(ህብር ሬዲዮ-ላስ ቬጋስ) የመኢአድ ሕጋዊው ፐ/ት አቶ ማሙሸት አማረ በአራዳ ምድብ በዝግ በታ ችሎት ፍርድ ቤቱ በአምስት ሺህ ብር ዋስ እንዲፈቱ ቢወስንም የዋስትናው ተከፍሎ ካለቀ በሁዋላ ፖሊስ በፍርድ ቤቱ ውሳኔ መሰረት እንዳልፈታቸው ከአዲሲ አበባ የፍርድ ቤቱን ውሎ ተከታትለው መረጃውን የላኩልን አረጋግጠዋል። አቶ ማሙሸት በፍርድ ቤት ትዕዛዝ ሳይፈቱ ሲቀር ለሁለተኛ ጊዜ ነው።
የፓርቲው የቀድሞ ም/የሕዝብ ግንኙነት ሀላፊ አቶ ለገሰ ወ/ሃና ዛሬ ሰኔ 10 ቀን 2007 በጊዜ ቀጠሮ ሚመላለሱበት አራዳ ምድብ ችሎት ጉዳያቸውን በዝግ ተመልክቶ አቶ ማሙሸት አማረ በአምስት ሺህ ብር ዋስ ወጥተው በቀጣዩ ቀጠሮ ሐምሌ 2 ቀን 2007 እንዲቀርቡ የወሰነ ቢሆንም ፖሊስ ለሁለተኛ ጊዜ የፍርድ ቤቱን ውሳኔ ወደ ጎን ትቶ አሁንም በእስር ላይ የሚገኙ መሆኑን ለማወቅ ተችሏል።
ግንቦት 5 ቀን 2007 ከቤታቸው አቅራቢያ ቦሌ ሚካኤል አካባቢ በተለምዶ ቴዲ ባር አጠገብ በደህንነቶች ታፍነው የታሰሩት የመኢአድ ሕጋዊው ፕ/ት አቶ ማሙሸት አማረ ሲኤም ሲ በሚገኘው ቦሌ ምድብ የመጀመሪያ ፍርድ ቤት ግንቦት 25 ቀን 2007 ክሱ ተቋርጦ ከእስር እንዲፈታ ሲሉ ጉዳዩን ሲያዩ የቆዩት ዳኛ ብርቱካን ገላው እንዲለቀቅ ትዕዛዝ ቢሰጡም ውሳኔው ተግባራዊ ሳይሆን ከዚያው ፍርድ ቤት ከቦሌ ፖሊስ ወደ አዲስ አበባ ፖሊስ እስር ቤት በተለምዶ ሶስተኛ ፖሊስ ጣቢያ በሚባለው ማዕከላው አጠገብ ወደሚገኘው እስር ቤት ተዛውረው በአዲስ ክስ የጊዜ ቀጠሮ እንደ አዲስ ተጠይቆባቸው ነበር።
አቶ ማሙሸት በቦሌ ምድብ በሚቀርቡበት ወቅት በአገዛዙ የቀረበባቸው ክስ ሚያዚአ 14 ቀን አይሲስ በኢትዮጵያውያን ላይ ያደረሰውን የግፍ ግድያ ለማውገዝ በመስቀል አደባባይ በተጠራው ሰልፍ ላይ በመገኘት ሁከት አስነስተዋል የሚል ክስ ቀርቦባቸው አገዛዙ ለክሱ የሀሰት ምስክር አቅርቦ ያስመሰከረ ሲሁን አቶ ማሙሸት ባቀረቡት የመከላከያ የሰውና የሰነድ ማስረጃ በተባለው ቀን እሳቸውን ከመኢአድ ፕሬዝዳንትነት በሕገወጥ ውሳኔ ያባረረውንና በፌዴራል ፖሊስ የመኢአድን ጽ/ቤት የተቆጣጠረውን ምርጫ ቦርድ ከሰው በፌዴራል የመጀመሪአ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ ችሎት መገኘታቸውን ፍርድ ቤቱ በጽሁፍ ሲያረጋግጥ በዕለቱ በፍርድ ቤቱ የነበሩ የትግል አጋሮቻቸውን በምስክርነት አቅርበዋል።
የግራ ቀኙን ምስክርነት የሰማው ፍርድ ቤት ግንቦት 25 ቀን 2007 ክሱ ተቃርጦ አቶ ማሙሸትን የያዛቸው ፖሊስ እንዲፈታ ትዕዛዝ ቢሰጥም ስርኣቱ ራሱ ለሚያቀርበው የፈጠራ ክስ ፍርድ ቤት የሚፈልገውን እስካልወሰነ ድረስ እንደማያከብር በማረጋገጥ ከእስር ቤት ወደ እስር ቤት የተዛወሩ ሲሆን በአራዳ ምድብ በቀረበባቸው የጊዜ ቀጠሮ መጠየቂያ ላይ የቀረበባቸው ውንጀላ በአይሲስ የተገደሉ ወጣቶች ቤተሰብ ቤት ወደሆነው ጨርቆስ ሔደው ለቅሶ በመድረስ ወጣቶችን አሳምጸዋል፣ በሕገ ወጥ መንገድ ኤርትራ ሄደው ከግንቦት 7 ጋር በትጥቅ ትግል እንዲታገሉ ወጣቶችን በመመልመልና ገንዘብ በመስጠት ወንጀል እንደሚፈለጉ ከቀረቡባቸው የፈጠራ ክሱት ተጠቃሽ ነበሩ። የቦሌው ፍርድ ቤት ውሳኔ ሳይከበር በእስር ላይ እንዳሉ በጊዜ ቀጠሮ ጉዳያቸውን ሲያይ የቆየው የአራዳ ፍርድ ቤት ዛሬ ሰኔ 10 ቀን 2007 ዓ.ም በሰጠው ውሳኔ አቶ ማሙሸት አማረ በአምስት ሺህ ብር ዋስ እዲወጡ በመወሰኑ የዋስትናው ክፍአ ተከፍሎ ሌሎች በዋስ ይውጡ የተባሉት ሲወጡ እሳቸው በተለመደ የፖለቲካ ውሳኔ በእስር ላይ ይገናሉ።
ከዚህ ቀደም የአገዛዙ የቀድሞ ባለስልጣን አቶ ስዬ አብርሃን ዛሬ አቶ ማሙሸትን ይፈቱ ባለው አራዳ ፍርድ ቤት ዳኛ ብርቱካን ሚደቅሳ ፖሊስ በጊዜ ቀጠሮ በተሰጠው ቀን ምርመራውን ባለመጨረሱ እና በሰባት ሺህ ብር ዋስ ይፈቱ የተባለውን ትዕዛዝ ባለማክበሩ ከችሎት ላይ እንዲፈቱ ብትወስንም አቶ ስዬን ፖሊስ ላለመፍታት የፍርድ ቤቱን በር እስከመግዛት ሄዶ ከሰዓታት ቆይታ በሁዋላ አቶ ስዬ ተፈቱ ተብሎ ከፍርድ ቤቱ እንደወጡ ተመልሰው የታሰሩ ሲሆን ዛሬ ከአስራ ሰባት ዓመት በሁዋላም አገዛዙ የፍርድ ቤት ውሳኔን ለሰዓታት እንኳን ለማክበር አለመቻሉን ያሳያል።
በአሁኑ ወቅት መቶ በመቶ ምርጫውን አሸነፍኩ ያለው አገዛዝ እውነተኛ ተቃዋሚዎችን እያሰደደ ሲሆን በአሁኑ ወቅት በርካታ የመኢአድ አባላትም በልዩ ልዩ እስር ቤቶች ይገኛሉ። በእስር ላይ የሚገኙት የመኢአድ አባላትን ዝርዝር አቶ ለገሰ ወ/ሃና ልከውልናል ተከትሎ ይነበባል።
በመላ ሀገሪቱ ባሉ እስር ቤቶች ታስረው የሚገኙ የመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት (መኢአድ) አባላት ዝርዝር
አላማጣ ውህኒ ቤት የታሰሩ
1, ኢያሱ ሁሴን አላማጣ ውህኒ ቤት የሚገኝ
2, በላይ ዳኛው 4 ቦታ ተፈንክቶ ፍርድ ቤት ያልቀረበ አላማጣ ፓሊስ ጣቢያ የሚገኝ
3, ሞላ መለሰ አላማጣ ውህኒ ቤት የሚገኝ
4, ጥጋቡ ሙላት አላማጣ ውህኒ ቤት የሚገን
በጎንደር ክ/ የታሰሩ
5, ዘመነ ምህረት ሰሜን ጎንደር አ ᎐ አ᎐ ማዕከላዊይ
6, መ/ር ጥጋቡ ሀብቴ ሰሜን ጎንደር
7, ጥላሁን አድማሴ ሰሜን ጎንደር
8, ስለሽ ጥጋቤ ሰሜን ጎንደር
9, ጌትነት ደሴ ጎንደር
10, መለሰ መንገሻ ሰሜን ጎንደር ማዕከላዊይ
ጎጃም ክ/ሀገር
11, ተስፋየ ታሪኩ ማዕከላዊይ
12, መቶ አለቃ ጌታቸው መኮንን
13, ኢ/ር መለሰ ያባቱን ስም ያልታወቀ ሌሎች ስማቸው ያልታወቁ
14 ሰዎች ማዕከላውይ ያሉ
ሰሜን ሸዋ
14, ዓስራት እሸቴ
- አቶ ጥላሁን አድማሴ ጎንደር
- አቶ ጥላሁን አበበ/ደ.ጎንደር
- አቶ አንጋው ተገኘ/ምዕ.ጎጃም
18, አቶ አባይ ዘውዱ/ምዕ.ጎጃም
- አቶ እንግዳው ዋኘው/ ምዕ.ጎጃም
20 አቶ አባይነህሲሳይ/ምዕ.ጎጃም
- አቶ አለባቸው ማሞ/ምዕ.ጎጃም
- ወጣት ታጀበ አለኸኝ/ ምዕ.ጎጃም
- አቶ ዮሐንስ ገደቡ/ምዕ.ጎጃም
24 አቶ አዝመራው ከፋለ/ምዕ.ጎጃም
25 ወጣት ተሥፋዬ አሥማረ/ንዕ.ጎጃም
- አቶ ችሎት ጎበዜ/ምዕ.ጎጃም
የመኢአድ አመራር በምጫ ቦርድ ውሳኔ መሠረት ከፅ/ቤት ከተባረርን በኋላ በተፈጠረ ክፍተትና ህጋዊው አመራር ምንም ዶክመንት ይዘው ስላልወጡ በዚህ ላይ ያልተካተቱ ሰዎች እንዳሉ አያይዘው ገልጸዋል። ተለጣፊው አመራር መኢአድን በምርጫ ቦርድ ውሳኔ ሲረከብ በቢሮ ስልክ ተደውለው ይደርስ የነበረው መረጃ በመቋረጡ የአባላቱን ዝርዝር በትክክል ማወቅ አልተቻለም ሲሉ ገልጸዋል።
Hiber radio Las Vegas ይህ ህብር ሬድዮ _የወቅታዊ መረጃ ምንጭ ነው። ህብር ሬድዮ ዘወትር ዕሁድ በአካባቢው ሰዓት አቆጣጠር ከምሽቱ 6፤30 ሰዓት እስከ 8 ሰዓት በቀጥታ በህብር ሬዲዮ ድህረ ገጽና በስልክ ለማዳመጥ 712 -432-8451 መደወል ብቻ በቂ ነው።