አንዷለም አራጌ ከመንገድ ልጁን ከት/ቤት ሊአመታ ሲል የታፈነ፣ያለወንጀሉ ወንጀል ተለትፎበት በእስር ቤት ሲማቅቅ እነሆ አራት ዓመት ሊሞላው ሁለት ወር ብቻ ይቀረዋል። አንዷለም አራጌ ሲታሰር ይሄ የመጀመሪአው አይደለም። ከዚህ ቀደም ከቅንጅት መሪዎች አንዱ በመሆኑ ምርቻ 97 ማግስት ታፍሰው ከታሰሩት የዚያ ዘመኑ ቅንጅት አመራሮች አንዱ በመሆን በእስር ፍዳውን አይቷል። አንዷል ያልተሄደበት መንገድ በሚል ከዚህ ቀደም ከቃሊቲ እስር ቤት መጽሐፍ አስነብቦ ነበር። ትላትን ገበያ ላይ የዋለው አዲሱ ሁለተኛው‹‹የሀገር ፍቅር ዕዳ – ከቀሳ፣ ጎንደር እስከ ቃሊቲ እስርቤት›› መጽሀፉን ለንባብ አብቅቷል። ይህን መጅሃፍ ለመጃፍ እንዴት ባለ አስቸጋሪ የክፉ እስር ውስጥ ሆኖ እንደጻፈው በመግቢያው በመጠኑ ገልጾታል። በአዲስ አበባ መጽሐፉ ከአንባቢያን እጅ የደረሰ ሲሆን በቅርቡ በውጭ አገር ይሰራቻል ተብሎ ይጠበቃል።
የወጣቱ የሰላማዊ ትግል አርበኛ አንዷለም አራጌ በአስቸጋሪ የእስር ቤት ሁኔታ ሆኖ እየከፈለ ያለውን መስዋእትነት ፣የሚደርስበትን ጫና ተቋቁሞ የጻፈው ይሄ መጽሐፍ ጽናቱን ለአገሩና ለወገኑ ያለውን ታላቅ ራዕይ በአፈና ውስጥ እንኳ አልበገር ባይነቱን የሚያሳኢ ነው።
መፅሐፉ 400 ገፅ ያለው ሲሆን በ32 ምዕራፎች የተከፋፈለ ነው፡፡ ዋጋውም 100 ብር እንደሆ ገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡ አንዷለም በግፍ የታሰረለት ፓርቲ አንድነት ለተላላኪዎች ተላልፎ ከተሰጠ በኋላም ያለምንም የሞራል መንገራገጭ መፅሀፍ ማበርከቱ ታላቅነቱን በድጋሚ ያስመሰከረ ምርጥ ሰው ነው ሲሉ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡
አንዷለም ከመፅሐፉ መግቢያ ላይ ካሰፈረው ተቀንጭቦ የተወሰደውን ቀጥሎ እናቀርባለን፡-
ለምን ይህንን ፃፍኩ?
ዶ/ር ማርቲን ሉተር ኪንግ በአንድ ወቅት የሚከተለውን ብለው ነበር፡- ‹‹አንድ አቋም ለመያዝ በምንነሳበት ጊዜ፣ ‹ፍርሃት› ይህ አቋም ምን አይነት አደጋ ያስከትልብኝ ይሆን? የሚል ጥያቄን ይመዛል፤ ‹አዋጭነት› በሌላ ወገን ይህን አቋም መያዝ ምን ያህል ብልጠት የተሞላ ነው? ሲል ይጠይቃል፤ ‹ከንቱነት› በበኩሉ ይህን አቋም መያዝ ምን ያህል ዝነኛ ያደርገኛል? ይላል፤ ህሊና ግን ከሁሉም የተለየ ጥያቄን ያነሳል፤ ይህ አቋም ምን ያህል ትክክለኛ አቋም ነው ሲል ይጠይቃል›› እንዲህ ዓይነት ምናባዊ ምልልሶች በተለያዩ መስኮች ተሰማርተው ለውጥ ለማምጣት በሚተጉ ግለሰቦች አይምሮ ውስጥ ተደጋግመው የሚሰሙ ድምፆች ይመስሉኛል፡፡ በተለይም ኢትዮጵያን በሚመስል የአምባገነንነት መናኸሪያ ሀገር በሰላማዊ ትግል የአገዛዝ ስርዓትን ወደ ዴሞክራሲ ለመለወጥ የሚታገሉ ዜጎች እለት እለት በህይወታቸው የሚያጋጥሟቸው ጥያቄዎች መሆናቸውን በጥሞና እገነዘባለሁ፡፡
የእነዚህና ሌሎች ጥያቄዎች ድምጽ ከመታሰሬ በፊትም ሆነ በኋላ እየተመላለሱ እረፍት ይነሱኛል፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ በሰላማዊ ትግል ለመታገል የሚነሳ ዜጋ ሀገር መውደዱ በቀይ መስመሮች መዥጎርጎሩን ለማስተዋል የሚያስፈልገው የቆመበትን መሬት ብቻ ጎንበስ ብሎ ማየት ነው፡፡ በኢትዮጵያችን የሰላማዊ ትግል ቀጠና የፈንጅ ወረዳ ነው፡፡ አገዛዙ ‹‹ህጋዊ፣ ዴሞክራሲያዊና ሰላማዊ›› የሚል ባነር የሰቀለበት ነገርግን በየእርምጃዎ ርቀት ፈንጅ የሰገሰገበት የፖሊቲካ መልክዓ ምድር ነው፡፡ በዚህ ቀጠና ውስጥ በተለይ ጎላ ያለ እንቅስቃሴ ሲደረግ ዶ/ር ኪንግ ያነሷቸው ጥያቄዎች መልስ ፍጥነት ይጨምራል፡፡
አቋምዎ ከእውነት ጋር በጽናት መቆም ከሆነ ቀጥለው የሚያስቡት፣ በህይወት ከቆዩ በሚያልፉበት የመከራ ሸለቆ ውስጥ ጉልበት የሚሰጥዎትንና ከግራ መጋባር የሚታደግዎትን ሀሳቦች ቀድመው ይዘጋጁባቸዋል፡፡ እኔም በትንሹ ከመታሰሬ ሁለት ዓመት በፊት ጀምሮ ከአገዛዙ ባህሪ አንፃር አሁን እያለፍኩበት ያለው ሁኔታ እንደሚፈጠር ለአፍታ ተጠራጥሬ አላውቅም፡፡ በተያዝኩባት ቅጽበት እንኳን ከጓደኛዬ በላይ ፈቃዱ ጋር እናወራ የነበረው ይኽንኑ ነው፡፡ ልክ በዚህ ጉዳይ ላይ እያወራን የመኪናው መስኮት ተንኳኳና ወደ ውጭ እንድወጣ ጠየቁኝ፡፡ የድንጋጤም ሆነ መገረም ስሜት አልመጣብኝም፡፡ የቀረኝ በማልፍበት የመከራ ሸለቆ ውስጥ ስለማነባቸው መፃህፍት፣ ስለምሰራው ስፖርትና ስለምፀልየው ፀሎት እያሰብኩ ወደ ግዞት ዓለም መነዳት ነበር፡፡
‹‹ምርጫ 97ን›› ተከትሎ ወህኒ ከወረደው የቅንጅት አመራር አንዱ ነበርኩ፡፡ ያን ጊዜ ወደ ወህኒ ስወርድ ትልቁ ህመም የሚሰማኝ ከእጮኛዬ በመለየቴ ነበር፡፡ አሁን ወደ ወህኒ ስወርድ የባለቤቴ ሃዘንና ግራና ቀኛቸውን የማይለዩት ልጆቼ ሁኔታም አብሮኝ ወህኒ ወረደ፡፡ የአምባገነንነት ኢሰብዓዊት ወደር የለውም፤ እነርሱም ኢትዮጵያን በተቀላቀሉ በጣም ጥቂት ጊዜ ውስጥ የአገዛዙ ሰለባ ሆኑ፡፡ በአባታቸው ማደግ የሚችሉ አባታቸው ከአገዛዙ የተለየ አቋም ካልያዘ ብቻ ነው፡፡ ነገር ግን ከአገዛዙ የተለየ አቋም መያዝ አደጋው ከፍ ያለ ቢሆንም ነገር ግን ትክክል ነበር፤ ትክክልም ነው፡፡ ይኽን አቋም ስይዝ በተስፋቢስነት ሳይሆን በተስፋ ሙላት ነው፡፡ እኔና ጓደኞቼ ልጆቻችንና ሚስቶቻችን እንዲሁም ሌሎች ዜጎች የሚከፍሉት መስዋዕትነት በከንቱ እንደማይቀር በፅኑ አምናለሁ፡፡ ምንም ያህል የተዋረድን፣ የተናቅንና የተረገጥን ብንሆንም ዓላማችን እውነት፣ ፍቅርና የሁሉም ዜጎች ልዕልና መከበር በመሆኑ አንዳች ምድራዊ ኃይል እውን ከመሆን ሊያስቆመው አይችልም፡፡ ያ ቀን እስኪነጋ ድረስ ግን የሚከፈለውን ዋጋ በፀጋ ከመክፈል ውጭ ሌላ አማራጭ የለም፡፡
ከማዕከላዊ የሁለት ወራት ቆይታ በኋላ ወደ ቃሊቲ እስር ቤት ስገባ አንድም ቀድሞ የማውቀው ፖሊስም ሆነ የፖሊስ ኃላፊ አላጋጠመኝም፤ እግሬ የእስር ቤቱን ቅጥር እንደረገጠ ግን ከሌሎች እስረኞች ነጥለው ወደ ተለየ አቅጣጫ ወሰዱኝ፡፡ ቅጣት ቤት ነው፡፡ ገና ከማዕከላዊ መድረሴ ነው፡፡ ግን ወደ ቅጣት ቤት ተነዳሁ፤ (ስለዚች ቅጣት ቤት የአቶ መለስ ስንብት በምትለው ንዑስ ርዕስ ስር በጥቂቱ ዘርዘር አድርጌ ለአንባቢ ለማስረዳት ሞክሬአለሁ)፡፡ በዚች የጭንቅ ማማ ውስጥ ሆኜ ማንበብ፣ ስፖርት መስራት፣ መፀለይና መፃፍ በየዕለቱ አቅም በፈቀደ የምሞክራቸው ተግባሮቼ ናቸው፡፡ በጥፍሬ ቆሜም ቢሆን ‹‹ያልተሄደበት መንገድ›› የተሰኘችዋን መጽሐፌን ለማበርከት ሞክሬአለሁ፡፡ ግቢዋ ውስጥ የነበሩት እነ አቶ በቀለ ገርባ፣ አቶ ኦልባና ሌሊሳ፣ አቶ ቶሎሳ በቾና ኮማንደር ፈቃደ ረጋሳ ከቅጣት ቤቷ ወደ ተለያዩ ቦታዎች ተወሰዱ፡፡ እኔ እና አንድ ሌላ እስረኛ ስንቀር ቅጣት ቤቷ በአዲስ 16 እስረኞች ተጥለቀለቀች፡፡ በተለያየ ወንጀል የተከሰሱና የተለያየ የዕድሜ ደረጃ ላይ ያሉ በአመዛኙ ከ18-30 ዓመት የዕድሜ ክልል የሚገኙ ወጣቶች ናቸው፡፡
በግቢዋ ውስጥ ያሉት ሶስት ትንንሽ ክፍሎች ሃያ አራት ሰዓት በእስረኛ የተሞሉ ናቸው፡፡ ከቤት ወደ ውጭ ሲወጣም ግቢዋ ስፖርት በሚሰሩ እስረኞች ትጨናነቃለች፡፡ ምኗም ለምንም አይመችም፡፡ ፈንጠር ብሎ ቆሞ ለማሰብ እንኳን አትመችም፡፡ ቀኑ ቀጥ ብሎ ይቆማል፡፡ ያልተሄደበት መንገድ ለአንባቢ መድረሷን ሰምቼ ደስ ቢለኝም ቆሞ የሚውለውን የጊዜ ተራራ ለመውጣት ግን አንድ ነገር ማድረግ አለብኝ አልኩ፡፡ የታሰርኩት ባነገብኩት ዓላማ ምክንያት ነው፡፡ የትም ቦታ በምንም ዓይነት ሁኔታም ሆኜ ለዓላማዬ መትጋት አለብኝ፡፡ ያልተፈጸመ ህልም ይዞ መተኛት ቢቻልስ እንዴት ይተኛል? ባልተሄደበት መንገድ አጎላድፌም ቢሆን አንድ የሚረባ መልዕክት እንኳን ለአንባቢ አድርሼ ከሆነ ትልቅ ነገር ነው፡፡ አሁንስ ሌላ አንድ ነገር ማለት ብችልስ? የሚል ጥያቄ ተመላለሰብኝ፡፡ ቀኑና ሃሳቤ አንድ ላይ ተዳምረው አዕምሮዬ ውስጥ ሌላ ተራራ ፈጠሩ፡፡ ቁጭ ብዬ የሀሳብ ውጥረትና የጊዜ መቆም እንዲገሉኝ ልፍቀድላቸው ወይንስ ጊዜንም ሃሳቤንም ምንም ያህል አስቸጋሪ ቢሆን በስራ ህይወት ልዝራባቸው? ጊዜም እንዲገድለኝ እኔም ጊዜን ልገድለው አያስፈልግም፤ እንደምንም ልጠቀምበት ወሰንኩ፡፡ ሌላ ዙር መጽሐፍ? ምኑን ከምን አድርጌ በምን ላይ እጽፋለሁ? ሌላ ጭንቅ፤ ለማን አማክረዋለሁ?
ካለሁበት ቅጣት ቤት ውስጥ ከባለቤቴና ከጥቂት የቤተሰብ አባላት ውጭ አብረውኝ ካሉ እስረኞች በተለየ እንዳልጠየቅ ተከልክያለሁ፡፡ ምክንያቱ ተቃዋሚነቴ ነው፡፡ ቅጣት ቤቷ ውስጥ የለመድኳቸው እስረኞች ቢሄዱም ከጥቂቶቹ ጋር መቀራረብ ጀመርኩ፡፡ ከመካከላቸው ፖለቲከኛ እኔ ብቻ ነኝ፡፡ አንዳንዶቹ በሚያስጨንቅ ሁኔታም ሆነው ስለ እኔ ይጨነቃሉ፤ ይበሳጫሉ፡፡ የመጠየቅ መብቴ በመገፈፉ ያዝናሉ፤ በአዲስ አበባ አውራ ጎዳናዎችና የሚቸበቸቡ መፃህፍት እንዳይገቡልኝ ስከለከል ድግሞ ስሜታቸው ይገነፍልና ለምን አንድ ነገር አናደርግም ይላሉ፡፡
በእኔ በኩል ቀደም ሲል በቅንጅት ታስሬ በነበርኩበት ወቅት ከፖሊሶችና ከኃላፊዎች ጋር የነበረኝን ኃይል የተሞላበት ግንኙነት ትክክል አልነበረም የሚል መደምደሚያ ላይ ደርሻለሁ፤ በመሆኑም ፖሊሶቹንም ሆነ ልጆቹን በትዕግስት የመገሰጽ ኃላፊነት በራሴ ላይ ጭኛለሁ፡፡ በፖሊሶችና በእስረኞች መካከል የተካረሩ ግጭቶች ሲፈጠሩ ሁሉንም እቆጣለሁ፡፡ በተለይ ልጆቹን በየተራ እመክራሉ፡፡ ችግሩ ሲፀና የበላይ ኃላፊዎች ሁሉ ከተጨማሪ የፖሊስ ኃይል ጋር ይደርሳሉ፡፡ ከዚያም ‹‹አንተነህ አይደል እያደራጀህ ይኽን የምትሰራው?›› ይላሉ፡፡ ሁልጊዜም ለሚፈጠረው ችግር ተጠያቂ እኔ ነኝ፡፡ ነገም ሌላ ችግር ይፈጠራል፤ መሳሪያ ተቀባብሎ ይነጣጠርብናል፤ በዚያም መሃል ግን ሁለቱንም ለማረጋጋት እሞክራለሁ ነገርግን አሁንም እኔ ላይ ዛቻው ይቀጥላል፡፡ በመጨረሻ ላይ የእኔም ትዕግስት ያልቃል፤ ‹‹ልታስፈራሩኝ ከምትሞክሩ የምታስቡትን ብትፈጽሙ ይቀለኛል!›› እላለሁ፡፡ በኃይል በር በላያችን ላይ ተቆልፎ ስሜታችን እንደደፈረሰ በጉዳዩ ላይ እንወያያለን፡፡ መዳፍ በምታክለው ግቢ ውስጥ በየተራ ልጆቹን አናግራለሁ፡፡ አንዳንዶቹን አመሰግናለሁ፤ አንዳንዶቹን እገስጽና በዚህ ሁኔታም ስለምን ብጽፍ ይሻላል? የሚል ጥያቄ እራሴን እጠይቃለሁ፡፡………….
በዚህ ዘመንና ትውልድ ፊት ብቻ ሳይሆን ባልተወለዱ ልጆቻቸውና በሚመጣው ዘመን ሚዛን ተመዝኖ የማይወድቅ አቋም እንደያዝኩ የጸና እምነት አለኝ፡፡ የኢህአዴግን አረመኔነት ለመረዳት የሚያስችል መከራ በህይወቴ ያልደረሰ የሚመስለው አንባቢ ሲኖር ይገርማል፡፡ ስቃዩን እኔ ብቻ ሳልሆን ልጆቼም ያውቁታል፡፡ በእያንዳንዷ ቀን ሰዓትና ደቂቃ የማልፍበት የእስር ህይወት የአገዛዙን ባህሪ ከመረዳትም በላይ ብዙ የሚናገረው ነገር አለ፡፡ እኔ የአገዛዙ አፈና ገፈት ቀማሽ የሆንኩት ሰው ቀርቶ የዓለም አቀፍ ማህበረሰቡ እንኳን በሚገባ ኢህአዴግን እንደሚረዳው እንድጠራጠር የሚያደርግ ምክንያት አይታየኝም፡፡ በሌላ በኩል ግን እራሳችን አምላካዊ ሌሎችን ደግሞ ሰይጣናዊ አድርጎ መውሰዱ ተገቢ ሆኖ አላገኘውም፡፡ መጽሐፉ ውስጥ እንደምናየው ይህ ባህሪ የአብዮታዊ ዴሞክራሲ ሁነኛ ባህሪ ነው፡፡ እንዲህ ዓይነት አቋም የያዙ ሰዎች ሁሉ ግን አብዮታዊ ዴሞክራሲ የተጠመቁ ናቸው ማለት አይደለም፡፡
ኢህአዴግንም ሆነ ሁላችንንም ያበቀለው የፖለቲካ ባህላችን ነው፡፡ በመጽሐፉ ውስጥ ከኋላ ጀምረን ለማየት ስንሞክር የአገዛዝ ባህላችን አሁንም ለምንገኝበት ዙሪያ መለስ መከራ ትልቅ ድርሻ እንዳለው እንረዳለን፡፡ የኢህአዴግን አይነት አምባገነን አዝሎ የሚንከራተት ነገር ግን ኢህአዴግን ከጫንቃው ለማውረድ እጅ ለእጅ መያያዝን የሞት ያህል የሚፈራ፤ ይልቅስ እርስ በእርሱ መነካከስና መጠላለፍን እንደ ትልቅ ስኬት የሚቆጥር ስንት ዜጋ እንዳለ ማን ማንን ሊያስረዳ ይችላል? ይኽስ ከኋላ ቀሩ የፖለቲካ ባህላችን የሚቀዳ መሆኑን ለመረዳት የሚቸገር ሊኖር ይችል ይሆን? አይመስለኝም፡፡ ሁልጊዜም በጣም ከባዱ ነገር ወደ ውስጥ ማየት እንጂ አሻግሮ ማየት አይደለም፡፡ ስለ ኢህአዴግ ምንነት ከሁለት አስርት ዓመታት በላይ አውርተናል፡፡ ነገር ግን ለምንድን ነው እስከአሁን ድረስ እላያችን ላይ እንደሰለጠነብን የቀጠለው? ከእኛ የጎደለውን ነገርም በድፍረት ማየት ተገቢ ነው፡፡
ኢህአዴግ ብሔራዊ እርቅን ተቀብሎ ሁላችንም ወደ አላስፈላጊ አዘቅት ተያይዘን እንዳንወርድ ቢሰራ የተሻለ መንገድ መሆኑን አምናለሁ፡፡ ይህን ማድረግ ካልፈለገ ግን ለህዝብ ፈቃድ መገዛት ግዴታው የሚሆንበት ሰዓት መድረሱ ሳይታለም የተፈታ ነው፡፡ ጊዜው እንደምናካሂደው ትግል ሊረዝምም ሊያጥርም ይችላል፡፡ በትጥቅ ትግል የሚያምኑ ሰዎች ስኬት የራቃቸው በሰላማዊ ትግል ምክንያት አድርገው ካሰቡ ስህተት ነው፡፡ በሰላማዊ ትግል የምናምን ሰዎችም በትጥቅ ትግል ምክንያት ሊሳካልን እንዳልቻልን ካሰብን ስህተት ነው፡፡
ለእኔ ከወሬ ባለፈ ሁለቱም ትግሎች ትርጉም ባለው መልኩ እየተካሄዱ ናቸው ብዬ አላምንም፡፡ ስለዚህ ሰላማዊ ትግልን እንዳልባሌ ነገር የሚፈርጁ ወገኖች መተቸት መብታቸው ቢሆንም ወደ ውስጣቸው ቢመለከቱ የተሻለ የሚያስከብር ተግባር ይመስለኛል፡፡
በግሌ አሁንም ግልጽ ለማድረግ የምወደው ነገር በሰላማዊ ትግል የሃይማት ያህል እንደማምን ነው፡፡ የኢትዮጵያን የመጠፋፋት የፖለቲካ ባህል ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ መለወጥ የሚቻለው የጸና ሰላማዊ ትግል በማድረግ ነው፡፡ ሰላማዊ ትግልን በሚገባ ጥቅም ላይ ማዋል ስንችል ያጎበጠንን የአገዛዝ ቀንበት ከላያችን ላይ ማስወገድ ብቻ ሳይሆን የአገዛዝ ስርዓቶች መፍለቂያ የሆነውን የፖለቲካ ባህላችንን ማዘመን እንችላለን፡፡
በአጭሩ ኢህአዴግ የአብዮታዊ ዴሞክራሲን በቁጥጥር የተለከፈና ሁሉንም ተቃዋሚዎች አጥፍቶና ህዝቡን እረግጦ የመግዛት አባዜ የተጠናወተው ከመሆኑም በላይ የኢትዮጵያ የመጠፋፋት ባህልም ወራሽ ነው፡፡ …………………
እንደ ልብ እንዳላነብ መጽሀፍት እንዳይገቡልኝ ይከለከላል፡፡ በማመልከቻ ጽፌ እንዲሁም በአካል ስንገናኝ ‹‹የሮዴዥያ ነጮች ሮበርት ሙጋቤን በአሰሩበት ወቅት እንኳን ትምህትርት አልከለከሏቸውም፤ ከሶስት ያላነሱ ዲግሪዎችን ሰርተው ነው የወጡት፤ እናም እኔም ባልጠቅማችሁ እንኳን በመማሬ አልጎዳችሁምና በተልዕኮ እንድማር ፍቀዱልኝ›› የሚል ጥያቄ ደጋግሜ ባቀርብም ፈቃደኞች አልሆኑም፡፡ የሚፈልጉት የእኔን ባክኖና መክኖ መቅረት እንደሆነ ግልጽ ነው፡፡ በእኔ በኩል ይኽንን ሁኔታ ለመቋቋም ቀደም ሲል የጠቀስኳቸውን የእስር ቤት መርሃ-ግብሮቼን አጠናክሬ መቀጠል እንደ ሰው ያለመምከን ጥረት ብቻ ሳይሆን በስር ቤት ውስጥ ህልውናዬንም የማስቀጠያ ስልት ነው፡፡ ከእስር ቤት አጥር ውጭ ካሉ ኢትዮጵያውያን ጋር ለሀገሬ ይበጃል የምለውን ነገር አንስቼ የመወያየት ሰብዓዊ መብቴን ተግባራዊ የማድረግ ህልሜ አውን ሆኖ ለማየት እፈልጋለሁ፡፡ አካሌ ቢገደብም መንፈሴ እንዲገደብ አልፈልግም፡፡ በዚህ ሁኔታ ሆኜ ነው ይኽንን መፅሐፍ መከተብ የጀመርኩት፡፡
እንደ ሁልጊዜው ሁሉም ነገር የሚከናወነው ፍራሽ ላይ ነው፤ ወንበር አይፈቀድም፤ ለማንበብ፣ ለመመገብም ሆነ ለመፃፍ ያለችኝ ቦታ ዘጠና ሲንቲ ሜትር ፍራሽ ነች፡፡ በእርሷም ላይ የማዘዝ መብት የለኝም፡፡ ድንገት ፀብ ከተነሳ የግብግብ አውድማ ትሆንና ልብሴም ሁሉም ነገሬም ይረጋገጣል፤ ግልብጥብጧ ይወጣል፡፡ ፀቡ ሲበርድ ወደ ቀድሞው ንባብ እመለሳለሁ፡፡ ቴሌቪዥኗን እስከ መጨረሻ ድምፀዋን እንድትሰጥ በማድረግ ከጭንቀታቸው ያረፉ የሚመስላቸው ልጆች ደግሞ ዳንኪራውን ያቀልጡታል፡፡ ከማንበብ ውጭ ግን ሌላ አማራጭ የለኝምና እቀጥላለሁ፡፡ በየጊዜው በሚደረገው ፍተሻ ምክንያት አንዷ ክፍል ውስጥ ያለን እስረኞች ልብስና የተለያዩ ንብረቶችን ሁሉ እየፈተሹ አንድ ላይ ይቆለላሉ፡፡ ትቢያ ይለብሳሉ፣ ይረጋገጣሉ፡፡ ከፍተሻው በኋላ ለረጅም ሰዓት ንብረቶቻችንን የመለየት ስራ እንሰራለን፡፡ በጣም አድካሚ ነው፤ ግን አማራጭ የለንም፡፡ በየፌስታላችን ንብረቶቻችንን ቆጣጥረን እንደ ቀድሞው ወደ ህይወት መመለስ ያስቸግራል፡፡ ሰው መሆናችን ጨርሶ ተዘንግቷል፡፡ ኢሰብዓዊነት እስር ቤት አውርዶኝም በዚያም ያሳድደኛል፡፡ ኢሰብዓዊነትን የማሸንፈው ግን ሰው በመሆን ነውና ሰብዓዊ ተግባሮቼን የሞት ሞቴን እቀጥላለሁ፡፡
በእንዲህ አይነት ሁኔታ እያለፍኩ አንዳንዴ ኃላፊዎች ይመጡና ‹‹ዋይ! እንዴት ነው ‹አንድ-ዓለም› ታረምክ?›› ይሉኛል፡፡ ነገሩ የሚያበሳጭና የሚያሳዝን ቢሆንም በአንክሮ ‹‹እኔ እኮ በተቀነባበረ ክስ የታሰርኩ የግፍ እስረኛ ነኝ፤ ከየትኛው ጥፋቴ ነው የምታረመው?›› እላቸዋለሁ፡፡ ‹‹ዋይ! አንተ ተው! ስንት ሰው አይዶለም እንዴ መንግስትን ተሳድቦ እቤቱ እያደረ ያለበት ሁኔታ ያለው! አንተን ነጥሎ መንግሥት ለምን ያስርሃል? በልዕ ዕስቲ ተናገራ!›› ይሉና ጥያቄዬን በጥያቄ ይመልሳሉ፡፡
በበኩሌም ‹‹ብዙሃንን ሰብስቦ ማሰር ሳይሆን ጥቂቶችን ነጥሎ በማሰር ህዝቡን ማስደንበርና ተሸማቆ እንዲኖር ማድረግ ነው – የአገዛዙ ስልት›› የሚል ምላሽ እሰጣቸዋለሁ፡፡ ‹‹ታዲያ አንተን ለምን መረጠ?›› የሚል ጥያቄ ያስከትላሉ፡፡ ‹‹ለምን እኔንና ጓደኞቼን እንደመረጠ በውል የሚያውቀው አገዛዙ ነው፡፡ ምናልባት ግን በጊዜው ፊት ለፊት ስለምንታይ የእኛን አንገት በመስበር ሌሎችን ‹እነርሱን የበላ እሳት እንዳይበላችሁ፤ እኔ እንደማዛችሁ ብቻ ተመላለሱ› ለማለት ነው፡፡›› የሚለው ምላሼ አያስደስታቸውም፡፡ ‹‹ዋዕይ! ላንተ ገና አልታረምክም!›› ይላሉ ‹‹ይልቅስ መታረም ያለበት የምታስተዳድሩት ተቋም ነው፤ የሁላችንም ተቋም ነው፤ ነገ የተሻለ ተቋም ሆኖ እንዲወጣ ከተፈለገ አሰራራችሁን አስተካክሉ፡፡ ሰውን እንደ ችቦ አንድ ላይ አስሮ በማንደድ ማጥፋት አይቻልም፡፡ የተለያዩ ስራዎችን በዝርዝር ነድፋችሁ ተግባራዊ ብታድጉ ይሻላችኋል›› የሚል ሃሳብ እሰነዝራለሁ፡፡………………
ከቤቴ ከወጣሁ ጀምሮ ለሁለት ዓመት ከስድስት ወር ያለአንዳች ምክንያት ቅጣት ቤት ውስጥ መሬት ላይ እንደትል ስንከባለል ከቆየሁ በኋላ ድንገት ‹‹ፍራሽህን ይዘህ ውጣ!›› ተባልኩ፡፡ ድንገት ወጥቼ ‹‹ኋይት ሀውስ›› ወይንም ‹‹ዋይታ›› ወደምትባል ጠባብ ቦታ ተወሰድኩ፡፡ ወረቀቶቼ በር ላይ እየተመነጠሩ ሲለቀሙ እስክንድርም መጣ፡፡ ከረጅም ጊዜ በኋላ ተገናኘኝ፡፡ በእለቱም ከ50 ገጽ በላይ ወደ መጨረሻ ረቂቅ ለመጻፍ የተዘጋጁ ወረቀቶቼ ተወሰዱብኝ፡፡ እንደገና ማንበብ፣ እንደገና መፃፍ ቀጠልኩ፡፡ የልጆቼ ናፍቆት፣ የሰላማዊ ትግሉ መቀዛቀዝ፣ ወረቀቶቼን የመነጠቅ ስጋትና በዚህ ሁኔታም ሆኜ የጀመርኩት ገደል የመውጣት ትግል በስኬት እንዲጠናቀቅ መትጋት የአዕምሮዬን ጓዳ ከሞሉ ሀሳቦች ውስጥ ጥቂቶቹ ናቸው፡፡ የፈጣሪ ፀጋ በዝቶልኝ ከብዙ አድካሚ ውጣ ውረድ በኋላ የሀገር ፍቅር ዕዳን በስኬት ለማጠናቀቅ ችያለሁ፡፡ ትንሽ ቅር ያለኝ ምዕራፍ አምስትን ሳዘጋጅ ጽሁፉ ከወጣ በኋላ የምዕራፉ 167 የግርጌ ማስታወሻ በፍተሻ ወቅት ስለተወሰደብኝ ሁኔታውን መለወጥ የምችልበትን ሁኔታ መፍጠር አልቻልኩም፡፡ ከዚህ ውጭ ያልተሄደበት መንገድ ላይ የተፈጠሩ ችግሮችን በዚህኛው መጽሐፍ ላለመድገም ጥሬአለሁ፡፡ …………….
ትግሉ የዴሞክራሲና የነፃነት ትግል በመሆኑ የዜጎች ልዕልና የሚከበርበት፣ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት በኢትዮጵያ እስኪገነባ ድረስ ትግሉ ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት ያሳስባል፡፡ ለዘመናት ያልነጋው ረጅሙ የአገዛዝ ሌሊት ሊነጋ የሚችለው የዴሞክራሲ ትግል ውጤት የሆነችው የዴሞክራሲ ጮራ በምድራችን ላይ ስትቀትር ነው፡፡
የዴሞክራሲ ትግሉ በተለይም በዚህ ሰዓት የተለየ ትርጉም ይሰጣል፡፡ አምስት፣ አምስት ዓመታትን እየቆጠረ አገዛዙ የሚተውነው አምስተኛው የምርጫ ተውኔት ተቃርቧል፡፡ የእኔ ፓርቲ አንድነት እንኳን የአገዛዙን አፈና ተቋቁሞ እልህ አስጨራሽ ትግል ውስጥ በመግባት ህዝብን ነፃ ለመውጣት የሞት ሽረት ትግል ለማድረግ ሲታትር በስርዓቱ መንጋጋ ውስጥ ወድቋል፡፡ በተቃዋሚው ታግለን ለውጥ ማምጣት አንችልም ብለው የሚያምኑ ግለሰቦች ለውጥ የሚያመጡበትን ወንበር ይዘው መቀጠል ለምን እንደሚፈልጉ ለእኔ እንቆቅልሽ ነው፡፡ ዘመኑ ከችግሩ በላይ የሚገዝፉ መሪዎችን ይፈልጋል፡፡ በተቃዋሚ ፓርቲዎች ዘንድ ያለውን በባዶ ‹‹እኔባይነት›› አባዜ ካልተወገደ ተቃዋሚዎች የዴሞክራሲ ትግሉን ወደ ፊት የሚያራምድ አቋም ሊላበሱ አይችሉም፡፡
በህዝቡ በኩልም ከመቼውም ጊዜ በላይ ቆሞ የሚያስብበት ጊዜ ነው፡፡ አሁን እያንዳንዱ ዜጋ እራሱን ነፃ ለማውጣት ምን እንዳደረገ እራሱን የሚጠይቅበት ወቅት ነው፡፡ ለሁሉም ነገር ምክንያት እየደረደርንና ሌሎችንም እየወቀስን ነገር ግን ከእኛ የሚጠበቅን አንዳች ሳንፈጽም የምንሸኘው ጊዜ ሊኖር አይገባም፡፡ በድፍረት ህዝቡ ሊወቀስ ይገባዋል፡፡ እያንዳንዱ ዜጋ ከዚህ በኋላ ስለእርሱ መጨቆን ማንንም ሊወቅስ አይችልም፡፡ ኢህአዴግን እንኳን ለመውቀስ መጀመሪያ ያመቻቸለትን ጀርባውን መከልከል ይገባዋል፡፡ ይኽንን ለማድረግ ደግሞ ጦር መምዘዝ ወይንም ዝናር ማንገብ አያስፈልገውም፡፡ ፍርሃትን ገድሎ በልበ ሙሉነት የሉዓላዊ ስልጣኑ ባለቤት ለመሆን መስራትና መታገል ነው፡፡ በፍርሃት መቃብር ላይ የፍትህ፣ የሉዓላዊነት፣ የዴሞክራሲና የወንችማማችነት ችግኞች ይንዘረፈፋሉ፡፡ አገዛዙ ይሄ እንዳይሆን መቁረጥ አለብኝ ያላቸውን እግሮች ሁሉ ቆርጧል፡፡ ቀሪው ትግል የእያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ ነው፡፡ እኔ ለዚህ ትግል ይረዳል ብዬ ያሰብኩትን ይኽንን መጽሐፍ ቀድሜ ተዘጋጅቼ አበርክቻለሁ፡፡
ፍፁም ለመኖር ሳይሆን ለማሰብ በሚከብድ ሁኔታ በአውራ ጣቴ ወደውቅያኖሱ እንዳልወድቅ በተራራው መሃል ላይ ትልቅ ጥረት በማድረግ ከፈጣሪ ጋር ቀጥ ያለውን ጋራ ተወጥቼዋለሁ፡፡ የታሰርኩለት ሰላማዊ የዴሞክራሲ ትግል ፎቀቅ ባለማለቱ ዘወትር ባዝንም ይህችን ትንሽ ነገር በምጥ ብዛት ሰርቼ በማጠናቀቄ የተወሰነ እፎይታ ተሰምቶኛል፡፡ ለጊዜው የገደሉ ጫፍ ላይ ቆሜ የወጣሁትን ገደል ርቀት እያየሁ ነው፡፡ ነገር ግን ብዕሬ ከጣቶቼ ሳይለይ ሌሎች ሊወጡ የሚገባቸው ገደሎች ተደርድረው ይታዩኛል፡፡ ዴሞክራሲ በሌለበት ሀገር ህይወታችን ሁሉ ጠመዝማዛ መንገድ የበዛበት ገደል ነው፡፡ ሸለቆው እስኪሞላ ገደሉም ሜዳ እስኪሆን ወገባችንንና መንፈሳችንን አጽንተን ለትግል እንነሳ፡፡ የሀገር ፍቅር ዕዳን እነሆ ብያለሁ፡፡