ነገር ግን የተካረረ የቃላት ጦርነት ውስጥ ገብተዋል።
ሁለቱ ፓርቲዎች የቆየ ልዪነቶች እንዳሏቸው ቢታወቅም ሰሞነኛው መሻኮት እና ተቃርኗቸው እንዲህ ገኖ እንዲወጣ ዋንኛ ምክንያት የሆነው ባለፈው ሰኔ 15 2011 ዓም በባህርዳር እና በአ/አ ከተሞች ውስጥ ለጠፋው የአምስት ከፍተኛ የክልል እና የፊደራል ባለስልጣናት ህይወት “የአዲፓ እንዝላልነት ነው” የሚለው የህዋት ማዕከላዊ ኮሚቴ ካካሄደው ስብሰባ በሁዋላ ይፋ ያደረገው የከረረ የ ወቀስ መግለጫውን ተከትሎ ነው።
እንደ ሕወሓት እምነት ለተፈጠረው የደህንነት ችግር ” አዲፓ በአማራ ክልል ውስጥ ስርአተ አልበኝነትእንዲፈጠር፣የትምክህት ሀይሎች እንዳሻቸው እንዲፈነጩ ፈቅዷል ፣ለተፈጠረው ችግሩም ህዝቡን ይቅርታ ካልጠየቀ፣አብረን የምንጓዝ አይመስለንም “ሲል ሕወሓት በመግለጫው አስፈራርቷል።
በትላንትናው እለት ባህርዳር ከተማ ውስጥ ለስብሰባ የተቀመጠው የአዴፓ ማእከላዊ ኮሚቴ በበኩሉ ” በሰሞኑ ችግር አገራችን ኢትዬጵያ እና ሕዝቦቿ የሀዘን ማቅ ባጠለቁበት በዚህ ወቅት ፣ህዝብን እና አገርን የበደሉ እና የዘረፉ ባለስልጣናትን ከተጠያቂነት ለማሸሽ በጉያው የደበቀ፣በአገሪቱ የተጀመረው ለውጡን ለመቀልበስ ከጥፋት ኃይሎች ጋር የወገነው ሕወሓት ይህንን መሰሉ ሀላፊነት የጎደለው መግለጫን በዚህ ወቅት ማውጣቱ በእጅጉ አሳፋሪ ነው፣ድርጊቱም በሰው ቁስል እንጨት የመስደድ ያህል ነው “በማለት የአዴፓ ማእከላዊ ኮሚቴ ከዚህ ቀደም በኢሕአዲግ እህትማማች ፓርቲዎች ታሪክ ያልታየ እጅግ ቅሬታ አዘል መግለጫውን ለህዝቡ ይፋ አድርጓል።
የ ሕወሓት ማእከላዊ ኮሚቴ መግለጫ በበኩሉ ” አዴፓ ውስጣዊ ችግሮቹን ውጫዊ እና ረጃጅም እጆች እንዳሉበት በማስመሰል የሚያቀርበውን ማደናገሪያውን ሊያቆም ይገባዋል”በማለት ያስጠነቅቃል።
የሕወሓትን ውንጀላን በጭራሽ እንደማይቀበል የገለጸው የአዴፓ ማእከላው ኮሚቴ”ሕወሓት ከጅማሮው ጸረ አማራ አቋም አራማጅ ነውና ፣ለመለወጥ ያልተዘጋጀ ፣የዘመናት ወንጀሎቹን ለመሸፋፈን እና ለውጡ እንዲመጣ ከውስጥ ሆኖ የታገለው አዴፓን የሕዝቡ ጠላት አድርጎ በማቅርብ እና በማደናገር ላይ ይገኛል” ሲል ሕወሓትን በጽኑ ወቅሶታል።
የቃላት ጦርነቱ ዋንኛ መንስኤ በግርድፉ:-
የሁለቱ የኢሕአዲግ እህትማማች ድርጅቶች የሆኑት የአዴፓ እና የሕወሓት እንደዚህ በአደባባይ ወጥቶ በቃላት መቆረቋቆስ የዘር ተኮሩ ኢሕአዲጋዊ አስተዳደር ውጤት እንደሆነ፣ይዘቱም የመሰነጣጠቅ አደጋ የመጀመሪያው ምልክት እና አገሪቱን ወደ ተሻለ ስርአት አሸጋግራታለሁ ብሎ ቃል ከገባ አመት ከስድስት ወር ያልሞላው ኢሕአዲግ በአሸዋ ላይ የቆመ፣ እርሱን እንኳን መጠገን እንደተሳነው ያመላክታል የሚሉ የፓለቲካ ታዛቢዎች ብዙዎች ናቸው።
እንደ እነዚህ የፓለቲካ ተጠባቢያን ምልከታ የኢህአዲግ አባል ፓርቲዎች የሆኑት ኦዲፓ፣ሕወሓት እና ደኢህዴን ዛሬም በለውጥ ሂደቱ ወቅት ሙሉ በሙሉ ከለውጡ ጋር ያለመናበብ፣የሕዝቡን የዲሞክራሲያዊ እና የእኩልነት ፍላጎትን ባለማጤን ” ሕዋቶች በድሮ በሬ ካልታረሰ ወደ ሚል የገመድ ጉተታ እና የእጅ ጥምዘዛ ውስጥ እንደገቡ ያመላክታል “ሲሉ ይተቻሉ።
የቃላት ጦርነቱ ወዴት ያመራ ይሆን?:-
በአገሪቱ ውስጥ (በተለይ በኦሮሚያ፣በአማራ እና በትግራይ ክልሎች) ከመከላከያ ሰራዊቱ ያልተናነሰ ፣ተጠሪነቱ ለክልሎቹ ብቻ የሆነ የታጠቀ የሚሊሺያ ኃይል እንደተከማቸ የፌደራል እና የመከለከያ ባለስልጣናት በቅርቡ በአደበባይ ሲያስጠነቅቁ እና የአገሪቱ የደህንነት ሁኔታም ከአጣብቂኝ ውስጥ መውደቁን ሲያመላክቱ ተስተውለዋል። ከዚህ አኳያ በአሁኑ ወቅት የሚታየው የቃላት እና የስነልቦና ጦርነትም ቢሆን ለፓርቲዎቹ፣ለክልሎቹ ሆነ ለአጠቃላይ ለአገሪቱ አንጻራዊ የሰላም እና የደህንነት ዋስትናን ያመጣል ተብሎ አይጠበቅም፣ከተጠበቀም እጅግ የዋህነት ነው።
ምን ማድረግ ይጠበቃል?:-
ከመቀሌ እና ከባህር ዳር ከተሞች የወጡት የሕወሓት እና የአዴፓ መግለጫዎች ምንም እንኳን የገዢው የኢህአዲግ አባላት የሆኑ የሁለት ፓርቲዎች ሽኩቻ ቢመስልም የቃላት ጦርነቱ አውንታዊ ወይም አሉታዊ መልእክት የሚያርፈው በክልሉ ለሚገኙ ብሔሮች ብቻ ሳይሆን ለመላው ኢትዬጵያዊ መሆኑ አያጠያይቅም።
ከዚህ አኳያ ከኢትዬጵያ አልፎ በጎረቤት አገራት:- በሱዳን እንዲሁም በሶማሊያ እና በኬኒያ መካከል ሳይቀር እርቅ ሰላም እናመጣለን የሚል ተስፋ የሰነቀው የጠ/ሚ/ር አብይ አሕመድ አስተዳደር ለጊዜው ወደ አጎራባች አገራት የሚያደርገው የዲፕሎማሳዊ እሩጫውን ተውት አድርጎ ያለ የሌለ ሀይሉን ወደ አገር ውስጥ ችግሮቹ በማተኮር፣ቤቱን በማጽዳት ያንጃበበውን ይውጥረት ዳመናን ቢገፈው ይመረጣል።
የሰሞነኛው የቃላት ጦርነት እና የጣት የመቀሳሰር ዘመቻው ዳፋው ከኢሕአዲግ እህት አባላቱ(የሕወሓት እና የአዴፓ) የሚዘል በመሆኑ የፓርቲ ፣ የድርጅት፣ የግንባር…ወዘተ ጭምብል ማጥለቁን፣በስሜት እና በእልህ ባህር መዋኘቱን ለጊዜው ገታ አድርጎ እየተንገዳገደ የሚገኘው ኢሕአዲግ ካለማቅማማት እና “የውስጥ ችግሮቼን ለእኔው ተዉልኝ፣ እራሴው እፈታዋለሁ “ከሚለው የሃያ ሰባት አመቱ ያረጀ እና ስንኩል አስተሳሰቡ ተላቆ ከ ተፎካካሪ ፓርቲዎች፣ከሀይማኖት አባቶች፣ከአገር ሽማግሌዎች ከሲቪክ ማህበረሰቡ፣ከአክቲቪስቶች እና ከጋዜጠኞች …ወዘተ ጋር በአፋጣኝ ሊለወጡ ወይም ሊጠገኑ በሚገባቸው ብሔራዊ እና አገራዊ ጉዳዬች ዙሪያ መምከር ፣መመካከር የግድ ይለዋል።
ይህ አይነቱ አቀራረብ የአሽናፊነት እና የተሸናፊነት መድረክን መፍጠር ሳይሆን ለአንዲት ኢትዬጵያ እና ለልጆቿ መጻኢ እድል ሲባል የሚከፈል መስዋትነት ተደርጎ ሊቆጠር ይገባዋል።እርምጃ ውም ጊዜ የማይሰጥ፣ብልህነት እና አርቆ እስተዋይነትም ጭምር ነው።