ህብር ሬዲዮ (ላስ-ቬጋስ) የሰማያዊ ፓርቲ የምስራቅ ጎጃም ዞን ጸሐፊና በዘንድሮው ምርጫ ፓርቲውን በመወከል ለፓርላማ የተወዳደረውና በከፍተና ድምጽ አሸንፎ እንደሌሎች ቦታዎች ድምጹ የተዘረፈበት ሳሙኤል አወቀ ትላንት ሰኔ 8 ቀን 2007 ከመኖሪያ ቤቱ አቅራቢያ በሁለት የአገዛዙ ሰዎች በደረሰበት ድብደባ ሆስፒታል ሄዶ ሕይወቱ አልፏል። የዘንድሮውን ምርቻ ተከትሎ ሳሙኤል ሲገደል ሶስተኛው የተቃዋሚ ፓርቲ አባል ነው።
አገዛዙ መቶ በመቶ አሸነፍኩ ያለበትን የዘረፈውን የምርጫ ውጤት እንዲቀበሉ የተቃዋሚ የምርጫ ታዛቢዎችንና ጠንካራ አባላትን እያሳደደ ያለው የህወሃት ኢህአዴግ አገዛዝ በሳሙኤል ላይ ያለመከሰስ መብት እያለው ግንቦት 21 ቀን 2007 ከፍተኛ ድብደባ ፈጽመውበት የነበረ ሲሆን ከዚያም በሁዋላ ተደጋጋሚ ጫና በደህነቶች ይደርስበት ስለነበር ከሁለት ሳምንት በፊት ለደብረ ማርቆስ ነዋሪዎች በፌስ ቡክ ገጹ ላይ ባሰፈረው ማስታወሻ << …ከገደሉኝም በተሌኢ እንደኔ ወጣቶች ትግሉን አደራ >> ሲል ጠይቆ ነበር።
ትላንት በአገዛዙ በደረሰበት ድብደባ ሕይወቱ ያለፈው ሳሙኤል አወቀ ዓለም ከሁለት ሳምንት በፊት በጻፈው በዚህ ማስታወሳው ላይ <<..ማንኛውም የምከፍለው ዋጋ ለሀገሬ እና ለነፃነት ነው፡፡ ከታሠርሁም ሕሊናዬ አይታሰርም ከገደሉኝም ትግሌን አደራ በተለይ የኔ ትውልድ አደራ! አገራችን የወያኔ ዘረኞች ብቻ መፈንጫ መሆን የለባትም! ትግላችን የነፃነት ጉዟችን ጎርባጣ መድረሻችን ነፃነት ታሪካችን ዘላለማዊ ነው! …>> ብሏል።ከዚህ በተጨማሪ ለሚደርስበት እስራትም ሆነ ድብደባ ወይም ግድያ ተጠያቂ ናቸው ያላቸውን በዚአው ጽሁፉ አስፍሯል። በዚያ ጽሁፍ ቃል በቃል <<ተገደልሁም፣ ታሠርሁም፣ ታፈንኩም ነፃነት አይቀርም እና ለማሰረጃነት የደሕንነቶችን ስም፤ ፎቶግራፍ ፤ እና አድራሻ እንዲሁም በሐሠት ምሰክርነት እና ከሳሽነት የተደራጁ አካላት እና ዋና ተወካዮች የደብረማርቆስ ከተማ 04 ቀበሌ አመራሮች እና ፖሊስ ለታሪክ አሰመዘግባለሁ፡፡…>> ሲል ሁኔታውን ገልጾት ነበር።
የዘንድሮውን ምርጫ ተከትሎ ሁለት የመድረኩ አባል የሆነው የእነ ዶ/ር መረራ ጉዲና የኦሮሞ ፌዴራሊስት ዲሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ኦ.ፌ.ዲ.ን) ሁለት የምርጫ ታዛቢዎች የህዝቡን ድምጽ አናዘርፍም በማለታቸው በአገዛዙ ታጣቂዎች መገደላቸው ይታወሳል።
አቶ ሳሙኤል አወቀ ትላንት ከመገደሉ አስቀድሞ ከሁለት ሳምንት በፌስ ቡክ ገጹ የጻፈውን እንድታነቡ አያይዘናዋል።
ውድ የደብረማርቆስ ከተማ ኗሪዎች!
ሰማያዊ ፓርቲን የመረጣችሁ ከ25’0000 በላይ መራጮች(ኮረጆውን) እርሱት እና በተጨማሪም በ31 ዩኒቨርስቲ የምትገኙ ከ14,000 በላይ ሰማያዊ ፓርቲን የመረጣችሁ ሌሎች ደጋፊዎች እና የኢሕአዴግ አባላትም የማያፍረው ብአዴን / ኢሕአዴግ ድምፅ መቀማቱ ሳያንስ በ21/08/2007 ዓም አፍነው ደብድበው ከሞት መትረፌ ቆጭቷቸው እሰር ቤት ለመወርወር ያለመከሰስ መብቴን እንኳን ተዳፍረው የሀሰት ክሰ እየፈጠሩ ነው!
በስልኬ እደተደወለም ያለፍላጎቴ ደሕንነት እያስገደደኝ ይገኛል፡፡
ተገደልሁም፣ ታሠርሁም፣ ታፈንኩም ነፃነት አይቀርም እና ለማሰረጃነት የደሕንነቶችን ስም፤ ፎቶግራፍ ፤ እና አድራሻ እንዲሁም በሐሠት ምሰክርነት እና ከሳሽነት የተደራጁ አካላት እና ዋና ተወካዮች የደብረማርቆስ ከተማ 04 ቀበሌ አመራሮች እና ፖሊስ ለታሪክ አሰመዘግባለሁ፡፡ ማንኛውም የምከፍለው ዋጋ ለሀገሬ እና ለነፃነት ነው፡፡ ከታሠርሁም ሕሊናዬ አይታሰርም ከገደሉኝም ትግሌን አደራ በተለይ የኔ ትውልድ አደራ! አገራችን የወያኔ ዘረኞች ብቻ መፈንጫ መሆን የለባትም! ትግላችን የነፃነት ጉዟችን ጎርባጣ መድረሻችን ነፃነት ታሪካችን ዘላለማዊ ነው! (ከሳሙኤል አወቀ ዓለም –
የሰማያዊ ፓርቲ የደብረ ማርቆስ የሕዝብ ተወካዮች እጩ ተወዳዳሪ